Wednesday, 31 March 2021 00:00

የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመርዳት ጥረት እየተዳረገ መሆኑ ተገለጠ 

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ  ውሳኔ መሠረት የተቋቋመው ድጋፍ አሰባሳቢና አስተባባሪ ዐቢይ ኮሚቴ በትግራይና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመረዳት እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን መጋቢት ፳ ቀን ፳፻፲፫  ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ገለጠ፡፡  በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ተቋቁሞ ወደ ሥራ እንዲገባ የተደረገው ይህ ዐቢይ ኮሚቴ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችለውን እቅድ አውጥቶ የተፈናቃዮችን ችግር ከግምት ውስጥ ያስገባ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን ከመግለጫው ለማወቅ ተችሏል፡፡  የዐቢይ ኮሚቴው ጸሓፊና የውጭ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ የሆኑት መ/ር ዳንኤል ሰይፈሥላሴ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት እንደተናገሩት ዐቢይ ኮሚቴው ከተቋቋመበት ጊዜ አንሥቶ በዋና ዋና ተግባራት ዙሪያ በጥናት ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው ርዳታ አሰባስቦ ለተጎጂ ወገኖች ከማድረስ ጎን ለጎን ተጎጂ ወገኖችን በቃለ እግዚአብሔር የማጽናት ሥራ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡  ለተጎጂ ወገኖች የሚሰጠው የማጽናኛ ትምህርት ቤተ ክርስቲያን ባሏት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አማካይነት በተለያዩ ቋንቋዎች እንደሆነ ያነሱት የዐቢይ ኮሚቴው ጸሓፊ በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት አማካይነትም የማጽናኛ ትምህርቱ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡  እስካሁን ድረስ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አሥራ አምስት ሚሊዮን ብር፣ ከቅዱስ ፓትርያርኩ  አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሽህ ብር፣ ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ አንድ ሚሊዮን ብር እንዲሁም ከካናዳና አካባቢው ሀገረ ስብከት ከአርባ ሺህ ዶላር በላይ የተሰበሰበ መሆኑን ገልጠው ጸሓፊው ተቋማቱ ላበረከቱት አስተዋፅኦም አመስግነዋል፡፡  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዲሁም የዐቢይ ኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ ይበቃል ሽፈራው በበኩላቸው ልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽኑ በማንኛውም ጊዜ እንደሚያደርገው ሁሉ በትግራይና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ነድፎ የተለያዩ ድጋፎችን ለማሰባሰብ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡  ኮሚሽኑ ለተፈናቃዮች በዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ ሁሉተኛውን ዙር ድጋፍ እንደሚያደርግ የጠቆሙት ኮሚሽነሩ ከጊዜያዊ ድጋፍ በተጨማሪ ተፈናቃዮች ተጠልለው ያሉበትን ቦታ ምቹ ለማድረግም ከዚህ ቀደም በህንጣሎ፣ ዋጅራት፣ ራያ አዘቦና ጨርጨር አካባቢዎች የውኃና የሽንት ቤት አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል፡፡  ኮሚሽኑ በመጀመሪያ ዙር የአንድ ሽህ ሰባት መቶ ሠላሳ አምስት ኩንታል ስንዴ ዱቄት፣ የአንድ መቶ ሰባ ሦስት ኩንታል ምስር ክክ፣ የአሥራ ስምንት ኩንታል ጨው እንዲሁም የአምስት ሽህ ሰባት መቶ ሊትር ዘይት ርዳታ እንዳደረገ ኮሚሽነሩ ገልጠው ይህ ድጋፍ በመቀሌ መጠለያ ለሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖች እንደደረሰም አስረድተዋል፡፡ በቀጣይም ከአንድ መቶ ኀምሳ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው በሁለቱም ክልሎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች እንደሚደርሱ ኮሚሽነሩ አያይዘው ተናግረዋል፡፡     
Read 614 times