ስምዐ ጽድቅ፦ አባታችን ከእርስዎ ጋር ይህን ቃለ መጠይቅ እንድናደርግ ስለፈቀዱልን ከልብ እናመሰግናለን። እስኪ የልጅነት ሕይወትዎን ይንገሩን? የት ተወለዱ? የእናትና የአባትዎ ስም ማን ይባላሉ?
መጋቤ ሐዲስ መምህር አባ አእምሮ ብሩ፦ እኔም ይህን ቃለ መጠይቅ እንዳደርግ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ። በርግጥ መነኩሴ እንኳ ሀገር አለኝ ማለት የለበትም ሆኖም ለእናተ ዓላማ የሚጠቅማችሁ ከሆነ የተወለድኩት ሰኔ ፳፯ ቀን ፲፱፻፵፫ ዓ.ም በጎንደር ክፍለ ሀገር (ደቡብ ጎንደር) ልዩ ስሙ የሾ ሚካኤል ከሚባል አጥቢያ ነው። አባቴ ቄስ አስረስ መኮንን ይባላሉ እናቴ ወ/ሮ የሺመቤት ብሩ ትባላለች እኔ የምጠራው በእናቴ አባት ስም ነው። የሚተዳደሩት በግብርና ነው።
ስምዐ ጽድቅ ፦ እስኪ ስለ አብነት ትምህርት ቤት ሕይወትዎ ይንገሩን የአብነት ትምህርት የት የት ተማሩ?
መጋቤ ሐዲስ መምህር አባ አእምሮ፦ ትምህርት ቤት የገባሁት በልጅነቴ ነው ዓመተ ምሕረቱን አሁን ላይ አላስታውስም። ትምህርት የጀመርኩት ከዚያው ከትውልድ ሀገሬ ደቡብ ጎንደር የሾ ሚካኤል ነው። ከፊደል አንስቶ እስከ ዜማ የተማርኩት ከዚያ ነው። ያስተማሩኝ መሪጌታ ውበቱ አድማሴ ይባላሉ። ትምህርቱን እንደጨረስኩ ከአቡነ ዜና ማርቆስ (አሁን አርፈዋል) ዲቁናን ተቀብያለሁ። በዲቁና ትንሽ ካገለገልኩ በኋላ መጀመሪያ የሔድኩት ወደ ደቡብ ጎንደር እስቴ መካነ የሱስ ደብረ ሃይማኖት ደብር ነው። አካሄዴ ከታላቁ መምህር ከመጋቤ ሐዲስ አባ ኃይለ ሚካኤል ዘንድ ሐዲሳትን ለመማር ነበር።
መጽሐፍ አስተምሩኝ ብዬ ወደ እርሳቸው ሄድኩ እንዳገኙኝ ‹‹ቅኔ ተምረሃል ወይ?›› ብለው ጠየቁኝ። አልተማርሁም አልኳቸው እሳቸውም ቅኔ ካልተማርህማ መጽሐፍ ሊሆንህ አይችልም መጀመሪያ ሂድ ቅኔ ተቀኝተህ ና አሉኝ። እኔም ቃላቸውን ተቀብዬ እንዳሉኝ ሁለት ዓመት ቅኔ ቤት ቆየሁ። መጀመሪያ እዚያው ደቡብ ጎንደር ከሚገኙት መሪጌታ ነገድ ተማርሁ፤ሁለተኛ ሞጣ ጊዮርጊስ ከነበሩት አንጋፋው መምህር ገብረ ሥላሴ (አሁን ሰዋሰወ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ ነው ያሉት) ተማርሁ። ቅኔ ተቀኝቼ ሳበቃ ተመልሼ ወደ ደቡብ ጎንደር እስቴ መካነ የሱስ ደብረ ሃይማኖት ታላቁ ደብር ከሚገኙት መጋቤ ሐዲስ መምህር ኃይለ ሚካኤል ዘንድ መጽሐፍ ጀመርኩ ማለት ነው እሳቸውም ተቀብለው ሐዲሳቱን አስተማሩኝ።
ስምዐ ጽድቅ፦ ምንኩስናን የት እና ከማን ተቀበሉ?
መጋቤ ሐዲስ መምህር አባ አእምሮ፦ ምንኩስናን የተቀበልኩት ሐዲሳትን ከተማርኩበት ታላቁ ደብር እስቴ መካነ የሱስ ደብረ ሃይማኖት ደብር ከመምህሬ ከመጋቤ ሐዲስ አባ ኃይለ ሚካኤል ነው። መጋቤ ሐዲስ በአካባቢው የሚታወቁ እና የሚከበሩ ታላቅ ሊቅ ናቸው። በሕይወቴ በትምህርት ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ ሕይወትም አብነት የምላቸው እሳቸውን ነው። በተለይ በምንኩስናው ዓለም ከትምህርቱ ያላነሰ የሕይወት ትምህርት ነው ከእርሳቸው አግኝቻለሁ።
ምንኩስናውን በኅዳር ወር ፲፱፻፹ ዓ.ም ተቀብዬ ወዲያው በታኅሣሥ ወር የቅስናን መዓረግ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ (ያኔ የጎንደር ክፍለ ሀገር ሊቀ ጳጳስ ነበሩ) ተቀበልኩ። መዓረገ ቅስናን እንደተቀበልኩ ወዲያው ወደ ሰሜን ጎንደር መንበረ መንግሥት ነው የሄድኩት። አካሄዴም ብሉይ ኪዳንን ለመማር ነው። ጎንደር መንበረ መንግስት መድኃኔ ዓለም አራቱ ጉባኤ ቤት ሄጄ ከሊቀ ሊቃውንት መንክር መኮንን ዘንድ (ዛሬ ሊቀ ሊቃውንት እዝራ የያዙትን ማለት ነው) ብሉይ ኪዳንን ማለትም ዳዊት ትርጓሜን ተማርኩ ሌሎች የጨመርኳቸውም አሉ። እሱን በጉባኤ እያካሄድኩኝ በትርፍ ጊዜዬ ደግሞ ፋሲል ግንብ አጠገብ ከሚገኝ አደባባይ ኢየሱስ ከሚባል ትልቅ ቦታ መሪጌታ ፅጌ ከሚባሉ መምህር ደብረ አባይ ቅዳሴን ቀጽያለሁ።
ስምዐ ጽድቅ፦ የአብነት ትምህርት ቤት ሕይወትን እንዴት ይገልጹታል?
መጋቤ ሐዲስ መምህር አባ አእምሮ፦ የአብነት ትምህርት ቤት ወይም የቆሎ ትምህርት ቤት ሕይወት ፈተናው ከባድ ነው። በእውነት ተስፋ የሌለው ሰው ሁሉ በተስፋ መንቀሳቀስ አለበት። እኔ በነበርኩበት ዘመን አብነት ትምህርት ቤት እጅግ በጣም ችግር የበዛበት ነበር። ለመማር ችግሩም ረሀቡን፣ ጽሙን፣ መታረዙን ሁሉ በትእግስት ማለፍ ነበረብን። በጊዜው በአብነት ትምህርት ቤት ብዙ ችግር አሳልፈናል።
አሁን ላይ ሁኜ ሳስበው ‹‹ያን ጊዜ የኔ ኃይል ነው እንዴ? አይደለም የእግዚአብሔር ኃይልና ጥበብ ነው ያኖረኝ›› ነው የምለው። እዚህ ለመዘርዘር ጊዜና ቦታ የማይበቃው ብዙ ችግር ነው ያሳለፍነው። ለምሳሌ በዚያን ጊዜ ልብሳችን አንድ አንሶላ እና አንድ ቁምጣ ብቻ ነበረ ቅያሪም የለንም ቀን ለብሰን እንውላለን እስዋኑ ደግሞ ለሌት አድርገ ነው የምንተኛው። ያን ጊዜ የከበደ ወቅት ነበር ማለት ነው። በምግቡም በኩል እንደዚያው ነው ልመና ተወጥቶ ከውሻ ታግሎ የሚገኘው ነገር ጥሬ ከፍ ካለም ወጥ የለው ለምለም እንጀራ ነው። በዚያ ላይ በሽታ አለ ፣ ያን ሁሉ ተቋቁሞ ነው በአብነት ትምህርት ቤት ውስጥ የሚኖረው።
ስምዐ ጽድቅ፦ በአብነት ትምህርት ቤት ሕይወት ውስጥ ውጣ ውረዱ እንዳለ ሆኖ ምን ያስደስቶታል?
መጋቤ ሐዲስ መምህር አባ አእምሮ፦ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ ከቤተሰብ ተለይቶ ርቆ በመሄድ የሚገኘው መንፈሳዊ እውቀት ነፍስን ያለመልማል ልብን ደስ ያሰኛል። በአብነት ትምህርት ቤት ሕይወቴ የምደሰትበት እሱ ነው። ሌላው የሚያስደስተኝ እስቴ መካነ ኢየሱስ እያለሁ አራቱን ወንጌላውያን ትርጓሜ በእጄ መገልበጤ ነው። ቀለም በጥብጬ ብዕር ቀርጬ ደብተር አስምሬ በመጻፌ ትዝ የሚለኝና የሚያስደስተኝ ትልቁ እሱ ነው ማለት ነው፡
እስቴ መካነ ኢየሱስ ከጉባኤ ቤት እያለሁ ወዲያው እንማራለን ጉባኤ ያሄዱልናል የተተረጎመልንን ወጥተን እንጽፋለን። የምንጽፍበትን ደብተር የምንገዛው ደግሞ የቀን ሥራ ሠርተን በምናገኘው ገንዘብ ነው። የሚሠራው ስራ አጨዳ ነበር ለእርሱ የሚከፈለን አንድ ብር ነው። አንድ ብር አራት ደብተር ይገዛል በዚያ ላይ ነው የወንጌላቱን ትርጓሜ ጽፌ የጨረስኩት። ከእስቴ ስወጣ ጽፌ ደጉሼ ነው የወጣሁት። ከአራቱ ወንጌላውያን ውጪም የጻፍኳቸው አሉ። ለምሳሌ ቅዳሴ ማርያም ውዳሴ ማርያም፣ ኪዳን፣ ባህረ ሃሳብ እነዚህን ሁሉ ጽፌ ነው የወጣሁት።
ዐይኔ እንደምታዪው የተፈጥሮ አይደለም ያን ጊዜ የተጎዳ ነው። አሁን በሀገራችን ፀሐፍያን ስንክሳር፣ ተአምረ ማርያም፣ ገድልን በብራና ሲጽፉ ለዐይናቸው ጥንቃቄ ያደርጋሉ። ከራሳቸው ላይ ቅቤ አድርገው ጥሩ ነገር እየበሉ ጥሩ ነገር እየጠጡ ነው የሚጽፉት፤ እኛ ግን በደረቁ ደረቅ ገብስ እየበላን ከተሻለ ደግሞ ከሳምንት አንድ ቀን ቁራሽ ይገኛል ለምለም እንጀራ መቼም አይታሰብም ያን እየበላን ነበር የምንጽፈው። የአብነት ትምህርት ቤት ፈተናው ብዙ ነው ስል ይህን ሁሉ ጨምሮ ነው። አሁን ላይ ሆኜ ያን ሁሉ ጽናትና ብርታት ያን ሁሉ ተስፋ እንድንችል አድርጎ ለዚህ ስላበቃኝ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለው።
ያው ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በእስቴ ጉባኤ ቤት ከትምህርቴ ጎን ለጎን ከላይ የጠቀስኩዋቸውን መጻሕፍት ከገለበጥኩ በኌላ ከመምህሬ ከመጋቤ ሐዲስ አባ ኃይለ ሚካኤል አቡነ ዘበሰማያት ተቀብዬ ብሉይ ኪዳንን ለመማር ሰሜን ጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔ ዓለም አራቱን ጉባኤ ቤት ነው የሔድኩት።
ስምዐ ጽድቅ ፦ በጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔ ዓለም አራቱ ጉባኤ ቤት የዳዊት ትርጓሜን እንዲሁም ሌሎች ትምህርቶችን መማርዎን ፤ በትርፍ ሰዓትዎ ደግሞ በአደባባይ ኢየሱስ ደብረ አባይ ቅዳሴን መቀጸልዎትን ነግረውኛል እዚያ ምን ያህል ጊዜ ቆዩ ምንስ ሠሩ?
መጋቤ ሐዲስ መምህር አባ አእምሮ፦ በጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔ ዓለም ብዙ አልቆየሁም በ፲፱፻፹፭ ዓ.ም በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የናዝሬት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ በስብከተ ወንጌል እና በመጽሐፍ መምህርነት እንዳገለግል በደብዳቤ ተመድቤ ወደዚያው ሄድኩ። እዚያ ለአራት ዓመታት አገልግያለሁ ያን ጊዜ ይሄን ያህል ሰውም አልነበረበትም፤ነገርግን እዚያ የቆየሁባቸው አራት አመታት ትልቅ አገልግሎትም የሰጠሁበትም ነበረ።