Tuesday, 09 February 2021 00:00

ገዳማትን ከጊዜያዊ ድጋፍ የማውጣት አስፈላጊነት

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጥንታዊና ታሪካዊ ገዳማት ባለቤት ናት።  በመላ ሀገሪቱ በርካታ ጥንታውያን ገዳማት የሚገኙ ሲሆን በእነዚህ ገዳማት ውስጥ የበቁና ዓለምን የናቁ አባቶችና እናቶች በአንድነት ተሰባስበው ገዳማዊ ሕይወትን ይመራሉ።  መታረዝ፣ መራብ፣ መጠማትና መውጣት መውረድ ለእነሱ የዘወትር ክብራቸው ነው።  ድንጋይ ተንተርሰው ጤዛ ልሰው ሕይወትን በመምራት የክርስቶስን መንግሥት ይናፍቃሉ።  ይሁን እንጅ እነዚህ ገዳማውያን የሚኖሩባቸው አንዳንድ ገዳማት በከፋ የኢኮኖሚና የመሠረተ ልማት ችግር ውስጥ ይገኛሉ፤ ቢሆንም ገዳማቱ ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት ቤተ ክርስቲያን ከሞላ ጎደል ያቅሟን እያደረገች ትገኛለች።  ከአቅም በላይ የሆነውን ደግሞ በጎ አድራጊ ምእመናንን በማስተባበር ገዳማቱ በሚደገፉበት ሁኔታ ላይ  ስትሠራ ቆይታለች።    በዚህ ረገድ አንዳንድ ገዳማት ከችግራቸው ወጥተዋል፤ በርካቶቹ አሁንም ድረስ በከፍተኛ ችግር ወስጥ ይገኛሉ።  የገዳማቱን ችግር ለመፍታት በማኅበረ ቅዱሳን በኩል በርካታ ስልቶች ተነድፈው ወደ ሥራ ከተገባ ዓመታት አልፈዋል።  ማኅበሩ ከአባላቱ ከሚያገኘው ገቢ በተጨማሪ በጎ አድራጊዎች ምእመናንን በማስተባበር ፕሮጀክት ቀርጾ ገዳማቱን ሲደግፍና ሲያግዝ ቆይቷል።  የዚህ በጎ ተግባር ማሳያ ከሆኑት አንዱ ፈለገ ጥበብ ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ  ለማኅበሩ  በስጦታ የሰጡትን “እመጓ” የተሰኘውን መጽሐፍ በመሸጥ በገቢው የሰባት ያህል ገዳማት ፕሮጀክቶች ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ አድርጓል።   ከመጽሐፉ ሽያጭ የተገኘው ከ፬.፰ ( አራት ነጥብ አምስት) ሚሊዮን ብር በላይ ለሰባት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ መሆኑንና ፕሮጀክቶቹ መጠናቀቃቸውን አስመልክቶ እንዲሁም ለፈለገ ጥበብ ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ ዕውቅና ለመሥጠት ጥር ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በባሕር ዳር ዩኒሰን ሆቴል  በተዘጋጀው መርሐ ግብር ሊቃውንተ  ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የመንግሥት ባለሥልጣናት የተገኙ ሲሆን በመርሐ ግብሩ ከተገኙት የመንግሥት ባለሥልጣናት መካከል የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያን በትምህርት ሚኒስትርነት እንዳገለገለች አስታውሰው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥር የሚተዳደሩ ገማትን ከጊዜያዊ ድጋፍ በማውጣት ቋሚ የሆነ የገቢ ምንጭ ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።  ዶ/ር ፍሬው አክለውም ፈለገ ጥበብ ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ “እመጓ” የተባለውን መጽሐፍቸውን ለቤተክርስቲያን በሥጦታ በማበርከት ከመጽሐፉ ሽያጩ የተሰበሰበው ገቢ ለሰባት የተለያዩ ገዳማት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ  እንዲሆን ማድረጋቸው ለቤተ ክርስቲያን፣ ለምእመናንና ለመንግሥት ትልቅ የቤት ሥራ የሠጠ ተግባር ነው ሲሉ ተናግረዋል።  ዘመናዊ የትምህርት ተቋማት ከመንፈሳዊ የዕውቀት ተቋማት ጋር ተለያይተው ሥራ መጀመራቸው አሁን በሀገራችን ለምናየው ምስቅልቅል መንሥኤ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ ለዚህ ሀገራዊ ችግር መፍትሔ ለመስጠትም ሀገራዊ  ዩኒቨርሲቲዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሀገር በቀል ዕውቀት ከፍተኛ ትኩረት እየሰጡ መሆናቸውን ጠቁመው  የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲም ለወደፊቱ ከገዳማት ጋር በጋራ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።  ሌላው በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ደራስያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን ፈለገ ጥበብ ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ የመጀመሪያ መጽሐፋቸውን በስጦታ በመለገስ የኢኮኖሚና የመሠረተ ልማት ችግር ያለባቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት እንዲረዱበት ማድረጋቸው የሚያስመሰግንና ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ነው ያሉ ሲሆን መጽሐፉ እጅግ ተነባቢ በመሆኑ ከንባብ ባህል ርቆ የቆየውን ትውልድ ወደ ንባብ ባህል እንዲመለስ ያደረገ መጽሐፍ እንደሆነም አስረድተዋል።  የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መላኩ አላምረው በበኩላቸው “አንዳንድ መጻሕፍት የጥላቻ ሐውልትን የሚተክሉ ሲሆኑ እንደፈለገ ጥበብ ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ ዓይነቱ መጽሐፍ ደግሞ ለአንባብያን የሥጋና የመንፈስን ዕውቀት ከመጨመራቸው ባሻገር የሚለካ መልካም ውጤትም ያስገኛሉ” ብለዋል።  በሀገራችን በአብዛኛው ለቱሪስት መስህብነት የሚያገለግሉት ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳማት እንደሆኑ የጠቆሙት ኃላፊው ገዳማቱ የጎብኝዎቻቸው ቁጥር እንዲጨምርና በገቢ ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንደሆነም ተናግረዋል።  

 

በዕለቱ ተገኝተው ቃለ ምዕዳን የሰጡት የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የገዳማትን ችግር መፍታት የቤተ ክርስቲያን ድርሻ ብቻ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ አንሥተው ገዳማትና የአብነት  ትምህርት ቤቶች የሀገር መሠረቶች በመሆናቸው የአሁኑ ትውልድ እነዚህን የሀገር መሠረቶች ጠብቆና ተንከባክቦ ለመጭው ትውልድ የማስተላለፍ ኃለፊነት እንዳለበት አስረድተዋል። 

ዘመን ክዷቸው ተሸፍነው የቆዩ ገዳማት “እመጓ” በተሰኘው የፈለገ ጥበብ ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ መጽሐፍ አማካይነት መተዋወቃቸውና ከመጽሐፉ ሽያጭ የተገኘው ሙሉ ገቢም ችግር ላይ ለወደቁ ሰባት ገዳማት ፕሮጀክት መፈጸሚያ መዋሉ አስደሳች እንደሆነ የተናገሩት ብፁዕነታቸው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያናቸው ያልታደሱ ገዳማት እንደገና ታድሰው፣ የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ  የሌላቸው  ገዳማውያንም ምግብና ልብስ አግኝተው የተጠናከረ ገዳማዊ ሕይወትን እንዲመሩ መሠራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።  እጅግ አስተማሪዎች፣ ትውልድን የሚማርኩ፣ የትውልዱን ማንነት የሚገነቡ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ የሚያስረዱ፣ ትወልድንም በሥነ ምግባር የሚያንጹ የጽሑፍ ሥራዎች ሊሠሩ እንደሚገባም ብፁዕነታቸው መክረዋል።  

ብፁዕነታቸው አያይዘውም ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን በገዳማት ላይ እየሠራ ያለው መልካም ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው ከዚህ በፊት ብዙ ሠርቷል፤ ብዙም እየሠራ ነው፤ ወደፊትም ብዙ እንደሚሠራ እናምናለን›› ብለዋል።  የእመጓ መጽሐፍ ደራሲ ፈለገ ጥበብ ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ በዕለቱ ባስተለፉት መልእክት አብዛኞቹ የቱሪስት መዳረሻዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሀብቶች መሆናቸውን አስረድተው እነዚህ የቱሪስት መዳረሻዎች የትውልዱን ሞራል ከመገንባት ባሻገር መንፈሳዊ ርካታን የሚሰጡ ቦታዎች ናቸው ካሉ በኋላ የገዳማቱን ገቢ በመጨመር ራሳቸውን የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል። 

ደራሲው አያይዘውም ኢትዮጵያ ከሌሎች ተቋማት ከምታገኘው ገቢ ይልቅ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሚተዳደሩ መንፈሳዊ ቅርሶችና የቱሪስት መስሕቦች የምታገኘው ገቢ ይበልጣል ካሉ በኋላ ሀገሪቱ ከምንጊዜውም በበለጠ ገቢ ለመሰብሰብ መንግሥት ገዳማቱን መንከባከብ፣ ማደስ እንዲሁም ራሳቸውን በገቢ እንዲችሉ ማገዝ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።  አክለውም ይህ ተግባር የመንግሥትና የቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱ ዜጎች ድርሻ ሊሆን እንደሚገባም በመጠቆም።  ‹‹እኔ ባለኝ አቅም የድርሻዬን ለመወጣት በማሰብ ጥሬ ገንዘብ የመሥጠት አቅም ባይኖረኝም የመጀመሪያ መጽሐፌ የሆነውን “እመጓ” መጽሐፍ ለገዳማት ማጠናከሪያ እንዲሆን በሥጦታ አበርክቻለሁ›› ያሉት የመጽሐፉ ደራሲ ፈለገ ጥበብ ዶ/ር ዓለማየሁ ‹‹መጽሐፉን ለማኅበረ ቅዱሳን በኃላፊነት መስጠቴ ከመጽሐፉ ሽያጭ የተገኘው ከ፬.፰ ( አራት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር) በላይ ለሰባት ገዳማት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ መዋሉ በትንሹም ቢሆን ክርስቲያናዊ ግዴታዬን እንደተወጣሁ እንዳስብ አድርጎኛል›› ብለዋል።  የእመጓ መጽሐፍ ሽያጭ ገቢ ሰባት ገዳማትን መርዳት ከቻለ ሁሉም የድርሻውን ቢወጣ መንፈሳዊ ቦታዎች ተጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችል ተግባር እንደሚሠራ ገልጸዋል።  

በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ማስተባበሪያ ም/ኃላፊ ዲ/ን አንድነት ተፈራ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባቀረቡት ሪፖርት የአብነት ትምህርት ቤቶች መምህራንና ተማሪዎቻቸው እንዲሁም ገዳማውያን ማንኛውም ዜጋ ከመንግሥት የሚያገኘውን ማኅበራዊ አገልግሎት እያገኙ ባለመሆናቸው ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን አስተባብራ የማኅበራዊ አገልግሎት ተቋማትንና መሠረተ ልማቶችን ተደራሽ እንደምታደርግ ተናግረዋል።  

ፈለገ ጥበብ ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ የመጀመሪያ መጽሐፋቸው የሆነውን እመጓ መጽሐፍ ለማስተባበሪያው በስጦታ ሰጥተው ከመጽሐፉ ሽያጭ የተገኘው ከ፬.፰ (አራት ነጥብ አምስት) ሚሊዮን ብር በላይ ለአርብዓ ሐራ መድኃኔ ዓለም ገዳም የአብነት ተማሪዎች ማደሪያ ሕንፃ ፣ ለናዳ ቅድስት ማርያም ገዳም ለእርሻ ትራክተር መግዣ፣ ለእመጓ ቅዱስ ዑራኤል ለልማት አገልግሎት የሚውል የከተማ ቦታ መግዣ፣ ለአምስቲያ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የመጠጥ ውኃ ፕሮጄክት፣ ለዋሻ አቡነ እንድርያስ የወፍጮ ፕሮጄክትና ለግሽ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ሙዚየም ግንባታ እንደዋለ በሪፖርቱ አብራርተዋል። 

ም/ኃላፊው አያይዘውም ፈለገ ጥበብ ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴን እንደ አብነት በማየት ምእመናንም ሆኑ የሀገር ቅርስ ይመለከተኛል የሚሉ ሁሉ ገዳማት በገቢ ራሳቸውን እንዲችሉ በሚደረገው ተግባር ሁሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

Read 801 times