Monday, 28 June 2021 00:00

የወር አበባ የመርገም ምልክት ነውን? ክፍል አንድ

Written by  በዝግጅት ክፍሉ
ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች! እንደምን ሰነበታችሁ? እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ደኅና ነኝ። ስሜ እኅተ ገብርኤል ይባላል የ፳፬ ዓመት ወጣት ስሆን የምኖረው ወሊሶ ከተማ ነው። ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች በሕይወቴ ውስጥ ጥያቄ ሆኖ የቆውን ጉዳይ ለእናንተ ላካፍል ወደድኩ። የወር አበባ በማይበት ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ እፈራለሁ ሕጉንም ስለማላውቅ ምናልባት ኃጢአት ይሆንብኝ ይሆናል በሚል የወር አበባ ላይ በምሆንበት ጊዜ የቤተ ክርስቲያኑን ቅጥሩን እንኳ መንካት እፈራለሁ። 

 

የትኛው ትክክል የትኛው ስሕተት እንደሆነ ለይቼ ባለማወቄም በተለያዩ ጊዜያት ላገኘኋቸው አባቶች የወር አበባን አስመልክቶ በጠየቅኋቸው ጊዜ የሰጡኝ መልስ የተለያየ በመሆኑ ግራ ተጋብቻለሁ። ‹‹የወር አበባ ላይ በምሆንበት ጊዜ ከምን ከምን ነው የምከለከለው? በማለት ላነሣሁላቸው ጥያቄ  አንደኛው ካህን የወር አበባ የመርገም ምልክት እንደሆነ እና በዚያ ወቅት ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድም ሆነ መግባት እንዲሁም የተለያዩ መንፈሳዊ ተግባራትን ማከናወን እንደሌለብኝ  ሲነግሩኝ ሁለተኛው ካህን በወር አበባ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን መግባት ፣ መስቀል መሳለም እና የመሳሰሉ መንፈሳዊ ተግባራት ማከናወን እንደሚቻል ፤ብዙ ጊዜ በወር አበባ ሰዓት ቤተ ክርስቲያን አትግቡ የሚባለው ከንጽሕና ጋር ተያይዞ መሆኑን ነገሩኝ።

እኔም የወር አበባ ላይ በምሆንበት ጊዜ የሚያሳስበኝ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ አለብኝ ወይስ የለብኝም የሚለው ጉዳይ ነው። ሌሎች ሰዎችንም ለማማከር ስሞክር የሚሰጡኝ የየራሳቸውን አመለካከት ነው እንጂ ውስጤን የሚያረካ አይደለም። በዚህም ምክንያት የተጨበጠ ነገር ሳልይዝ መሀል መንገድ ላይ ነኝ። ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍሎች የወር አበባ ላይ በምሆንበት ጊዜ ምን ማድረግ አለብኝ? የወር አበባስ የመርገም ምልክት ነውን? እነዚህን ጥያቄዎች እንድትመልሱልኝ በእግዚአብሔር ስም እጠይቃችኋለሁ።

ውድ ጠያቂያችን እኅተ ገብርኤል በቅድሚያ ጥያቄ ሆኖ  በውስጥሽ ሲመላለስ የነበረውን ጉዳይ መልስ አገኛለሁ ብለሽ ስላካፈልሽን እናመሰግናለን፤ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች የብዙ እኅቶቻችን ጥያቄዎች ሊሆኑ ይችላሉና ለዚህ ዝግጅት እንዲስማማ አድርገን አቅርበነዋል፤ መልካም ንባብ።

በመጀመሪያ የወር አበባ ለሴቶች ብቻ የተሰጠ በተለይም ልጅ ለመውለድ የሚያስችላቸው ልማድ ነው። የሁላችን እናት የሆነችው ሔዋን የወር አበባን በማየት የመጀመሪያዋ ናት። እናታችን ሔዋን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተላልፋ የተከለከለውን ዕፀ በለስ ቆርጣ እርስዋም በልታ ለባልዋ ለአዳም በመስጠትዋ ምክንያት በእግዚአብሔር ከተረገመችው ርግማን መካከል አንዱ የወር አበባ የመርገም ምልክት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል ዘፍ. ፫፥፲፮። ነገር ግን ይህ ርግማን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ከሔዋን እና ከልጅ ልጆቿ ባጠቃላይ ከሰው ዘር በሙሉ ተወግዷል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን በቀዳማዊ አዳም አለመታዘዝ ምክንያት የመጣ ኃጢአትና ርግማን በዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም መታዘዝ ርቆልናል፣ ቀርቶልናል። ምክንያተ ሞት በሆነች በቀዳማዊት ሔዋን አለመታዘዝ የመጣ ርግማን ምክንያተ ሕይወት በሆነች በዳግሚት ሔዋን በድንግል ማርያም መታዘዝና ትኀትና ቀርቶልናል። መቅድመ ተአምረ ማርያም “የሔዋን ጽኑ (የሚጎዳ) ማሠሪያዋ በአንቺ የተቆረጠላት እመቤቴ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ” እንዲል። በዚህ መልኩ በዘመነ ሐዲስ ርግማን መሆኑ ቀርቶ የሴቶች ወርኃዊ ልማድ ሆኗል። ምንም እንኳ በዘመነ ሐዲስ የወር አበባ የመውለድ ምልክት እንጂ ርግማን መሆኑ ቢቀርም ከሚያስከትላቸው አካላዊና ሥነ ልቡናዊ መገለጫዎች የተነሣ እንዲሁም ስለ ክብረ ቤተ ክርስቲያን ሴቶች በወር አበባ ወቅት የክርስቶስ ሥጋና ደም ተፈትቶ ለምእመናን ወደሚሰጥበት የቤተ ክርስቲያን ክፍል (ቅድስት ወይም ቅኔ ማኅሌት) እንዳይገቡ የቤተክርስቲያን ሥርዓት ይደነግጋል።

ውድ እኅታችን እኅተ ገብርኤል ሴቶች በወር አበባ (ደመ ጽጌ፣ ልማደ አንስት) ወቅትና ድኅረ ወሊድ (ሕፃን ልጅ እስኪጠመቅ ድረስ) ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባት የለባቸውም የሚለው የሠለስቱ ምዕት ትዕዛዝ (ፍት ነገ አንቀጽ ፮) ባልተገባ መልኩ በመተርጎም በልማድ የዳበሩ የተሳሳቱ አመለካከቶች ጉዳይ ነው። የፍትሐ ነገሥቱን ክልከላ ዓላማ በሚገባ ያልተረዱ አንዳንድ ወገኖች የወር አበባን በዘሌ ፲፪፥፩-፰ ካለው መርገም ጋር አሁንም ድረስ አንድ አድርገው ይቆጥሩታል። በዚህም የተነሳ በወር አበባ ላይ ያሉ ሴቶችን በተለየና ከርኲሰት ጋር በማያያዝ የሚመለከቱ አሉ። የወር አበባን ከርግማን ጋር በማነጻጸር ሴቶችን ወደ ቤተክርስቲያን ከመሄድ፣ ጸሎት ከመጸለይ፣ መስቀል ከመሳለምና ሌሎች መሰል መንፈሳዊ አገልግሎቶችን የሚከለክሉ እንዳሉ ሁሉ የፍትሐ ነገሥቱን ክልከላ መሠረታዊ ምክንያት ባለመረዳት “ሴቶች በወር አበባ ወቅት ቤተ ክርስቲያን ቢገቡ ምንም ችግር የለውም” የሚሉም ይሰማሉ።

ይህን ሴቶች በወር አበባ ወቅት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይገቡ የሚከለክለውን የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ከሁለት የተሳሳቱ ሐሳቦች ጋር የሚያገናኙ ወገኖች አሉ። አንደኛው ስሑት ሐሳብ የወር አበባን እንደ መርገም ከመቁጠር የመነጨ ነው። ይህም የሰው ልጅን ፍጹም ድኅነት በሚገባ ካለመረዳትና የወር አበባን ምንነት ጠንቅቆ ካለማወቅ የሚመጣ ስሕተት ነው። የወር አበባ ልማዳዊ  አጀማመር ከሔዋን አለመታዘዝ ጋር መገናኘቱ በዘመነ ሐዲስ በክርስቶስ ቤዛነት የተዋጁ ሴቶች ካላቸው ልማዳዊ ዑደት ጋር መምታታት የለበትም። ዛሬም በርግማን ሥር እንዳለን አድርጎ ማሰብና ማስተማር የክርስቶስን አዳኝነት ማቃለል፣ የሰውነትን ክብር ማዋረድ ነው።

ከሰናዖር ሰዎች ዐመፅ የተነሳ በመደበላለቅ (ርግማን) ብዙ ቋንቋዎች ቢፈጠሩም በዘመነ ሐዲስ ግን እነዚያ ቋንቋዎች (ልሳናት) የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ማሳያ እንደሆኑት ሁሉ ከርግማን ጋር የተያያዘ መነሻ ታሪክ ያለው የሴቶች የወር አበባም በዘመነ ሐዲስ ልማድ እንጂ መርገም  አይደለም።

ከላይ እንደተገለጠው በወር አበባ ወቅት ሴቶች ወደ ቤተ መቅደስ መግባትና ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል የሚከለከለው በርግማን ምክንያት ሳይሆን የወር አበባ ፈሳሽ በሚፈጥረው ወይም ይፈጥረዋል ተብሎ በሚገመተው አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጫና ምክንያት ነው። እንደመነሻ የሚጠቀሰውም   በዘሌ. ፲፭፥፲፱“ ላይ ‹‹ሴት ፈሳሽ ነገር ቢኖርባት በሥጋዋም ያለው ፈሳሽ ነገር ደም ቢሆን፥ በመርገምዋ ሰባት ቀን ትቀመጣለች፤ የሚነካትም ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው››  የሚለው የቅዱስ መጽሐፍ  ንባብ ነው። 

ነገር ግን ከርግማንና ከቁራኝነት ጋር የተያያዙ የዘመነ ብሉይ ንባባት ከዘመነ ሐዲስ የክርስቶስ ቤዛነት ጋር ተስማምተው መነበብና መተርጎም እንዳለባቸው የታወቀ ነው። በክርስቶስ ድኅነት የተፈጸመለት ሰው (ሴትም ወንድም) በኃጢአት ምክንያት የሚመጣ ርኩሰት ካልሆነ በቀር በተፈጥሮው መርገም የለበትም። የወር አበባ የሚባለው በማሕፀን ውስጥ ፅንስን ለመቀበል የተዘጋጀ መደላድል፤ ፅንስ ሳይመጣ ሲቀር ለሌላ ዑደት ቦታውን የሚለቅበት ሂደት እንጂ መርገም አይደለም። ልማደ አንስት በዚህ ዘመን እንደ ርኲሰት ወይም እንደ መርገም አይቆጠርም። ሴቶችም በዚህ ወቅት “ርኩስ ነኝ” የሚል ስሜት ሊሰማቸውም ከቶ አይገባም።

ሁለተኛው ስሕተት ደግሞ ሴቶች በደመ ጽጌ ወቅት ወደ ቤተ ክርስቲያን ቢገቡ ቤተ ክርስቲያኑን ያረክሱታል ከሚል የአይሁድ ሥርዓት የተወሰደ ነው። በመጀመሪያው እንዳየነው የወር አበባ መርገም/ርኲሰት ስላልሆነ ማንንም አያረክስም። በሌላ በኩልም በሰዎች ምክንያት የምትረክስ ቤተ ክርስቲያን የለችንም። ሰዎች ሥርዓቷን ቢጥሱ እንኳን ራሳቸው በኃጢአታቸው ይረክሳሉ እንጂ ቤተ ክርስቲያንን አያረክሷትም። ስለዚህ የዚህ ስሕተት ሌላው መሠረቱ ቤተ ክርስቲያን የማትረክስ መሆኗን ካለማስተዋልም ጭምር የመጣ ነው። ሴቶችም በዚህ ወቅት ቤተክርስቲያን ብሄድ፣ መስቀል ብሳለም፣ የጸሎት መጻሕፍትን ብነካ ‘ላረክስ እችላለሁ’ የሚል ስጋት ሊገባቸው ከቶ አይገባም።

 

Read 1692 times