Tuesday, 09 February 2021 00:00

የድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር የመልካም ሥራ ተምሳሌት መሆኑ ተገለጠ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
የድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር ለቤተ ክርስቲያን እያበረከተ ባለው አስተዋጽኦ የመልካም ሥራ ምሳሌ መሆኑን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሳነ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ  ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ገለጡ።   ቅዱስነታቸው ይህንን የገለጹት የድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባና የሥራ ባልደርቦቻቸው ለቤተ ክርስቲያን ልማትና ሰላም ላበረከቱት አስተዋፅኦ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በተዘጋጀላቸው የምስጋናና የዕውቅና መርሐ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልእክት ነው።   ቅዱስነታቸው በጽሕፈት ቤታቸው የጋበዟቸውን እንግዶች ባነጋገሩበት ወቅት የድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር ለቤተ ክርስቲያን እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አድንቀው ይህ መልካም ሥራ ለሌሎች ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አርአያ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።  ‹‹ሃይማኖታችን የተለያየ ቢሆንም ፍቅራችንና አንድነታችንን አያሳሳውም ኢትዮጵያዊነታችንንም አያጠፋውም›› በማለትም አክለዋል።    እንደ ቅዱስነታቸው ገለጻ ሀገራችን የጋራ እስከሆነች ድረስ ዜጎች ሰብአዊ መብታቸው ተከብሮ በጋራ በአንድነትና በፍቅር ሊኖሩ ይገባል።  መገፋፋትና የርስ በርስ ግጭት ውስጥ መግባትን አስወግዶ ለሀገር ልማትና እድገት መሥራት ያስፈልጋል።  የሀገራችንን ሰላም፣ አንድነትና ፍቅር የምንጠብቀው በሃይማኖት ልዩነት፣ በዘርና በቀለም ሳንለያይ ከሆነ ብቻ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው የድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር የሰላምና የልማት ምሳሌ መሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ደስ ሊለው ይገባል፤ በሀገራችን ያሉ ሁሉም የፖለቲካ አመራሮች የድሬ ደዋን የመልካም ሥራ ምሳሌነት በመውሰድ ለእውነትና ለሀገር አንድነት አጥብቀው እንዲሠሩ መክረዋል።   የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ኃላፊ አፈ መምህር አባ ገ/ሥላሴ ጌትነት በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር ተወርሰው የተመለሱ የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች እንዳሉ ጠቅሰው ከውርስ ከተመለሱት ቦታዎች መካከል በአንዱ ላይ ለገቢ ማስገኛ የሚውል ሕንፃ ለመሥራት ታኅሣሥ ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ቅዱስ ፓትርያርኩ የመሠረት ድንጋይ እንዳስቀመጡ ተናግረዋል።   የድሬ ደዋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ማትያስ በቀለ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት በድሬ ደዋ ሀገረ ስብከት ላለፉት ሦስት ዓመታት ከፍተኛ የሆነ ሁከትና ብጥብጥ ውሥጥ በመቆየቱ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን በነፃነት ሥርዓተ አምልኳቸውን ማከናወን መቸገራቸውንና የአደባባይ በዓላትንም በሥጋት ያከብሩ እንደነበር ጠቅሰው፤ “አሁን ያለው የከተማ አስተዳደር አመራር ቁርጠኛ በመሆኑ ከቤተ ክርስቲያን ጋር በሰላምና በልማት ላይ ተቀራርቦ እየሠራ ነው” ብለዋል።   ሥራ አስኪያጁ አያይዘውም “የድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር በተለይ ዘንድሮ ፴ ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ለአደባባይ በዓላት ማክበሪያነት እንዲውል ከመስጠቱ ባሻገር የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ያልነበራቸው የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች ሁሉ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ እንዲኖራቸው አድርጓል›› ብለዋል።   ሀገረ ስብከቱ የመካነ መቃብር እጥረት እንዳለበት ለከተማ አስተዳደሩ ባቀረበው ጥያቄ መሠረትም በቅርቡ ለመካነ መቃብር የሚውል ተጨማሪ መሬት እንደሚሰጥ ያስታወቁት ሥራ አስኪያጁ “ሌሎች ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር በመማር መንግሥትና የእምነት ተቋማት በጋራ መሥራታቸው ለሀገር ሰላምና ልማት ሊኖረው የሚችለውን ድርሻ ሊገነዘቡ ይገባል” ብለዋል።   በዚሁ የዕውቅናና ሽልማት መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አሕመድ መሐመድ ቡህ ከተማ አስተዳደራቸው ለቤተ ክርስቲያን ባበረከተው አስተዋጽኦ የምስጋናና የዕውቅና ሽልማት ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጠው ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸው ዕውቅና ለበለጠ መልካም ሥራ እንዲነሳሱ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ተናግረዋል።   “ቤተ ክርስቲያን ለሀገራችን የኪነ ሕንፃ ጥበብ እድገት ያበረከተቻቸውን አስተዋጽኦ ያደነቁትና ለተደረገላቸው መስተንግዶና አቀባበል እንዲሁም ለተሰጣቸው የዕውቅና ሽልማት ምስጋናቸውን ያቀረቡት የድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ልዩ አማካሪና የድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር ብልፅግና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መብራት ገብረየስ ናቸው።   
Read 590 times