Wednesday, 24 March 2021 00:00

የወላይታ ዞን አስተዳድር ሀ/ስብከቱ ላቀረባቸው ቅሬታዎች መፍትሔ ለመስጠት ኮሚቴ ማዋቀሩን ተገለጠ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በወላይታ ሀገረ ስብከት የወላይታ ዞን ፕሮቴስታንት የመንግሥት አመራሮች ቤተ ክርስቲያንን ሆን ብለው ላለፉት ዐሥር ዓመታት  ሲበድሉ እንደነበር የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም ቀሲስ ቦኪቻ ኢንጋ ገለጡ።  የዞኑ ፕሮቴስታንት የመንግሥት አመራሮች በተለይ በገጠር ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ይዞታ ላይ ከፍተኛ በደል ይፈጽሙ እንደነበር ያስታወቁት ሥራ አስኪያጁ ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታትም ከወረዳ እስከ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ደርሶ አቅጣጫ የተቀመጠ ቢሆንም አመራሮቹ ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኞች ሳይሆኑ እንደቀሩም ተናግረዋል።  ቤተ ክርስቲያን ያሏት ጥያቄዎች በሙሉ እንዲመለሱ ላለፉት ዐሥር ዓመታት ለወላይታ ዞን አመራሮች አቤቱታ ስታቀርብ ብትቆይም በአመራሮቹ በኩል ምንም ዓይነት አወንታዊ ምላሽ እንዳልተሰጠ ሥራ አስኪያጁ አስታውሰዋል።  በቅርቡም አንድ የፕሮቴስታንት ‹‹ሰባኪ ነኝ›› የሚል ግለሰብ ወላይ ሶዶ ከተማ በሚገኙ አጥቢያዎች እየዞረ በጥሩምባ በመታገዝ ‹‹የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጠንቋይ ናት፤ ከዚህ ውጡ፤ ያለበለዚያ ኢየሱስን አታገኙም›› እያለ ሲረብሽ በአግባቡ ይዘን ለሕግ አካላት ብናቀርብም ሕጋዊ ርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ድርጊቱን የተቃወሙ ኦርቶዶክሳዊ ወጣቶችን አስረዋል፣ ደብድበዋል እንዲሁም አንገላታዋቸዋል ሲሉ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።  “የታሠሩ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችን ከእስር ለማስፈታት ጥረት በምናደርግበት ወቅትም የአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች በምእመንና በእኔ ላይ ተጨማሪ ወከባና ድብደባ ፈጽመዋል” ያሉት ሥራ አስኪያጁ “ከፖሊስ ጋር በተደረገው እልህ አስጨራሽ ሙግት የታሠሩ ወጣቶች ወዲያውኑ ከእስር እንዲፈቱ ስናደርግ ቤተ ክርስቲያንን ሲያንቋሽሽ የነበረው ግለሰብም በድጋሚ እንደዚህ ዓይነት ተግባር እንዳይፈጽም ፖሊስ ጣቢያ ፈርሞ እንዲወጣ የፀጥታ ኃይሎችን ጠይቀናል” ብለዋል።  ሆስፒታሎችን ጨምሮ በአንዳንድ የመንግሥት ማኅበራዊ ተቋማት ላይ ፕሮቴስታንት ሠራተኞች በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ እያደረሱ ያሉትን ሃይማኖታዊ ትንኮሳ እንዲያቆሙ ለዞን አስተዳዳሪው እንዳሳወቁ ያስረዱት ሥራ አስኪያጁ ዞኑም ቤተ ክርስቲያን የምታነሳው ጥያቄ በሙሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመመለስ ቃል ገብቶ ሁከት ያስነሳው ግለሰብና ድብደባና ወከባ የፈጸሙ የፖሊስ አባላት በሕግ እንዲጠየቁ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።  ሥራ አስኪያጁ አያይዘውም “በዞኑ አመራሮች የተወሰኑ ውሳኔዎችንና የቤተ ክርስቲያንን ጥያቄ ሁሉ ለማስፈጸመም ዝግጁ ነን ካሉ በኋላ በግለሰቡም ሆነ ግፍ በፈጸሙ የፖሊስ አባላት ላይ ሕጋዊ የርምት ርምጃ እንዲወስድባቸው ሰሞኑን ክስ እንመሠርታለን” ብለዋል።  የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ ዶ/ር እንድርያስ ጌታ በበኩላቸው የወላይታ ሀገረ ስብከት ያቀረባቸውን ቅሬታዎች በሙሉ ተመልክተው ለእያንዳንዱ ቅሬታ መፍትሔ ለመሥጠት ኮሚቴ ተዋቅሮ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጠው በወላይታ ሶዶ ከተማ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ሁከትና ብጥብጥ ያስነሳው ግለሰብም ሆነ አባቶችንና ምእመናንን ያዋከቡ የፖሊስ አባላትም በሕግ እንደሚጠየቁ አስረድተዋል።  ቤተ ክርስቲያን በድለውኛል ባለቻቸው አካላት ላይ ክስ እንድትመሠርትና ድጋፍ እንደሚያደርጉ የገለጡት አስተዳዳሪው በቀጣይም በወላይታ ዞን ባሉ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ያለውን የይዞታ ጥያቄ ዞኑ ትኩረት እንደሚሰጠውና ከሀገረ ስብከቱ ጋር ተናቦ እንደሚሠራ እንዲሁም ለተነሱት ቅሬታዎች ሁሉ አፋጣኝ መልስ ለመስጠት አቅጣጫ ማስቀመጡን አስገንዝበዋል።  በተከለከሉ ቦታዎች በተለይም በመንገድ ላይ፣ በሌሎች እምነት ተቋማት አቅራቢያ እንዲሁም በገበያ ቦታ ላይ በአጠቃላይ ከራሳቸው ቤተ እምነት ውጭ አግባብ ባልሆነ መንገድ ‹‹ወንጌል እንሰብካለን›› በሚሉ አካላት ላይ ዞኑ አስተማሪ ርምጃ እንደሚወስድ የገለጡት አስተዳዳሪው “በሕክምና ተቋማትና በሌሎች ማኅበራዊ ተቋማት ላይ የሚፈጸመውን ሃይማኖታዊ ትንኮሳን ጭምር ለማስቀረት ርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ተናግረዋል።   
Read 520 times