ላለፉት በርካታ ዓመታት በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ ሲፈጻጸም የቆየውን በደል የፖለቲካ ድርጅቶች ድምፅ እንዳላሰሙ እንዲሁም ግፉን እንዳላስቆሙ ያስታወሱት ዋና ጸሓፊው ይህ ችግር ዳግም እንዳይከሠት፣ የቤተ ክርስቲያንና የምእመናን ድምፅ የሚሰማበት ዘመን እንዲመጣ ምእመናን በቀጣዩ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ መክረዋል።
ይሁን እንጂ የሥራ አመራር አባላት፣ የሥራ አስፈጻሚ አባላት፣ ማእከላት፣ ወረዳ ማእከላት እንዲሁም የግቢ ጉባኤያት አመራሮች የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ እንደማይችሉ የማኅበሩ የሥራ አመራር መመሪያ በክልከላ ያስቀመጠ መሆኑን ዋና ጸሓፊው አያይዘው ተናግረዋል።
ከማኅበሩ አገልግሎት ከለቀቁ የቆዩ የቀድሞ አመራሮች ደግሞ እነሱ ከፈለጉ የፖለቲካ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚችሉ እና በአሁኑ ሰዓት በፖለቲካው ውስጥ ያሉ ደግሞ ከላይ በዝርዝር ክልከላ ከተደረገባቸው የማኅበሩ የአገልግሎት ዘርፎች ውጭ ማገልገል እንደሚችሉ ዋና ጸሐፊው አስረድተዋል።
ምእመናን በፖለቲካ ውስጥ መሳተፋቸው ከማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ሊያርቃቸው እንደማይችል ያስረዱት ዋና ጸሓፊው ከኦዲትና ኢንስፔክሽን፣ ሚዲያ ክፍልና ኤዲቶሪያል ቦርድ ውጭ ባሉ የማኅበሩ የአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ የሚያገለግሉበት ሂደት መመቻቸቱን አስረድተዋል።
በመጨረሻም ኦርቶዶክሳውያን የፖለቲካ ተሳትፎ እንዳያደርጉ የሚከለክል መመሪያ እንደሌለ ተረድተው በወደዱና በመረጡት የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ ሀገራቸውን፣ ቤተ ክርስቲያናቸውንና ምእመናንን የሚያገለግሉበትን ዕድል እንዲፈጥሩ ጥሪ ያቀረቡት ዋና ጸሓፊው ‹‹የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ብቻ ተመርጦ ሀገር መምራት አለበት የሚል እምነት የለንም፤ ሆኖም ግን ሀገርን የሚያስተዳድረው አካል እምነቱ ምንም ይሁን ምን በፍትሐዊነትና በእኩልነት ሊመራ ይገባዋል›› ብለዋል።