Friday, 22 January 2021 00:00

‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግር በዘላቂነት መፍታት ካልተቻለ   የነገዋን ቤተ ክርስቲያን ላናገኝ እንችላለን›› - ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ደረጄ ብርሃኑ ክፍል ሁለት 

Written by  በእህተ ሚካኤል
የተወደዳችሁ አንባብያን የዚህን ቃለ መጠይቅ የመጀመሪያ ክፍል ባለፈው እትማችን ላይ ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ በዚህ እትማችን ደግሞ ክፍል ሁለትን ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ በጥሞና ትከታተሉ ዘንድ ግብዣችን ነው፡፡ ስምዐ ጽድቅ ፦ በቀጣይ በቃለ ወንጌል በእምነታቸው እንዲጸኑ በማድረግ በሀገረ ስብከቱ እንደ እቅድ የተያዘ ነገር አለ?  እየተሠራ ነው? ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ደረጄ ፦ አዎን እነዚህን ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች በተለየ መልኩ ተይዞ እየተሠራ ነው፡፡ አደራጅቶ በሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ክፍል የሚመራ ቡድን/ልኡክ አለ ይህን ልኡክ፣ ማኅበራትን በማቀናጀት ሰፋፊ ጉባኤያትን እየሠራን ነው፡፡ በእቅድም ይዘን ለመሥራት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ አሁን በቅርቡም ከአዲስ አበባ ዘማርያን እና ሰባክያነ ወንጌልን በመጋበዝ  በመቻራ ወረዳ ላይ ታላቅ ጉባኤ አዘጋጅተናል፡፡ በቀጣይም ከአብያተ ክርስቲያናት ሰበካ ጉባኤ ጋር በመነጋገር እንደዚህ ዓይነቱን የማጽናናት ሥራ በሌሎችም ወረዳዎች አጠናክረን የመቀጠል እቅድ ነው ያለን፡፡  ስምዐ ጽድቅ ፦ በቀጣይ ቤተ ክርስቲያን የሚቃጡባትን መሰል ጥቃቶች ለመመከት ምን ማድረግ  አለባት? ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ደረጄ ፦ ስለ ቀጣይ ቤተ ክርስቲያን ሥራ ስንነጋገር በመጀመሪያ ቅዱስ ሲኖዶስ ትልቅ ኃላፊነት አለበት ብለን እናስባለን፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ሲኖዶስ ከማናቸውም የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥልጣን መዋቅር ትልቁና የመጨረሻው ሥልጣን ሰጪና ወሳኝ አካል ነውና፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በተለያየ ጊዜ ከተለያዩ ሀገረ ስብከቶች ጥቃቶችን አስመልክቶ የቀረቡለትን ሪፖርቶች በመረጃ በመያዝ ከሚመለከታቸው የመንግሥት የጸጥታ አካላት ጋር ቀርቦ በመነጋገር እነዚህ ችግሮች መስመር የሚይዙበትን መፍትሔ በማምጣት መመሪያዎችን በተዋረድ ወደታች ሊያወርድልን ይገባል፡፡ 

 

ከዚህ ባሻገር ለምሳሌ እንደ ምዕራብ ሐረርጌ ፤እንደ ሀገረ ስብከታችን ደግሞ በሀገረ ስብከታችን ካሉት የዞን የመንግሥት አካላት፤ የወረዳ የመንግሥት አካላት እንዲሁም የቀበሌ መስተዳደሮች አጠቃላይ የመንግሥት መዋቅር ጋር የቤተ ክርስቲያን ኀላፊዎች ተቀራርበው በመሥራት ችግሩ እንዲፈታ ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ጥቃት እየደረሰበት ያለው ክፍል ከሌላ ዓለም የመጣ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ደግሞ በየትኛውም ቦታ የመኖር ፣የመሥራት፣ ሀብት የማፍራት፣ የመንቀሳቀስ  ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳለው ይታወቃል፡፡ መብቱ እንዲጠበቅለት የሚወጡ መመሪያዎችና ውሳኔዎች መሬት ላይ ወርዶ ሊሠራባቸው ይገባል፡፡ 

በዚህ መንገድ የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግር በዘላቂነት መፍታት ካልተቻለ እና ችግሩ የሚቀጥል ከሆነ የነገዋን ቤተ ክርስቲያን ላናገኝ እንችላለን፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የታሪክ ባለቤት ናት፤ ሀገርን ከነሙሉ ክብሩ፣ ከነቅርሱ ከነጀግንነቱ ያቆየች፣የሀገር አንድነትን አጽንታ የያዘች ቤተ ክርስቲያን ናት፤ ስለዚህ ልትጠቃ ልትጎዳ አይገባም፡፡ በእኛ ቤተ ክርስቲያን በኩልም ከአጥቢያ ሰበካ ጉባኤ ጀምሮ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ያለው መዋቅር መጀመሪያ መጠናከር አለበት፤ የእርስ በርስ የውስጥ መጠላለፍ ቀርቶ በጋራ በመሆን መዋቅሩን አጠናክረን ችግሩ ከመድረሱ በፊት የቅድመ መከላከል ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ከዚህ በዋናው ማእከል ተቋቁሞ ከቅዱስ ሲኖዶሱ እስከ ታች ድረስ ወርዶ በእዝ ሠንሠለት በመዋቅር የተገናኘ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል ከዚህ በኋላ የምናንቀላፋበት ጊዜ ሊኖር አይገባም፡፡ 

ስምዐ ጽድቅ ፦ ፴፱ኛውን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ለመካፈል ሀገረ ስብከትዎን ወክለው ነው የመጡት ከጉባኤው ምን አገኙ?

ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ደረጄ ፦ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በየዓመቱ የሚከናወን ነው፡፡ ይህ ፴፱ኛው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ጥሩ ተሳትፎ ተደርጎበታል፡፡ ነገር ግን በዚህ በኮቪድ-፲፱ ወረርሺኝ ምክንያት ሰፊ የሆነ የጋራ ውይይት ለማድረግ አልተቻለም፡፡ ሆኖም ግን  የየአህጉረ ስብከቱ ሪፖርት በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ  በኩል ነው የቀረበው እና የተነበበው፡፡ ለወደፊቱ እግዚአብሔር በሰላም ቢያደርስን ሰፊ ውይይት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በዘንድሮው ዓለም አቀፍ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ በወቅታዊው የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የችግሩ ገፈት ቀማሾች በተለይ ችግሩ ያለባቸው ዞኖች፣ ሀገረ ስብከቶች የነበረባቸው ችግር ውይይት አልተደረገበትም ምክንያት ቢኖረውም፡፡ ችግሩ ሲነሳ፣ ለውይይት ሲቀርብ፣ ሲታወቅም ነው መፍትሔውም ሊገኝ የሚችለው፡፡ 

የችግሩ ምንጭ እዚህ ጋር ነው፤ የችግሩ መንሥኤም  ይህ ነው በመሆኑም   መፍትሔው ደግሞ ይህ ነው ተብሎ በዝርዝር ሊቀመጥ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ቁጭ ብሎ መወያየት ያስፈልጋል፡፡ አሁን በኮቪድ ምክንያት ያንን ማድረግ አልተቻለም፡፡ ለቀጣዩ ግን ይህ እንዲሆን ሐሣቦች  ከተሳታፊዎች ቀርበዋል፡፡ በአጠቃላይ እንደ ምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት በነበረው ስብሰባ ደስተኞች ነበርን፤ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በሥራ አፈጻጸም ግምገማ ከምድባችን የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት አንደኛ ወጥተን መሸለማችን ነው እግዚአብሔር ይመስገን፡፡

 ስምዐ ጽድቅ ፦ በ፴፱ኛው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ቤተ ክርስቲያን ላይ ከደረሱ ጥቃቶች ጋር ተያይዞ የተሰጠ መፍትሔ ፤ እንደ አቅጣጫ የተቀመጠ ሐሳብ አለ? 

ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ደረጄ ፦ በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ባለ ፲፭ ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተን ነው የተለያየነው፡፡ ይህ የአቋም መግለጫ ለቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ ቅዱስ ሲኖዶስ ከተነጋገረበት በኋላ ወስኖ ወደ ታች ይወርዳል ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ   ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመቀራረብ እና አንድ ላይ በመሥራት  ሊፈታቸው የሚገባቸው ነጥቦች እዚህ የአቋም መግለጫ ላይ ተካተዋል፡፡ ስለዚህ እዚያ ላይ የቀረቡት ነጥቦች በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከተወሰነ በኋላ ወደ ታች ይወርዳል፡፡ 

ከዚህ ጋር ተያይዞ ትልቁ ነገር መወሰኑ ብቻ አይመስለኝም ከተወሰነ በኋላ ውሳኔው ተግባራዊ እንዲሆን መሬት የወረደ ሥራ መስራቱ ነው ቁም ነገሩ፡፡ ከዚህ ቀደም ብዙ ውሳኔዎች ተላልፈዋል፤ ነገር ግን ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር ክፍተት አለ፡፡ የተላለፉ ውሳኔዎችን  ተከታትሎ የሚያስፈጽም አንድ ክፍል ሊቋቋም ይገባል ፡፡ አባቶች ይወስናሉ አባቶች የወሰኑትን ውሳኔ ማነው ተከታትሎ መሬት ላይ የሚያወርደው? ለምሳሌ ከመንግሥት አካል ጋር ተነጋግሮ ማለቅ ያለበት ጉዳይ ከሆነ ይህንን እስከመጨረሻው ጫፍ አድርሶ የሚያስወስን፤ የሚያስፈጽም አካል ያስፈልጋል፡፡

ውሳኔን የሚያስፈጽም አካል ካለ በየደረጃው የሚወርዱና የሚተላለፉ ውሳኔዎችንና መመሪያዎችን መፈጸም አለመፈጸማቸውን መከታተል ያስፈልጋል፡፡ ሁላችንም የሚተላለፉትን ውሳኔዎች ተግባራዊ እያደረግን ከመጣን ችግሮች ይፈታሉ፡፡ አሁን በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ የሕዝብ ግኑኝነት መምሪያ ተቋቁሟል፡፡ በሀገረ ስብከትም ደረጃ እንዲቋቋም ደግሞ መመሪያ ተላልፏል በዚያ መሠረት አቋቁመናል፡፡ ቶሎ ቶሎ ግንኙነት በማድረግ ችግሮችን ለመፍታት የተቋቋመ መምሪያ ነው፡፡ ይህ መምሪያ ቢጠናከር ዘመኑ በሚጠይቀው ቴክኖሎጂ እየተጠቀምን መረጃ ለመቀባበል፣ለመለዋወጥ እና የተሻለ ሥራ ለመሥራት ያግዛል፡፡ 

ስምዐ ጽድቅ ፦ በመጨረሻ የሚያስተላልፉት ቀረ የሚሉትም ነገር ካለ ቢነግሩን?

ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ደረጄ ፦ ይህች ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት እና ታሪካዊት የሆነች በክርስቶስ ደም የተመሠረተች ቃል ኪዳን ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ‹‹የገሃነም ደጆች አይችሉአትም›› የተባለች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ብዙዎች በየዘመናቱ እየተነሱ ቤተ ክርስቲያንን ሊያጠፉ ሞክረዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሰማዕትነትን ዘመን  አሳልፋለች ገፊዎቿ የሉም ፣ ጠላቶችዋ ጠፍተዋል እስዋ ግን ሁሉን አሳልፋ ዛሬን አለች ወደፊትም ትኖራለች፡፡ በትንቢተ ናሆም ‹‹ በመከራቸው ቀን ለሚታገሡ እግዚአብሔር ቸር ነው፤እርሱን የሚፈሩትንም ያውቃቸዋል፡፡›› ናሆ ፩፥፯ ብሎ እንደተናገረው ቤተ ክርስቲያን መጠለያ ናት ፤እውነተኛ አምባችን ናት ፤ለጠላት አሳልፎ የማይሰጥ እውነተኛ እረኛ አባት እግዚአብሔርን የምናመልክባት ናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን፡፡ 

ይህችን ቤተ ክርስቲያን ለማጥፋት ከውጭም ከውስጥም ጠላት በዝቶባታል፡፡ ስለዚህ ምእመናን በእምነታቸው ጸንተው እና ተግተው ቤተ ክርስቲያናቸውን ሊጠብቁ ይገባል፡፡ በቤተ  ክርስቲያን በኀላፊነት የተቀመጥን እረኞች በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቅ፣ ምእመናንን የመጠበቅ ኀላፊነት አለብን፡፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች፣ ምእመናን ይበልጥ ወደ እርሱ እንድንቀርብ እግዚአብሔርን የረሱ፣ የዘነጉ በንሰሓ እንዲመለሱ አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር የተለያዩ ነገሮችን ያመጣል፤ ስለዚህ  መከራውና ፈተናው ለበጎ መሆኑን አምኖ በትዕግሥት ማለፍ ያስፈልጋል፡፡

 እግዚአብሔር እንደ ዳዊት ሊያነግሥ ሲፈልግ ጎልያድን ያህል ትልቅ መከራ ያመጣል፡፡  ምእመናንም በመጣው ፈተና ሊደነቁ አይገባም አምላካችን ክርስቶስም መከራ ተቀብሎአል ግን ዓለምን አሸንፏል፤ እኛም የክርስቶስ ልጆች ነን፡፡ ከፈተናው የምንማረውን ድክመታችንን አርመን ፣አስተካክለን እግዚአብሔርን የረሳንበት፤ እግዚአብሔርን ያላስታወስንበት፤ እግዚአብሔርን በሚገባ ያላገለገልንበትን ጊዜ በማሰብና ወደ ውስጣችን በመመልከት በንሰሓ ወደ እግዚአብሔር ልንመለስ ይገባል፡፡

ሌላው ሳላነሳው የማላልፈው እንደ ሀገረ ስብከታችን ስብከተ ወንጌልን ፤ ምእመናንን ለማጠናከር በማሰብ ከሀገረ ስብከቱ የማኅበረ ቅዱሳን አሰበ ተፈሪ ማእከል ጋር በጋራ በመሆን ጥሩ የሆነ የአብነት /የአዳሪ ትምህርት ቤት/ ተገንብቶ አልቆ አሁን በቅርቡ የምርቃት ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል፡፡ በዚህ ትምህርት ቤት ከገጠር ፣በዞኑ ውስጥ ካሉ በአካባቢ ያሉና አማርኛም ኦሮሚኛም የሚናገሩ ልጆችን በማሰባሰብ በየቋንቋው የሚያስተምሩ ዲያቆናትን  ተተኪ ሰባኪያንን ለማፍራት የሚያስችል ሥልጠና ለመስጠት እየተዘጋጀን ነው፡፡   

 ከዚያም ባሻገር ቀደም ሲል በሀገረ ስብከቱ G+2 ሁለ ገብ የሆነ ሕንጻ እያስገነባን ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሕንፃው ከ፹፭ በመቶ በላይ ስራው እየተጠናቀቀ ነው፡፡ የምድር ቤቱን ሙሉ በሙሉ ጨርሰናል፡፡ አንደኛና ሁለተኛ ፎቅ ደግሞ የሰባኪያን ማልጠኛ፣ለሀገረ ስብከቱ ቢሮ እና ለሌሎች አገልግሎቶች ይውላል፡፡ እነዚህ ነገሮች ተጠናክረው ከቀጠሉ የሀገረ ስብከቱ አጠቃላይ  እንቅስቃሴ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ ለማስኬድ ምቹ ይሆናል፡፡  

በአጠቃላይ እረኛው የእረኝነቱን ተግባር በአግባቡ ከተወጣ፤ በጎችም የበግነታቸውን ከእረኞቻቸው ሥር ሳይጠፉ በእምነታቸው ሊጠነክሩ ይገባል፡፡ ከእረኛው እና  ከበረቱ የወጣች በግ አንድም ለእርድ አንድም ለገበያ ነው ልትቀርብ የምትችለው፡፡ ምእመኑ  በረቱን እናት ቤተ ክርስቲያንን ጥሎ ሊሄድ አይገባም፡፡ ከበረቱ ሊያስኮበልሉ የሚገፋፉ ብዙ መከራዎች ፤ብዙ ፈተናዎች ከውስጥም ከውጭም አሉ፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተቃዋሚዎቿ ብዙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ነቅቶ በመጠበቅ ፤ተደራጅቶ በመሥራት ፤ በውስጥ አሰራር እርስ በርስ የምንጋጭባቸውንና አለመግባባት ውስጥ የሚከቱንን ነገሮች ወደ ጎን ትተን ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን በቅንነት ልንቆም ይገባል፡፡

ስምዐ ጽድቅ ፦ ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ደረጄ ይህን ቃለ መጠይቅ ስለሰጡን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን?

ሊቀ ኅሩያን ቀሲስ ደረጄ ፦ እኔም ለዚህ ቃለ መጠይቅ እንግዳ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡

 

Read 584 times