Wednesday, 28 April 2021 00:00

የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በአጣዬና አካባቢው ለተፈናቀሉ ምእመናን ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በተፈጸመ ጥቃት  ለተፈናቀሉ የአጣዬ ከተማና አካባቢው ምእመናን የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ማድረጉን የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ነቃዐጥበብ አባቡ አስታወቁ፡፡  በቅርቡ በአጣዬ ከተማና አካባቢው የጥፋት ኃይሎች በፈጸሙት ዘርና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ጥቃት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ አስከፊ ጉዳት እንደደረሰ ሥራ አስኪያጁ ገልጠዋል፡፡ በተፈጸመው ጥቃት ሀብት ንብረት እንደወደመና ቁጥሩ በውል ያልታወቀ የሰው ሕይወት እንደጠፋ ያስረዱት ሥራ አስኪያጁ በጥቃቱም እስካሁን ድረስ ከሁለት መቶ ሃምሳ ሽህ በላይ ምእመናን ተፈናቅለው በተለያዩ ጊዜያዊ መጠለያዎች እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡  ከጥቃቱ የተረፉ ምእመናን በደብረ ብርሃን፤ በደብረ ሲናና በመሐል ሜዳ ከተሞች ጊዜያዊ መጠለያ እንደሚገኙ የገለጡት ሥራ አስኪያጅ ሀገረ ስብከቱም አቅም የፈቀደውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በአጣዬ ከተማና አካባቢው አክራሪዎች ባደረሱት ጥቃት ምክንያት በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የዘገበ ሲሆን ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚሠራው ሥራ ላይ ሀገረ ስብከታቸው በቀጣይነት ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡  ሀገረ ስብከቱ በተለይ በመሐል ሜዳ ተፈናቅለው ለሚገኙ ምእመናን አስቸኳይ ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን ያስረዳው ዘገባው ድጋፍ የተደረገላቸው ምእመናንም ለተደረገላቸው ድጋፍ ማመስገናቸውን አስረድቷል፡፡  ሰሞኑን በሚከበረው የትንሣኤ በዓል ወቅት ምእመናን በጥቃቱ ጉዳት ከደረሰባቸው ምእመናን ጋር በጋራ በማክበር ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ብፁዕነታቸው አሳስበዋል፡፡ በአካባቢው ተመሳሳይ ችግር ድጋሚ እንዳይከሰት ሀገረ ስብከታቸው ከፌደራልና ከክልሉ መንግሥት ጋር ተቀራርቦ እየሠራ መሆኑንን ብፁዕነታቸው አንስተው በሌሎች አካባቢዎች በጊዜያዊ መጠለያ ላሉ ምእመናን ጭምር አስቸኳይ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውንም ዘገባው  አስረድቷል፡፡   
Read 460 times