የተወደዳችሁ አንባብያን የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ከዚህ በፊት በነበረው እትም ላይ ማቅረባችን ይታወሳል። ቀጣዩንና የመጨረሻውን ክፍል ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ስምዐ ጽድቅ፡- የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ ጥፋት ሲያደርሱ እንደቆዩ ይታወቃል። ቤተ ክርስቲያን ጥፋቱ ከደረሰ በኋላ ጊዜያዊ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በመንግሥት ላይ ጫና ማሳደር እንዴት አልቻለችም?
ብፁዕ አቡነ አብርሃም፡- በመንግሥትም ሆነ በሌላ አካል ላይ ጫና አሳድሮ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ከማድረግ በፊት የሚቀድመውን ማስቀደም መልካም ነው። ይኸውም መጀመሪያ በጽንፈኞች ጥቃት ችግር ላይ የወደቁ ምእመናን በተቻለን አቅም መረዳት፣ ከጎናቸው መሆናችንን ማሳየትና ሥነ ልቡናቸውን ማደስ ያስፈልጋል። ይህንን ካደረግን በኋላ ደግሞ ችግሩ በዘላቂነት የሚፈታበትንና ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች እንደማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ ሰብአዊ መብታቸው ተከብሮላቸው እንዲኖሩ የሚያስችላቸውን ሥራ ከመንግሥትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆኖ መሥራት ያስፈልጋል።
ሰላምን ከሌላ አካል ከመጠበቅ ደግሞ እኛ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ተናበንና ተግባብተን መሥራት መቻል አለብን። መናበባችን ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያና ምእመናን ድረስ የሚደርስ መሆን አለበት። ቤተ ክርስቲያን ከሠራችው ያልሠራችው ይበልጣልና የቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያ ሥራ መሆን ያለበት የልጆቿን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ነው። እንዴት ማስጠበቅ አለባት ለሚለው የመጀመሪያው አምላኳን በጸሎት በመጠየቅና ከመንግሥትና ከሌሎች አካላት ጋር በጋራ በመሥራት ሊሆን ይገባል። በዚህ ዘመን በመንግሥት ላይም ሆነ በሚመለከተው አካል ላይ ጫና ተፈጥሮ ችግሮችን ማስተካከል ይቻላል ማለት ትንሽ ይከብዳል። ለአብነት በመተከል ዞን በንጹሓን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ለማስተካከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀር በቦታው ተገኝተው ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርገው ነበር። ዳሩ ግን እርሳቸው ከተመለሱ በኋላ በርካታ ንጹሓን ወዲያው ተገድለዋል። ስለዚህ መንግሥትን የማይሰማ እንዲሁም እግዚአብሔርን የማይፈራ ትውልድ ምንም ጫና ብትፈጥር ከጥፋት ድርጊቱ አይመለስም።
እንደ ኦሪቱ ዘመን ያጠፋህን አጥፋው፣ የገደለህን ግደለው የሚሆን ከሆነ አያዛልቀንም፤ለሀገር አንድነትና ሰላምም የሚጠቅም አይደለም። ቤተ ክርስቲያን ሁሌም ሰላምን፣ አንድነትንና ፍቅርን ነው የምትሰብከው፤ ታጠቅ የገደለህን ግደል፤ ዝረፍ የሚል አስተምህሮም የላትም። ቤተ ክርስቲያን የትዕግሥት ቤት ናት፤ ትናትናም ክብሯን ጠብቃ ኖራለች፤ ዛሬም እየኖረች ነው፤ ነገም ለሀገር ጠቃሚና አሳቢ ሆና ትቆያለች። በሰዎች ላይ ጥፋት ስለሚያደርሱ ሰዎች ሁሉ ፈጣሪዋን ትለምናለች። ለጥፋት የተሰማሩ ኃይሎች ከጥፋታቸው እንዲመለሱና ለሰው አሳቢና የቀና ሕይወት እንዲመሩ ቤተ ክርስቲያን ሁሌም ትጸልያለች።
የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ እጅግ እየተበላሸ መጥቷል። ለሀገርና ለወገን የማይጨነቁና የማያስቡ ፖለቲከኞች ተፈጥረው እየተመለከትን ነው። በሰው ሞት፣ ስደት፣ ስቃይና ችግር ሀብት ለማካበትና ሥልጣን ለመቆናጠጥ የሚያልሙ የፖለቲካ ሰዎች እየተበራከቱ መጥተዋል። ለወገን ደራሽ የመሆን ስሜት ያላቸው ሳይሆኑ አንዱን ጥሎ የማለፍ ሥሜት ያላቸው ሰው መሰል ግን አውሬ የሆኑ ፖለቲከኞች በየአካባቢው ተፈጥረዋል። በተለይ ለራሳቸው ዘውግና ሃይማኖት ብቻ የሚሠሩ በርካቶች ናቸው። ስለሆነም በሌላው ዘውግና ሃይማኖት ላይ ጫናና ጥቃት እንዲደርስ ሆነ ብለው እየሠሩ ያሉ በርካታ ፖለቲከኞች እንዳሉ የትላንቱና የዛሬው የሀገሪቱ ታሪክና ሁኔታ ማሳያዎች ናቸው።
ከዛሬ ፖለቲከኞች የወገንን ቁስል የሚጠግን ንግግር ሳይሆን የሚወጣው የሐሰት ትርክትና ድል አድራጊነት እንዲሁም ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ ሀሳብ ነው። የራሳቸውን ጥሩ ኑሮ የሚኖሩ የሌላውን ኑሮ ደግሞ የሚያጨልሙ በርካቶች ናቸው። ትንኮሳውንና ብጥብጡን ሲፈልጉ የሃይማኖት እያደረጉ ካልሆነ ደግሞ የብሔር መልክ እያላበሱ ይኖራሉ። እነዚህን እግዚአብሔር ወደ ኅሊናቸው እንዲመልሳቸውና ወገናዊ ፍቅር እንዲኖራቸው እንጸልያለን።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ያለውን የፀጥታ ችግር ለማስተካከል የክልል የፀጥታ ኃይልን ጨምሮ መከላከያና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በቦታው ቢሰማሩም አሁንም ድረስ በአካባቢው በየቀኑ ሞትና መርዶ አለ። ሰዎች በግፍ ተፈናቅለዋል፤ በአካባቢያቸው ለዘመናት ያፈሩት ሀብት ንብረት ወድሞባቸዋል። ይህ ተግባር እንዲቆም ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ጊዜያት “ከታሪክ እንማር፣ ከክፉ ነገር እንመለስ እንዲሁም ለሀገር ሰላምና አንድነት እንቁም “ እያለች ያለምንም ልዩነት ጥሪ እያቀረበች ነው።
ስምዐ ጽድቅ፡- የምእመናንና የቤተ ክርስቲያንን ደኅንነት ለመጠበቅ በሀገረ ስብከትዎ ያለው የወጣቶች አደረጃጀት ምን ይመስላል?
ብፁዕ አቡነ አብርሃም፡- ወጣቶች የቤተ ክርስቲያናችንና የሀገረ ስብከታችን ጌጦች ናቸው። ወጣቶቻችን የእኛ አባቶች እጣፈንታዎች ናቸው። በወጣቶቻችን ደግሞ መሥራት ያለብንን ሁሉ እንሠራለን። ቤተ ክርስቲያን እንጠብቅበታለን፤ ሕዝቡን እናንጽበታለን፤ ማንኛውንም ተልእኮ እናከናውንበታለን። ወጣቱን ትውልድ በሃይማኖትና በምግባር አቅንቶ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መጠቀም ዘመኑ የሚጠይቀው ተግባር ነው። ቤተ ክርስቲያን ከወጣቶች የራቀና የተለየ አገልግሎት የላትም። ቤተ ክርስቲያን ወጣቶቿን በአብነት ትምህርት ቤትና በሰንበት ትምህርት ቤት አቅፋ ስታስተምር ቆይታለች። አሁን የምናያቸው ዲያቆናት፣ ካህናትና ጳጳሳት ከአብነት ትምህርት ቤቶች የወጡ ናቸው። እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑና በሥነ ምግባር የታነጹ ወጣቶች ደግሞ ከሰንበት ት/ቤት የወጡ ናቸው።
ከጥንት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን ከወጣቶች የተለየ አገልግሎት ኖሯት አያውቅም። በሀገራችን በየአካባቢው ምእመናን ተገደሉ፣ ተፈናቀሉ፣ አብያተ ክርስቲያናት ተዘረፉና ተቃጠሉ የሚሉ ዜናዎችን መስማት እየተለመደ የመጣ ተግባር በመሆኑ እነዚህ እኩይ ተግባራት ወደ ሀገረ ስብከታችን ከመምጣታቸው በፊት ቅድመ ዝግጅት አድርገናል። ዘመኑ መለወጡንና አሰላለፉ መቀየሩን በመረዳታችን ወጣቶችን ማደራጀትና ማሰባሰብ ጀምረናል። ይህ ወጣት ሀገሩን ወገኑን እንዲወድና በሃይማኖቱ የቀና በሥነ ምግባር የታነፀ እንዲሆን እየሠራን ነው። ከዚህ ባሻገር ወጣቱ ትወልድ የቤተ ክርስቲያንና የምእመናንን ድኅነትን ተደራጅቶ እንዲጠብቅ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ ወደፊትም በትኩረት ይሠራሉ። ወጣቶችን ለማሰባሰብ ሲታሰብ መጀመሪያ የተወሰደው ርምጃ የጽዋ ማኅበራትን ወደ አንድ ማሰሳበብ ነው። ስልታዊ እቅድ ነድፈን ከቀን ሠራተኛ እስከ መንግሥት ሠራተኛ ድረስ ሕግና መመሪያን እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓት የተከተለ አደረጃጀት ፈጥረናል። ለወደፊቱ ከተደራጁ ወጣቶች መካከል ቋሚ የሥራ እድል ያልተፈጠረላቸውን ወጣቶችን በመለየት የሥራ እድል የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት ቢቻልም መልካም ነው።
በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሥር የተደራጁ ወጣቶች ‹‹የባሕር ዳር የወጣቶች ኅብረት›› የሚባል ሲሆን በማንኛውም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡ እነዚህ ወጣቶች በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ ሲደርሱ የነበሩ ችግሮችን የቀረፉና ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩ አካላትንም ወደ ሕግ ሲያቀርቡ የቆዩ ናቸው። ወጣቶች አንድነታቸውን ባጠናከሩ ቁጥር ኃይል እንዳላቸውና ቤተ ክርስቲያናቸውን ከክፉ ነገር መጠበቅ እንደቻሉ አሳይተዋል። ለወደፊቱም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሁሉ ወጣቱን ያቀፈ ከሆነ ቤተ ክርስቲያን የማትሻገረው ፈተና አይኖርም ብዬ አምናለሁ።
ስምዐ ጽድቅ፡- ቀረ የሚሉት ነገር ካለ?
ብፁዕ አቡነ አብርሃም፡- በእኛ ሀገረ ስብከት ያሉ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት የቤተ ክርስቲያንን ትልቅነትና ኃያልነት የተረዱ በመሆናቸው ቤተ ክርስቲያን በምታዛቸው ጊዜ ሁሉ ታዛዥ ናቸው። ሃይማኖታቸው ምንም ይሁን ነገር ግን ሁሉም ለቤተ ክርስቲያን ቀና የሆነ አመለካከትና የታዛዥነት መንፈስ አላቸው። ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ባውለታ መሆኗን በደንብ የተገነዘቡ በመሆናቸው እኛ ወደ እነርሱ ሳንሄድ እነርሱ ወደ እኛ መጥተው አስፈላጊውን ማኅበራዊ አገልግሎት ይሰጡናል።
በዚህም ቤተ ክርስቲያን ለመንግሥት አካላቱ እውቅና ትሰጣለች። ከባሕር ዳር የመንግሥት ባለ ሥልጣናት በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ያሉት ልምድ ሊወስዱና ሊማሩ ይገባል። ቤተ ክርስቲያንን በወራሪና በጠላትነት ፈርጀው በርሷ ላይ ጥቃት የሚፈጽሙና የሚያስፈጽሙ በተለይ የታችኛው የመንግሥት አካላት ከድርጊታቸው ተቆጥበው የመልካም ሥራዎች ተምሳሌት የሆኑ አካባቢዎች ላይ ልምድ ቢወስዱ መልካም ነው።