Friday, 26 March 2021 00:00

አዲሱ የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥን ስቱዲዮ ተመረቀ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
አዲሱ የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥን ስቱዲዮ አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት መጋቢት ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ተመረቀ፡፡  በምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የምሥራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሮ ወለጋና ምዕራብ ሸዋ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በቤተ ክርስቲያን የሚዲያ ታሪክ ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ደረጃውን የጠበቀ ስቱዲዮ እንዳልተገነባ ጠቅሰው የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡  ስቱዲዮው የቀደሙ ጉባኤ ቤቶችን እንድናስታውሳቸው ተደርጎ መሠራቱ እንዳስገረማቸው የተናገሩት ብፁዕነታቸው ይህም ወንጌል ላይ የተመሠረተችውን የቀናች ሃይማኖት ለማስፋፋትና ለመስበክ አጋዥ እንደሆነ ገልጠዋል፡፡  ጊዜውን የቀደሙ “ቴክኖሎጂዎችን” ሁሉ በመጠቀም ወንጌልን ለዓለም ሁሉ ማዳረስ ወቅቱ እንደሚጠይቅ ካሉ በኋላ “ስቱዲዮው የቤተ ክርስቲያናችንን ሥርዓት፣ ትውፊትና የምእመናንን ዘመናዊና ባሕላዊ የአኗኗር ዘይቤ ያንጸባረቀ ሆኖ መገንባቱ ደግሞ በተለየ ሁኔታ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በቀላሉ ለማስረዳት ያግዘዋል” ብለዋል፡፡  “ከቴክኖሎጂ” ርቀት የተነሳ ምእመናን በየቤታቸው ሆነው ወንጌልን መስማት የሚችሉበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ያሉት ብፁዕነታቸው “ለዚህ ደግሞ ደረጃው ከፍ ብሎ የተሠራ እስቱዲዮ መኖሩ ወንጌል ከምእመናን ቤት ድረስ ለማድረስ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡  የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ በበኩላቸው ባዩት ነገር ተደስተው ማኅበሩ የሠራው የቴሌቭዥን ስቱዲዮ ከዚህ በላይ የበለጠ መሥራት እንደሚቻል የተረዱበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡  የስቱዲዮው የተለያዩ ክፍሎች በጉባኤያት መሰየማቸው ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜም በጉባኤያት እንደምታምንና  ጉባኤው የክርስቶስ መሆኑን የምንረዳበት ነው ካሉ በኋላ “በዚህ ስቱዲዮ ውስጥ መልካም ዜና የሚሰማበትና የእግዚአብሔር ወልድ ወንጌል የሚሰበክበት ይሆናል” ብለዋል፡፡  እንደነዚህ ያሉ “በቴክኖሎጂ” የጎለበቱ ሥራዎች ሊሠሩና ሊጎለብቱ እንደሚገባ ያስረዱት ብፁዕነታቸው “ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ለማይችሉ ምእመናን መንፈሳዊ መርሐ ግብራትን ቤታቸው ድረስ እንዲከታተሉ ለማድረግ እንደነዚህ ዓይነት ደረጃቸውን የጠበቁ ስቱዲዮ መገንባታቸው የወንጌል ተደራሽነትን ያግዛል” ብለዋል፡፡  የማኅበረ ቅዱሳን ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግዛቸው ሲሳይ ባሰሙት የመግቢያ ንግግር እንዳስታወቁት የተገነባው ስቱዲዮ የሃያ አራት ሰዓት የቴሌቭዥን አገልግሎት ለመሥጠት የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ስበከተ ወንጌልን በተገቢው መንገድ ለማስፋፋት ሚዲያ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተው “የሚዲያ አጠቃቀማችን ለማዘመን የስቱዲዮ ግንባታ ወሳኝ ነው” ብለዋል፡፡  ስቱዲዮውን ለመገንባት ብዙ ውጣ ውረዶች እንደታለፉ ያስገነዘቡት ምክትል ሰብሳቢው ፈተናዎች ሁሉ ታልፈውና የተለያዩ አካላት እገዛ ተጨምሮበት ይህ ዘመናዊ ስቱዲዮ እውን እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳንና የቤተ ክርስቲያን ቴሌቭዥን ጣቢያዎች ተናበው እንዲሠሩም ም/ሰብሳቢው ጠይቀዋል፡፡  በተለይም ምእመናን በፈተና በሚወድቁበት ጊዜ የቴሌቭዥን መርሐ ግብራት አስፈላጊ እንደሆነ ያነሱት ም/ሰብሳቢው የበለጠ ሃይማኖታዊ ዕውቀት እንዲኖራቸው እንደሚያግዛቸውም  ተናግረዋል፡፡ በዘርፉ ብቁ የሆኑ የሰው ኃይል ማፍራት እንሚያስፈልግ ያስገነዘቡት ም/ሰብሳቢው ይህንንም ለማድረግ የመንፈሳዊ ጋዜጠኝነት ሙያን ሊያግዙ የሚችሉና ሥልጠናዎችን የሚሰጡ መንፈሳዊ ተቋማት ሊኖሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡  በመጨረሻም ለስቱዲዮው መጠናቀቅ ከአሳብ ጀምሮ ድጋፍና እገዛ ላደረጉ ብፁአን አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ምእመናንና እንዲሁም አሠሪ ኮሚቴውን ላደረጉት አስተዋጽኦ ም/ሰብሳቢው ምሥጋና አቅርበዋል፡፡      
Read 986 times