Monday, 10 August 2020 00:00

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እና መዘዙ

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

  አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማለት የአንድ ሀገር መንግሥት ሕዝቡ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በሚገባበት ወቅት ዜጎች ማድረግና መደረግ የሌለባቸውን ጉዳዮች በዝርዝር የሚያስቀምጥ ሲሆን ዜጎች ማድረግ እያለባቸው ሳያደርጉ ሲቀሩ ወይም ማድረግ የሌለባቸውን ሲያደርጉ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ የአንድ ሀገር መንግሥት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ሊጥል የሚችለው ተፈጥሮአዊ አደጋ ሲከሰት፣ የእርስ በእርስ ግጭት ሲፈጠር፣ ረኀብና ድርቅ ሲከሰት እንዲሁም የማኅበረሰቡን ጤና የሚጎዳ ወረርሽ ሲከሰት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ታዲያ መንግሥታት እንደተፈጠረው ሁኔታ ዜጎቻቸው እንዲጠነቀቁና የሕይወት ዘይቤአቸውን እንዲቀይሩ ለማድረግ አስቸኳይ የሆነ አዋጅን ያውጃሉ፡፡ በዘመናችን አንዳንድ ሀገራት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተመሳሳይ መልኩ በዜጎቻቸው ላይ ገደብ ወይም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲጥሉ ተስተውሏል፡፡ እነዚህ ሀገራት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከጣሉበት ምክንያት ከላይ ከተዘረዘሩት ችግሮች መካከል አንዱ በመከሰቱ ነው፡፡ ይኽውም የሰውን ልጅ ጤና የሚያውክ እና ለሞት የሚዳርግ ኮሮና ቫይረስ (COVID -19) የተባለ ወረርሸኝ በመከሰቱ ነው፡፡ ታድያ በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ የዓለማችን ሀገራት በዜጎቻቸው ላይ የተለያየ ገደብ በተለያየ ጊዜ ጥለዋል፡፡  ኮሮና ቫይረስ (COVID -19) የዓለምን ሁለንተናዊ  እንቅስቃሴ ያናጋ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያም የዚህ ገፈት ቀማሽ በመሆኗ እንደሌሎች የዓለም ሀገራት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀች እነሆ ወራቶች ተቆጥረዋል፡፡ በኢትዮጵያ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተጣለ ጊዜ ጀምሮ ታዲያ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች ተስተጓጉለዋል፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  ከሌሎች እምነት ተቋማት በተለየ መልኩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ እጅግ ውስብስብ የሆኑ ችግሮችን ፈጥሯል፡፡ አገልጋይ አባቶችን ለኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል፡፡ ቤተክርስቲያንም ከምእመናን ታገኝ የነበረውን የገንዘብና የቁስ ድጋፍ አስቀርቶባታል፡፡ ከእነዚህ ችግሮች በተጨማሪ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቤተክርስቲያን በፀጥታ ችግር እንድትቸገርና የተደራጁ አክራሪ ቡድኖችንና አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሽፋን ያደረጉ አንዳንድ የፀጥታ ኃይሎች ምእመናንን ያለአግባብ እንዲደበድቡና በእስር እንዲያንገላቱ በር ከፍቶላቸዋል፡፡ መንግሥትና ሕዝብ ባለበት ሀገር ላይ አንዳንድ የፀጥታ ኃይሎች ለሚከተሉት ሃይማኖት ወግነው አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን  እንደሽፋን ተጠቅመው ምእመናንን ይደበድባሉ፣ ያስራሉ አለፍ ሲልም በኢኮኖሚ ለማዳከም የብር መቀጮ ይጠይቃሉ፡፡

 

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተጣለ ወዲህ በተለይ በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች የምእመናን መደብደብና የካህናት መታሰር የተለመደ ሆኗል፡፡ አንዳንድ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች  ሕገ መንግሥቱን ተከትለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማስፈጸም ሲገባቸው ነገር ግን የተጣለውን ገደብ እንደሽፋን በመጠቀም የግል ፍላጎታቸውንና ለሚከተሉት እምነት በመወገን ወቅቱን ተጠቅመው ቤተ ክርስትያንንና ምእመናን በከፍተኛ ሁኔታ እያጠቁ ያለፉበት እንደሆነ ከየአካባቢው እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅት ምእመናን ከቤተክርስቲያን ማግኘት ያለባቸውን አገልግሎት እያገኙ ስላልነበረ ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት ጋር ባደረገችው ውይይት ምእመናን የመንግስትንና የጤና ባለሙያዎችን ምክር ተግባራዊ በማድረግ አገልግሎት እንዲያገኙ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በመሆኑም ምእመናን ክርስትና ማስነሳት፣ መቁረብና ማስቆረብ እንዲሁም በመጠኑም ቢሆን ማስቀደስ ችለዋል፡፡ እነዚህ ሥርዓቶች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሞላ ጎደል ቢፈጸሙም በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ግን ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን ትልቅ ችግር ገጥሟቸዋል፡፡

ምእመናንና አገልጋዮችን የፀጥታ ኃይሉ እንዳይተናኮልና እንዳያንገላታ ቤተክርስቲያን ከመንግሥት ጋር የተስማማችውን ስምምነት የሚያስረዳ ግንቦት 5 ቀን 2012ዓ.ም ባለ አምስት ገጽ ሸኚ ደብዳቤ ለየአህጉረ  ስብከቱ ተልኮአል፡፡ አህጉረ ስብከቶችም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተወሰኑና በደብዳቤው ላይ የተቀመጡ ዝርዝር ጉዳዮችን ለማስፈጸም ለየገዳማቱና አድባራቱ አሰራጭተዋል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔ ካሳለፈባቸው ነጥቦች መካከል “ምእመናን በአምልኮ ወቅት ርቀታቸውን እንዲጠብቁ፣ የጤና ባለሙያዎችን ምክር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲያደርጉ፣ ወርኀዊም ሆነ ዓመታዊ ክብረ በዓላት እንዲከበሩ፣ ካህናትንና ምእመናንን ያንገላቱ የፀጥታ ኃይሎች በሕግ እንዲጠየቁ እንዲሁም በየአብያተ ክርስቲያናቱ በር ላይ ያሉ የፀጥታ ኃይሎች እንዲነሱ” የሚሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ውሳኔዎች ታዲያ በመንግሥት ታምኖባቸው ነው ቤተ ክርስቲያን መመሪያው እንዲተገበር ወደ የአጥቢያውና ገዳማቱ ያወረደችው፡፡ ነገር ግን በክብረ በዓላትም ሆነ ዘወትር የቤ ተክርስቲያን አገልግሎት ወቅት አብያተ ክርስቲያናቱ ከቅዱስ ሲኖዶስ የተላከላቸውን ሕጋዊ ደብዳቤ ቢያሳዩም ሕግን ተከትለው መስራት የማይፈልጉ አንዳንድ የፀጥታ ኃይሎች በአገልጋዮችና ምእመናን ላይ የሽብር ተግባር እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡

እነዚህ የፀጥታ ኃይሎች ታዲያ ሕግና ደንብን ለማስከበር ሳይሆን ወቅቱን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የራሳቸውን ድብቅ ዓላማ ለመፈጸም መጓጓታቸውን የሚያሳይ ተግባር ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከፈተና የራቀች ባትሆንም አሁን እየደረሰባት ያለው ፈተና ግን የተለየ መልክ ተላብሶ ቀርቧል፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተጣለ ጀምሮ በቅርብ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን፣ በምእመናንና በአገልጋዮች ላይ  በየአካባቢው የተፈጸሙ ወንጀሎችን በዚህ ክፍል  የምንመለከት ይሆናል፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ የምንመለከተው ለኦርቶዶክሳውያን የደም ምድር በመሆን የሚታወቀውን የጅማ ሀገረ ስብከት ይሆናል፡፡ ይህ ሀገረ ስብከት እንደሚታወቀው ክርስቲያኖች በጭካኔ የሚታረዱበት፣ የሚሰደዱበት እንዲሁም ሀብት ንብረታቸው የሚነጠቅበት አካባቢ ነው፡፡ በ09(9 ዓ.ም እንኳን በጅማ በሻሻ በሚባለው አካባቢ በአክራሪ ሙስሊም አማካይነት በርካታ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በጭካኔ በስለት ተቆራርጠው ሰማዕት እንደሆኑ ይታወሳል፡፡ የቅርብ ዓመታቱን ወንጀል ያየን እንደሆነ ደግሞ በዚሁ አክራሪ ሙስሊም አማካይነት ‘’እምነታችሁን ቀይሩ’’ በማለት ኦርቶዶክሳውያኑን ገሚሱን ገድሎ ሌሎችን ደግሞ ለዘለዓለማዊ የአካል ጉዳት ዳርጓቸዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በኦርቶዶክሳውያኑና በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰው ዘርፈ ብዙ ጥቃት መልኩን ቀይሮ ሕግን እናስከብራለን በሚሉ የፀጥታ ኃይሎች በኩል መከሠት ጀምሯል፡፡ በጅማ ሀገረ ስብከት የሚገኙ አንዳንድ የፀጥታ ኃይሎች የተጣለውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደ ሽፋን በመጠቀም በምእመናን ላይ በደል እየፈጸሙ ነው፡፡ ይህ ድርጊት ታዲያ በአሁኑ ወቅት አልፎ አልፎ በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች የሚፈጸም ቢሆንም በጅማ ሀገረ ስብከት የሚፈጸመውን ያህል ግን የሆነ የለም፡፡ ከሀገረ ስብከቱ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በቤተ ክርስቲያን፣ በምእመናንና በአገልጋዮች ላይ እየተፈጸመ ያለው ነውረኛ ድርጊት ለማንም የሚመኙት አይደለም፡፡ 

በዚሁ በጅማ ሀገረ ስብከት በቅርቡ እንኳ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነውን ውሳኔ ለየአድባራቱና ገዳማቱ ደብዳቤ በማሰራጨት ላይ የነበሩትን የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሰላም መምህር ተስፋ ሚካኤል አስፋን ያለምንም በደላቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሽፋን በማድረግ አስሯቸው ነበር፡፡ የሰኔ ሚካኤል የንግሥ በዓል በመከበር ላይ በነበርበት ወቅት እንዲሁ የጅማ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የሆኑትን መልአከ ሣህል ቆምስ አባ ገብረ ኢየሱስን ‘’በዓሉን ለምን ታከብራላችው’’ በሚል ሰበብ ታስረው እንደነበረ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በተለይ በጅማ ከተማ ክርስቲያኖችን የሚያሳድዱና ቤተ ክርስቲያንን በክፉ ዐይን የሚመለከቱ አንዳንድ የፀጥታ ኃይሎች የደረጃ እድገት ተጠቃሚ እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ለአብነት ተጠቃሽ የሚሆነው ደግሞ የጅማው ሳጅን ጅማል ሐጂ ነው፡፡ ከአካባቢው እንደተገኘው መረጃ ከሆነ ሳጅን ጀማል ሃጂ ክርስቲያኖችንና ቤተክርስቲያንን አምርሮ ከመጥላቱ የተነሳ ‘’የእኛ ሰዎች ቤታቸው እየሰገዱ እናንተ ማናችሁና ቤተ ክርስቲያን ከፍታችሁ የምትጸልዩት’’ በማለት የግፍ ንግግር ይናገራል፡፡ ያሻውን ያስራል፣ ያሻውንም ይፈታል። ለሚከተለው ሃይማኖት ወግኖ ክርስቲያኖችን ያዋክባል፣ ያስራል፡፡

የፀጥታ ኃይሎች በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ ከፍተኛ ጥፋት ያደረሱ ሲሆን ምእመናንን ከማዋከብ፣ ከመደብደብ፣ ከማሰር ጀምሮ በኢኮኖሚ የደቀቁ እንዲሆኑ የብዙ ሺዎች ብር መቀጮ ይጥሉባቸዋል፡፡ እስካሁን ባለው መርጃ መሠረት ከኀምሳ ስምንት በላይ አገልጋዮችና ምዕመናን ታስረዋል፡፡ ለእስር የበቁበት ምክንያት ደግሞ ‘’አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሳችኋል’’ የሚል ቢሆንም  ነገሩ ግን ከዛ የዘለለ ነው።  ምእመናን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አክብረው ሥርዓተ አምልኳቸውን በመፈጸማቸው ብቻ ይታሰራሉ ይደበደባሉ። ክርስትና ሲያስነሳ ሲቆርብ ወይም ሲያቆርብ የተገኘ ደግሞ በሌለ ሀብቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ መቀጮ ይጠየቃል፡፡ በዚህ ወቅት ከአንድ ሺህ ብር ጀምሮ እስከ አስራ አምስት ሺህ ብር የተቀጡ ምእመናን እንዳሉ መረዳት ተችሏል፡፡

ይህንን እምነት ተኮር እንግልትና እስር የፈሩ በርካታ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ከሚኖሩበት ጅማ አካባቢ እየተሰደዱ ይገኟሉ፡፡ በተደራጁ አክራሪ ጽንፈኛ ቡድኖች ከሚደርሰው ጥቃት በዘለለ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ይጠብቃሉ ተብሎ ተስፋ ከሚጣልባችው  የፀጥታ አካል እንዲህ ዓይነት ዓይን ያወጣ የወንጀል ድርጊት ሲፈጸም ማየት በእርግጥም ያስደነግጣል፡፡ የመንግሥት አንድ አካል ነኝ የሚለውና ሕግን ለማስከበር ዘብ ቆሚያለሁ የሚለው ሕግን ከጣሰ የተደራጀው ጽንፈኛ ቡድን ቤተ ክርስቲያንን ቢበድል፣ ክርስቲያኖችን ቢያርድና ቢያሳድ ምን ይፈረድበታል ‘’አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ’’ እንዲሉ በጅማና አካባቢው እየሆነ ያለው ነገር በጣም አሳሳቢ ነው፡፡

በጅማ ሀገረ ስብከት እየተፈጸመ ያለው ዘርፈ ብዙ ጥቃት እጅግ ሰፊ በመሆኑ ሁኔታውን በጥቂቱ ለማሳወቅ አንኳር አንኳር ጉዳዮችን ብቻ ጠቅሰናል፡፡ የጅማውን ጉዳይ እዚሁ ገታ እናድርግና ከጅማ ባልተናነሰ መልኩ ሌላው የኦርቶዶክሳውያን የመከራ ቀንበር ወደሚገኝበት ስልጤ ዞን እናቀናለን፡፡ በስልጤ ዞን የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትና ምእመናን ከዚህ ቀደም የጭንቅና የመከራ ጊዜ ሲያሳልፉ እንደነበረ እናስታውሳለን። የተደራጀ እስላማዊ አክራሪ ቡድን ወቅት እየጠበቀ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ ከፍተኛ ጥቃት ይፈጽም እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

በዚሁ አካባቢ ሰሞኑን ሰኔ !1 ቀን !)02 ዓ.ም የእመቤታችንን ክብረ በዓል ለማክበር አዲስ አበባን ጨምሮ ከተለያየ አካባቢዎች ተሰባስበው በሄዱ ምእመናንና አገልጋዮች ላይ እንደተለመደው በአከባቢው የፖሊስ ኃይል አጋዥነት የተደራጀ ጽንፈኛ ቡድን ከፍተኛ የሆነ ድብደባ ፈጽሟል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ መሠረት በስልጤ ዞን ቂልጦ አዝርነት በርበሬ ወረዳ በምትገኘው ሎዛ ቅድስት ማርያም ገዳም ክብረ በዓልን ለማክበር በሄዱ ምእመናን ላይ በተፈጸመ ድብደባ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የነበሩ ምእመናንና አገልጋዮች ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ‘’አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሳችሁ ተሰብስባችኋል’’ በሚል ቢሆንም እውነታው ሲገለጥ ግን ቤተ ክርስቲያን በአካባቢው ለምን ተሰራ የሚል ሆኗል፡፡ በመሆኑም የአካባቢው የፀጥታ ኃይልም ሆነ የተደራጀው ጽንፈኛ ቡድን የምእመናንን በብዛት መሰባሰብንና አዲስ ቤተክርስቲያን መቋቋሙን የወደደው አይመስልም፡፡ 

ለራሱ ሃይማኖት የወገነው የፀጥታ ኃይል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሽፋን ምእመናንን በምሽት ከቅጥረ ቤተክርስቲያን ውጡ በማለት በሚያስገድድበት ወቅት ከሁለት መቶ በላይ የተደራጀ ጽንፈኛ ቡድን ድምጽ አልባ መሳሪያ ይዞ ውጭ ጥቃት ለማድረስ ይጠባበቅ ስለነበረ ምእመናኑም ወደ ውጭ አንወጣም የሚል ምላሽ ሰጡ፡፡ በአከባቢው የነበረው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሽፋን የሚንቀሳቀሰው የፀጥታ ኃይልም የሕግ ከለላ እንደሚሰጣቸው ነግሯቸው ተስማምተው ወደ ውጭ ምእመናኑ በወጡበት ወቅት ውጭ ላይ ሥጋ እንዳየ ውሻ ይጠባበቅ የነበረው ጽንፈኛ አክራሪ ኃይል በታጠቀው ድምፅ አልባ መሳሪያ ምእመናንን ክፉኛ ደበደበ፡፡ ብዙ ምእመናንም በሞትና በሕይወት መካከል ተገኙ፡፡

እነዚህ በሞትና በሕይወት መካከል የተገኙ ምእመናንም በአቅራቢያ በሚገኝ የህክምና ተቋም የህክምና እርዳታ እንዲደረግላቸው ቢጠየቅም የትም መሄድ አይችሉም፤ ሁሉንም እዚሁ እንጨርሳቸዋለን የሚል ምላሽ ተሰጠ፡፡ በወቅቱ በቦታው ከፈጣሪ በታች ሊታደጋቸው የቻለ አንድም ምድራዊ ኃይል አልተገኘም፡፡ አውጥቶ ለጅብ አሳልፎ የሰጣቸው ሕግ አስከባሪ መስሎ ሕግ ጣሽ የሆነው የፀጥታ ኃይልም ዳር ቆሞ በምእመናን ስቃይ ተደሰተ፡፡ ብዙዎቹ ምእመናን በጣም ጉዳት ስለደረሰባቸው ለተሻለ ህክምና ዘግይቶ በደረሰው የክልሉ ልዩ ኃይል ርዳታ ወደ አዲስ አበባ እንደተላኩም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን አሁንም በየአቅጣጫው ጉዳቷ ቀጥሏል፡፡ 

ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ምእመናን የጽንፈኞች መጫወቻ  ከሆኑ ሰነባበተዋል፡፡ የተደራጁ አክራሪ ጽንፈኞች እንዳሻቸው ይፈነጩባቸዋል፡፡ የምእመናንን ሥቃይ የሚያስታግስ ስልታዊ በሆነ መንገድ የሚሰራ አካል እስካሁን ድረስ አልተገኘም፡፡  ጉዳዩ ባለቤት አጥቷል፡፡

በየጊዜው የጉዳት ሰለባ የሚሆኑ ምእመናንም የሚመለከተው የመንግሥት አካልና የቤተ ክርስቲያን መሪ አባቶች አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጡ ሁልጊዜ ይጠይቃሉ፡፡ ሀገር ባቆመች ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን ግፍና መከራ በኦርቶዶክሳዊ ቁመና በአንድነት ሕጋዊ መንገዶችን በመከተል የቤተ ክርስቲያንን ዘለቄታዊ መብትና ጥቅም ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ ምእመናኑ በየጊዜው ያሳስባሉ፡፡ እኔም እጅግ የከፋ የመከራ ዘመን እንዳይመጣ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ የጋራ ማድርጉ ይበጃል እላለሁ። 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

  

 

Read 812 times