Wednesday, 10 March 2021 00:00

ዛሬም ያላቆመው የዐደባባይ በዓላትን ዒላማ ያደረገ ትንኮሳ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምታከብራቸው የዐደባባይ በዓላት በሥርዓት እንዳይከበሩ፣ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ሆኑ የቤተ ክርስቲያን አባቶች በሰላም ወጥተው በሰላም እንዳይገቡ ዘርፈ ብዙ ትንኮሳዎች ሲደርስባቸው ቆይቷል። በምእመናንና በአባቶች ካህናት እንዲሁም ከተለያዩ ሀገራት በሚመጡ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ታጅበው የሚከበሩት እነዚህ የዐደባባይ በዓላት የተጋረጠባቸው የፀጥታ ስጋት ከዓመት ዓመት ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አልታየም።  የትንኮሳውን ዓይነትና ቦታን በመቀያየር ኦርቶዶክሳውያንን የማሳቀቅ፣ ስጋት ውስጥ የመክተትና ክብረ በዓላቸውን በሰላም እንዳያከናውኑ የማጨናገፍ ሴራ ከዕለት ዕለት እየጨመረ፣ ጡንቻውን እያፈረጠመ እዚህ ደርሷል። በአንዳንድ አካባቢዎች በፀጥታ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ለማክበር ቢሞከርም በተወሰኑት አካባቢዎች ደግሞ ምንም ዓይነት ከልካይና ሃይ ባይ ባለመኖሩ(ቢኖርም የይስሙላ በመሆኑ) ምእመናን በገዛ ሀገራቸው ላይ ሃይማኖታቸውን በነፃነት እንዳያካሄዱ ተገደዋል። በዚህ ዓመት ብቻ እንኳ በመስቀል እና በጥምቀት በዓላት ላይ ከመከበራቸው በፊት እየተከበሩ እና ከተከበሩ በኋላ የተፈፀሙት ፀረ ኦርቶዶክሳውያን ትንኮሳዎች በከተማውም ሆነ በገጠሩ ጥቂት የማይባሉ ነበሩ። የመስቀልም ሆነ የጥምቀት በዓል በመጣ ቁጥር ለትንኮሳ የሚዘጋጁ ፀረ ኦርቶዶክሳውያን ኃይሎች በርካቶች ናቸው። ከእነዚህ ተንኳሽና ዕረፍት የለሽ ፀረ ኦርቶዶክሳውያን ኃይሎች መካከል አክራሪ እስላሞች በቀዳሚነት ተጠቃሾች ናቸው። እነዚህ አክራሪ እስላሞች በርከት ብለው በሚገኙባቸው አንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች ሁሉ የዐደባባይ በዓላቱ የሚከበሩበትን ወቅት ጠብቀው በውኃ ቀጠነ በዓሉን ሊያውክ ይችላል የሚሉትን ተግባር ሁሉ ይፈጽማሉ። ሲያሻቸው “ታቦት ይዛችሁ በእኛ አካባቢ አትለፉ” ወይም ደግሞ ‹‹ሰንደቅ ዓላማ አትስቀሉ››፤ ‹‹አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለም ያለበት ልብስ አትልበሱ››ይላሉ። የዚህ ሁሉ መዳረሻው ወይም የጥቃቱ ምክንያት “ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ለምን ሆናችሁ?” የሚል ሆኖ እናገኘዋለን። ‹‹ለምን የእኛን ሃይማኖት አልመሰላችሁም›› የሚል ፍላጎት እንዳለበትም ከድርጊታቸው መረዳት እንችላለን።  ዐይን ያወጣውን የአክራሪዎች የወንጀል ድርጊት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያስተካክል የፀጥታ ኃይል ባለመኖሩም ጥቃቱ በማን አለብኝነት በተደጋጋሚ ይፈጸማል። የፀጥታ ኃይሎች በየአካባቢው ቢኖሩም ለሚከተሉት ሃይማኖት ያደሉ ወይም ለእውነት ያልቆሙ በመሆናቸው ችግሩን ለመፍታት አይሞክሩም፤ ለክርስቲያኖች በደልና እንግልትም አይጨነቁም። ዘንድሮ ማለትም ጥር ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም የተከበረው የጥምቀት በዓል እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ በፀጥታ ችግር ውስጥ ማለፉ አልቀረም። በተለይም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሀላባ ዞን ሀላባ ቁሊቶ ከተማ  በጥምቀትና በቃና ዘገሊላ ዕለት የአካባቢው አክራሪ እስላሞች በበዓሉ ተሳታፊ ምእመናንና አገልጋዮች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥቃት ፈጽመዋል። በዚህ ጥቃትም ምእመናንና አገልጋዮች መለስተኛና ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። እኛም በጉዳዩ ዙሪያ የአካባቢው የሃይማኖት አባቶችንና የመንግሥት አካላትን በስልክ አነጋግረናል።  የከምባታ፣ ጠንባሮና ሀላባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ቆሞስ አባ ሚካኤል ታደሰ ለዝግጅት ክፍላችን በስልክ በሰጡት መረጃ “የእመቤታችንና የገብርኤል ታቦታት ከባህረ ጥምቀት ቦታቸው ተነሥተው ወደ መንበራቸው ሲመለሱ መስጅድ ውስጥ የነበሩ በርካታ አክራሪ ሙስሊሞች በምእመናንና በታቦታቱ ላይ በድንጋይ ጥቃት ፈጽመዋል ብለዋል። በወቅቱ በዓሉን በማክበር ላይ የነበሩ ምእመናን ችግር ይኖራል ብለው ባለመጠርጠራቸው መለስተኛና ከፍተኛ የሆነ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።  የአካባቢው አክራሪ እስላሞች ‹‹ታቦታቱን በአካባቢያችን አናሳልፍም›› ከማለታቸው ባሻገር በታቦታቱና በምእመናን ላይ ከፍተኛ የሆነ የድንጋይ ናዳ በማውረድ ጉዳት አድርሰዋል። ወደ ፌዴራልና ክልል መንግሥታት ስልክ ተደውሎ የፌዴራል ፖሊስ፣ መከላከያና የክልሉ ልዩ ኃይል ደርሰው ካረጋጉ በኋላ ሕዝበ ክርስቲያኑ በከፍተኛ ቁጭት፣ ለቅሶና ኀዘን ሆነው ታቦታቱን ወደ መንበረ ክብራቸው እንደሸኙ ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል። በወቅቱ በአካባቢው የነበሩት  የፀጥታ አካላት ቁጥራቸው አነስተኛ ከመሆኑም ባሻገር መሣሪያ ሳይሆን ዱላ ብቻ የያዙ በመሆናቸው ሕዝበ ክርስቲያኑን ከጥቃት የመከላከልምና  የመጠበቅ አቅምም ሆነ ፍላጎት አልነበራቸውም ብለዋል። ይባስ ብለው አብዛኛዎቹ የፀጥታ አካላት በምእመናንና በታቦታቱ ላይ ይደርስ የነበረውን ጥቃት በታዛቢነት ይመለከቱ ነበር።  እነዚህ የፀጥታ አካላት አልፎ አልፎ ይህን እኩይ ተግባር ይፈጽሙ ከነበሩት አካላት ጋር በመወገን በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ጥቃት ይፈጽሙ እንደነበርም ተናግረዋል። አንዳንድ የአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች ደግሞ ጥቃቱን እንዲያስቆሙ ሲጠየቁ ‹‹ትእዛዝ አልተሰጠንም›› የሚል መሠረተ ቢስ ምክንያት ያቀርቡ እንደነበር የገለጹ ሲሆን ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የጥምቀትና የመስቀል በዓላትን በዐደባባይ እንደምታከብር እየታወቀ ልዩ ጥበቃ አለመደረጉ ለፀረ ኦርቶዶክሳውያን  ኃይሎች ጥቃት ተጋላጭ አድርጎናል ብለዋል።  ሥራ አስኪያጁ አክለውም የአካባቢው አክራሪ እስላሞች ከዚህ ቀደም ማለትም በ፳፻፬ ዓ.ም በተመሳሳይ ወቅትና ቦታ በታቦታትና በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ከፍተኛ ጥቃት የፈጸሙ ቢሆንም የዘንድሮው ግን ከዚያ የተለየና የባሰ መሆኑን ገልጸዋል። አክራሪ እስላሞች ከዚህ ቀደም በተለያየ ወቅት አብያተ ክርስቲያናትን ለማቃጠል ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ባደረጉት ተጋድሎ ሳይሳካላቸው ቀርቷል። የዘንድሮው ጥቃት የሚለየው ቁጥራቸው ከሦስት መቶ እስከ አራት መቶ የሚሆኑ አክራሪ እስላሞች ከገጠር ተሰባስበው በመምጣት ‹‹መስጅድ ተቃጠለ›› በሚል ሰበብ በሕዝበ ክርስቲያኑና በታቦታት ላይ ጥቃት መፈጸማቸው ነው ብለዋል። ካደረሱት የድንጋይ ጥቃት በተጨማሪ አብያተ ክርስቲያናትን ለማቃጠልና የባሕረ ጥምቀቱን  የግንብ አጥር ለማፍረስ ጥረት ሲያደርጉም ቆይተዋል ብለዋል።  የአካባቢው የፀጥታ ኃይልም መስጅድ ውስጥ ሆነው በሕዝበ ክርስቲያኑና በታቦታቱ ላይ በድንጋይ ጥቃት ሲፈጽሙ የዋሉትን ትተው በቦታው ያልነበሩና በሁከቱ ያልተሳተፉ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችን ለእስር እንደዳረጓቸው ሥራ አስኪያጁ አስረድተው ቤተ ክርስቲያን ወጣቶቹ ለምን እንደታሠሩባት ስትጠይቅም ‹‹አጣርተን እንለቃቸዋለን›› የሚል መልስ መስጠታቸውን ገልጸዋል ። በሀላባ ቁሊቶ ከተማ ያሉ አንዳንድ የመንግሥት አካላት ለሚከተሉት እምነት ያደሩ መሆናቸውን በመግለጽ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር በክልሉ መንግሥት በኩል ውሳኔ እንዲያገኝ ሀገረ ስብከቱ ጠይቋል ብለዋል።   በሀላባ ቁሊቶ ከተማ የሦስቱ አድባራት ዋና አስተዳዳሪ መልአከ ኃይል ቆሞስ አባ ብርሃነ መስቀል በበኩላቸው ጥር ፲ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በሀላባ ቁሊቶ ከተማ በሚገኝ ዐደባባይ አቅራቢያ ባለ መስጂድ ውስጥ የነበሩ በርካታ አክራሪ እስላሞች በምእመናንና በታቦታቱ ላይ ጥቃት እንደፈጸሙ ተናግረዋል። በወቅቱ በድንገት በተፈጠረው ችግር ምእመናንና አባቶች እንደተደናገጡ ያስረዱት አስተዳዳሪው በዕለቱ ከፍተኛ የሆነ የመሣሪያ ድምፅ ስለነበረ የቅዱስ ገብርኤልን ጽላት ይዘን በቅርብ ትገኝ ወደነበረችው የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን አስገብተናል ብለዋል። አክራሪ እስላሞች በፈጸሙት በዚህ ጥቃትም አራት ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን የተጎዱ ሲሆን  የአንደኛው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ለተሻለ ሕክምና ወደ ሐዋሳ ሆስፒታል እንደተላከ አስተዳዳሪው አስረድተዋል። የጥምቀትና የቃና ዘገሊለ በዓላት ካለፉ በኋላ የአካባቢው የፀጥታ ኃይላት ኦርቶዶክሳዊ ወጣቶችን እያደኑ ያለምንም ጥፋታቸው አስረዋል። ወጣቶቹ  በበዓለ ጥምቀትም ሆነ በቃና ዘገሊላ ዕለት ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥረት ሲያደርጉ ነበር  ያሉት አስተዳዳሪው መስጅድ ውስጥ ሆነው በሕዝበ ክርስቲያኑና በታቦታቱ ላይ የድንጋይ ናዳ ሲያወርዱ የነበሩ አክራሪ እስላሞች ግን አንዳቸው እንኳን አለመታሰራቸውን ገልጸዋል።  አክራሪዎቹ ይፈጽሙት ለነበረው ጥቃት የአጸፋ ርምጃ ባልወሰዱ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ላይ ፍትሐዊ ያልሆነ የእስር ርምጃ መውሰድ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደሆነ አስተዳዳሪው ተናግረው አንድ የሰበካ ጉባኤ አባልን ጨምሮ አስራ ሰባት ኦርቶዶክሳውያን ያለምንም ወንጀል በእስር ላይ ይገኛሉ ብለዋል። እነዚህ የታሰሩ ወጣቶች በተለይ ቤተ ክርስቲያንን መኪና ከማቅረብ ጀምሮ በሁሉም ነገር እገዛ ሲያደርጉ የነበሩና ሌሎችም በበዓለ ጥምቀት ወቅት በቦታው ያልነበሩ እንደሆነ አስተዳዳሪው አስረድተዋል።  የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስም ወጣቶቹ በታሰሩባቸው አካባቢዎች ተገኝተው ያጽናኑ ሲሆን ከመንግሥት አካላት ጋርም በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን፤ ጉዳያቸው  እየተጣራ ከእስር እንደሚፈቱ የመንግሥት አካላቱ እንዳሳወቋቸው ገልጸዋል። ብፁዕነታቸው በራሳቸው ዋስትናም ወጣቶቹ ከእስር እንዲፈቱ የአካባቢውን የመንግሥት አካላት መጠየቃቸውን እንዲሁም መንግሥት በሚፈልጋቸው ጊዜም ለማቅረብ ዝግጁ እንደሆኑ መናገራቸውን አስተዳዳሪው አክለዋል። ይሁን እንጂ ወጣቶቹ እስካሁን ድረስ ከእስር እንዳልተፈቱ አስታውቀዋል። ቤተ ክርስቲያን ወጣቶቹ ከእስር እንዲፈቱ ተግታ እንደምትሠራና ከዚህ ቀደም እንደተደረገው ሁሉ ወጣቶች ተደራጅተው ራሳቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲጠብቁ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል። በበዓለ ጥምቀት ወቅት አክራሪ እስላሞች የፈጸሙትን ጥቃት የአካባቢው የፀጥታ አካላት ድርጊቱን እንዳወገዙና እስልምናን የማይወክል ነገር ግን የአክራሪዎች ተግባር እንደሆነ መናገራቸውን አስተዳዳሪው አንሥተዋል። የሀላባ ቁሊቶ ከተማ የሦስቱ አብያተ ክርስቲያናት የሰበካ ጉባኤ ም/ሰብሳቢ አቶ አድነው ወልዴ እንደተናገሩት ደግሞ በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸመው ትንኮሳ አሁን የተጀመረ እንዳልሆነ ገልጠው ከዚህ ቀደምም ብዙ ሃይማኖት ተኮር ትንኮሳዎች እንደነበሩ አስረድተዋል። ለዐደባባይ በዓላት ማክበሪያነት እንዲውል ፴፯ ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ በሕጋዊ መንገድ ከተሰጠን በኋላ ቦታውን ማልማት ስንጀምር ለሚከተሉት ሃይማኖት ያደሩ የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ‹‹አታለሙም አቁሙ›› ብለው ከልክለውናል ሲሉ በአካባቢው እየተፈጸመ ያለውን በደል በማሳያነት አንሥተዋል።  የጥምቀት በዓል ከመድረሱ በፊት የፀጥታ ሥጋት እንዳለብን ለሀላባ ቁሊቶ ከተማ አስተዳዳር ልዩ ጥበቃ እንዲያደርግልን በደብዳቤ ያሳወቅን ቢሆንም ጥያቄያችን ችላ በመባሉ አክራሪ እስላሞች መስጅድ ውስጥ ሆነው ጥቃት ፈጽመውብናል ብለዋል። አንዳንድ የአካባቢው የመንግሥት አካላት ለአክራሪዎች እኩይ ተግባር የተገዙ በመሆናቸው ጥቃት ሲፈጸምብን በቸልታ ከማየት ባሻገር ቤተ ክርስቲያን መብቷን ስትጠይቅ እንዳይፈጸምላት የሚሠሩ እንደሆኑ አስረድተዋል።  ለሀላባ ዞን ፖሊስ መምሪያ (ኢ/ር ታረቀኝ ጉራች)፣ ለሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ (ዶ/ር መሐመድ ኑርዬ)፣ ለሀላባ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ (አቶ ሱሌይመን ሀሰን)፣ ለሀላባ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ (አቶ አብዱቃልድር ሎላሽ) እንዲሁም ለሀላባ ቁሊቶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ (አቶ ሀሩና አህመድ) ስልክ ደውለን መረጃ ለመጠየቅ ጥረት ብናደርግም የተወሰኑት የመንግሥት አካላት ስልክ አንሥተው መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ያለመሆናቸውን የገለጡ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ስልክ ሊያነሱልን ባለመቻላቸው ምላሻቸውን በዚህ ጽሑፍ ማካተት አለተቻለም።  
Read 481 times