Thursday, 08 April 2021 00:00

የብፁዕ (ዶ/ር) አቡነ ጢሞቴዎስ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

Written by  በጋዜጣው ሪፖርተር
የብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ሥርዓተ ቀብር ረቡዕ መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ።  ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ (ዶር) ከአባታቸው ከባላምባራስ ተስፋ ተክሉ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ታህሣ ኃይሉ በግንቦት ወር ፲፱፻፴ ዓ.ም በትግራይ ክልል ብዛታ ወረዳ ፍልፍሎ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ እንደተወለዱ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል። ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደረሰም በተወለዱበት አካባቢ ከአባታቸው ወንድም አባ ገብረ አረጋዊ ፊደል ንባብ የቃል ትምህርት ተምረዋል። በአቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ሃሌ ሉያ ገዳም ከመምህር ገብረ እግዚአሔር መዝገበ ቅዳሴን፣ ከመሪጌታ ይትባረክ ጸዋትወ ዜማን አጠናቀው የተማሩ ሲሆን በጎጃም ጠቅላይ ግዛት እነማይ አውራጃ መንግሥቶ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ከመምህር ደጉ ቅኔን ከነ አገባቡ አጠናቀዋል። 

 

ብፁዕ (ዶ/ር) አቡነ ጢሞቴዎስ የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሀገር ውስጥ  ጨርሰው ለሁለተኛና ለሦስተኛ ዲግሪያቸው ወደ ራሽያ (የቀድሞው ሶቪየት ኅብረት) በመሄድ ከሌሊንግራድ ዩኒቨርሲቲ የዶክተሬት ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል።

ብፁዕነታቸው በ፲፱፻፵፪ ዓ.ም መዓርገ ዲቁናን የኤርትራና ትግራይ ክፍለ ሀገር ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት  ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ እጅ፣ በ፲፱፻፵፭ ዓ.ም፣ መዓርገ ምንኵስናን በአቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ሃሌ ሉያ ገዳም፣ በ፲፱፻፵፮  ዓ.ም መዓርገ ቅስናን ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ የቀድሞው የኤርትራና የትግራይ ሊቀ ጳጳስ  እንዲሁም በ፲፱፻፸፪ ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ተብለው ተሹመዋል።

ብፁዕ (ዶር) አቡነ ጢሞቴዎስ  ከልጅነታቸው በግብረ ዲቁና የጀመሩትን አገልግሎት በገዳም በረድዕነት፣ በመጋቢነት በመምህርነት እና በአፈ መምህርነት፤ በሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ 

ጳውሎስ መንፈሳዊ ት/ቤት በዳይሬክተርነት፣ በቤተ ክህነት ትምህርት ክፍል ኃላፊነት፣ በገዳማት መምሪያ ኃላፊነት ያገለገሉ ሲሆን መዓርገ ጵጵስና ከተቀበሉ በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ ምክትል ኃላፊነትና ጸሓፊነት፣ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በሊቀ ሥልጣንነት፣ በትንሣኤ መጻሕፍት ማሳተሚያ ድርጅት በዋና ኃላፊነት፤ በሰበታ ቤተ ደናግል በበላይ ኃላፊነት፤ በውጭ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊነት፣ በክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በኃላፊነት፣ በከፋ፣ማጂ፣ኩሎ ኮንታ በሊቀ ጳጳስነት እንዲሁም በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በበላይ ኃላፊነት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ አገልግለዋል።

ብፁዕነታቸው ከ፳፻፲፪ ዓ.ም ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ በጸሎትና በቡራኬ ሆነው በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ባለ ሙሉ ሥልጣን ረዳት ሊቀ ጳጳስ ተመድቦላቸው የበላይ ጠባቂ ሆነው እያገለገሉ ይገኙ ነበር።  

በተወለዱ በ፹፫ ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት ብፁዕ (ዶ/ር) አቡነ ጢሞቴዎስ ሥርዓተ ቀብራቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በክብር ተፈጽሟል።

 

Read 503 times