Wednesday, 24 March 2021 00:00

የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ለተገደሉ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች .ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ኪሪል በግፍ ለተገደሉ ኦርቶዶክሳውያን ኀዘናቸውን ገልጸዋል

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሰሞኑን በኦሮምያ ክልል ሆሮ ጉድሮ ወለጋ ዞን አቢ ደንጎሮ ወረዳ ዴቢስ ቀበሌ በታጣቂዎች ለተገደሉ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ድጋፍ እንደምታደርግ  ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ኪሪል ማስታወቃቸውን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ አስነበበ።  ቅዱስነታቸው ይህንን ያስታወቁት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ  ትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማት በጻፉት የአጋርነትና የድጋፍ ደብዳቤ እንደሆነ ዘገባው አስረድቷል።    በንጹሓን ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመው ጥቃት የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን እንዳሳዘነ የገለጹት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ኪሪል ለሟቾች እንጸልያለን ብለዋል። በሃይማኖታቸው ብቻ ግፍና በደል ለሚደርስባቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ጠንካራ ድጋፍ እንደሚያደርጉ መግለጻቸውን ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል።  ሰሞኑን በኦሮምያ ክልል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ በተፈጸመ አሰቃቂ ጥቃት በርካታ ምእመናን፣ እናቶች፣ ሕፃናትና ካህናት መገደላቸውን ቅዱስነታቸው በላኩት ደብዳቤ አስታውሰው ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስና ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትን ተመኝተዋል።  በንጹሓን ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለው አሰቃቂ ጥቃት የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን እጅግ ያሳሰበ ጉዳይ መሆኑን የገለጡት ቅዱሰነታቸው ቤተ ክርስቲያናቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያኖች በሀገራቸው በነፃነትና በደኅንነት እንዲኖሩ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደምታደርግ “ቃል እገባለሁ” ሲሉ  ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አሳውቀዋል።  “በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእምነታቸው ምክንያት የሚገደሉ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ፍትሕ እንደሚያገኙ ተስፋ አደርጋለሁ” ማለታቸውንም ከደብዳቤው መረዳት ተችሏል። የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በእምነታቸው ምክንያት በሚሰደዱ ኢትዮጵያውያንና በሌሎች ቦታዎች የሚገኙ ክርስቲያኖችን ከጥቃት ለመከላከል ቁርጠኛና ግንባር ቀደም እንደሚሆኑ ቅዱስነታቸው የገልጠዋል።  እ.ኤ.አ በታኅሳስ 2020 ‹‹የአፍሪካ ክርስቲያኖችን ከጥቃት መከላከል›› በሚል ስያሜ የተካሄደው የቪዲዮ ኮንፈረንስ የተዘጋጀው በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና በሩሲያ የሃይማኖት ነፃነት አስጠባቂ ማኅበራት አነሳሽነት መሆኑ ተገልጿል። ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ፣ የፓን ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ማኅበር የኮንፈረንሱ አጋሮች  ከተሳታፊዎች መካከል እንደነበሩ ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል።
Read 649 times