Wednesday, 28 April 2021 00:00

‹‹ከሌላ ሴት ብወልድ ኃጢአት ይሆንብኝ ይሆን?››

Written by  በጋዜጣው ሪፖርተር
ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች! እንደምን ሰነበታችሁ? እኔ እግዚአብሔር ይመስገን ድኅና ነኝ። ስሜ ገብረ ትንሣኤ ይባላል የ፵፭ ዓመት ጎልማሳ ነኝ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ፈተና የሆነብኝን ነገር ላካፍችሁ ወደ እናንተ ጻፍኩ። ነገሩ እንዲህ ነው እኔ እና ባለቤቴ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ቊርባን ከተጋባን ዐሥር ዓመት ሆነን ነገር ግን ቤታችን በልጅ አልተባረከም። የሞላ ሀብት ቢኖረንም እስከዛሬ ድረስ ልጅን መውለድ አልቻልንም። የመጀመሪያዎቹን ሦስት ዓመታት እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ ጠበቅን ምንም ነገር የለም።  በመሀል እኔ እንድንመረመር ለባለቤቴ ጥያቄ አቀረብኩና ወደ ሆስፒታል ሄድን ስንመረመር እኔ መውለድ እችላለሁ እርሷ መውለድ አትችልም(መሀን ናት)። ይህ ውጤት ግን ለቤታችን ሰላምን ይዞ አልመጣም በመሀከላችን የነበረው ፍቅር እየቀዘቀዘ ከመሄዱም በላይ ዘወትር በረባ ባረባው መጨቃጨቅ ሥራችን ሆነ። ለዚህ ደግሞ ትልቁን ድርሻ የምትወስደው የትዳር አጋሬ ናት። በሆነ ባልሆነው ይከፋታል ሲያሻት ታኮርፈኛለች። በስሕተት ስለ ወለዱ ሰዎች ካወራሁ ወይም ከጓደኞቼ ጋር አምሽቼ ከገባሁ ‹‹እኔ መውለድ ስለማልችል ጠልተኸኝ ነው፤ የምትወልድ ማግባት ትችላለህ ›› እያለች ወደ ውጪ እንዳይ ትገፋኛለች። እኔ መፋታት ኃጢአት ነው ብዬ አስባለሁ ፤ነገር ግን በየዕለቱ  በዚህ ምክንያት ቤቴ መግባት እስኪያስጠላኝ ደርሻለሁ።

 

እኔም ልጅ እንዲኖረኝ በብርቱ እጓጓለሁ ዘር ተክቼ ባልፍ ንብረቴን የሚወርስ ልጅ ቢኖረኝ ደስ ይለኛል። ከሌላ ወልጄ አምጥቼ አብረን ብናሳድግ ብዬ አስባለሁ ነገር ግን ይህንን ለባለቤቴ መንገር እፈራለሁ። አንዳንዴ በድብቅ ባደርገውስ ባወቀች ጊዜ ትወቅ የሚል ሐሳብ ይመጣብኛል። ውድ የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጆች በእነዚህ ሁለት ሐሳቦች ውስጥ ወድቄአለሁና ምን ትመክሩኛላችሁ? ‹‹ከሌላ ሴት ብወልድ ኃጢአት ይሆንብኝ ይሆን?››  

ውድ ወንድማችን ገብረ ትንሣኤ በቅድሚያ ችግርህን (ምሥጢርህን) ስላካፈልከን እናመሰግናለን፤ እንዲህ ዓይነት ገጠመኞች በብዙ ሰዎች ሕይወት ውስጥ በወንዶችም በሴቶችም ላይ ይከሠታሉና የአንተ የሕይወት አጋጣሚ በእንዲህ ዓይነት ሕይወት ውስጥ ላሉ ሁሉ ሊጠቅም ስለሚችል እና አስተማሪ በመሆኑ ለዚህ ዝግጅት እንዲስማማ አድርገን አቅርበነዋል፤ መልካም ንባብ።

ውድ ወንድማችን አንተን የገጠመህ ችግር የባለቤትህ (የትዳር አጋርህ) መሀን መሆን ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ በቤታችሁ ውስጥ ሰላም የማጣታችሁ ጉዳይ ነው። ይህ በቤትህ ውስጥ መፈጠሩ ደግሞ ልብህ ‹‹ከሌላ ሴት ልጅ ወልጄ ላምጣ›› ወደሚለው ሐሳብ እያዘነበለብህ ነው። በተለይ የባለቤትህ ጠባይ ከዕለት ወደ ዕለት እየተለወጠ መምጣቱ እና በሆነ ባልሆነው አኩራፊ መሆንዋን ልትረዳት ይገባል። አንተው እንደገለጽክልን እንዲህ ዓይነት ጠባይ ያመጣችው መሀን መሆንዋን ካወቀች በኋላ ነውና እንደ አንድ የትዳር አጋር ልትንከባከባት እና የምትናገረውንም ልታልፋት ይገባል። የነቢዩ ሳሙኤል እናት ሐና ሳሙኤልን እስክትወልድ ድረስ በጣውንቷ ትቀናባትና ታዝን ነበር ከዚያም አልፎ ትበሳጭ፣ ምግብ አልበላም በማለትታለቅስም ነበረ በዚህ ጊዜ ባለቤትዋ ሕልቃና ግን እንዳታለቅስ እንዳታዝን ምግብም እንድትበላ ይመክራት ነበር (፩ኛ ሳሙ ፩ ፥ ፩—፰።) አንተም ስሜትዋ የተጎዳ ባለቤትህን ልታዝንላት ልትንከባከባት እና ልትመክራት ይገባል እንጂ ልትበሳጭባት አይገባም። 

በትዳር እያለህም ከሌላ ሴት ልጅ ወልዶ ማምጣትም ከላይ በዝርዝር ለማስቀመጥ እንደሞከርነው ኃጢአት ነው። በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ከጋብቻ ውጪ የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግኑኝነት እጅግ ኃጢአት ነው:: አንተም ከተከበረው ትዳርህ ውጪ የምታደርገው ግኑኝነት ፍጹም ኃጢአት ነውና ወደዚያ ልታስብ አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ  ‹‹ ከዝሙት ራቁ ፤ ኃጢአት የሚሠራ ሰው ሁሉ ከሥጋው ውጪ ይሠራልና፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን ራሱ በሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል።›› (፩ኛ ቆሮ ፮፥፲፰) ይላልና አንተም ከባለቤትህ ተለይተህ በዝሙት ኃጢአት መውደቅ አይገባህም። ‹‹ሴሰኞች በእግዚብሔር መንግሥት ርእስት እንደሌላቸው ይህንን ዕወቁ›› (ኤፌ.፭፥፭) ተብሎ የተጻፈውን ልታስተውል ይገባል። ሴሰኝነት አመንዝራነት ማለት ደግሞ በከበረ ትዳር ላይ ሄዶ ማመንዘር ነው። ሐዋርያው እንደነዚህ ያሉትን ነው አመንዝሮች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም በማለት የሚያስጠነቅቃቸው። 

ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ከሴት ጋር የሚያመነዝር ግን አእምሮ የጎደለው ነው። እንዲህም የሚያደርግ ነፍሱን ያጠፋል››  ይላል ምሳ. ፮፥፴፪ ፩ኛቆ ፯፥፴፮ በመሆኑም በልጅ ፍለጋ ሰበብ  ከትዳርህ ውጪ የምታደርገው የግብረ ሥጋ ግኙኝነት ለሥጋ ብቻ የሚተርፍ ሳይሆን ነፍስንም የሚያጠፋ ነው። በመሆኑም ከእንደዚህ ዓይነት ነፍስን እስከማጣት ከሚያደርስ ኃጢአት ልትሸሽ ልትርቅ ይገባል። ቅዱስ ጳውሎስም ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው መልእክቱ ‹‹በዋጋ ተገዝታችኋልና የራሳችሁ አይደላችሁም ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ›› ፩ኛቆሮ. ፯፥፴፮  እንዳለ ከእግዚአብሔር የተሰጠህን ቅዱስ ሥጋ ለጊዜያዊ ምኞትህ የልብህን መሻት ለመፈጸም ብለህ  በፍጹም ሥጋህን ማርከስ አይገባህም። ምክንያቱም  አንተ የአንተ ሳትሆን የፈጣሪህ የክርስቶስ አካል ነህና። እንዲህ ዓይነቱ ፆርም አንተን ከእግዚአብሔር ሊለይህ የመጣ ፈተና ነውና ከእንደዚህ ዓይነቱ የኃጢአት ምኞት በጊዜ ልትርቅ ይገባል። 

ውድ ወንድማችን ከትዳር አጋርህ ጋር ሆነህ ከዚህ ይልቅ በተስፋ በመጠበቅ በጸሎት በምልጃ ብትጸኑ አንድ ቀን እግዚአብሔር ለጸሎታችሁ መልስ ይሰጣችኋል። ቅድስት ሐና የሳሙኤል እናት ለረጅም ጊዜ ልጅ አልነበራትም በዚህ ምክንያት ሁል ጊዜ ታዝን ትተክዝ ነበረ። አብዝታ ወደ እግዚአብሔር በመጮዃ እግዚአብሔር አምላክ ለጸሎትዋ ለልቅሶዋ መልስ ሰጣት የእግዚአብሔርን ቤት የሚያገለግል የእስራኤልን ነገሥታት የሚቀባ ታላቁን ነቢይ ሳሙኤልን ሰጣት (፩ኛሳሙ.፩፥፩—፳፰)

ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚያስተምረን አብርሃም እና ሣራም ልጅ አልነበራቸውም ፤ሁለቱም ፈጽመው ባረጁበት ሰዓት ሣራም የሴት ወግ ማየት ባቆመችበት የእርጅና ዘመን እግዚአብሔር ይስሐቅን ሰጣቸው። (ዘፍ. ፲፰፥፱—፲፭) ይስሐቅን መስጠት ብቻ ሳይሆን ለሣራ አሕዛብና የአሕዛብ ነገሥታት ከእርስዋ እንደሚወጡ ነግሯታል። (ዘፍ.፲፯፥፲፮) በአዲስ ኪዳንም በተመሳሳይ ካህኑ ዘካርያስና ሚስቱ ኤልሳቤጥ ልጅ አልነበራቸውም ካህኑ ዘካርያስ በቤተ መቅደስ እያጠነ ሳለ የእግዚአብሔር መልአክ ልጅ እንደሚወልድ ሲነግረው ሁለቱም አርጅተው ስለነበረ የመልአኩን ቃል አላመነም ፤ነገር ግን መልአኩን ስላላመነ ዲዳ ከሆነ በኋላ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ሲወለድ አንደበቱ እንደተፈታለት እናያለን። (ሉቃ. ፩፥፭—፳፭) 

ውድ ወንድማችን እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ በጸሎት እየተጋህ በቤቱ ልትኖር ይገባል። ‹‹ ጌታ ቅርብ ነው። በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (ፊል. ፬፥፮-፯) አንተም ከዚህ በኋላ ሚስቴ ልጅ ልትወልድ አትችልም በሚል ስጋት ውስጥ ገብተህ ሐሳብህን በሁለት መክፈል የለብህም። ይልቁንም ሁሉን ነገር ለእግዚአብሔር አሳልፈህ በመስጠት ከእርሱ የሚመጣውን በረከት ብትጠብቅ መልካም ነው። አምላካችን እግዚዘብሔር የታመነ አምላክ ነውና የልብ መሻታችንን እና ጩኸታችንን ሰምቶ ፈቃዳችንን ለመፈጸም የሚሳነው ነገር የለም:: ይህ ይፈጸም ዘንድ ከአንተና ከባለቤትህ የሚጠበቀው ፍጹም እምነት ነው።  

ስለዚህ ውድ ወንድማችን ገብረ ትንሣኤ ‹‹ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና›› ሉቃ. ፩፥፴፯ አንተ እና የትዳር አጋርህ የልባችሁን ሥጋት እና ጥርጣሬ ከውስጣችሁ አስወግዳችሁ ልባችሁን በእግዚአብሔር ላይ በማድረግ እርሱን በተስፋ ልትጠብቁት ይገባል። ከጸሎታችሁም ባሻገር እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ በእርጅና ዘመናቸው ሁሉ ሲጠብቁት በስተመጨረሻ በልጅ የባረካቸውን እነዚህን ቅዱሳን የእግዚአብሔር ሰዎች አብነት ማድረግ ይኖርባችኋል። በእግዚአብሔር ፊትም በመንበርከክ በጸሎት፣ በምልጃ ልትማጸኑት ይገባል። አብርሃምና ሣራን፣ ሕልቃናንና ሐናን እንዲሁም ካህኑ ዘካርያስንና ኤልሳቤጥን፣ ጸጋ ዘአብንና እግዚእ ኃሪያን ያሰበ አምላክ እናንተንም ያስባችኋል ፤ በልጅም በረከት ይባርካችኋል። አስቀድመን እንደተናገርነው ከእናንተ የሚጠበቀው በእምነት ወደ እግዚአብሔር ቀርባችሁ በፍጹም ልብ መለመን ብቻ ነው። መጽሐፍ ‹‹ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና›› (ሉቃ. ፩፥፴፰) እንዲል የልባችሁን መሻት ይሰጣችኋል። እግዚአብሔር አምላክ ጸሎታችሁን ሰምቶ የልባችሁን መሻት ይሰጣችሁ ዘንድ መልካም ፈቃዱ ይሁን።

 

Read 791 times