Wednesday, 10 March 2021 00:00

መንግሥት ለአብያተ ክርስቲያናት፣ ለቅርሶችና ምእመናን የሕግ ከለላ እንዲሠጥ ተጠየቀ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
መንግሥት ለአብያተ ክርስቲያናት፣ ለቅርሶችና ምእመናን የሕግ ከለላ እንዲሠጥ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ጠየቁ። ቅዱስነታቸው ይህንን የጠየቁት የዐቢይ ጾም መግባቱን አስመልክቶ የካቲት ፳፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው።  በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች በተከሠተው ችግር ምክንያት ብዙ ኢትዮጵያውያን ለርኀብ፣ ለእርዛትና መፈናቀል መዳረጋቸውን ያነሡት ቅዱስነታቸው ችግሩ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን መላው ዓለምን ያሳሰበ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።  ይህም ሆነው በሀገራችን በተከሠቱ ችግሮች ምክንያት በውስጣችን ፍቅርና ሰላም በመጥፋቱ ነው ያሉት ቅዱስነታቸው ችግሮቹ መፍትሔ እንዲያገኙ ሁሉም ወገን ያላሠለሰ ጥረት እንዲያደርግ መክረዋል። አብዝተን ልንሠራው ከሚገባው ነገር ሁሉ ሰላም፣ ፍቅር፣ ስምምነት፣ ይቅርባነት፣ መተጋገዝ፣ መራራትና ካለው ላይ አካፍሎ ለሌላው መሥጠት ሊሆን እንደሚገባም ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።  ከዚህ በኋላ በሀገራችን የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ፣ አብያተ ክርስቲያናት እንዳይደፈሩ፣ ንዋየ ቅድሳትና  ቅርሶች እንዳይዘረፉ መንግሥት ድርጊቱን በማስቆም ለሁሉም የሕግ ከልላ እንዲያደርግላቸው ቅዱስነታቸው አሳስበው የሃይማኖት ተቋማት፣ ማኅበረሰቡና በጎ አድራጊዎችም በችግር ላይ  ያሉ ወገኖችን በመደግፍ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።  
Read 537 times