Tuesday, 23 February 2021 00:00

“የቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያ ሥራ መሆን ያለበት የልጆቿን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ነው” -ብፁዕ አቡነ አብርሃም (የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ) ክፍል አንድ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አዊ ብሔረሰብ አስተዳድር ቻግኒ ከተማ ዙሪያ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠልለው ይገኛሉ።    የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለማጽናናት፣ ለመባረክ እንዲሁም ከሀገረ ስብከቱ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ርዳታ ለማስረከብ በቦታው በተገኙበት ወቅት ከማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ያደረጉትን አጭር ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል። መልካም ንባባ።     ስምዐ ጽድቅ፡-  በፀጥታ ችግር ምክንያት ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው በአማራ ክልል ቻግኒ ከተማ ዙሪያ የተጠለሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሲያዩ ምን ተሰማዎት? ምንስ ታዘቡ? ብፁዕ አቡነ አብርሃም፡- ቻግኒ ላይ ያየሁት ሁኔታ እጅግ አሳዛኝና ልብን የሚሰብር ክስተት ነው። ከፖለቲካ የራቁና ሠርቶ አርሶ ከመብላት ውጭ ምንም የማያውቁ ዜጎችን ከሞቀ ቤታቸው እያስወጡ በጭካኔ መግደልና ማሳደድ በእውነት ሰብአዊነትን ያላከበረ ተግባር ነው። ምንም የማያውቁ ሕፃናት፣ ለዘመናት ሀገራቸውን በተለያየ መስክ ያገለገሉ የዕድሜ ባለጸጐች ሴቶችንና እናቶችን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ መግደልና ማፈናቀል የወንድነት መለኪያ መስፈርት ሊሆን አይገባም።  ከሞት ጥላ አምልጠው በቻግኒ ከተማ አቅራቢያ ተጠልለው ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የቀን ፀሐይ የማታ ብርድ እየተፈራረቀባቸው ማየት ደግሞ ከምንም በላይ ልብን ያቆስላል።           

        

ይህን ግፍ አይቶ የማያወግዝና በቃ የማይል አካል ካለ ሰውነቱ ያጠራጥራል። እኔ እንደ ሃይማኖት አባትነቴ በቦታው ተገኝቼ ጉዳት የደረሰባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በማፅናናቴና አባታዊ ቡራኬ በመስጠቴ እጅግ ደስ ብሎኛል።    በአንጻሩ ደግሞ ያየሁት ሁኔታ እጅግ ልቤን የሰበረውና ምን ልሠራ እንደሚገባኝ የቤት ሥራ የሰጠኝ ክስተት ሆኖ አግኝቼዋለሁ።  በቦታው በነበረኝ ቆይታም አረመኔ፣ ጨካኞችና ለሰው ልጅ ይሉኝታ የሌላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በሀገራችን እንዳሉ ተረድቻለሁ። ከራሳቸው ስሜት በስተቀር የሰው ቁስልና ስቃይ የማይሰማቸው ሰው መሳይ አውሬዎች እንዳሉ ታዝቤያለሁ። እግዚአብሔር በአምሳሉ ለፈጠረው የሰው ልጅ የማይጨነቁ የመንግሥት አመራሮች በሀገራችን እንዳሉ በቆይታዬ ለመረዳት ችያለሁ።    የተፈናቀሉ ወገኖችን ቦታው ድረስ ሄደን በጠየቅንበት ወቅት የተፈናቃዮቹ ደስታና ያሳዩት የተስፋ ስሜት ለተመልካች ብዙ ያስተምራል።    ይኸውም በሀገራችን ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ምክንያትና ፀጥታ ችግር ለተፈናቀሉና ለተጎሳቆሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በቶሎ ልንደርስላቸው እንደሚገባ ያስተምረናል።  ሀብት አሰባስበን በየቦታው እየሄድን ተጎጂ ወገኖቻችንን በመጠየቅ ሐዋርያዊ ተልእኳችንን ባለመወጣታችን በበኩሌ ተሰምቶኛል።    ሁልጊዜም ቢሆን ከተገፉትና ከተጎሳቆሉት ጎን መቆም ያስፈልጋል። በዚህ ዘመን ለአራዊት እንኳን ጥበቃ እየተደረገላቸው መብትና ክብራቸው በተከበረበት ወቅት በተቃራኒው ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ከአውሬ በታች ሁኖ እየታደነ የሚገደልበት ጊዜ ላይ መድረሳችን እጅግ ያሳዝናል።    

ወገን በወገኑ ላይ ሰይፍ የሚያነሳበት ዘመን ላይ በመገኘታችን አብዝተን እንድንጸልይ እንድንጾም እንዲሁም የሆነብንን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲያስታግስልን ልንለምን ይገባናል።  ይህ መፈናቀልና ሞት እግዚአብሔር ጠብቆን ካልሆነ በስተቀር መላው ኢትዮጵያውያንን ደም የሚያቃባና ሀገራችንን ለከፋ ችግር የሚያጋልጥ እንስሳዊ ተግባር ነው። እየተፈጸመ ያለው የአውሬያዊ ተግባር የሚፈጸመው በኢትዮጵያ ምድር መሆኑ አንዳንዴ ያጠራጥራል።    በውጭው ዓለም የምንሰማው የመጠፋፋት ተግባር በቅድስት ሀገራችን እየተከናወነ መታየቱ በእውነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ራሱን ሊፈትሽና ለሰላም፣ ለፍቅርና ለአንድነት አጥብቀን እንድንሠራ የምንገደድበት ወቅት ላይ እንገኛለን።    

የመፈቃቀር፣ የአንድነትና የሰላም ተምሳሌት የሆነች ሀገራችን በአንድ ጀንበር የሰው ልጆች መጠፋፊያ ምድር መሆኗ በጣም ያሳዝናል።    ሀገራችን ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆን አማኝ ያለባት ሀገር ናት ከተባለ ከእምነት አስተምህሮ ያፈነገጠ ድርጊት በሰው ዘር ላይ ሲፈጸም ምን እየሠራን ነበር? ‹‹ሰው ነን ሃይማኖትም አለን›› የሚሉ ሰዎች ከአውሬ ባላነሰ ሁኔታ በነፍስ ገዳይነት ሥራ ተሰማርተው ማየት በእውነት የከፋ ጊዜ እየመጣ መሆኑን ያመላክታል። እነዚህ አካላት የሰው ህመምና ኀዘን የማይሰማቸው ጨካኝ ፍጥረቶች ናቸው።    እነዚህ መሰል ችግሮች እንዴትስ ነው? ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኙት የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋል። የሃይማኖት አባቶች ትኩረት ሰጥተን ብንሠራ ኖሮ ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ ማምጣት እንችል ነበር የሚል እምነት አለኝ።    በትኩረት እየሠራን ባለመሆናችን ግን በሀገራችን ሰው መሠል አውሬዎች ተፈጥረው ሰውን የሚያሳድዱበትና የሚገድሉበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።    

ስምዐ ጽድቅ፡- በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሰማንያ በላይ አብያተ ክርስቲያናት ተዘግተዋል፤ በርካታ ካህናት ጽላት ይዘው ተሰደዋልና እርስዎ ይህንን ሲሰሙ ምን ተሰማዎት?

 

ብፁዕ አቡነ አብርሃም፡- የተሰማኝ ስሜት መግለጫ የለውም፤ የምጠቀመው ቋንቋም ልቤ በኀዘን መሰበሩን ያስረዳኛል ብዬ አላምንም። እንኳንስ የራስ የሆነች ቤተ ክርስቲያን እንደዚህ ሁና ማየት ይቅርና የሌላ ቤተ እምነትም ቢሆን እንደ ሃይማኖት አባትነቴ በጣም ያሳዝነኛል።  ጉዳዩ እጅግ ከማሳዘኑ የተነሳ በቦታው ተገኝቼ ባደረኩት ቅኝት በምእመናን በካህናት ላይ ከፍተኛ የሆነ ጭንቀትና መረበሽ አስተውያለሁ። የተወሰኑ ካህናትም በአካባቢው ስለተጎዳችው ቤተ ክርስቲያን አናግረውኛል። አንዳንድ አጥቢያዎች ላይ ጽላቶች እንዳልወጡም አጫውተውኛል።  በወቅቱም ከመተከል ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቶማስ ጋር መነጋገር እንዳለባቸው መክሬ ነገር ግን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከትም አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ እንዲያደርግላቸው ተነጋግረናል። ሊቀ ጳጳሱም ችግሩን ለመፍታት እየሠሩ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ።    ችግሮች በተደጋጋሚ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ እየተከሰቱ ነው።  ስለሆነም ቤተ ክርስቲያንና እኛ አባቶች ልዩነትን አርቀን አንድነትን መስርተን የተጋረጠብንን ፈተና በጋራ በጥበብ ማለፍ ይጠበቅብናል።    

 

ስምዐ ጽድቅ፡- በበርካታ የሀገራችን ክፍሎች በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሄዷል፤ ይህን በተመለከተ ቤተ ክርስቲያን ምን ማድረግ አለባት ይላሉ?

ብፁዕ አቡነ አብርሃም፡- እኛ የሃይማኖት አባቶች ጠባቂ የበጎች እረኞች ተብለን ነው የተሰየምነው።    እንደጠባቂነታችን ችግር የገጠማቸው ምእመናን ካሉበት ቦታ ድረስ በመሄድ ማጽናናትና መደገፍ ይጠበቅብናል።   የምእመናን ኀዘን ኀዘናችን፣ ስቃያቸው ስቃያችን ፈተናቸው ፈተናችን ሊሆን ይገባል ነውም።  ምእመናን ችግር ባጋጠማቸው ቁጥር በየሀገረ ስብከቱ ያሉ አባቶች ቦታው ድረስ ሄደው ምእመናንን መደገፍ፣ ማጽናናትና ከአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በመመካከር ችግሩ በዘላቂነት የሚፈታበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል።   የምእመናን ስደታቸው ስደታቸን  ሞታቸው ደግሞ ሞታችን ሊሆን ይገባል።    

ምእመናንን በመጠበቁ ሂደት ላይ የሚመጣ የሕይወት መሥዋዕትነት ካለም ወደ ኋላ ማለት የለብንም።    በጎችን በተኩላ አስነጥቆ የተማረከ ወታደር መስሎ መቀመጥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መሻር ነው። ይህንን ባናደርግ ደግሞ ከተጠያቂነት አናመልጥም። ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ እውቅና ያለውና ዘመኑን የዋጀ ተወርዋሪና ጠንካራ ግብረ ኃይል ልታቋቁም ይገባታል።   ይህ ግብረ ኃይል ችግሮች ከመፈጠራቸውና ከተፈጠሩ በኋላም የተበደሉትን የሚያስክስ፣ ፍትሕ የተጓደለባቸውን ፍትሕ የሚያሰጥ፣ የቤተ ክርስቲያንን ክብርና መብት የሚያስጠብቅ ይሆናል።    ምእመናን በያሉበት ቦታ ሁሉ መብታቸውና ክብራቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ የሚሟገትና የሚከራከር ይሆናል። የቤተ ክርስቲያንን ይዞታዎች ያለ አግባብ ሲነጠቁ ወይም ለመንጠቅ አዝማሚያዎች ሲታዩ ቀድሞ ችግሩን የሚፈታ እንዲሆን ተደርጎ መዋቀር አለበት።    ይህ ግብረ ኃይል ብፁኀን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ ካህናት አባቶችን ያካተተ መሆን አለበት።    

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁ በቀላል የምትታይ አይደለችም። እኛ ራሳችን እያቃለልናት፣ እያዳከምናትና እያሳነስናት ብንሆንም ጠላቶቿ ግን ግዙፋዊነቷንና ታላቅነቷን በማመናቸው ሁልጊዜም ቢሆን የጥፋት ኢላማ ያደርጓታል። ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለመበታተን ቀድመው ቤተ ክርስቲያንን ያጠቃሉ፤ ያዳክማሉ።  ጠላቶቻችን ሀገሪቱን እንዳልሆነ ለማድረግ በቤተ ክርስቲያን ላይ ድሮም ሲያሴሩ ነበር፤ አሁንም እያሴሩ ይገኛሉ።   የመተከሉ ፖለቲካ ቀውስ ሃይማኖታዊ ጭፍጨፋ ሀገርንም የማፍረስ ምልክት ነው። ይህ ተግባር የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የባዕዳን ድብቅ ሴራ ጭምር ነው። እርስ በርስ ማጫረስ፣ የፖለቲካ ተሳትፎ፣ የትጥቅ ልምድ የሌላቸውን ንጹሕ ለፍቶ አዳሪ ማጥቃትና ማስጠቃት የዛሬ ተግባር ብቻ ሳይሆን የቆየ ነው።   ትላንት እንደዚህ ዓይነት አሳፋሪና አሳዛኝ ታሪክ ብናሳልፍም አሁን በዚህ ዘመን በንጹሐን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግን እጅግ የተለየ ነው።    

Read 502 times