Wednesday, 28 April 2021 00:00

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለሩሲያ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ የምስጋና ደብዳቤ ላኩ

Written by  በጋዜጣው ሪፖርተር

Overview

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳስ ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በኢትዮጵያ ሃይማኖትን መሠረት የደረጉ ጥቃቶች ለደረሰባቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ላደረጉት ጸሎት እና ድጋፍ ለሩሲያ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ክሪል ሚያዚያ ፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም  የምስጋና ደብዳቤ መላካቸውን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ዘግቧል። ቅዱስነታቸው የምስጋና ደብዳቤውን የላኩት የሞስኮና የመላው ሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ክሪል በኦሮምያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያን ምእመናን መገደላቸውን አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የኀዘን መግለጫ እንዲሁም የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ድጋፍ እንደሚያደርጉ የሚገልጽ ደብዳቤ መላካቸውን ተከትሎ ነው። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በሀገሪቱ ውስጥ እየተካሄዱ ያሉት ጥቃቶች በዋነኝነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ መሆናቸውን በምስጋና ደብዳቤያቸው ላይ አክለው ገልጸዋል። የሞስኮና የመላው የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ክሪል በየካቲት ወር ፳፻፲፫ ዓ.ም ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የኀዘን መግለጫ ደብዳቤ መላካቸውን አስመልክቶ መዘገባችን ይታወሳል።  
Read 479 times