Saturday, 15 May 2021 00:00

ቤተ ክርስቲያን የዴር ሱልጣን ገዳምን ከወረራ የታደጉ አካላትን አመሰገነች

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
በሰሙነ ሕማማትና በትንሣኤ በዓል ወቅት በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳም ላይ የግብፅ መነኮሳትና ሊቃነ ጳጳሳት ያደረጉትን ወረራ የታደጉ አካላትን በመንበረ ፓትርያርክ የውጭ ጉዳይ ጽ/ቤት ሚያዚያ ፳፰ቀን  ፳፻፲፫ ዓ.ም በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ቤተ ክርስቲያን አመሰገነች።  በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የሚገኘው ጥንታዊውና ታሪካዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይዞታ የሆነው የዴር ሱልጣን ገዳም ላይ ግብጻውያን አሁን  ድረስ ያለማቋረጥ  በሚፈጥሩት ትንኮሳና ግጭት የቤተ ክርስቲያንን የባለቤትነት መብት ለመንጠቅ በሚያደርጉት  ጥረት በተረጋጋ ሁኔታ ገዳሙን ለማስተዳደርና ለማልማት እዳልተቻለ መግለጫው አስገንዝቧል።  በየዓመቱ የትንሣኤ በዓልን ለማክበር ዝግጅት በሚደረግበት ወቅትና በበዓላት አከባበር ላይ ግብጻውያኑ የሚፈጥሩት ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የጠቀሰው መግለጫው በዚህ ዓመትም በበዓለ ትንሣኤ አከባበር ላይ በተደራጀና በተጠና መልኩ በቤተ ክርስቲያን ይዞታ ላይ ግልጽ የሆነ ወረራ ከመፈጸማቸው ባሻገር በአባቶች ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ እንዲሁም ድብደባ መፈፀማቸው ተመላክቷል።  ችግሩ ከተፈጠረ ጀምሮ በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለ ሙሉ ሥልጣን ክቡር አምባሳደር ረታ ዓለሙ፣ መንበረ ጵጵስናው፣ የገዳሙ መነኰሳትና በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የእስራኤል የሀገር ውሰጥ የደኅንነት ምክትል ሚኒስቴር አቶ ጋዲ ይቫርከን እገዛ አድርገዋል። የሕግ የበላይነትን በማስከበርና ግብጻውያኑን በፖሊስ ከአካባቢው በማወስጣት ችግሩ በቁጥጥር ሥር ውሎ የትንሣኤ በዓል በሰላም መከበር እንደቻለ በመግለጫው ተገልጧል።  በተለይ በወቅቱ የኢየሩሳሌም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዕንባቆምና የገዳሙ ዋና መጋቢ አባ ዘበአማን ሳሙኤል ከአበው መነኮሳት ጋር በጋራ ባሰሙት ጥሪ ችግሩን በቁጥጥር ሥር ማዋል እንደተቻለ ያስረዳው መግለጫው የኢስራኤል የሀገር ውስጥ ምክትል የደኅንነት ሚኒስቴር አቶ ጋዲ ይቫርከን ግብጻውያን የወረሩትን የገዳሙ ክፍል ቶሎ ለቀው እንዲወጡ ማድረጋቸው በመግለጫው ተጠቅሷል።  በገዳሙ የተፈጠረውን ችግር ቶሎ በቁጥጥር ሥር በማዋልና የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ይዞታ በማስጠበቅ የትንሣኤ በዓል በሰላም እንዲከበር ላደረጉ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ፣ መነኮሳት፣ የእስራኤል የሀገር ውሰጥ የደኅንነት ምክትል ሚኒስቴር አቶ ጋዲ ይቫርከን፣ በእስራኤል የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ክቡር አቶ ረታ ዓለሙ እንዲሁም በእስራኤል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመግለጫው ምስጋና ቀርቦላቸዋል።  የኢትዮጵያ መንግሥት የቤተ ክርስቲያን ይዞታ እንዲከበር ከእስራኤል መንግሥት ጋር በጋራ እንዲሠራ፣ በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን  በጋራ ጫና እንዲፈጥሩና የሃይማኖት ወገኖቻችን የሆኑት የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከጥፋት ተግባራቸው በመቆጠብ ለዘመናት የቆየውን ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ትስስር እንዳይሸረሸር ማድረግ እንደሚገባቸው በመግለጫው ጥሪ ቀርቧል።     
Read 587 times