Friday, 06 August 2021 00:00

የወር አበባ የመርገም ምልክት ነውን? ክፍል ሁለት

Written by  በዝግጅት ክፍሉ

Overview

የተወደደዳችሁ አንባብያ የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ከዚህ በፊት በነበረው እትም ላይ ማቅረባችን ይታወሳል።ቀጣዩንና ሁለተኛውን ክፍል ደግሞ እነሆ፦ ውድ እኅታችን እኅተ ገብርኤል! ሴቶች በወር አበባ ወቅት ወደ ቤተ ክርስቲያን የማይገቡበት ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት አንዱ ከሆነው ከቅዱስ ቁርባን ክብር ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው። ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄደው ለማስቀደስና የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ለመቀበል ነው። ከቅዱስ ቁርባኑ የሚቀበል ሰው ደግሞ መንፈሳዊና አካላዊ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅበታል። ከአካላዊ ዝግጅት መካከልም ከሰውነት የሚወጣ ፈሳሽ (ሕልመ ሌሊት፣ ደመ ጽጌ፣ የቁስል ፈሳሽ፣ የአፍንጫ ፈሳሽና የመሳሰሉት) ሊኖረው አይገባም የሚለው አንዱ ነው። ይህም የሚሆነው ለቅዱስ ቁርባን ከሚሰጠው ልዩ ክብር የተነሣ ነው።  በዚህም መሠረት ሴቶች በወር አበባ ወቅት፣ ወንዶችም ሕልመ ሌሊት ከታያቸው፣ ባለትዳሮችም ለሦስት ቀናት ራሳቸውን ከሩካቤ ካልከለከሉ ከቅዱስ ቁርባኑ አይቀበሉም (ዘሌ ፮:፲፱-፳፩)። በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፮ ላይም  “ከቀሳውስትና ከዲያቆናት ወገን አንዱስ እንኳ አደፋፍሮ ከግዳጅዋ (ከደሟ) ያልነጻችውን ሴት ቤተ ክርስቲያን ያስገባ በደሟም ወራት ሥጋውንና ደሙን ያቀበላት ቢኖር ከሹመቱ ይሻር። ምንም ከነገሥታት ሴቶች ወገን ብትሆን፡፡” በማለት ሥርዓቱ ተቀምጧል። ከዚህ ውጭ ግን ከማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይሳተፉ የሚከለክላቸው ነገር የለም።

 

እናቶች ድኅረ ወሊድ ወቅት ለተወሰኑ ሳምንታት ከማሕፀናቸው ደም/ፈሳሽ እንደሚፈሳቸው ይታወቃል። ይህም ድኅረ ወሊድ እስከ አራት ሳምንት ድረስ ሊቆይ ይችላል። በተጨማሪም እናቶች በዚህ ወቅት በእርግዝናና በወሊድ ወቅት ከደረሰባቸው አካላዊ ድካም እንዲያርፉ፣ ጨቅላ ሕፃኑ(ኗ)ንም ጡት እንዲያጠቡና እንዲንከባከቡ ሲባል ከመደበኛ ሥራም ጭምር ያርፋሉ። በመንፈሳዊውም አገልግሎት እንዲሁ ጾምና ስግደት የግድ አይጠበቅባቸውም። ጸሎትም ቢሆን የቻሉትን ያህል እንዲጸልዩ ይመከራሉ። ከዚህ ባሻገር ስለየወር አበባ በተገለጸው ምክንያትም አካላዊ ዝግጅት ስለሚያስፈልጋቸው በዚህ ወቅት ቅዱስ ቁርባንን አይቀበሉም። ሕፃኑ(ኗ) ፵/፹ቀን ሲሆነው/ናት ወደ ቤተክርስቲያን ወስደው ያስጠምቃሉ፣ ያስባርካሉ። 

ይህም ቀን እግዚአብሔር ልጅን ስለሰጣቸው የሚያመሰግኑበትና የተሰጣቸውም ልጅ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ የሚወለድበት የደስታ ቀን ነው። የባለትዳሮች የፍቅርና የአንድነታቸው ፍሬ እንዲሁም የእግዚአብሔር ስጦታ የሆነውን ልጅ በመውለድ በሴቶች ላይ የሚመጣ መርገም/ርኩሰት አለ ብሎ ማሰብ ምንኛ አለመታደል ነው?!። በተጨማሪም በብዙ ድካም የወለደችን እናት ከድካሟ እንኳን ሳታገግም ደስታዋን በመካፈልና በማበርታት ፈንታ የረከሰች አድርጎ መቁጠር፣ አለመቅረብ፣ ዕቃ እንኳን ብትነካ ይረክሳል ብሎ ማሰብ ኃጢአትም በደልም ነው። 

አንዳንዶች “ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ይፈሳት የነበረች ሴት ክርስቶስን ነክታ ከዳነች ለምንድን ነው ሴቶች በወር አበባ  ወቅት የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም የማይቀበሉት?” ሲሉ ይጠይቃሉ። ይህንን ለመረዳት ሁለት ነጥቦችን ማስተዋል ያስፈልጋል። አንደኛው ይህች ሴት ያለማቋረጥ ደም ይፈሳት የነበረው በወርኃዊ ልማድ ሳይሆን በበሽታ ምክንያት ነበር። ወደ ክርስቶስም የመጣችው ከዚህ በሽታዋ ለመፈወስ ነበር። ሁለተኛው በፍጹም እምነት የነካችውም የልብሱን ጫፍ ብቻ ነበር። እነዚህ ሁለት ነጥቦች የዚህችን ሴት መዳን ከሴቶች የወር አበባ  እና የቅዱስ ቁርባን ሥርዓት ጋር በፍጹም የማይነጻጸር ያደርጉታል(ማቴ.፱፥፳—፳፪)።

በሌላ በኩል ጥንት በነበረው ሥርዓት (ንጽሕና መጠበቂያ ግብዓቶች ባልነበሩበት ዘመን) ሴቶች በወር አበባ ወቅት ቤተ ክርስቲያን አይግቡ መባሉ እና አሁን ሁሉ ነገር በሠለጠነበትና ዘመናዊ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ባሉበት ዘመንም እንዴት ተመሳሳይ ሥርዓት ሊኖር ይችላል? ብለው የሚጠይቁ ወገኖችም አሉ። ከዚህ ላይ ማስተዋል የሚያስፈልገው ሥርዓቱ የተሠራው የቅዱስ ቁርባንን ክብር፣ የቤተ ክርስቲያንን ክብር፣ እንዲሁም “ከሰውነት የሚፈስ ፈሳሽን” ምክንያት በማድረግ እንጂ የንጽሕና መጠበቂያ ግብዓት አለመኖርን መነሻ በማድረግ አይደለም። ሴቶችም በወር አበባ ወቅት ወደ ቤተ ክርስቲያን የማይገቡት ቤተ ክርስቲያንን እና ቅዱስ ቁርባንን ከማክበር አንጻር መሆኑን በሕሊናቸው ሊያኖሩት ይገባል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በቤተ ክርስቲያን ውስጥም ሆነ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ የሚደረግ ጸሎትና የሚቀርብ ምስጋና ወደ እግዚአብሔር ከመድረስ አንጻር ልዩነት የለውም። ይልቁንም በትሕትና፣ ራስን ዝቅ በማድረግ ሕሊናን ሰብስቦ መጸለይና ማመስገን ላይ ነው ዋናው ቁም ነገሩ ያለው።

ውድ እኅታችን ብዙዎች ይህን ሥርዓት ባለማወቅ ሴቶችን ያገለለ ነው ሲሉ ይደመጣሉ።ነገር ግን ሥርዓቱ የተሠራው ሴቶችን በወርኃዊ ልማድ በሚያዩት የወር አበባ ወይም የድኅረ ወሊድ ፈሳሽ ምክንያት ለማግለል ሳይሆን ለቅዱስ ቁርባን የሚሰጠውን ክብር ለመግለጽ የተሠራ ሥርዓት ነው። ሴቶችም በወር አበባቸው ምክንያት ምንም አይነት መገለል ሊደርስባቸው እንደማይገባ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ያስረዳል። ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን የወር አበባና የድኅረ ወሊድ ወቅትን በተመለከተ ለብዙዎች እኅቶቻችን በሚረዱበት ልክ ማስተማር ተገቢ መሆኑን እናምናለን።

፻፲፩ ተአምራትን በያዘውና በ፲፱፻፹፱ ዓ.ም በታተመው ተአምረ ማርያም መጽሐፍ ፵፰ኛው ተአምር ላይ ከተመዘገበው  በወር አበባ ምክንያት እንደርኩስ ተቆጥራ የአምላክን ሰው መሆን በሚያናንቁ ንስጥሮሳውያን ዕርቃኗን በተተፋባት አንዲት ሴት ታሪክ መረዳት እንችላለን። ይህች ሴት ስለ ቤተ ክርስቲያን ፍቅር ስትል በወር አበባዋ ሰዓት ወደ ቤተ ክርስቲያን በገባች ጊዜ ከሓዲው ሊቀ ጳጳስ ንስጥሮስ ልብስዋን አስገፍፎ እና ራቁቷን እንድትሆን አድርጎ ‹‹እግዚአብሔር ከሴት በሥጋ እንደተወለደ የሚያምን ርጉም ይሁን›› እያለ ሕዝቡ ምራቁን እንዲተፋባት ሲያዝ የተመለከተው ዮሐንስ የተባለ ካህን በሚተፉባት ሰዎች ፊት ለተዋረደ እና ለተተፋበት ኃፍረተ ሥጋዋ ክብር ስሞ “እኔስ እግዚአብሔር ከሴት በሥጋ እንደተወለደ አምናለሁ” በማለት እምነቱን በመመስከሩ ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበረችው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል በሰው አንደበት ‹‹የእመቤታችንን ንጽሕናዋን አሰበ እንጂ የራሱን ርኵሰት አላሰበም ስትል ዮሐንስ አፈወርቅ›› ብላዋለች። የቅዱሳት መጻሕፍትን ምስጢር የማይረዱ መናፍቃን ግን የዚህን ጻድቅ ታሪክ በማይረባ መልኩ እየተረጎሙ ስተው ያስቱበታል። 

በእውነት ከወር አበባዋ ሳትነጻ፣ ምራቅ እየተተፋበት ያለን የሴት አካል ከሥጋዊ ፍትወት ጋር አነጻጽረው የሚያምታቱ መናፍቃን ምን ያህል የጎሰቆለ አዕምሮ እንዳላቸው እንረዳለን። እነርሱ የቅዱሳት መጻሕፍት ጠላቶች መሆናቸው የተገለጠ ነውና። ካህኑ ዮሐንስ ግን ሰው የሚጸየፈውን ከወር አበባዋ ያልነጻችውን ለዚህች ሴት ዕርቃን  ክብር መስጠቱ ሴቶችን ከባሕርያቸው የተነሳ ርግማን ያለባቸው አድርጎ ማሰብ የተሳሳተ መሆኑን ያስረዳናል። ስለሆነም በወር አበባም ሆነ ድኅረ ወሊድ በሚመጣ ፈሳሽ የተነሳ ሴቶችን ማቃለልም ሆነ ማግለል ተገቢ አይደለም ሴቶችም በወር አበባ ወቅት ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባትና ቅዱስ ቁርባንን ከመቀበል ስለተከለከሉ የመገለል ስሜት ሊሰማቸው አይገባም። ይልቁንም ይህን ጊዜ የሚጸልዩበት፣ በቂ ዕረፍት የሚያደርጉበትና ራሳቸውን የሚንከባከቡበት ሊያደርጉት ይገባል።

ቤተ ክርስቲያን የገነት ምሳሌ ናት። ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያስረዱን ሔዋን ከአዳም ጋር በገነት ለሰባት ዓመታት ስትኖር የወር አበባ አልነበረባትም። ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን የገነት ምሳሌ መሆኗን ለማሳየት ሴቶች በወር አበባ ወቅት፣ ወንዶችም ሕልመ ሌሊት ከታያቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን አይገቡም። ነገር ግን አገልግሎቱን የሚከታተሉበት ሥፍራ እንደየ አካባቢው ሁኔታ በሚገባ ሊዘጋጅላቸው ይገባል። ለምሳሌ እንደየቦታው የቴክኖሎጂ ተደራሽነት የሚወሰን ቢሆንም ቅዳሴውን ከውጭ ሆነው ቀጥታ እያዳመጡና እያዩ የሚከታተሉበት ሁኔታ እንዲመቻች ጥረት ሊደረግ ይገባል። ከዚህም በተጨማሪ ይህ እኅቶችና እናቶች የሚያስቀድሱበት ቦታ መለየቱን መነሻ በማድረግ እዚያ ሆነው የሚያስቀድሱት ላይ ሌላ መገለል እንዳይደርስ ምእመናንን ስለየወር አበባ ምንነትና ተያያዥ ጉዳዮች ማስተማር ይገባል። ይህንን ሳያደርጉ “መግባት የለባቸውም” ማለት ብቻ ሴቶችን ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲርቁ ሊያደርጋቸው ይችላልና። 

ውድ እኅታችን እኅተ ገብርኤል አንቺም ከላይ የተሰጠውን መንፈሳዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማብራሪያ በደንብ በመገንዘብ እንደ ቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት ልትመላለሺ ይገባል።የተለያዩ ሰዎች የሚሰጡሽን የተለያየ አስተያየት በመቀበልም ራስሽን ማስጨነቅ አይገባም።ቃሉን ሰምተሸ የምትጠቀሚበት ያድርግሽ ረድኤተ እግዚአብሔር አይለይሽ!

Read 832 times