Friday, 22 January 2021 00:00

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል (ዶ/ር) ሊቀ ጳጳስ ከ፲፱፻፴፫-፳፻፲፫ ዓ.ም

Written by  መጽሐፈ ሲራክ

Overview

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ላለፉት ፹ ዓመታት ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት አገልግለዋል፡፡ መንፈሳዊ አገልግሎታቸው በሀገር ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም ከሀገር ውጪም እንጂ፡፡ በትምህርት ረገድም በሀገር ውስጥ እና በውጭው ዓለም ብዙ ዕውቀትን ገብይተዋል፡፡ በተለይ የአብነት ትምህርትን በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረው በሀገሪቱ ውስጥ አሉ ከሚባሉ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ቀስመዋል:: የአብነት ትምህርት ለመማር ወጥተው ወርደዋል ፣የትውልድ ሀገራቸውን ትተው፣ ከውሻ ተከላክለው ፣ ቁራሽ እንጀራ ለምነው ፣ ደበሎ ለብሰው ፣ ተርበው ተጠምተው ጸዋትወ መከራውን በመታገሥ ሁሉን በጸጋ ተቀብለዋል፡፡ ብዙ የሕይወት መሰናክሎችን አልፈው ለትልቅ ማዕረግ በቅተዋል፡፡   የብፁዕነታቸውን የ፹ ዓመታት የሕይወት ጉዞ እና ሥራዎቻቸውን በሁለት ክፍል ለማቅረብ ወደድን የመጀመሪያውን ክፍል ከተወለዱበት ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ በጸሎትና በቡራኬ እንዲቆዩ እስከተወሰነበት ጥቅምት ወር ፳፻፲፫ ዓ.ም ድረስ ያለውን የሕይወታቸውን ገጽ ወይም ዜና ሕይወት እንደሚከተለው አቅርበነዋል መልካም ንባብ፦

 

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ፦ ከልጅነት እስከ ማዕረገ ጵጵስና

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል (ዶ/ር) ሊቀ ጳጳስ በመጀመሪያ ስማቸው ሣህለ ማርያም ከአባታቸው ከመምህር ቀሲስ ገብረ ሕይወት ወልደ ሐዋርያት እና ከእናታቸው ወ/ሮ ብርነሽ ቸኮል በቀድሞ ወሎ ክፍለ ሀገር በዋግ ሕምራ አውራጃ ታኅሣሥ ፲፱ ቀን ፲፱፻፴፫ ዓ.ም ተወለዱ፡፡  

ከካህን ቤተሰብ የተገኙት ብፁዕነታቸው ከፊደል ጀምሮ እስከ ግብረ ዲቁና ከዚያም እስከ ቅስና ያሉትን የቤተ ክርስቲያን ሙያዎች ከወላጅ አባታቸው  ከመምህር ቀሲስ ገብረ ሕይወት እና ከአደጉበት አካባቢ ከነበሩ መምህራን ጀምረው ዐሥር ዓመት ሲሞላቸው ከቤተሰባቸው ተለይተው እና ከአካባቢያቸው ርቀው ወደ ዛታ ከተማ በመሔድ ከክርስትና አባታቸው ከመምህር ገብረ ጻድቅ ንባብና ዳዊት ፣ መዝገበ ቅዳሴን እስከ ሰዓታት ተምረዋል፡፡

በመቀጠል ወደ ደብረ ዘመዳ ቅድስት ድንግል ማርያም አንድነት ገዳምና ደብረ ማርያም መሐጎ ማርያም በመሄድ ከየኔታ ወልደ እግዚእ ተጨማሪ ትምህርቶችን የተማሩ ሲሆን በተለይ በቅድስና ሕይወታቸው ከሚታወቁት መምህር ኤልሳዕ ወልደ ገብርኤል ጸዋትወ ዜማ በሚገባ ተምረው አጠናቀዋል፡፡ በወቅቱም ከወሎ ክፍለ ሀገር እስከ አሰብ ድረስ ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ከአቡነ ይስሐቅ የዲቁና ማዕረግ ተቀብለዋል፡፡ ከታላቁ ደብር ደብረ ሳሙኤል ከሚገኙት ጸጋ ዘአብ ወልደ ኢየሱስ የውዳሴ ማርያምንና የዳዊትን ትርጓሜ ተምረው አጠናቀዋል፡፡

ብፁዕነታቸው ለቅኔ ካላቸው ከፍተኛ ፍቅር እና ተሰጥዖ የተነሳ በዘመናቸው አሉ ከሚባሉ የቅኔ መምህራን ቅኔን ከነአገባቡ በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረው ተምረዋል፡፡ ወርጫት ቅዱስ መድኃኔ ዓለም ደብር ከሚገኙት አረጋዊ መምህር ከየኔታ ጥዑመ ልሳን አማራው፣ ከመምህር ውቤና እና ከየኔታ መኮንን በሚገባ ቅኔን ከነአገባቡ ተምረዋል፡፡ እንዲሁም በወሎ ክፍለ ሀገር በራያ ቆቦ ዞብል አደባባይ ኢየሱስ ከነበሩት ከታላቁ ምስክር ከሊቀ ኅሩያን ወልደ ሰንበት የቅኔንና የአገባብን ይትበሃል በሚገባ አጠናቀው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡ ከቅኔው ጎን ለጎን የቅዱስ ያሬድን ዜማ እና የአቋቋም ትምህርት ያላቸውን ጊዜ በሚገባ በመጠቀም ተምረዋል፡፡

በአንድ ወቅት የሥጋ ዘመዳቸው በነበሩት ዋግ ሹም ወሰን ኃይሉ አማካኝነት ወደ አዲስ አበባ የመምጣት እድል አግኝተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ይህንን እድል በመጠቀምም በኮልፌ ሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ አዳሪ ትምህርት ቤት ተወዳድረው እና የተሰጠውን የቅኔ፣የዜማና የአቋቋም ፈተና በብቃት አልፈው አዳሪ ትምህርት ቤቱ የመግባት እድል አገኙ፡፡ በዚያም ከ፲፱፻፶፬ ዓ.ም እስከ ፲፱፻፶፰ ዓ.ም ለአራት ዓመታት የብሉያት መጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርት የኔታ ገብረ ማርያም እና የኔታ ታመነ ከተባሉ የታወቁ መምህራን ዘንድ ተምረው በማጠናቀቅ በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡

ብፁዕነታቸው በምንኩስና የቅድስና ሕይወት ጉዞ የጀመሩትና ለታላቁ ማዕረግ እንዲደርሱ የእግዚአብሔር ጥሪ የደረሳቸው በ፲፱፻፷፩ ዓ.ም ነው፡፡ በዚህ ዓመት ወደ ደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም በመሄድ በጻድቁ ቃል ኪዳንና በአበው መነኮሳት ፈቃድ መነኰሱ፡፡ በመቀጠልም መስከረም ፮ ቀን ፲፱፻፷፪ ዓ.ም በጊዜው የወለጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት  ከብፁዕ አቡነ ያዕቆብ የቅስና እና የቁምስናን ማዕረግ ተቀብለዋል፡፡ 

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል (ዶ/ር) ሊቀ ጳጳስ በልጅነታቸው በወልድያና በደሴ ከተማ የጀመሩትን ዘመናዊ ትምህርት ወደ አዲስ አበባ ከመጡም በኋላ በትጋት ቀጥለዋል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኮልፌ ሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት በማጠናቀቅ ወደ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ተዘዋውረው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን  በጥሩ ውጤት ጨርሰዋል፡፡ 

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በወቅቱ በነበራት የውጭ ግኙኝነት መሠረት የውጭ ሀገር የትምህርት ዕድል ከተሰጣቸው ስድስት ተማሪዎች መካከል አንዱ በመሆን ወደ ሩሲያ መስኮብ የቀድሞው ፒተርስበርግ በኋላ ሌኒን ግራድ ለትምህርት ተላኩ፡፡ በሌኒን ግራድ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሚሰጠውን የአምስት ዓመት ትምህርት በከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ በሃይማኖተ አበው (ፓትሮሎጂ) የጥናት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማዕረግ አጠናቀው ተመርቀዋል፡፡ ከዲግሪው በተጨማሪ በማስተር ኦፍ ዲቪኒቲ (Master of Divinity) በትምህርተ መለኮት ዲግሪ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ አጠናቀው ተመርቀዋል፡፡  

የማዕረግ ተመራቂ የነበሩት ብፁዕነታቸው በነበራቸው ከፍተኛ ውጤት ዩኒቨርስቲው ተጨማሪ የትምህርት ዕድል በመስጠት በነገረ ክርስቶስ የዶክትሬት ዲግሪ (PhD) ጥናታቸውን እንዲቀጥሉ አደረገ፡፡ ለዶክተሬት ትምህርት የሚያበቃቸውን መሥፈርት ለማሟላት Christology of non Chalchedonian Church በሚል ኬልቄዶንን የማይቀበሉ ክርስቲያኖች ስለ ነገረ ክርስቶስ ፣ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ ፣ ስለ ነገረ ማርያም ፣ ስለ ምሥጢረ ቅዱስ ቊርባን ያላቸውን እምነትና ከምሥራቃውያን ኬልቄዶናውያን ጋር ያለውን ልዩነት የሚያስረዳ ከ፪፻፶ ገጽ በላይ የጥናት ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም የአንጾኪያና የእስክንድርያ ትምህርት ቤቶች አንድነታቸውንና የሚለያዩበትን መሠረታዊ ነጥብ ፻፴  ገጽ በማቅረብ የዶክትሬት ዲግሪ ትምህርታቸውን ለመቀጠል የሚያበቃቸውን መሥፈርት አሟልተው በትምህርተ ሥጋዌ (Christology) የዶክትሬት ኦፍ ዌዎሎጂ ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡  

ብፁዕነታቸው ወደ ሰሜን አሜሪካም በመሄድ ከፕሪስተን ዩኒቨርሲቲ (Preston University) ማስተር ኦፍ ቴዎሎጂ ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡ በዚሁ ዘመናዊ ትምህርት ጉዞ በከፍተኛ ውጤት የተቀበሏቸውን የዶክተሬት ዲግሪ ሞስኮና ኒዮርክ በሚገኙት የትምህርት ኮሚሽኖች ሰነድ ማረጋገጫ መሥፈርት መርምሮ አጽድቆላቸዋል፡፡ በነበራቸው ከፍተኛ የትምህርት ዝግጅትም በሰሜን አሜሪካና በሩሲያ የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ መምህር ሆነው በመመደብ አገልግለዋል፡፡ 

በ፲፱፻፸ ዓ.ም ሦስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለይፋዊ ጉብኝት እና ስብሰባ ሩሲያ በሔዱበት ጊዜ ‹‹ቤተ ክርስቲያንህ ትፈልግሃለች ወደ ሀገርህ መምጣት አለብህ›› በሚል አባታዊ ጥሪ ብፁዕነታቸውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ወደ ሀገር ቤት ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ዋና ጸሓፊ ፣የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የካህናት አስተዳደር መምሪያ እና መንፈሳዊ አገልግሎት መምሪያ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በዚህ ኃላፊነት ላይ እያሉም ጥር ፬ ቀን በ፲፱፻፸፪ ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዶ/ር አባ ኢያሱ ይባሉ የነበሩት ብፁዕ አባ ገብርኤል ተብለው የመንፈሳዊ ኮሌጅ ኤጲስ ቆጶስ (ዲን)፣ የድሬዳዋና የአካባቢው ኤጲስ ቆጶስ ተብለው ተሹመዋል፡፡

ብፁዕነታቸው በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ በጸሎትና በቡራኬ እንዲቆዩ እስከተወሰበት ጥቅምት ፳፻፲፫ ዓ.ም ድረስ በሀገር ውስጥ እና በውጪው ዓለም ቤተ ክርስቲያን ባሰማራቻቸው ቦታዎች ሁሉ በርካታ መንፈሳዊ ሥራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ 

በ፲፱፻፸፫ ዓ.ም የኤርትራ ክፍለ ሀገር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን ለሦስት ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በ፲፱፻፸፮ ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመዘዋወር የትንሣኤ ማሳተሚያ ድርጅት ኀላፊ ሆነው በመስራት ላይ እያሉ የኤርትራ ሀገረ ስብከት ካህናት እና ምእመናን እንዲመለሱላቸው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ወደ ኤርትራ ተመልሰው እስከ  በ፲፱፻፹፫ ዓ.ም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በመሆን አገልግለዋል፡፡ በ፲፱፻፹፫ ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመመለስ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የበላይ ኀላፊ ሆነው ለአንድ ዓመት ከሦስት ወር አገልግለዋል፡፡ በነበራቸውም ቆይታ በሀገረ ስብከቱ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ፣ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ ፣ ሰንበት ት/ቤት እንዲደራጅ ብዙ ጥረዋል፡፡

ብፁዕነታቸው በውጭ ሀገር በነበራቸው መንፈሳዊ አገልግሎት በጥቅምት ፲፱፻፹፭ ዓ.ም በቅዱስ በሲኖዶስ ትእዛዝ ወደ ካረቢያን ሀገራት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተመድበው  በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ ከዚያ ተመልሰውም በግንቦት ወር ፲፱፻፹፭ ዓ.ም ወደ ሰሜን ወሎ ወልዲያ ሀገረ ስብከት ተዛውረው ስድስት ወር ሐዋርያዊ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተው ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ወደ ሀገረ ስብከቱ ሲመለሱ ብፁዕነታቸው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል፡፡ በ፲፱፻፹፮ ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ የሕዝብ ግንኙነትና የውጭ ጉዳይ ኀላፊ በመሆን ለአምስት ወራት እንዲሁም የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን ለሦስት ዓመት ከአምስት ወር አገልግለዋል፡፡ ከ፲፱፻፺ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ፳፻ ዓ.ም ድረስ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ተመድበው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ጥንታውያን ገዳማትን አስተዳድረዋል፡፡

ብፁዕነታቸው እስከ ፳፻፫ ዓ.ም በሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ለሦስት ዓመታት የትምህርት ቤቱ የበላይ ኀላፊ ሊቀ ጳጳስ በመሆንም አገልግለዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል (ዶር) ከኅዳር ወር ፳፻፫ ዓ.ም ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ በጸሎትና በቡራኬ እንዲቆዩ እስከተወሰነበት እስከ ጥቅምት ፳፻፲፫ ዓ.ም ድረስ የሲዳማ፣ጌዴኦ አማሮና ቡርጂ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ 

Read 613 times