Thursday, 08 April 2021 00:00

‹‹የቅባት እምነት አራማጅ ነን›› የሚሉ ኃይሎች አገልጋዮችን ከአገልግሎት ማሰናበታቸው ተገለጠ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ‹‹የቅባት እምነት አራማጅ ነን›› የሚሉ የተደራጁ ኃይሎች እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን ከአገልግሎት እያገዱና እያሰናበቱ መሆኑን ቅሬታቸውን ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ያቀረቡ አባቶች ገለጡ፡፡   የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ የነበሩትና አሁን ከአገልገሎት ከታገዱት አገልጋዮች መካከል አንዱ የሆኑት ሊቀ ኅሩያን ባሕረ ጥበብ አያሌው ከማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ከፍተኛ የሆነ የሃይማኖት፣ የመልካም አስተዳደርና የገንዘብ አጠቃቀም ችግር ያለበት መሆኑን ተቃውመው ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነትና ቅዱስ ሲኖዶስ በመውሰዳቸው ምክንያት ከአገልግሎት እንደታገዱ አስረድተዋል፡፡ 

 

ችግሩ መፍትሔ ያልተገኘለት መሆኑና ‹‹የቅባት እምነት አራማጅ ነን›› የሚሉ ኃይሎችን በመቃወማችው ከደመወዝና ከአገልግሎት መታገዳቸውን ያነሡት ሊቀ ኅሩያን ባሕረ ጥበብ ከመጋቢት ፲ ቀን ፳፻፲3 ዓ.ም ጀምሮ በተጻፈ ደብዳቤ እርሳቸውን ጨምሮ ዐሥር ያህል አገልጋዮች ከአገልግሎት መሰናበታቸውን ተናግረዋል፡፡ 

በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የጎዛመን ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት መልአከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ኪዳነ ማርያምም በበኩላቸው በሀገረ ስብከታቸው ከዚህ ቀደም ‹‹የቅባት እምነት›› የሚባለው ከወሬ በዘለለ እንደማይታወቅ ጠቅሰው ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ከ፳፻፬ ዓ.ም ጀምሮ በሀገረ ስብከቱ በሊቀ ጳጳስነት ከተሾሙ በኋላ ግን ለቤተ ክርስቲያን የህልውና ፈተና እየሆነ እንደመጣ አስረድተዋል፡፡ 

‹‹የቅባት እምነት››  ለአካባቢው ምእመናንና አገልጋዮች የቅሬታ ምንጭ ሆኖ እንደዘለቀ ያነሡት ሥራ አስኪያጁ በጉዳዩ ዙሪያ ቅሬታ ያሰሙ ምእመናንና አገልጋዮች ለዓመታት ከአገልግሎት እንዲታገዱ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡ 

ከጎዛመን ወረዳ ቤተ ክህነት  ብቻ አሥራ ሰባት አገልጋዮች በመሰናበታቸው በአገልጋይ እጥረት ምክንያት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዳይታጎል ለጉዳዩ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጠው በማለት ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ለአጣሪ ኮሚቴ ቅሬታቸውን ማቅረባቸውንም አክለዋል፡፡ 

ብፁዕ አቡነ ማርቆስ በሀገረ ስብከቱ በሚኙ አድባራትና ገዳማት እየተዘዋወሩ ‹‹ጎጃም ተጠመቅ ተብለሀል›› የሚል ተንኳሽና ቀስቃሽ ንግግር በመናገር አንድ ዓይነት ሃይማኖት የሚከተለውን የአካባቢውን ኅብረተሰብ እርስ በእርሱ በክፉ እንዲተያይና እንዲጋጭ አለመግባባትም እንዲፈጠር እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት የደብረ ማርቆስ ወረዳ ቤተ ክህነት የካህናት ክፍል ኃላፊ የነበሩት መልአከ ጽዮን ቆሞስ አባ ላእከ ማርያም ገ/ሕይወትም እንዲሁ “የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ከተሳሳተ መንገድ እንዲመለሱ እስካሁን ድረስ ብንታገሥም፤ ነገሩ እየከረረና ጫፍ እየወጣ በመምጣቱ ጉዳዩን ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ለማሰማት አዲስ አባባ ድረስ  መጥተናል” ብለዋል፡፡ 

ከዚሁ አያይዘውም በአሁኑ ሰዓት በሀገረ ስብከቱ አገልጋዮች እየተሰደዱ የዘረፋ ተግባራትም እየተፈጸሙ መሆናቸውን የገለጡት የካህናት ክፍል ኃላፊው አንዳንድ በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ የአገልግሎት ቢሮዎችም መታሸጋቸውን ‹‹የቅባት እምነት አራማጅ ነን›› የሚሉ ኃይሎች ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውጭ የሆነ አደረጃጀት መፍጠራቸውን ጨምረው ገልጠዋል፡፡   

ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ከተሾሙ በኋላ በወረዳ ቤተ ክህነቱ በአንድ ገዳም ብቻ ከ፳ በላይ መነኰሳት፣ የአቋቋምና የመጽሐፍት መምህራን ከአገልግሎት እንደተሰናበቱ ያስታወቁት መልአከ ጽዮን ቆሞስ አባ ላእከ ማርያም ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ማሕሌታዊ ሆነው አገልግሎት ሁሉ ክብር ባለመስጠታቸውና አገልግሎቱን  በመናቃቸው በቤተ ክርስቱያን ላይ የተፈጸመ በደል መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

 

Read 964 times