Tuesday, 09 February 2021 00:00

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል (ዶ/ር) ሊቀ ጳጳስ ከ፲፱፻፴፫-፳፻፲፫ ዓ.ም ክፍል ሁለት

Written by  መጽሐፈ ሲራክ

Overview

የተወደዳችሁ አንባብያን የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ከዚህ በፊት በነበረው እትም ላይ ማቅረባችን ይታወሳል።  ቀጣዩንና የመጨረሻውን ክፍል ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።  ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ከ፲፱፻፺ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ፳፻ ዓ.ም ድረስ ‹‹በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ተመድበው ጥንታውያን ገዳማትን አስተዳድረዋል›› በሚለው ዐረፍተ ነገር የዓ.ም ስሕተት አለበት።  ብፁዕነታቸው በኢየሩሳሌም የቆዩት ለ፲ ዓመት ሳይሆን ከ፲፱፻፺ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ፲፱፻፺፫ ዓ.ም ለ፫ ዓመት ከ፭ ወር ነው።  ቀሪውን ማለትም ከ፲፱፻፺፫ ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ እስከ ፳፻ ዓ.ም ድረስ ያለውን ጊዜ የቆዩት ደግሞ አሜሪካን ሀገር መሆኑን እየገለጽን ለተፈጠረው ስሕተት ይቅርታ እንጠይቃለን።   ብፁዕነታቸው የመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በሩሲያና በአሜሪካን ተምረው እዚያው ኮሌጅ ተመድበው የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናትን ታሪክ በማስተማር ላይ ነበሩ።  በ፲፱፻፸ ዓ.ም ለይፋዊ ጉብኝት እና ስብሰባ ወደ ሩሲያ በሄዱት ሦስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጥሪ እንደተደረገላቸው አውስተናል።  በጊዜው የቅዱስነታቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት የመጡት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል (ዶ/ር)ወቅቱ በ፲፱፻፸ ዓ.ም ቀይ ሽብር የሚካሄድበትና ብዙ ሰው የሚገደልበት ወቅት ስለነበር በተለይም በሀገራችን ታላቅ ሕዝባዊ ቀውስ ስለነበር ሰዎች እዚያው እንዲቀሩ ቢለምኗቸውም የቅዱስ ፓትርያርኩን ‹‹ሀገርህ ትፈልግሃለች ›› ጥሪ ችላ ብለው ጥሪያቸው ማርኳቸው ወደ ሀገር እንደተመለሱ የሕይወት መቅረት እንዳልቻሉ ይልቁንም አባታዊ ፍቅራቸውና ታሪካቸው ይናገራል።   

 

መንፈሳዊ አገልግሎትን  በዚያው በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የጀመሩት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል (ዶ/ር) ሊቀ ጳጳስ እስካረፉበት ኅዳር ወር ፳፻፲፫ ዓ.ም ድረስ ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት በሙሉ አቅማቸው፣ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ሲያገለግሉ ኖረዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ሆነው በሚሠሩበት ጊዜም ብዙ መንፈሳዊ ሥራዎችን አከናውነዋል።  በአምስት ክፍላተ ሀገራት የካህናት ማሠልጠኛ እንዲከፈቱ አድርገዋል፤ካህናት በስብከተ ወንጌልና በሌሎችም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲሳተፉ እና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግም ችለዋል። 

ቤተ ክርስቲያን በብዙ መንገድ ራስዋን እንድትችል መንፈሳዊነቷን ጠብቃ መዘመን ይገባታል የሚለውን ሐሳብ ያራምዱ የነበሩት ብፁዕነታቸው ይህን በጎ ሐሳባቸውን በተመደቡበት ቦታ ሁሉ ለመተግበር ሞክረዋል።  በተለይ እርሳቸው ተመድበው ባገለገሉባቸው መምሪያዎች ለምሳሌ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት እንዲሁም በመንበረ ፓትርያርክ የሕዝብ ግንኙነትና የውጭ ጉዳይ መምሪያ ቀደም ብለው የተቋቋሙ ሆነው ሳለ እንደ ዕድሜያቸው እድገት እና ለውጥ አለማሳየታቸውን በቁጭት ይናገራሉ።  በተመደቡበት የሥራ መስክ ለውጥን ለማምጣት ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር ቤተ ክህነቱ አምባገነናዊና ዝርክርክ አሠራርን እንዲያስወግድ፣ የቤተ ክህነትንና የቤተ ክርስቲያንን የሥራ ችግር ሊፈታ የሚችል ሥር ነቀል የሆነ የአሠራርና የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲሁም ዘመኑን የተከተለ የአስተዳደር ዘይቤ ያስፈልጋል በማለት በግልጽ ይናገሩ ነበር።  

ብፁዕነታቸው የኤርትራ ክፍለ ሀገር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን ከአንዴም ሁለት ጊዜ ባገለገሉባቸው ዓመታት ሕዝቡን ከማስተማርና ከማጽናናታቸው ባሻገር ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎችን ሠርተዋል።  ‹‹እግዚአብሔር የለም›› በሚለው የደርግ ሥርዓት ውስጥ ቤተ ክርስቲያንን እና ኢትዮጵያን በተመለከተ ደርግን ፊት ለፊት በድፍረት በመናገር፣ በመገሠጽ እንዲሁም በመምከር አባታዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል።  በ፲፱፻፸፬ ዓ.ም በደርግ እና በሻዕቢያ መካከል እየተፋፋመ በመጣው ጦርነት ሳቢያ በነበረው ስብሰባ ላይ የተገኙት ብፁዕነታቸው ከሌሎች በተለየ የሀገሪቱን መሪ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ‹‹ጦርነት ቆሞ ሰላምና ዕርቅ ሊወርድ ይገባል፤ እልቂቱንም አንደግፍም›› በማለት ፊት ለፊት ሞግተዋል።  በኋላ ላይ የተነሣውንና ተግባራዊ የሆነውን የኤርትራን መገንጠል ጉዳይ “ኤርትራ አንገት ናት አትገነጠልም” በማለት እንደ አንድ መንፈሳዊ አባት የኢትዮጵያውያንን የመንፈስና የሥጋ ትስስር እንዲሁም ለዘመናት የቆየ አንድነት አስተጋብተዋል። 

በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመነ ፕትርክና በቅዱስነታቸውና በቅዱስ ሲኖዶስ ትእዛዝም  በካረቢያን ሀገራት ሊቀ ጳጳስ ሆነው በመመደብ አገልግለዋል።  በጊዜው በውጭው ዓለም ሲኖዶስ የመመሥረት ሙከራ እና እንቅስቃሴ ስለነበር ቤተ ክህነቱ ለሁለት እንዳይከፈል ሕዝቡን በማረጋጋት  የመንፈሳዊ አባትነት ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል።  በዚያም ለ፳ ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩት አባት ኤጲስ ቆጶስ እንዲኾኑ ለፓትርያርኩና ለቅዱስ ሲኖዶሱ ጥቆማ በማቅረብ ወደ አዲስ አበባ በመማጣት በሢመተ ጵጵስና ብፁዕ አቡነ ታዴዎስ ተብለው ተሰይመው ወደ ትሪናዳድና ቶቤጐ እንዲሄዱ አድርገዋል።  የካረቢያንና ላቲን አሜሪካ ሀገሮችን (ሀገረ ስብከት) መንበርንም ለእርሳቸው በማስረከብ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ወጥነት ባለው መልኩ እንዲካሄድ በማድረግ እና አባታዊ ተልእኮአቸውን በመወጣት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። 

ብፁዕነታቸው በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በነበራቸው የሦስት ዓመት አገልግሎት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ጥንታውያን ገዳማትን አስተዳድረዋል።  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢየሩሳሌም ባላት ገዳማት ላይ ባለ መብት እንድትሆን በጊዜው ከነበሩት የኢትዮጵያ አምባሳደር በእስራኤል እንዲሁም ከእስራኤል መንግሥት ጋር ብዙ ሠርተዋል።  በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ርስት የሆነው የዴር ሡልጣንን ጉዳይ  ለቅዱስ ሲኖዶስ  በማቅረብ ቅዱስ ሲኖዶስ ተወያይቶበት ጉዳዩን የሚከታተሉ የመንግሥት እና የቤተ ክርስቲያን አካላት ያሉበት ኮሚቴ እንዲቋቋም አስደርገዋል።  ከዚህም በተጨማሪ ከመንግሥት ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ርስት የሆነውን ዴር ሡልጣንን ሊቀሙን የተለያየ ዘዴ እየተጠቀሙ ያሉትን ግብጻውያንን ለማስቆምና ቤተ ክርስቲያን የርስቷ ሕጋዊ ባለቤት ሆና እንድትዘልቅ መንግሥት ከቤተ ክርስቲያን ጎን እንዲቆም ሲያሳስቡ ኖረዋል።  

ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል (ዶ/ር)ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱም በኋላ በተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረው ቤተ ክርስቲያንን አገልግለዋል።  ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎት ከሰጡባቸው ቦታዎች ውስጥ  የሲዳማ፣ጌዴኦ አማሮና ቡርጂ ዞን ሀገረ ስብከት አንዱ ነው።  ከኅዳር ወር ፳፻፫ ዓ.ም ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ በጸሎትና በቡራኬ እንዲቆዩ እስከተወሰነበት እስከ ጥቅምት ፳፻፲፫ ዓ.ም ድረስ በርካታ ሐዋርያዊ አገልግሎትን በሀገረ ስብከቱ ላይ አከናውነዋል።  በሀገረ ስብከቱ የሚነገሩ የሲዳምኛ፣ጌዴኦኛ፣ ኮሬ እና ቡርጂኛ ማስተማር የሚችሉ ካህናትን እና ሰባክያንን ወንጌል በማሠልጠን እንዲሁም በማሰማራት ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ አድርገዋል።  በዚህ መንፈሳዊ እንቅስቃሴም ከ፶ ሺህ በላይ አዳዲስ አማንያንን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ተወልደው ልጅነትን እንዲያገኙ አድርገዋል።  በሐዋርያዊ ጉዞም ምእመናንን በዕለታዊ የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብራት ከመሳተፍ ጀምሮ በክብረ በዓላት እንዲሁም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ወቅትም ጭምር  ችግሩ በተከሠተበት አካባቢ በአካል በመገኘት ምእመናንን ሲያስተምሩ እና ሲያጽናኑ ቆይተዋል። 

ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል (ዶ/ር)አብያተ ክርስቲያናት ባልተተከሉባቸው አካባቢዎች የስብከተ ወንጌል ኬላዎች እንዲከፈቱ በማድረግ ትምህርተ ወንጌል እንዲሰጥ አድርገዋል።  በዚህ ረገድ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በመሆን በሀገረ ስብከቱ የሚያከናውሙ የስብከተ ወንጌል አገልግሎቶችን በማስፋፋት እንቅስቃሴዎች ውጤታማ እንዲሆኑ አድርገዋል።  የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳምም ዕውቅና እንዲያገኝና በደብዳቤ እንዲጸድቅ አድርገዋል።  ወንዶ ገነት ደብረ ገነት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳምም እንዲሁ ዓመታዊ የበጀት ድጋፍ እንድታገኝ ክትትል በማድረጋቸው ገዳማዊ ሥርዐት እንዲጠናከር አድርገዋል። ለሐዋሳ ደብረ መንክራት ቅዱስ ሚካኤል ወቅዱስ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም ደግሞ በድጋፍ መልክ በጀት በመስጠት ገዳሙ የአብነት ትምህርት ማዕከል እንዲሆን በማድረግ አገልጋዮችና መምህራንን እንዲያፈራ አስችለዋል። 

ከዚህ ቀደም ተሠርተው በአዲስ መልኩ ከታነፁት በርካታ አብያተ ክርስቲያናት በተጨማሪ ፵፰ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነጹ አድርገዋል።  ገዳማትና አድባራት ገቢ ማስገኛ ሕንፃዎችን እንዲያንጹ፣ የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን ዕጽዋት በየጊዜው እንዲተክሉ እንዲሁም ዳቦ ቤት፣ ከብት ርባታ፣ ትምህርት ቤት እና የመሳሰሉት የልማት ተቋማት እንዲሠሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።  

ብፁዕነታቸው ቤተ ክርስቲያን በዘመነ መንገድ ተደራጅታ ራስዋን እንድትችልና ከልመና እንድትወጣ በዘመናቸው ሲሠሩ ኖረዋል።  ከልጅነት የአብነት ትምህርት ቤት ሕይዎታቸው ጀምሮ ከዚህ ዓለም ድካም እስካረፉበት ጊዜ ድረስ ብዙ ፈተናዎችን በትዕግሥት በማለፍ ለቤተ ክርስቲያን ሲሠሩ ኖረዋል።  በተለይ የሲዳማ፣ጌዴኦ አማሮና ቡርጂ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ሲያገለግሉ በቁጥር አነስተኛ የሆነው የሀገረ ስብከቱ ምእመን በሌሎች እምነት ተከታዮች የሚደርስበትን ጫናና ፈተና አብረው በመካፈል በዚህ ረገድ በጎ ሥራዎችን ሠርተዋል።  ከመንግሥትም ሆነ ከሌሎች ቤተ እምነቶች የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት፣ ምእመናንንም በማጽናናት እንዲሁም የፈረሱ እና የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናትን እንደገና አሳንፀዋል። 

በተለይ በሀገረ ስብከቱ ላይ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ መሠረቱን ጥሎ ለመስፋፋት ጥረት ሲያደርግ በነበረበት ወቅት ወደ ጥፋት መንገድ እየተጓዙ የነበሩ እኅቶችና ወንድሞችን በጸሎትና በትምህርት እንዲመለሱ አድርገዋል።  በስሕተታቸው ጸንተው የሚገኙትና በምክር መመለስ አሻፈረኝ ያሉትን ግለሰቦች ተገቢ መረጃዎችን ለቅዱስ ሲኖዶስ በማቅረብ ከምእመናን አንድነት እንዲለዩ ከማድረግ ባሻገር እንዲህ አይነቱን ሁኔታ በዘላቂነት ለመከላከል የተጠናከረ የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ሲያስፋፉ ቆይተዋል። 

ብፁዕነታቸው በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸውን መንፈሳዊ አገልግሎት በትጋት ከመወጣት ባሻገር ከሌሎች አኃት አብያተ ክርስቲያናት ጋር የጠበቀ ግኑኝነት እንዲኖራት ብዙ ሠርተዋል።  ለምሳሌ በኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያት ክርስቲያናትና በምሥራቅ ኦርቶዶክስ መካከል በነበረው የነገረ መለኮት ውይይት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በመወከል በርካታ ውይይቶችን ተሳትፈዋል።  በደርግ ዘመንም ሁለተኛው ቅዱስ ፓትርያርክ በግፍ በመገደላቸው ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና የእስክንድርያ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግንኙነት እንደገና እንዲጀመር፣ በሌሎች ኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የነበረው ግንኙነትም ይበልጥ እንዲጠናከር ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። 

በኦሪንታል ኦርቶዶክስና እና በሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በቪየና ሲደረግ የነበረውን ይፋዊ ያልሆነ የነገረ መለኮት ውይይትና የኦሪየንታል አብያተ ክርስቲያናት ከአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ጋር በነበረው ውይይት የዓለም አቀፉ የነገረ መለኮት ጉባኤ አባል በመሆን አገልግለዋል።  በአውሮፓውያን አቆጣጠር ፳፻፲፫  በእኛ በጥቅምት ወር ፳፻፭ ዓ.ም ደቡብ ኮርያ ቡሳን ላይ በተካሔደው በዐሥረኛው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት አጠቃላይ ጉባኤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ልዑካን በመምራት የጠቅላላ ጉባኤው አባል በመሆን ተሳትፈዋል።  

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ጉባኤ በመመሥረት እንዲሁም ለተከታታይ ስድስት ዓመታት ያህል የጉባኤው የቦርድ ሰብሳቢና የካውንስል ጉባኤው ሰብሳቢ በመሆን ከሐዋሳ አዲስ አበባ ድረስ እየተመላለሱ ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸውን ኃፊነት በብቃት በመወጣት ያለመሰልቸት አገልግለዋል።   

በአንዳንዶች ዘንድ ‹‹ ለውጥ ፈላጊ ጳጳስ ›› የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል (ዶ/ር)በቤተ ክህነቱ ውስጥ የሰፈነውን ደካማና ኋላ ቀር አስተዳደር እንዲሻሻል ይፈልጉ እንደነበር ከሥራዎቻቸው ባሻገር በየጊዜው የሚጽፏቸው መጣጥፎች ምሥክሮች ናቸው።  በተለያዩ በመገናኛ ብዙኃን ላይ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ጉዳይ ላይ የሚያዩትን ክፍተቶች እርምት እንዲሰጥባቸው፣ ምእመናንም ሊያውቋቸው ይገባል ያሏቸውን ሞጋች የኾኑ ሐሳቦችን በማንሣት በበርካታ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ጽፈዋል፤ ሞግተዋል፤ አባታዊ አበርክቶአቸውን አስነብበውናል።  ለምሳሌ ሊቃነ ጳጳሳት በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፣ ሰላም ይስፈን፤ በቤተ ክህነት ባለሥልጣናትና ከሥራ በተወገዱ ሊቃውንት መካከል የተፈጠረው የከረረ ጸብ በዕርቅ ይፈታ፤ የገንዘብ ምዝበራው ይቁም፤ ቤተ ክርስቲያን በሕገ ሐዋርያት በሲኖዶስ ትመራ፤ በየጋዜጣው የሚጻፈው የዘለፋና የነውር ደብዳቤ በዕርቅ ይቁም… ከጻፏቸው መጣጥፍ ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው። 

ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል (ዶ/ር)በቋንቋ ደረጃ ከሀገራቸው ቋንቋዎች በተጨማሪ የእንግሊዝኛ፣ ቤሎሩስ፣ ሁለት የሩሲያ ዲያሌክት፣ የግሪክ ቋንቋዎችን በብቃት የሚናገሩ ሲሆን  አርመንያን ቋንቋ በመጠኑ የሚናገሩ፣ ዓለም አቀፍ ሰብዕና የነበራቸው፣ መጻሕፍትን ማንበብና መመርመር የሚያስደስታቸው ታላቅ ምሁርና አባት ነበሩ። ብፁዕነታቸው ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በጸሎት፣ በጸበልና በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ፹ ዓመታቸው  ኅዳር ፳፮ ቀን ፳፻፲፫  ዓ.ም ከዚህ ዓለም ወደማያልፈው ዓለም ከሞት ወደ ሕይወት ከድካም ወደ ዕረፍት ተሻግረዋል።  

የተከበረ አስከሬናቸውም በዕለቱ ከቀኑ ዐሥር ሰዓት ላይ ወደ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተወስዶ ጸሎተ ፍትሐት ሲደረስበትና ሲቀደስበት ካደረ በኋላ ሥርዓተ ቀብራቸው ፦ 

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ወኤጲስ ቆጶሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የየመሪያውና የየድርጅቱ ኃላፊዎች

የአዲስ አበባ ሀገረ ሰብከት ሠራተኖች የሥራ ኃላፊዎች አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች

እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት 

 

ኅዳር ፳፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ከጠዋቱ በ፬፡ሰዓት በአዲስ አበባ መንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።  

 

Read 167 times