Tuesday, 23 February 2021 00:00

የአብነት ትምህርት ቤቶችን የማስፋትና የማጠናከር ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ተገለጠ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን የአብነት ትምህርት ቤቶችን የማስፋትና የማጠናከር ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ የቅዱሳት መካናትና መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ማስተባበሪያ ምክትል ኃላፊ ዲ/ን አንድነት ብርሃኑ ገለጡ።    በአብነት ትምህርት ቤቶች ማስፋፊያ መርሐ ግብር ላይ የአብነት ትምህርት ቤቶች የሌላቸው አካባቢዎች ተለይተው አዳዲስ ትምህርት ቤቶች የሚቋቋሙ ሲሆን በማጠናከሪያ መርሐ ግብር ደግሞ የአብነት ትምህርት ቤቶችን የማሻሻልና የመደገፍ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ም/ኃላፊው ገልጸዋል።    ማኅበረ ቅዱሳን ሃያ አምስት አህጉረ ስብከት ለይቶ የአብነት ትምህርት ቤቶችን በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ የገለጡት ኃላፊው “በዚህ ዓመት ብቻ በአራት አህጉረ ስብከት የአብነት ት/ቤቶችን ለመሥራት እቅድ ይዟል” ብለዋል። እቅድ ከተያዘላቸው አራት አህጉረ ስብከት መካከል አፋር፣ ሶማሌ፣ አርሲና ምሥራቅ ወለጋ አህጉረ ስብከት እንደሚገኙበት ያስታወቁት ኃላፊው የሶማሌ ሀገረ ስብከት የአብነት ትምህርት ቤት በቅርቡ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት ሲሆን በዚህ ወርም የግንባታ ሥራው እንደሚጀመር ተናግረዋል።    ሌሎች ተመሳሳይ የአብነት ትምህርት ቤቶች ግንባታም በሂደት ሥራቸው እንደሚጀመር አስረድተዋል።    አዲስ በሚቋቋሙ የአብነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የአካባቢያቸውን ባህልና ቋንቋ ጠንቅቀው የሚያውቁ ወጣቶች ተመልምለው እንደሚገቡ ያስረዱት ኃላፊው በሚኖራቸው የሁለት ዓመት ቆይታም የቤተ መቅደስና የዐውደ ምህረት አገልግሎትን እንደሚቀስሙ ተናግረዋል።    ኃላፊው አያይዘውም ማኅበረ ቅዱሳን የአብነት ት/ቤቶችን ከማቋቋምና ከማጠናከር ባሻገር ጊዜያዊ የገንዘብ ድጋፍም እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል።    አጠቃላይ ለተማሪዎችና ለመምህራን የሚደረገው ወርኅዊ የገንዘብ ድጋፍ በዓመት እስከ አምስት ሚሊዮን እንደሚደረስም አስረድተዋል።    ባልታወቀ ምክንያት ጥር ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም የሳት ቃጠሎ አደጋ የደረሰበት የጨጎዴ ሃና የቅኔ ማስመሥከሪያ ጉባኤ ቤት በአዲስ መልክ እየተሠራ መሆኑን ም/ ኃላፊው ተናግረዋል።   የቅኔ ማስመስከሪያ ጉባኤ ቤት ፕሮጀክት የተጀመረው ፳፻፪ ዓ.ም ሲሆን ለፕሮጀክቱ የዋለውን ፳ ሺህ ካሬ መሬት የሰጠው የምዕራብ ጎጃም ዞን የቋሪት ወረዳት መንግሥት ነው።    ፕሮጀክቱ የተማሪዎች ማደሪያ፣ የመምህራን መኖሪያ፣ የተማሪዎች መፀዳጃ ቤትና የምግብ ማብሰያ ያካተተ ሲሆን ሲጠናቀቅም በርካታ ነባርና አዳዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ እንደሚያስተናግድ ም/ኃላፊው ገልጸዋል።    ፕሮጀክቱ ከ፵፭ በመቶ በላይ የደረሰ ቢሆንም በዚህ ወቅት ግን የበጀት እጥረት እንደገጠመው አስረድተው የተፈለገው ያህል በጀት የሚገኝ ከሆነ ግን በቅርቡ መጠናቀቅ እንደሚችል አስታውቀዋል።    የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጭ እስከ አምስት ሚሊዮን ብር የሚደርስ ሲሆን ከዚህ ቀደም ወጭ የተደረገው  ገንዘብ ከምእመናን ድጋፍ የተገኘ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው “አዳዲስ የሚቋቋሙና ነባር የአብነት ትምህርት ቤቶች ራሳቸውን በገቢ የሚችሉበትን መንገድ መፈለግ ያስፈልጋል” ሲሉም ተናግረዋል።   
Read 691 times