Thursday, 08 April 2021 00:00

ስለ ድንግልናዬ አፍራለሁ

Written by  በዝግጅት ክፍሉ
ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች እንደምን ከረማችሁ? ስሜ  ወለተ ሥላሴ ይባላል የምኖረው አዲስ አበባ ሲሆን የምተዳደረው በንግድ ሥራ ነው። በሥራዬ ጸባይ ምክንያት ከብዙ ሰዎች ጋር እገናኛለሁ። በዚህ ግንኙነት ውስጥም በንግዱ ሥራ ከተዋወቅሁት ሰው ጋር የፍቅር ግኑኝነት ጀምሬ ነበር። ይህ ግንኙነት አድጎ ብዙ ጊዜያችንን የምናሳልፈው አንድ ላይ ሆነ፤ በዚህ  ብቻም ሳንወሰን ወደ ግበረ ሥጋ ግንኙነት ገብተን በዚያ አጋጣሚ ድንግልናዬን ለማጣት በቃሁ። ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች!  ከዚያ የፍቅር ጓደኛዬ ጋር ብዙ መዝለቅ ባለመቻላችን ግማሽ መንገድ እንደተጓዝን ተለያየን። በዚህም ምክንያት እጅግ ተጎድቼ ስለነበር ለብዙ ጊዜ የወንድ ጓደኛ ሳልይዝ ቆይቻለሁ። ከጊዜ በኋላ ከሌላ የወንድ ጓደኛ ተዋወቄ ትዳር ለመመሥረት ተስማማን። ካለፈው ጊዜ ትምህርት ስለወሰድኩ ከአሁኑ ጓደኛዬ ጋር ያለኝ ግንኙነት የተቆጠበና ጥንቃቄ የተሞላበት ነው። በዚህም በወንድ ጓደኛዬ ዘንድ ድንግል እንደሆንኩ ተቆጥሬያለሁ። ስለጋብቻችን ስናወራም በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ነው የምንጋባው ይለኛል። ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች! ለወንድ ጓደኛዬ የቀደመ ሕይወቴን፣ ድንግል አለመሆኔን መናገር አልቻልኩም፤ ከዚህም በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ነው የምንጋባው ስላለኝ ኃጢአተኛ ሆኜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት እቆማለሁ የሚለው ያሰጋኛል። ድንግል ያለመሆኔን ሳስብ በሁለት መንገድ ፍርሃቴ ይጨምራል። እጅግ ተቸግሬአለሁና ምን ትመክሩኛላችሁ።

 

ውድ እኅታችን ወለተ ሥላሴ ለጥያቄሽ መልስ አገኛለሁ ብለሽ ወደእኛ ጥያቄሽን ይዘሽ በመምጣትሽ እንዲሁም ጥያቄሽን ሳትሸሽጊ በግልጽ በመጠየቅሽ እናመሰግንሻለን። ‹‹በሽታውን የደበቀ መድኃኒት አይገኝለትም›› እንዲሉ አባቶቻችን። እኛም ከጥያቄሽ ተነስተን መልስ ለመስጠት እንሞክራለን። ወለተ ሥላሴ በጥያቄዎችሽ ውስጥ  መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ያለሽን ዕውቀት አብረሽ ብትገልጪልን ጥሩ ይሆን ነበረ። ሆኖም ጥያቄሽ ላይ ተመሥርተን የሚከተለውን መልስ እንሰጥሻለን።

ወለተ ሥላሴ አንቺው እንደነገርሽን ትዳር ለመያዝ ስትፈልጊ ያስጨነቁሽ ሁለት ነገሮች እንዳሉ  ከጥያቄሽ ለመረዳት ችለናል። ድንግል አለመሆንሽን ለወደፊት የትዳር አጋርሽ አለመንገርሽ እና የኃጢአተኛነት ስሜት ስለሚሰማሽ  በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መፍራትሽ ነው። 

ውድ እኅታችን ሰዎች በተለያየ ምክንያት ድንግልናቸውን ሊያጡ ይችላሉ። አንደኛው እና በብዛት የሚታወቀው ከተቃራኒ ጾታዎች ጋር በሚኖራቸው ከልክ ያለፈ ግኙኝነት ለእንደዚህ ዓይነት ስሕተት መጋለጣቸው ነው። ሁለተኛው ሰዎች በተፈጥሮ ድንግልናቸውን ሊያጡ ይችላሉ። በእርግጥ አንቺ እንደነገርሽን ድንግልናሽን ያጣሽው ከወንድ ጓደኛሽ ጋር በነበረሽ ተራክቦ ነው። በሰዎች ላይ እንዲህ ዓይነት ስሕተቶች ይከሰታሉና አንቺም ይህን አንድ ጊዜ የተፈጸመ ስሕተት በመጀመሪያ እንደስሕተት ተቀብለሽ እና በደል መሆኑን አውቀሽ ንስሓ ልትገቢ ይገባል። እግዚአብሔር አምላክ እጅግ ርህሩህ አምላክ፣ ሁሉንም በቸርነቱ የሚያኖር መሆኑን አውቀሽ ወደ እርሱ መጠጋት ይገባሻል። በውስጥሽ ይዘሽ የኖርሽውን እና ዘወትር የሚያስጨንቅሽን ነገር አውጥተሸ ለካህን በመንገርሽ ሰላማዊ ኑሮን እንድትመሪ ከማድረጉም በላይ ለቀጣይ ሕይወትሽ መስተካከልም ዋስትና ነው። 

እንዲሁም በወደፊት የትዳር አጋርሽ እና በአንቺ መካከል ምንም ዓይነት ድብብቆሽ ሊኖር አይገባም። ብዙ ጊዜ በጥንዶች መካከል የሚኖረው ትዳር የሚፈርሰው፤ ባይፈርስም እንኳ በቤታቸው ውስጥ ሰላም የሚታጣው ሁለቱ ተቃራኒ ጾታዎች በእጮኝነት ዘመናቸው አንዱ ለሌላው መንገር የሚገባውን ነገር ሳይነግረው ሲቀር (በመከላቸው የተሸሸገ ነገር ሲኖር) ከትዳር በኋላ የተደበቀው ነገር ሲታወቅ የሚፈጠረው አለመተማመን ነው። በመሆኑም አንቺም የነገው ትዳርሽ እንዲቃናና ሰላማዊ ኑሮን ለመምራት እንዲያስችላችሁ የወደፊት የትዳር አጋርሽ ስለአንቺ ማወቅ የሚገባውን ነገር ሁሉ ልትነግሪው ይገባል። ያለፈ ሕይወትሽን በደሎች በንስሓ መታጠብሽን፣ ዛሬ ላይ አዲስ ሰው መሆንሽን እና ከእርሱ ጋር ባላችሁ ግንኙነት ሰላማዊ ኑሮን ለመመሥረት እንደምትፈልጊ ጭምር ልትነግሪው ይገባል። እርሱም ቢሆን አንቺ ልታውቂው የሚገባው ነገር ሁሉ ላንቺ መንገር ይጠበቅበታል። እንዲህ ዓይነቱ ግልጽ ውይይት ወደፊት በሚኖራችሁ የትዳር ሕይወት ውስጥ መሠረት የሚሆንና መተማመንን የሚፈጥር ነው።

ሁለተኛው በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ለምትፈጽሚው ጋብቻ በእግዚአብሔር ፊት እንዴት እቆማለሁ የሚለው ፍርሃትሽ ነው። በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሁሉን በንስሓ የሚቀበል ቸር አምላክ አባታችን ነውና በዚህ መንገድ ልትረጂ ይገባል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጋብቻን በተመለከተ የራስዋ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ አላት። ስለዚህም የወደፊት የትዳር አጋርሽ የጋብቻ ሥርዓቱ በቤተ ክርስቲያን እንዲፈጸም መፈለጉ የተቀደሰ ሐሳብ ነውና ልትደግፊው ይገባል። 

በዚህ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ውስጥ በሥርዓተ ተክሊል የሚጋቡ ጥንዶች በመጀመሪያ ንጽሕናቸውን ጠብቀው በድንግልና ሊኖሩ ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ የንስሓ አባት ሊኖራቸው እና ስለ ጋብቻቸው እንዲሁም ስለሌላው ሕወታቸው ንስሓ ሊገቡ እርስ በርሳቸውም ሆነ ከንስሓ አባታቸው ጋር መመካከርም ይጠበቅባቸዋል።

በቤተ ክርስቲያን ‹‹ተክሊል›› ማለት ክብር ማለት ሲሆን ከለለ፣ አከበረ፣ ጋረደ ከሚለው ግስ የወጣ ሲሆን በተክሊል ሁለቱ ጥንዶች ጽኑ ኪዳን (የማይፈርስ ውል) የሚቀበሉበት ስለሆነ በሥርዓተ ተክሊል የሚደረግ ጋብቻ የከበረ ነው። ‹‹መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ነው፥ለመኝታውም ርኲሰት የለውም፤›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ምዕራፍ ፲፫ ፥፬። ተክሊል በቤተ ክርስቲያን የከበረ፣ የተቀደሰ ሁለቱን ጥንዶች እስከ ሞት ድረስ ሳይለያዩ እንዲኖሩ የሚያደርግ ውል ነው። 

ሌላው ‹‹ተክሊል›› ማለት ‹‹መቀዳጀት›› ማለት ሲሆን ሁለቱ ጥንዶች በጋብቻ ሥርዓታቸው ቀን በራሳቸው ላይ የሚደፉት አክሊል ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ በዕለቱም ለሙሽሮቹ ጸሎትና ሥርዓተ ቁርባን የሚፈጸም ሲሆን ሥርዓቱ ‹‹ሥርዓተ ተክሊል›› ይባላል። ይህ ሥርዓት በሚፈጸምበት ጊዜም  ጸሎቱ በጆሮ የሚሰማ፣ አክሊሉ፣ ልብሱ  በዓይን የሚታይ ቢሆንም በሙሽሮቹ ላይ የሚያድረው በረከት እና ጸጋ ግን በዓይን የማይታይ፣ በእጅም የማይዳሰስ ረቂቅ ነውና ሥርዓቱ ‹‹ምሥጢረ ተክሊል›› ይባላል።

በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ተክሊል የሚፈጸመው ንጽሕናቸውን ጠብቀው፣ በድንግልና ጸንተው ለኖሩ ጥንዶች ብቻ መሆኑን በፍትሐ ነገሥት ሲገልጽ፤ ከሚጋቡት አንዱ ድንግል ቢሆን ሥርዓተ ተክሊል ይፈጸምለታል የሚል አንቀጽ ፳፬ ቁጥር ፱፻፮ ላይ ተደንግጎ እናገኛለን። በሥርዓተ ተክሊል ለሚጋቡ ሰዎች ሥርዓተ ተክሊል ይፈጸማል፣ ወንጌል ይነበባል፣ ቅብዐ ሜሮን ይደረግላቸዋል። በቃል ኪዳን ቀለበታቸውም ላይ ጸሎት ተደርጎ የመጨረሻውን ሥርዓት ቅዱስ ቁርባንን በመቀበል ጋብቻቸውን ያትማሉ። ይህም ሥርዓት ለሁለቱ ጥንዶች በንጽሕና በድንግልና ተወስነው ለመኖራቸው መገለጫ ነው። 

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ንጽሕናቸውን ጠብቀው ለኖሩ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ሥርዓት ስታደርግ ድንግልናቸውን በልዩ ልዩ ምክንያት ላጡ ሰዎች ደግሞ ‹‹የመዓስባን ጸሎት›› ወይም ‹‹ጸሎተ አስተሥርዮ›› ታደርግላቸዋለች። ጸሎተ አስተሥርዮ ማለት የይቅርታ (የንስሓ) ጸሎት  ማለት ሲሆን  ድንግልናቸውን በተለያየ ምክንያት ያጡ ሰዎች ኃጢአታቸውን እግዚአብሔር  ይቅር እንዲላቸው የሚጸለይ ጸሎት ነው። በቀኖና ቤተ ክርስቲያንም ድንግልናውን ያጣ ሰው ሥርዓተ ተክሊል እንዳይደረግለት ፤ ከሌላጋራ የምትሆነው ሁተኛይቱ ግቢ ግን ከፊተኛይቱ ታንሳለች ስለዚህም የማስተሥረያ ጸሎት ያድርጉ እንጂተክሊል እንዳይደርስላት በሕግ ተጻፈ ይላል። ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፳፬ ቁጥር ፰፻፴፬። በጥንዶች መካከል በድንግልና ምክንያት ልዩነት ካለም ሥርዓተ ተክሊሉ የሚደረግለት ድንግል ለሆነው ብቻ እንደሆነ በፍትሐ ነገሥት ፳፬ ቁጥር ፱፻፮ ተጠቅሶ ይገኛል። ከነዚህ ሕጎች ውጪ በሥርዓተ ጋብቻ ጊዜ ሥርዓተ ቁርባንን በመቀበል ድንግል የሆኑትም ሆነ ያልሆኑት እኩል ይቀበላሉ ማለት ነው። 

ወድ እኅታችን ወለተ ሥላሴ ከላይ ስለ ሥርዓተ ጋብቻ በጥቂቱ ለመዘርዘር እንደሞከርነው በመጀመሪያ ከወደፊት የትዳር አጋርሽ ጋር ያለውን ነገር በግልጽ ከተወያያችሁ በኋላ ንስሐ አባት በመያዝ ንስሓን መቀበል እና መመካከር ይገባሻል። እንደ የትዳር አጋርሽ ምኞት ሥርዓተ ጋብቻችሁን በቤተ ክርስቲያን ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረስ ይጠበቅባችኋል። ምክንያቱም ከዚያ ጋር ተያይዞ ንስሐ መግባት መዘጋጀት፣ በእምነት መቀበል ያስፈልጋልና ነው። ሥርዓተ ጋብቻችሁን በቤተ ክርስቲያን ማድረግ ስምምነት ላይ ከደረሳችሁ በኋላ በቤተ ክርስቲያን በሚኖረው ሥርዓተ ጋብቻችሁ ድንግል ያልሆንሽው አንቺ ብቻ ከሆንሽ ለባለቤትሽ ብቻ ተክሊል እና ከተክሊሉ ጋር የተያያዘው ጸሉት ሲደረግለት ላንቺ ደግሞ ተክሊል ሳይደረግልሽ ‹‹የመዐስባን ጸሎት›› ወይም ‹‹ጸሎተ አስተሥርዮ›› ይደረግልሻል። በመጨረሻም ሁለታችሁም አንድ የምትሆኑበትን ሥርዓተ ቁርባን በአንድነት ትቀበላላችሁ ማለት ነው።

ስለዚህ እኅታችን ከላይ በዝርዝር ለማንሳት እንደሞከርነው ያለፈ ሕይወትሽን በደሎች በንስሓ አስወግደሽ እና ለአዲሱ ትዳር እራስሽን ማዘጋጀት ይጠበቅብሻል። ከወደፊት የትዳር አጋርሽ ጋር ምንም ሳትፈሪና ሳትሳቀቂ በመወያየት እና በመግባባት እንዲሁም ንስሓ በመግባት የወደፊት ሕይወታችሁን የምትመሩበትን መንገድ መወሰን ይጠበቅባችኋል።  የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በመጠበቅም በእግዚአብሔር ፊት በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ማግባት ትችያለሽ ማለት ነው። ወለተ ሥላሴ! ሕይወትሽ ተስተካክሎ፣ ያሰብሽው ተፈጽሞ ለዚያ ታላቅ ቀንም እንዲያበቃሽ ጸሎታችን ነው።

Read 1627 times