የተወደዳችሁ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደምን አላችሁ? አሜን የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን። የክርስትና ስሜ ወልደ ሚካኤል ይባላል። የምኖረው ጎባ ከተማ ነው። በሞያዬ መምህርና የ፴፪ ዓመት ወጣት ነኝ። ትዳር አልያዝኩም፣ እጮኛም የለኝም የምኖረውም ብቻዬን ነው። ጠንካራ ክርስቲያን ባልሆንም አልፎ አልፎ በሰንበት ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ እሳለማለሁ እጸልያለሁ።
ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች! በተደጋጋሚ የማየው አጸያፊ ሕልም እየረበሸኝ ተቸግሬአለሁ። እሱም ተኝቼ ሳለ በሕልሜ ዝሙትን ስፈጽም አያለሁ። ዝሙትን የምፈጽመው ከተለያዩ ሰዎች ጋር ነው አንዳንዶቹን አውቃቸዋለሁ አንዳንዱቹን በመልክም በስምም የማላውቃቸው ናቸው። በሕልሜ ዝሙት ከፈጸምኩ በኋላ በእውን ያደረኩት ይመስለኝና ደንግጬ እነሣለሁ። በዚያ ሰዓት የዘር ፈሳሽ በሰውነቴ በልብሴ ላይ አገኛለሁ። በማግሥቱ ከሰው ጋር መገናኘት ያስጠላኛል ቤተ ክርስቲያን መሄድ እስኪያስፈራኝ ድረስ ራሴንም እንደርኩስ፣ እንደተረገመ ሰው እቆጥራለሁ። ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች! ይህ ለብዙ ጊዜ የተቸገርኩበት የኔ ምሥጢር ነው። ለሰው ለምቀርባቸው ጓደኞቼ እንኳ ለማማከር እፈልግና ፍርሃት እና ይሉኝታ ይይዘኛል። በዚህም እጅግ ተቸግሬአለሁ። እናንተ ለብዙዎቹ ጥያቄዎች እና ቸግሮች መልስ እንዲሁም መፍትሔ ስትሰጡ አያለሁና የኔንም ጥያቄ ትመልሱልኛላችሁ ብዬ በማመን በውስጤ ይዠየው የቆየሁትን ምሥጢር ወደ እናንተ ለመጻፍ ተገደድኩ። እባካችሁ ከችግሬ የምላቀቅበትን መፍትሔ ጠቁሙኝ። ለመሆኑ በሕልሜ ዝሙት መፈጸሜ ኃጢአት ይሆንብኝ ይሆን?
ውድ ጠያቂያችን ወልደ ሚካኤል በቅድሚያ በሕይወትህ የተቸገርክበትን ጉዳይ ደብቀህ ብቻህን ከመብሰልሰልና ከመጨነቅ ይልቅ መፍትሔ አገኛለሁ ብለህ ልታካፍለን ወደ እኛ በመጻፍህ በእግዚአብሔር ስም እናመሰግንሃለን። በመቀጠል እንዲህ ዓይነት ገጠመኞች ያንተ ብቻ ሳይሆኑ በብዙ ሰዎች ወንዶች እና ሴቶች ላይ የሚከሰቱ ነገሮች ናቸውና አብዝተህ ልትጨነቅ አይገባህም።
በተደጋጋሚ የምታየው ሕልም ኃጢአት ነው ኃጢአት አይደለም የሚለውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ከምንነቱ መነሳት አስፈላጊ ነው። እንዲህ ዓይነት ሕልሞች ‹‹ ሕልመ ሌሊት›› በመባል ይታወቃሉ። ሕልመ ሌሊት ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ሰዎች በሚተኙበት እና በጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ በሚሆኑበት ሰዓት ክፉ ክፉ ሕልሞችን በማሳየት ይፈታተናቸዋል። ከነዚህ ክፉ ክፉ ሕልሞች መካከል አንደኛው የሴትን ወይም የወንድን ገላ በማሳየት አሊያም ወንድና ሴት ተራክቦ ሲፈጽሙ በማሳየት ሰውየውን ወይም ሴትየዋን ለዚህ ዓይነት እኩይ ሐሳብ እንዲገዙ ያደርጓቸዋል፡ ይህ ሰው ባየው ወይም ይህች ሴት ባየችው ሕልም ይሳቡና በሕልማቸው ዝሙት ሲፈጽሙ ያድራሉ።
እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ጸዋግ(ኅሡም) በመባል ይታወቃል። ይህም ማለት በሌላ አነጋገር ክፉ ሕልም ማለት ነው። በመጽሐፈ መነኰሳት ላይ ‹‹ሰይጣናት የሰውን ልጅ ቀን ቀን ክፉ ሐሳብ በማሳሰብና በማሠራት በሌሊት ደግሞ ዝሙት የሞላበት አጸያፊ ሕልም ያሳዩታል›› በማለት ሰይጣን ምን ያህል የሰውን ልጅ አእምሮ በመቆጣጠር በሕልሙ ሳይቀር አጸያፊ ሕልም በማሳየት እንዴት እንደሚዋጋ በዚህ መረዳት እንችላለን።
እንዲህ ዓይነቱ የሰይጣን ፈተና ወይም ድርጊት ወንዱን ወይም ሴትዋን ለሕልመ ሌሊት ወይንም ለዝንየት አሳልፎ ይሰጣል። ‹‹ሕልመ ሌሊት(ዝንየት) አንድ ወንድ ወይም ሴት እንደ ገሀዱ ዓለም በሚመስል ሩካቤ ከሰውነት ፈሳሽ የሚወጣበት ሂደት ነው። በመሆኑም ሕልመ ሌሊት ወይም ዝንየት ጾታ ሳይለይ በሁለቱም ላይ የሚከሰት ነው። ውድ ወንድማችን እንደነገርከን እኛም እንደተረዳንህ አንተም በነዚህ ሂደቶች ውስጥ እንደምታልፍ ነው። በመጀመሪያ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ዝሙትን ስትፈጽም ታያለህ ቀጥሎ ሕልመ ሌሊት(ዝንየት) ይመታሃል። ይህ ዋናው መገለጫ ነውና።
ሕልመ ሌሊት በተለያዩ መንገዶች ሊከሠት ወይም ሊመጣብን ይችላል። ከነዚያም መካከል አንዱ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው በጥንተ ጠላታችን በሰይጣን አማካኝነት ሌት በተኛንበት በምትሐት የማይገባ ነገር በማሳየት እና እኛም በስሜት ወደዚያ እንድንገባ በማድረግ በሕልማችን ሩካቤን እንድናደርግ በመገፋፋት ነው። ሁለተኛው የዝሙት መንፈስ ያለባቸው ሰዎች ለዚህ ኃጢአት በእጅጉ የተጋለጡ ናቸው። ይህም ማለት አንድ ሰው በአእምሮው ስለዝሙት የሚያስብ በልቡናው የሚያመላልስ ከሆነ በሕልሙ ከመፈጸም አልፎ ሕልመ ሌሊት (ዝንየት) ሊፈትነው ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ የዝሙት መንፈስ በአብዛኛው የሚታየው ያላገቡ እና ወጣቶች ላይ ሲሆን አልፎ አልፎ ያገቡ ሰዎችም ላይ ይከሠታል።
ውድ ወንድማችን! ሰዎች በጠለቀ እንቅልፍ ውስጥ ሆነው የሚከሠት በሕልም ዝሙት መፈጸም(ሩካቤ መፈጸም) እንደ ኃጢአት እንዲቆጠርና እንዳይቆጠር የሚያደርጉ የተለያዩ ሁኔታዎች አሉ:: ስለዚህ በደፈናው ሕልመ ሌሊትን ኃጢአት ነው ወይም አይደለም ማለት አይቻልም:: ነገር ግን እንደ ኃጢአት እንዲቆጠር የሚያደርጉ ሁኔታዎች አሉ እነሱም፦
- የሰው ልጅ አጋንንት የሚያቀርቡለትን እንዲህ ዓይነቱን ፈተና ደስ እያለው ሲቀበል
- ወደ ዝሙት የሚያመሩ ማንኛውንም ነገሮች ሲጠቀም ለምሳሌ ከዝሙት ጋር የተያያዙ መጻሕፍትን፣ መጽሔት ጋዜጣ ሲያነብ አሊያም ከዚህ ዓይነት ነገር ጋር የተያያዙ ፊልሞችን ሲያይ . . . ወዘተ
- ወደ ዝሙት የሚገፋፉ ነገሮችን ከመቃወም ይልቅ ሲቀበል
- ኃጢአትን እንደ ኃጢአት ቆጥሮ ሳይናዘዝባት ሲቀር
- ስለ ተቃራኒ ጾታ አብዝቶ ሲመኝ እና በዚያ መንገድ ሲመጣ እንዲሁም
- ማር ይስሐቅ በአንቀጽ ፳ ምዕራፍ ፩ ላይ ‹‹በኃይል አብዝቶ መመገብ ከወጣትነት ኃጢአት ጋር ተያይዞ ሐሳብን በግድ እንዲያመጣ ያደርጋሉ›› እንዲል አብዝቶ በመብላትና በመጠጣት ሕልመ ሌሊት ያየ ሰው
- በማር ይስሐቅ አንቀጽ ፳ ምዕራፍ ፪ ላይ ‹‹ ከሰውነቱ ምንጭ የሚነቃ ርኩስ ዘር በዝቶ ሳለ የፈሰሰ ጎስቋላ ምንጣፉ፣ ልብሱ፣ ደስ የተሰኘ ሥጋው ሁለንተናው የረከሰ ነው። ሥጋ ሁል ጊዜ ያነቃዋልና ዘር የሚፈሰው በሌሊት ብቻ አይደለም ። ሕሊናውንም ያረክሰዋል። ›› ተብሎ እንደተጻፈ በዚህ እና ከላይ በተዘረዘሩ ምክንያቶች ሁሉ ኃጢአት ይሆንበታል ማለት ነው።
ነገር ግን አንድ ሰው በንቁ ልቡናውእያለ በቀን የሚመጡበትን ኃጢአት እየተቃወመ ሳለ በተኛ ጊዜ ሆኖ ሕልመ ሌሊት (ዝንየት ቢያገኘው) በሕልሙ የፈጸመው ወይም ሕልመ ሌሊቱ ኃጢአት አይሆንበትም።
ውድ ወንድማችን ሕልመ ሌሊት(ዝንየት) ያገኘው ሰው ኃጢአት የሚሆንበት እና የማይሆንበት ምክንያት እንዳለ ሆኖ በቤተ ክርስቲያ ሥርዓት ፦
- ሕልመ ሌሊት ያገኘው ሰው በዕለቱ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ቅዱስ ቁርባንን መቀበል አይችልም፣ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባት ይከለከላል (መግባት ካለበት እንኳ ልብሱን እና ገላውን ታጥቦ በማግስቱ ነው)፣ በመኝታ ወቅት ሕልመ ሌሊት ሊከሰት ስለሚችል በቤተ ክርስቲያን ፈጽሞ መተኛት አይቻልም፣ ወደ ቤተ መቅደስ ፈጽሞ መግባት ባይቻልምመላ ሰውነትንና ልብስን ካጠቡ በኋላ በቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው ቅጽር በመግባት መጸለይ፣ ትምህርት መማር ጉባኤ መካፈል የተፈቀደ ነው ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ገጽ ፻፳፬።
ሌላው በሕልም ከሚደረጉ እኩይ ነገሮች ለመራቅ ሕልሙን ደስ እየተሰኙ አለማሰብ፣‹‹ ሌሊት በሕልም ከሴት ጋር የተገናኘህ መስሎህ ዘር ቢወርድህ በመዓልት አታስባት›› እንዲል መጽሐፈ መነኰሳት ለሌሊት ሕልም የጋበዘህን እኩይ ሐሳብ በቀን መቃወም ተገቢ ነው። ሕልመ ሌሊት በሚታይበት ጊዜ ቸል ብሎ ከመተኛት ተነስቶ ተጣጥቦ መጸለይ ቢቻል መስገድ ጾርን ያጠፋል። እንዲሁም በመኝታ ሰዓት ምግብ አብዝቶ አለመብላትና ውሃን አብዝቶ አለመጠጣት ከእንዲህ ዓይነቱ ፈተና ይታደጋልና ተግባራዊ ማድረጉ ጠቃሚ ነው።
ውድ ወንድማችን ወልደ ሚካኤል ከላይ በመግቢያው ላይ በዝርዝር ልትገልጽልን እንደሞከርከው እንዲህ ዓይነቱ መጥፎ ድርጊት እንደገጠመህ እንጂ በምን ምክንያት እንዳገኘህ አልገለጥክልንም። ከላይ ያነሳኸው ማብራሪያ እንዳለ ሆኖ ወደ አንተ ስንመጣ በሕልምህ ዝሙት ስትሠራ ማየትህና በሕልመ ሌሊት መመታትህ ቀን ወይም በማንኛው ሰዓት ስለ ዝሙት ወይም ስለተቃራኒ ጾታ አብዝተህ በማሰብ ፣ የተለያዩ ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ መጽሐፍ፣ መጽሔት አሊያም ጋዜጣ በማንበብ፣ እንዲሁም ፊልሞችን በማየት ምክንያት ከሆነ ይህ የመጣብህ ጦር ኃጢአት ነውና ንስሓ ልትገባ ይገባል።
ከእንዲህ ዓይነቱ ፈተና ለመሸሽ ወይም ለመራቅ እኩይ የሆኑ የዝሙት ሐሳቦች ከመጡብህ በተቻለ መጠን በጾም በጸሎት በስግደት ከውስጥህ ልታስወግዳቸው እንዲሁም አጥብቀህ ልትቃወማቸው ይገባል። ምክንያቱም በንቁ ልቡናህ ቀን አጥብቀህ ከተቃወምከው እና ከልብህ አውጥተህ ከሰደድከው ሌሊት በሕልም ወደ አንተ ተመልሶ አይመጣምና ነው።
በእርግጥ ዘር ፍሰት (ሕልመ ሌሊት) ማየት የአፍላ ጉልምስና ከሆኑት ምልክቶች አንዱ ሲሆን ሰዎች በጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ሆነው ሕልመ ሌሊት ወይም ዝንየት ሊያጋጥማቸው ይችላል። ለዘር የበቁ ወጣቶች ተኝተው ሳለ በጠለቀ እንቅልፍ ውስጥ ሆነው ሕልም በሚያልሙበት ወቅት ይታያቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ ሕልም ‹‹ ሕልመ ጽምረት(የመስቆርርት ሕልም) ይባላል። ሕልሙን ያየ ሰውም ዝንየት አገነኝ (ሕልመ ሌሊት መታኝ) ይላል።
ውድ ወንድማችን ምንም ዓይነት እኩይ የዝሙት ሐሳብ በውስጥ ሳይኖር እንዲህ ዓይነት ዝንየት ሲያገኝህ ተነሥተህ መላ አካልህን በመታጠብ ጸሎት ማድረስ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሳትገባ በርቀት ሁነህ ሄደህ መጸለይ፣እንዲሁም መስገድ፣ በጉባኤ ሰዓት ጉባኤ መካፈል ትችላለህ። ነገር ግን ዝንየት ባገኘህ ቀን ጸበል መጠጣት ቅዱስ ቁርባን መቀበል አትችልም። በአጠቃላይ ከእንዲህ ዓይነቱ ጾር ለመሸሽ አብዝቶ መጸለይ ፣ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣ መስገድ፣ ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ ፊልሞችን አለማየት፣ ጋዜጣና መጽሔቶችን አለማንበብ እንዲሁም የምንወስደውን ምግብ እና መጠጥ በመጠኑ ማድረግ ተገቢ ነው። ከዚህም ባሻገር ከንስሓ አባትህ ጋር መመካከር ሌላውና ትልቁ መፍትሔም ነው። ውድ ወንድማችን ወልደ ሚካኤል ከላይ ከሰጠንህ ምክር በላይ ደግሞ እግዚአብሔር አምላክ ከዚህ ጾር ያወጣህ ዘንድ ጸሎታችን ነው እግዚአብሔር ይርዳህ።