Tuesday, 23 February 2021 00:00

ቤተ ክርስቲያንን ያከበረች ከተማ…

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ፈተና ያልተለያት እንደሆነች በዘመናት ውስጥ ከተጻፉ የታሪክ ድርሳናት  መረዳት ይቻላል። ቤተ ክርስቲያን በፀረ ክርስቲያን ኃይሎች መፈተኗ አላጠፋትም፤ ምእመናንንም ከአምልኮተ እግዚአብሔር አላራቃቸውም።   ይልቁንም ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮዋን እያሰፋች ለዓለም ብርሃን መሆኗን ቀጥላለች።    ከዘመናዊ ትምህርት ዘርፉ ከሚገኝ ዕውቀት በበለጠ የቋንቋ፣ የሥነ ጥበብ፣ የኪነ ሕንፃና የፍልስፍና ምንጭ ሆና መቀጠሏ ዓለም ያወቀው ገሃድ ነው።  ይሁን እንጂ ኃያልነቷንና ታሪካዊነቷን የተረዱና ያልተረዱ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ሌት ተቀን ከሚያልሙ ፀረ ክርስቲያን ኃይሎች መገኛ ሀገራት መካከል ሀገራችን ኢትዮጵያ አንዷ ናት።    

 

ሀገራችን ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር ከመሆኗ ጋር ተያይዞ  በሰላምና በፍቅር ተከባብሮ አብሮ በመኖር የዓለም ተምሳሌት ብትሆንም በጉያዋ የበቀሉ አንዳንድ እሾሆች ግን ቤተ ክርስቲያንን ሲወጓት ይስተዋላሉ። እነዚህ ኃይሎች ቤተ ክርስቲያንን ለመውጋታቸው መነሻ ምክንያት ምንድነው ብለን ስንጠይቅ በስሑት ትርክት ተነሣሥተውና ‹‹የእኛ›› የሚሉትን ሃይማኖት በሌላው ላይ ለመጫን በማለም እንደሆነ ድርጊታቸው ይመሰክራል። ከዚህም ባሻገር በሀገሪቱ ኦርቶዶክሳዊ ዕሤቶቻችን በማጥፋት የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማዳከምና የማትጠፋውን ቤተ ክርስቲያን ለማጥፋት ይታትራሉ። 

የጥፋት ኃይሎች የጥፋት እጃቸውን በመላው ኢትዮጵያ ባሉ ኦርቶዶክሳውያ ክርስቲያኖች ላይ የሚሰነዝሩ ቢሆኑም በተለይ ግን ሕዝበ ሙስሊሙ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ማለትም በሶማሌ፣ በሐረሪ እና በኦሮምያ ክልሎች፣ በድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር እና በአማራ ክልል የኦሮሞ ልዩ ዞን አካባቢዎች ለክርስቲያኖች የሥጋት ቀጠናዎች ሆነው ቆይተዋል።   በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ከጥንት እስከዛሬ አልፎ አልፎ በእምነታቸው ምክንያት በግፍ ሲገደሉ፤ ሃይማኖታቸውን ተገደው እንዲቀይሩ ሲደረግ፤ ሀብት ንብረታቸው ሲዘረፍ ሲቃጠል እንዲሁም ከማኅበራዊና ፖለቲካዊ አደረጃጀቶች ሆን ተብሎ እንዲገለሉ ሲደረግ ቆይቷል።

በቅርቡ እንኳን በ፳፻፲፪ ዓ.ም በርካታ ኦርቶዶሳውያን ክርስቲያኖች በእምነታቸው ምክንያት ብዙ ዋጋ ከፍለዋል።   ቤተ ክርስቲያን በየጊዜው ለሚመለከተው አካል አቤቱታ ብታቀርብም ችግሩ ከመስፋቱ ውጭ ተጨባጭ መፍትሔ ሳታገኝ በርካታ ጊዜያት አልፈዋል።    

ነገር ግን አንዳንድ አካባቢዎች የመንግሥትን ማስጠንቀቂያና የቤተ ክርስቲያንን አቤቱታ አድምጠው ችግሩን በሂደት ያስተካከሉ መኖራቸውን መናገር ተገቢ ነው። ከእነዚህ አካባቢዎች መካከል የሶማሌ እና የሐረሪ ክልሎች እንዲሁም የድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር ይገኙበታል።  ሌሎቹን በሌላ ጊዜ የምናነሣቸው ሆኖ የድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደር ከጊዜ በኋላ ለኦርቶዶክሳውያንና ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ተከትሎ ቤተ ክርስቲያን ስለሰጠችው ዕውቅና በአጭሩ የምንቃኝ ይሆናል።    እንደሚታውቀው በድ ሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምእመናን የዐደባባይ በዓላትን በነፃነት የማያከብሩበት፤ ሥርዓተ አምልኳቸውን በነፃ የማይፈጽሙበትና ከማኅበራዊና ፖለቲካዊ አደረጃጀቶች የተገለሉበት እንደነበር በተለያዩ ጊዜያት ሰምተናል፤ ዓይተናልም። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት በኋላ ከተማ አስተዳደሩ ባስቀመጠው ቁርጠኛ አቅጣጫ የቤተ ክርስቲያንና የምእመናን መብትና ደኅንነት እንዲከበር ተደርጓል።    

ይህም በመሆኑ የምእመናን የደኅንነት ሥጋት ተቀርፏል፤ የቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ጥያቄዎች ተመልሰዋል፤ እንዲሁም የአባቶችና የምእምና ተቀባይነትና አካባቢያዊ ተሳትፎ ጨምሯል። ይህንን መልካም ሥራ በአንክሮት የተመለከተው የድሬ ዳዋ ሀገረ ስብከት በቤተ ክርስቲያን ደረጃ የድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደር ዕውቅና እንዲሰጠው በወሰነው መሠረት ጉዳዩን ለጠቅላይ ቤተ ክህነት አቅርቦ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ከነ ሙሉ ካቢኒያቸው (የሥራ ባልደረቦቻቸው) በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የምስጋናና ዕውቅና መርሐ ግብር ተዘጋጅቶላቸዋል።    በዚህ የዕውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ሙሓዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት (የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ) ተገኝተዋል።    

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያት ፓትርያርክ ርእሳነ ሊቃ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደር ለቤተ ክርስቲያን እያደረገ ባለው ሁለንተናዊ ድጋፍ የመልካም ተምሳሌት መሆኑን ገልጠዋል።   ከተማ አስተዳደሩ ለቤተ ክርስቲያን ያበረከተው አስተዋጽኦ ለሌሎች ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አርአያ ሊሆን እንደሚችል የተናገሩት ቁድስነታቸው አብዛኛው የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ከኦርቶዶክስ እምነት ውጭ መሆናቸውን ጠቅሰው የሃይማኖት ልዩነት ቢኖረንም ፍቅራችንና አንድነታችንን አያሳሳውም ኢትዮጵያዊነታችንም አያጠፋውም ብለዋል።    

ሀገራችን የጋራ እስከሆነች ድረስ ሁሉም ዜጎች ሰብአዊ መብታቸው ተከብሮላቸው በጋራ በአንድነትና በፍቅር ሊኖሩ ይገባል ሲሉም አስረድተዋል።    ቅዱስ ፓትርያርኩ አክለውም ‹‹አንድነታችንና ፍቅራችንን ልንጠብቀው የሚገባው በሃይማኖት፣ በዘርና በቀለም ሳንለያይ ከሆነ ብቻ ነው›› ብለዋል።  የድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደር የሰላምና የልማት ተምሳሌት መሆኑ አመራሮቹ ደስ ሊላቸው ይገባል ካሉ በኋላ ሁሉም የሀገራችን የፖለቲካ አመራሮች የመልካም ሥራ ምሳሌዎችን በመውሰድ ለእውነትና ለሀገር አንድነት እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።    

የድሬ ዳዋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ቀሲስ ማትያስ በቀለ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት የድሬ ዳዋ ሀገረ ስብከት ላለፉት ሦስት ዓመታት ከፍተኛ የሆነ ሁከትና ብጥብጥ ያስተናገደ አካባቢ እንደነበረ አስታውሰው ኦርቶዶኮሳውያን ምእመናን በነፃነት የማያመልኩበትና የዐደባባይ በዓላትንም በሥጋት የሚያከብሩት ወቅት እንደነበረ ተናግረዋል።  ነገር ግን አሁን ያሉት የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ቁርጠኛ በመሆናቸው በሰላምና ልማት ዙሪያ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ተቀራርበው እየሠሩ እንደሆነ አስረድተዋል።    

ቤተ ክርስቲያን በምታደርገው የሰላምና የልማት እንቅስቃሴ ሁሉ ከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ ማድረጉን ያነሡት ሥራ አስኪያጁ ለዚህ መልካም ሥራቸውም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የዕውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር እንደተዘጋጀላቸው አንሥተዋል።  ከተማ አስተዳደሩ ለቤተ ክርስቲያን ተጨማሪ ይዞታዎችን ከመስጠት ባሻገር የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ለሌላቸው የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎችም የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ሠርቶ እንደሰጠም ሥራ አስኪያጁ በዕለቱ አስታውቀዋል።    

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና የልማት ድርጅት ኃላፊ አፈ መምህር አባ ገብረ ሥላሴ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደር ተወርሰው የተመለሱ የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎች እንዳሉ ጠቅሰው ከውርስ ከተመለሱት ቦታዎች መካከል በአንዱ ላይ የገቢ ማስገኛ ሕንፃ ለመሥራት ታኅሣሥ ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በቅዱስ ፓትርያርኩ አማካይነት የመሠረት ድንጋይ እንደተቀመጠ ተናግረዋል።   

የድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አሕመድ መሐመድ ቡህ ለከተማ አስተዳደራቸው ቤተ ክርስቲያን የሰጠችው ዕውቅና እንዳስደሰታቸው ገልጠው ይህም በቀጣይ ለሌላ መልካም ሥራ እንዲነሣሡ እገዛ እንደሚያደርግላቸው ተናግረዋል። ሌላው በመርሐ ግብሩ የተገኙት የድሬ ደዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ልዩ አማካሪና የድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መብራት ገብረየስ በበኩላቸው ቤተ ክርስቲያን ለሀገራችን የኪነ ሕንፃ ጥበብ ዕድገት ያበረከተችውን አስተዋፅኦ አድንቀው ለተደረገላቸው መስተንግዶ፣ አቀባበልና ዕውቅና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።    

የቤተ ክርስቲያንን ጥንታዊትና ዓለም አቀፋዊነት በመረዳት በሀገራችን ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ መደበኛና ኢመደበኛ አደረጃጀቶች  ተገቢውን እውቅናና ድጋፍ በመሥጠት ቤተ ክርስቲያን ለሀገርና ለወገን ያበረከተችውንና እያበረከተች ያለውን አስተዋፅኦ እንድትቀጥልበት ማድረግ ይገባል።  በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች የምትገኙ የፖለቲካ አመራሮችና ቡድኖች የድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደር የመልካም ሥራ ተሞክሮን በመመልከት ለቤተ ክርስቲያን ሁሉን አቀፍ እገዛና ትብብር ልታደርጉ ይገባል እንላለን።   

 

Read 487 times