Saturday, 15 May 2021 00:00

በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ መንግሥታዊ ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑን ማኅበረ ቅዱሳን አስታወቀ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና ላይ የተቀናጀና የታቀደ መንግሥታዊ ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑን ማኅበረ ቅዱሳን ግንቦት ፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቀ።  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች የመንግሥት መዋቅርን ተጠቅመው ቤተ ክርስቲያንን በልዩ ልዩ መንገድ ሲያጠቋትና ክርስቲያኖችን ሲገድሉ፤ ሲያሳድዱና ሲያፈናቅሉ እንደነበር ማኅበሩ ገልጦ በዚህ ሁኔታ ላይ ለጠፋው ጥፋት መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን ይቅርታ ሳይጠይቅ መቆየቱ እንዳሳዘነው ገልጧል።  “በቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ይዞታዎች ላይ አንዳንድ አካላት ያለ አግባብ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መንግሥት መልስ ለመስጠት የሚያሳየው ቁርጠኝነትና በሌሎች ቤተ እምነቶች ላይ ላልተከሠቱ ችግሮችም እንደተከሠቱ አድርጎ ይቅርታ ሲጠይቅ ይስተዋላል” ያለው ማኅበሩ ይህ ድርጊቱም በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለው የተቀናጀ ጥቃት በመንግሥት በኩል የሚፈጸም ተደርጎ እንዲወሰድ ማድረጉንም አንሥቷል።  መንግሥት የተለያዩ ውሳኔዎችን ሲወስን የቤተ ክርስቲያንን መብት በመጋፋትና ፍትሕን በማዛባት ሳይሆን በዕውቀትና በሕግ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ያሳሰበው ማኅበሩ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን በሀገሪቱ ለሚደርሰው የሰላም መደፍረስ ችግር ኃላፊነቱን ሊወስድ እንደሚገባው  አሳስቧል።  በዚህ ወቅት ቤተ ክርስቲያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ችግር ውስጥ መውደቋን ምእመናን በትክክል እንዲረዱ ያስገነዘበው ማኅበሩ ቀደምት አባቶቻችን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ስደት የተቀበሉበትን መንገድ ለመከተል መዘጋጀት እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርቧል።    ሀገርና ሰላም ወዳድ ኢትዮጵውያን በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን የተቀናጀና የተደራጀ መገፋትና ስደት በመረዳት ከቤተ ክርስቲያን ጎን እንዲቆሙና የበኩላቸውን እንዲያደርጉም ማኅበሩ ጠይቋል።
Read 901 times