Wednesday, 28 April 2021 00:00

ማኅበረ ቅዱሳን የስድስት ወር የሥራ አመራር ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ

Written by  በጋዜጣው ሪፖርተር

Overview

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የስድስት ወር የሥራ አመራር ጉባኤውን ከሚያዚያ ፩ እስከ ሚያዚያ ፫  ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም አካሄደ። ለሦስት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው በዚሁ ጉባኤ ላይ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገር የተወከሉ የማዕከላት አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኝተዋል። በጉባኤውም የሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ፣ የኤዲቶሪያል ቦርድ ማስተባበሪያ፣ የኦዲት አገልግሎት ሪፖርታቸውን ያቀረቡ ሲሆን የስድስት ወር የሥራ አመራር ቃለ ጉባኤም ጸድቋል።  በቀጣይ ቀናትም የቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ አገልግሎት ተግዳሮትና ቀጣይ አቅጣጫዎች፣ ስልታዊ ዕቅድ ማሻሻያ፣ የተቋማዊ  ለውጥ መነሻ ሐሳቦች እንዲሁም የኢንቨስትመንት ፖሊሲ መነሻ ሐሳብ  የሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ተነሥተው  ውይይት ተደርጎባቸዋል።  ማኅበሩ ስልታዊ ዕቅድ ከጀመረ አራተኛ ዓመት ላይ እንደሚገኝ የገለጹት የማኅበሩ ዋና ጸሓፊ አቶ ውብሸት ኦቶሮ የስልታዊ ዕቅዱ አጠቃላይ ይዘት ስድስት ወሳኝ ጉዳዮችን፣ ፳፱ ግቦችን ፪፻፳፫ ስልቶችና አመላካቾች የተካተቱበት እደሆነ፤ የስልታዊ ዕቅዱ ዋና እሳቤም ከአጋር እና ከተባባሪ አካላት ጋር በጋራ እንደሚሠራ እንዲሁም የሰው ኃይል ልማት ላይ እንደሚያተኩርም ገልጸዋል።   በጉባኤው መዝጊያም የማኅበሩ ዋና ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ  በሀገራችን በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክተው ችግሩ እጅግ እየተወሳሰበ መምጣቱን ገልጸዋል። አክለውም የማኅበሩ አባላት ከወትሮ በተለየ መልኩ ሱባኤ ገብተው ጸሎት በማድረግ እንዲሁም በማስተማር እና በመምከር ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።  
Read 566 times