ትውልዱ፣ቤተ ክርስቲያንና ሀገር የቅዱስ ያሬድን ትሩፋቶች በተገቢ መንገድ እንዳልተጠቀሙባቸው የደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም ፕሮጀክት አቢይ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ የነበሩት ላእከ ሰላም ባያብል ሙላቴ ገለጡ።
ላእከ ሰላም ባያብል ሙላቴ ይህንን የገለጡት በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በበየዳ ወረዳ ጥጉና ጣና ቀበሌ የሚገኘው የደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም ፕሮጀክትና ዘጋቢ ፊልም የካቲት ፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በኢንተር ኮንትኔታል ሆቴል ይፋ በሆነበት ወቅት ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት ነው።
ትውልዱ የቅዱስ ያሬድን ትሩፋቶች ...
በደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም እንዲሠራ የታሰበው ፕሮጀክት ትውልዱ የቅዱስ ያሬድን አሻራዎች እንዲረዳና ከትሩፋቶቹም ተጠቃሚ እንዲሆን ያደርጋል ያሉት ላእከ ሰላም ባያብል ገዳሙ ያልተበረዘ ሁሉን ዓይነት የአብነት ትምህርት የሚሰጥ ማእከል በመሆኑ የዕውቀትና ኪነ ጥበብ ምንጭ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።
ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮጵውያንና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዘመን የማይሽረው አስተዋጽኦ ያበረከተ ሊቅ መሆኑን ላእከ ሰላም ባያብል ከጠቆሙ በኋላ “በገዳሙ ተግባራዊ የሚሆነው ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የተለየ ድርሻ ይኖርዋል” ብለዋል።
ገዳሙ ከሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አዋሳኝ በመሆኑ በተለይ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች መጥተው በሚጎበኙበት ወቅት ሀገርና ገዳሙ ከውጭ ምንዛሬ ተጠቃሚ እንደሚሆን ላእከ ሰላም ባያብል ተናግረዋል። ገዳሙ ፲፻፭፻ ዓመታት ታሪክ ባለቤት በመሆኑም ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ሁኔታ ሊጎበኝ እንደሚችልም አስረድተዋል።
የሰሜን ወሎና ከሚሴ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት ጥዑመ ልሳን ቅዱስ ያሬድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መልክና ውበት እንደሆነ ገልጠው “የእርሱን ሁለንተናዊ ሀብት ሊያሳይ የሚችል ፕሮጀክት እስከ አሁን ድረስ ያለመሠራቱ የሀገርና የቤተ ክርስቲያን ጉድለት ነው” ብለዋል።
ብፁዕነታቸው አያይዘው ‹‹በዚህ ወቅት ቅዱስ ያሬድን የሚዘክሩ ዘጋቢ ፊልሞችና ፕሮጀክቶች መዘጋጀታቸው መልካም ጅምር ነው። ፕሮጀክቶቹ የዘገዩ ቢሆንም ከአሁን በኋላ ለሚመጣው ትውልድ አቅምና ጉልበት ይሆናሉ›› ሲሉ ተናግረዋል። ቅዱስ ያሬድ የዜማ ሊቅ ብቻ እንዳልሆነ፤ ብሉያትንና ሐዲሳትን፣ ሊቃውንትን እንዲሁም አዋልድ መጻሕፍትን ጭምር የተረጎመ፤ ያብራራና ያመሰጠረ መሆኑንም አስረድተዋል።
የጥበብ ምንጭ የሆኑትን የጥዑመ ልሳን ቅዱስ ያሬድን ትሩፋቶች ደራሲያንና የዜማ ሰዎች በደንብ ሊጠቀሙባቸው እንደሚገባ ያሳሰቡ ሲሆን በደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም ሊተገበር የታቀደውን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ በየትኛውም ዓለም ያለ ሕዝበ ክርስቲያን የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። የቤተ ክርስቲያን ሀብቶች የሀገር ሀብቶች መሆናቸውን በመረዳት መንግሥትም ቤተ ክርስቲያን የምታከናውነውን የልማት ሥራ ሊያግዝ ፤እንዲሁም የሚያሥፈልጉ መሠረተ ልማቶችን ሊያሟላ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚንስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሙሓዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው ቅዱስ ያሬድን የሚዘክሩ ሥራዎች እንዳልተሠሩ አስታውቀው ያሁኑ ትውልድ እርሱን የሚዘክሩ ሥራዎች በመሥራት ቀሪውን ደግሞ ለመጭው ትውልድ የቤት ሥራ ትቶ ማለፍ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
የደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም ፕሮጀክት የወቅቱ ዐቢይ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ አቶ ታደሰ አለማየሁ በዕለቱ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳስታወቁት ጥዑመ ልሳን ቅዱስ ያሬድን በመላው ዓለም ለማስተዋወቅ የተደገው ጥረት አናሳ መሆኑን አስረድተው በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ የሚያግዝ ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ተግባር ሊገባ እንደሆነ አስረድተዋል።
በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በበየዳ ወረዳ በጥጉና ጣና ቀበሌ የሚገኘው የቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም ፪ ሺህ ተማሪዎችን የሚያስተናግድ የአብነት ትምህርት ቤትን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንደሚሆኑ ያስገነዘቡት ም/ሰብሳቢው ገዳሙን የልሕቀት ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነም ተናግረዋል።
ከአብነት ትምህርት ቤቱ በተጨማሪ በገዳሙ ግዙፍ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ የቅዱስ ያሬድን ሥራዎችና ተጋድሎዎች የሚያሳይ ዘመናዊ ሙዚየም እንደሚሠራ ያስረዱት ሰብሳቢው ገዳሙ ከተለያየ ዓለም ለሚመጡ ጎብኝዎች መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ እንደሆነና የፕሮጀክቱ ሥራዎች በቅርቡ ለመጀመርም በሀገር አቀፍ ደረጃ ኮሚቴ ተዋቅሮ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል።