በተመሳሳይ ሐምሌ !፻01 ዓ.ም የሲዳማ ዞን ያቀረበውን የክልልነት ጥያቄ ተከትሎ ቀን ቆርጦ በተፈጸመ ጥቃት አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፤ ኦርቶዶክሳውያን ተገድለዋል። ዞኑ የክልል ልሁን ጥያቄውን ማቅረብ ያለበት ለመንግሥት፣ መልስም መጠበቅ የነበረበት ከመንግሥት ሆኖ ሳለ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማጥቃት መነሻው ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ከስምንት ያላነሰ አብያተ ክርስቲያናትን በማቃጠልና ኦርቶዶክሳውያን በመግደል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው ግለሰቦች ክሳቸው ተቋርጦ በነጻ ተሰናብተዋል።
ከዚያም በኋላ ጥቅምት !፻0፪ ዓ.ም መንግሥት ጥበቃዎቼን ሊያነሣብኝ ነው የሚል የአንድ ግለሰብን የተከብቤያለሁ ጩኸት ተከትሎ በተከፈተ ሃይማኖት ተኮር ጥቃት ንጹሐን ዜጎች ተገድለዋል። ከዚህ ቁጥር ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ኦርቶዶክሳውያን ሲሆኑ በተለይም በባሌ፣ በዶዶላ፣ በኮፈሌ፣ በምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ ብዙ ኦርቶዶክሳውያን ተገድለዋል። ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ንብረታቸው ወድሞባቸዋል። በዚህ ጥፋት የተወሰደውን ርምጃ ስንመለከት ደግሞ ክስ ከተመሠረተባቸው ውስጥ የሚበዙት አጥፊዎች ሳይሆኑ ተጠቂዎች ነበሩ። ለማሳያ ያህል እነዚህን ጠቀስን እንጂ በተለያዩ አካባቢዎች በቤተ ክርስቲያን ላይ ተደራራቢ ጥቃቶች ሲፈጸሙ፣ በአጥፊዎችም ላይ ምንም ርምጃ ሳይወሰድ በአጸፋው ቤተ ክርስቲያን እንዳይቃጠልም ሆነ ራሳቸውን ከሞት ለማዳን የተከላከሉ ኦርቶዶክሳውያን እስርና እንግልት ሲፈጸምባቸው ታይቷል።
በሰኔ ወር ፳፲፲፪ዓ.ም ደግሞ በአዲስ አበባና በተለያዩ አካባቢዎች የጥፋት ኃይሎች በሰነዘሩት ጥቃት የንጹሐን ዜጎች ሕይወት ሲያልፍ ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ኦርቶዶክሳውያን ናቸው። በአዲስ አበባና በኦሮሚያ በተለያዩ አካባቢዎች ኦርቶዶክሳውያን በሃይማኖታቸው ምክንያት ብዙ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ፣ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ብዙ ናቸው። ቤታቸውና ለብዙ ዓመታት በድካም ያፈሩት ሀብት ንብረታቸው እንዳልነበረ ሆኖ በእሳት ወድሞባቸዋል። ቤተ ክርስቲያን የማንኛውም ሰው ሞት የማያስደስታት ብትሆንም በሞት ያጣችው የራሷ ልጅ ሆኖ ሳለ፣ በሐዘን ላይ ሐዘን ለመጨመር ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሌሎች ልጆቿንም በሞት አጥታለች።
በአጠቃላይ ራሳቸውን ከሕግ በላይ ያደረጉ አካላት የሚያደራጁት ቡድን ጥቃት፣ የዞኖች የክልል እንሁን ጥያቄ፣ የዘውግ ፖለቲካ አራማጆች አቀባበል፣ የግለሰቦች የተከብቤያለሁ ጩኸትና የግለሰቦች ሞት ቤተ ክርስቲያንን ማጥቂያ መሣሪያ ሆነው አገልግለዋል። በእነዚህ ሁከቶች መሣሪያነት ቀድሞ የታሰበና የታቀደ በሚመስል መልኩ በቤተ ክርስቲያን ላይ ጥቃቶች ተፈጽመዋል። ከጥቃቱም በኋላ ጥፋት የፈጸሙ ወንጀለኞች ምንም ሳይደረጉ ሲቀሩና በተቃራኒው ተጠቂዎች ሲንገላቱና ሲታሰሩ ሲታይ ጥቃቱ መዋቅራዊና ስልታዊ ሆኖ የተፈጸመ ይመስላል።
ቤተ ክርስቲያን በሠራችው አገር፣ ባቀናቸው ቀዬ በሁሉ እየተገፋች ነው። እነዚህ ሁሉ ጥቃቶችና መገፋቶች ሕዝበ ክርስቲያኑን በአገሩ ተስፋ እንዲቆርጥ፣ የሚጠብቀው መንግሥት እንደሌለ በማሰብ ራሱን ለመጠበቅ ወደ መገደድ ጠርዝ እየገፉት ይገኛሉ። ይህ ቀቢጸ ተስፋ ደግሞ በአገር ላይ የማያባራ ግጭት ሊያመጣ የሚችል ስለሆነ በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶች ከዚህ ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ጥቃት እያደረሱ ባሉ አካላት ላይ መንግሥት የማያዳግም ርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ በተጨማሪም በተቃራኒ የጥቃቱ ሰለባ በሆነው ሕዝበ ክርስቲያን ላይ የሚደርሱ መገፋቶችና እንግልቶችም ሊቆሙ ይገባል።