በቅድሚያ ለሁላችሁም ሰላመ እግዚአብሔር ይድረሳችሁ! ሞት በነገሠበት ቸነፈር ጥላውን በጣለበት ዓለም ውስጥ በሕይወት ጠብቆ በሀብት ስቦ በረድኤት አቅርቦ ለእመቤታችን የትንሣኤ እና የዕርገት በዓል በሰላም ስላደረሰን ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን !
ከነሐሴ ፩-፲፮ ጾመ ፍልሰታን ጾመን በነሐሴ ፲፮ የምናከብረው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የዕርገት በዓል ነው። ለጾሙ ምክንያት የሆኑት የእመቤታችን እረፍት፣ ትንሣኤ እና ዕርገት ናቸው። ጾሙን የጾሙት ቅዱሳን ሐዋርያት ሲሆኑ የጾሙበት ምክንያት የእመቤታችን ጉዳይ እረፍት፣ ፍልሰት፣ ዕርገት ስለ ሆነ ጾመ ፍልሰታ ለማርያም በሚል ስያሜ ይጠራል። በተጨማሪም በጸዋሚዎች ጾመ ሐዋርያትም ይባላል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አክብራ ከተቀበለቻቸው ሰባት አጽዋማት ሰፍራ ቆጥራ ለምእመናን አስተምራ ከምትጾማቸው አንዱ ጾመ ፍልሰታ ለማርያም የሚባለው ጾም ሲሆን ጾሙ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በልዩ ፍቅር የሚወደድ ጾም ነው ።
ከስያሜው ስንነሣ ጾም እና ፍልሰት የሚሉ ሁለት ቃላትን አጣምሮ ጾሙን እና የጾሙን ምክንያት አስተባብሮ የሚገልጥ ነው ። አሁን የምንመለከተው ጾም የሚለውን ሳይሆን ለጾሙ መነሻ የሆነውን የእመቤታችንን ዕርገት ነው ። ይህን የእመቤታችንን የእረፍት ፣የትንሣኤ እና የዕርገት በዓል ስናስብ በእግረ ኅሊና ወደ ኋላ ተመልሰን ወደ ፵፱ ዓመተ ምሕረት እንጓዛለን። እመቤታችን ያረፈቸው በ፵፱ ዓ.ም ጥር ሃያ አንድ ቀን ሲሆን የተነሣችው እና ያረገችውም በዚያው ዓመት ነሐሴ ወር አሁን ፍልሰታ ለማርያም ብለን በምናከብረው ወቅት ነው። ይህም ማለት የዛሬ ፲፱፻፷፫ ዓመት በዘመነ ማቴዎስ የተከናወነ ነው :: ፍልሰታ የሚለው የግእዝ ቃል ፈለሰ ተሰደደ ከሚል ግሥ የወጣ ቃል ነው ዐውዳዊ ፍችውን ስንመለከት እንደየአገባቡ ልዩ ልዩ ትርጉም ይሰጣል። መፍለስ፣ መሰደድ፣ መለየት፣ ቦታን መልቀቅ፣ መሰወር፣ ከሰው ርቆ መኖር፣ እርገት ወዘተ ••• ተብሎ ይተረጎማል።
ፍልሰታ ለማርያም ሲባል የእመቤታችንን ከዚህ ዓለም በሞት መለየትን በትንሣኤ ከመቃብር መውጣትን በዕርገት ከምድር ወደሰማይ ማረግን የሚገልጽ ቃል ነው :: እመቤታችን በዚህ ዓለም ስድሳ አራት ዓመታትን ኖራለች። በእርግጥ የዚህ ዓለም ኑሮ መኖር አይባልም መኖር ከሚለው መቆየት የሚለው ይስማማዋል መቆየት ጊዜያዊነትን ሲያሳይ መኖር የሚለው ደግሞ :: ዘለዓለማዊነትን ገላጭ ነው ::
የዚህ ዓለም ቆይታዋ በንጽሕና በቅድስና ያጌጠ ንጽሕናን ቅድስናን ለዓለም የገለጠ ክብሯም ከፍጡራን የበለጠ እና ለማንም ያልተሰጠ ነው ::
በዚህች ምድር ላይ “ቀደስኩከ እምከርሰ እምከ፤ በእናትህ ሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፤ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ” (ኤር.፩፥፭) ከተባለ ከኤርምያስ፣ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ በኤልያስ ግብር ጸንቶ ይኖራል ከተባለለት ከዮሐንስ መጥምቅና ከሌሎችም በቅድስና ከኖሩ በንጽሕና ከከበሩ ቅዱሳን በተለየ ቅዱስ ሕይወት የነበረች ፣ያለችና የምትኖር ናት። ልዩ የሚያደርጋትም ክብሯና ቅድስናዋ እንደ ሌሎች ቅዱሳን ጤዛ ልሶ ደንጊያ ተንተርሶ ድምፀ አራዊትን ግርማ ሌሊትን ታግሶ እንደ ሰማዕታት ከነደደ እሳት ገብቶ አንገትን ለሰይፍ ስለት፣ ሰውነትን ለእሳት ሰጥቶ በገድል የተገኘ አይደለም። የእግዚአብሔር እናት ለመሆን ሰው ሊያውቀው አእምሮ ሊያራቅቀው በማይችል ድንቅ የእግዚአብሔር ጥበብ በመመረጥ የተገኘ እንጂ። የእመቤታችን ክብሯ ልዩ ነው ከሰማያውያን መላእክት ከምድራውያን ደቂቀ አዳም ይልቅ እጅግ የተለየች እና የተመረጠች ናትና ። ክብሯ ልዩ ነው የመመረጧ ግብርም ድንቅ ነው። የሔዋን ልጆቿ በቁጥር እጅግ ብዙ ናቸው መርገሟን ማስወገድ ዕዳ በደሏን ማሰረዝ የቻለች የሔዋን ዕዳ ከፋይ የሆነች ግን እመቤታችን ብቻ ናት ።
ጥበበኛው ሰሎሞን በመኃልዩ ይህን ሲያስረዳ “ርግቤ መደምደሚያዬም አንዲት ናት፤ ለእናትዋ አንዲት ናት ለወለደቻትም የተመረጠች ናት። ቈነጃጅትም አይተው አሞገሱአት፥ ንግሥታትና ቍባቶችም አመሰገኑአት።” እንዲል (መኃ. ፮፥፱) የሔዋን ጆሮ ምክረ ከይሲን ሰምቶ ከእግዚአብሔር ጋር መጣላትን አመጣ የሰው ልጆችን ከገነት አስወጣ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ፣ ገነትን ያህል ቦታ፣ ልጅነትን ያህል ክብር ገነት መንግሥተ ሰማያትን ያህል ሀገር አሳጣ ይህ ሁሉ የሆነው በሄዋን ምክንያት ነበር። ይህ የተገለበጠው ደግሞ በቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያም ነው። ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሃይማኖተ አበው ይህን ሲገልጽ “ነገር ግን ሔዋንን ዲያብሎስ አሳታት የሞት ምክንያት የሚሆን ቃየልን ወለደች ማርያም ግን መልአክ ባበሠራት ጊዜ ሁሉን ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚመራ አካላዊ ቃልን በሥጋ ወለደች። የሔዋን ልብላ ልብላ ማለቷ ዕፀ በለስ የሞት ምክንያት እንደሆነ አስረዳ በዚያም ዕፅ አዳም ተድላ ደስታ ካለበት ከገነት ወጣ ከድንግል የተወለደ አካላዊ ቃል ግን መስቀል የድኅነት ምክንያት እንደሆነ ገለጠ በዚያም መስቀል ቀማኛ ወንበዴ የነበረው ሰው ከአባቱ ከአዳምና ከቀደሙ አባቶች ሁሉ ጋር ተድላ ደስታ ወዳለበት ገነት ገባ” (ሃ.አበ. ፷፯፥፬-፭) በማለት አስረድቷል።
ይህም የሚያስረዳን የሔዋን ዕዳ በደል የተወገደው በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማካኝነት ነው። ዓለም በሔዋን ምክንያት ከገነት ሲሰደድ በድንግል ማርያም አማካኝነትም ወደ ገነት ተመልሷል። ሊቃውንቱ መልክአ ውዳሴ በተባለ ድርሰት “ለሔዋን እምነ ከይሲ ዘአስሐታ እግዚአብሔር ናዘዛ ኪያኪ በወሊዶታ፤ ከይሲ ያሳታት እናታችን ሔዋንን አንቺን በመውለዷ እግዚአብሔር አረጋጋት” በማለት የሔዋን ኃዘን የተወገደው፣ ሔዋን ከሞት ወደ ሕይወት ከሲኦል ወደገነት የተመለሰችው ድንግል ማርያምን ያመሰግናሉ።
በቅዱስ መጽሐፍ “አዳምም ለሚስቱ ሔዋን” ብሎ ስም አወጣ። የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና። እግዚአብሔር አምላክም ለአዳምና ለሚስቱ የቁርበትን ልብስ አደረገላቸው፥ አለበሳቸውም። እግዚአብሔር አምላክም አለ፦ እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፤ አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ፥ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ፥ ለዘለዓለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ ከዔደን ገነት አስወጣው፥ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ። አዳምንም አስወጣው፥ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔደን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ።” ዘፍ ፫÷፳-፳፬ ተብሎ የተገለጽውን ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም “በእንተ ሔዋን ተዐፅወ ኆኅተ ገነት ወበእንተ ማርያም ድንግል ተርኅወ ለነ ዳግመ-በሔዋን ምክንያት የገነት ደጅ ተዘጋብን ዳግመኛ በድንግል ማርያም ተከፈተልን” በማለት በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ እንደገለጸው የሰው ልጆች ጥያቄ መልስ ያገኘው በእመቤታችን ነው። ዳግማይ አዳም ዋሕድ ቃለ እግዚአብሔር አካላዊ ቃልን ወልዳልናለችና።
ከሔዋን በተለየ ግብር ጸንታ ከሔዋን የተገኘች ስትሆን ከሔዋን ተለይታ ለሰው ልጆች ሕይወትን የሚሰጠውን ወለደችልን። በዚህ ልዩ ምሥጢር እግዚአብሔር ከእርሷ ተወልዶ ተገለጠ ሞት በሕይወት ተለወጠ ። ለዘመናት በሰው ልጆች ላይ ሠልጥኖ የነበረው ዲያብሎስ ደነገጠ ሞት የሰውን ልጅ ገድሎ ወደ መቃብር ይሸኘዋል። በዚህም መንገድ ሥጋ በመቃብር ሲፈርስ ሲበሰብስ ነፍስም በፍዳ ተይዛ በሲኦል ተግዛ ትኖር ነበር ከእርሷ የተወለደው አምላክ ወልደ አምላክ በሞቱ ሞተ ነፍስን ደመሰሰልን የሞተ ነፍስ መነሻ የመከራ ነፍስ መገስገሻ የነበረውን ሞተ ሥጋን የትንሣኤ እና የዕርገት መናገሻ አደረገልን ። አስደንጋጭ የነበረው ሞት የሕይወት መንገድ መሆኑ በክርስቶስ ሞት ተገለጠ። በትንሣኤውና በዕርገቱ ይበልጥ ተረጋገጠ። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲያስረዳ “ከእኛ አንድ ስንኳ ለራሱ የሚኖር የለምና፥ ለራሱም የሚሞት የለም፤ በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፥ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን። ስለዚህ ነገር ሙታንንም ሕያዋንንም ይገዛ ዘንድ ክርስቶስ ሞቶአልና ሕያውም ሆኖአልና።” (ሮሜ ፲፬ ÷፯-፱) በማለት ገልጾአል።
እመቤታችንም የሞተችው ሞት ይህን መሰል ቅዱሳን ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር የናፈቁት ሞት ነው። ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ የነበሩ አበው ከሞቱት ሞት ይለያል። ያኛው ፍዳን ያስከትላል ይህኛው ግን ሕይወትን የሚያስከትል ነው። ከእግዚአብሔር ጋር የሚያኖር ነውና። እመቤታችንም ደግሞ ከሁሉም ቅዱሳን ይልቅ በሕይወተ ሥጋ ቅድመ ፀኒስ እግዚአብሔር በረድኤት ያልተለያት ጊዜ ፀኒስ ድኅረ ፀኒስ እግዚአብሔር በኩነት ማለት ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆኖ አብሯት የኖረ ከቤተ ልሔም እስከ ቀራንዮ ከመካነ ልደቱ እስከ መካነ ሞቱ ያልተለየችው እግዚአብሔርም ያልተለያት ከፅንስቱ እስከ እርገቱ ለኅሊናችን እሩቅ ለልቡናችን ረቂቅ የሆነውን ምሥጢር ተሸከማ ልዩ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሆና የኖረች ናት ።
እርሷ የሞተችው ሞት ለዘለዓለም ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር መሆኑ ግልጥ ነው። ይህንን ነው ፍልሰታ ለማርያም የምንለው ከዚህ ዓለም በሞት ከመቃብር በትንሣኤ ከትንሣኤ ቀጥሎ ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረውን ሕይወት ለመኖር መለየት፣ መሰደድ፣ መፍለስ፣ መራቅ፣ መሰወር፣ ዕርገት ነው ፍልሰታ ማለት። ከላይ የጽሑፋችን መነሻ ያደረግነው የቅዱስ ያሬድ ዝማሬ ይህን የሚገልጥ ስለ እመቤታችን ዕርገት የሚያስረዳ ነው። “ተለዐለት እምድር በስብሐት ውስተ ሰማያት ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ በየማነ አብ ወመንፈስ ቅዱስ፤ ከምድር በክብር በምስጋና ወደሰማያት ከፍ አለች( ዐረገች) አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በሚሰጡት ክብር ከልጇ ጋር በዚያ ተቀመጠች” በማለት የእመቤታችን ዕርገቷን የገለጠበት ምስጋና ምስክርነትም ነው። “ተለዐለ” የሚለው ግስ ከፍ ማለትን ወደ ላይ ወደ ሰማይ መውጣትን ማረግን የሚገልጥ ግሥ ነው ይህ ግሥ ለጌታችን ዕርገት መነገሩን ልብ ይሏል “ወዘንተ እንዘ ይብሎሙ ተለዐለ ወነስአቶ ደመና ወዐርገ ሰማየ፤ ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው።” (ሐዋ. ፩፥፱)
በዚህ አንጻር “ተለዐለት” ማለት ዐርገት ማለት መሆኑን እናስተውል :: የእመቤታችን ትንሣኤ እና ዕርገት ከቅዱሳት መጻሕፍት የምናገኘው ነው እንጂ ልብ የወለደው አእምሮ የፈጠረው አይደለም። አስቀድሞ በነቢያት የተነገረ ነው እንጂ እንዲህ ተብሎ “አቤቱ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት።” (መዝ. ፻፴፩፥፰) አቤቱ ተነሥ የሚለው የጌታችን ትንሣኤ ገላጭ ሲሆን የመቅደስህ ታቦት የተባለችው ቅድስት ድንግል ማርያም ናት ።
መቅደስ የተባለ ሰውነቱ ነው። ይህም በቅዱስ ወንጌል “ንሥትዎ ለዝንቱ ቤተ መቅደስ ወበሠሉስ ዕለት አነሥኦ ወውእቱሰ ይቤሎሙ በእንተ ቤተ ሥጋሁ፤ ኢየሱስም መልሶ፦ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው። … እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር።” (ዮሐ. ፪÷፲፱-፳፩) ተብሎ ተገልጾአል። ስለዚህ አንተ ተነሥ በማለት የትንሣኤያችን በኩር የሆነ የጌታችንን ትንሣኤ ትእዛዛዊ በሆነ እንደማይቀር በሚያስረግጥ መልኩ የተነገረበት ሲሆን “የመቅደስህ ታቦት” ሰው ሆነህ ያደርክባት የተገለጥክባት እርሷም እመቤታችን ትነሣ በሚል ምልዐተ ንባብ የእመቤታችን ትንሣኤ ትንሣኤ ዘጉባኤን ሳይጠብቅ ከእርሱ ቀጥሎ የሚፈጸም መሆኑ የተነገረበት ትንቢት እና ምስክርነት ነው::
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተነሣች ካልን ዐረገች ማለት ግድ ነው። ምክንያቱም ትንሣኤ የዕርገት ዋዜማ ነውና። እመቤታችን በጥር ፳፩ አረፈች፤ በነሐሴ ፲፬ ተቀበረች፤ ዕለቱን በነሐሴ ፲፬ ተነሣች፤ በነሐሴ ፲፬ በዕለተ እሑድ ዐረገች። ከመ ትንሣኤ ወልዳ እንደ ልጇ ፍጹም ትንሣኤ ተነሣች ከመ ትንሣኤ ወልዳ ማለት ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊትን አያመለክትም ዕለተ እሑድ መሆኑንና የትንሣኤዋን ፍጹምነት ዳግም ሞት የሌለበት ትንሣኤ መነሣቷን እንጂ። ያን ጊዜ ዕርገቷን ያየ ቶማስ ብቻ ነበር ሌሎች ሐዋርያት አላዩም ነበርና በነሐሴ አስራ ስድስት በዓመቱ ጌታችን ለቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችን ዕርገቷን የገለጠበት ዜና ትንሣኤዋንና ዜና ዕርገቷን እንዲሰብኩ ያዘዘበት “ዘፀውዐ ስመኪ ወዘገብረ ተዝካረኪ እምሕር ለኪ፤ ስምሽን የጠራውን መታሰቢያሽን ያደረገውን እምርልሻለሁ” ብሎ ለእመቤታችን ጽኑእ የሆነ ቃል ኪዳን ገብቶላታል።
እንዲሁም “ዘፀውዐ ስመክሙ ወዘገብረ ተዝካረክሙ እምሕር ለክሙ፤ ስማችሁን የጠራውን መታሰቢያችሁን ያደረገውን እምርላችሁአለሁ” ብሎ ለሐዋርያትም ተናግሮ የማያስቀረውን ጽኑእ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል። ነሐሴ ዐሥራ አራት ትንሣኤዋ እና ዕርገቷ ሲሆን ዐሥራ ስድስት የትንሣኤዋ እና የዕርገቷ መታሰቢያ በዓል የሚከበርበት፣ ትንሣኤዋንና ዕረገቷን ላላዩ ሐዋርያት ጌችንና መድኃኒታችን ለሐዋርያት የተገለጠበት፣ ቃል ኪዳን የሰጠበትነው።
ዕርገቷም እንደ ትንሣኤዋ ሁሉ በመጻሕፍት የተነገረ ሲጠበቅ የኖረ ነው:: “ወትቀውም ንግሥት በየማንከ በአልባሰ ወርቅ ዑፅፍት ወኁብርት፤ በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።” (መዝ. ፵፭፥፱) ትቀውም የሚለውን መተርጉማን ትነብር ይሉታል ንግሥት በቀኝህ ትቀመጣለች ማለት ነው። “ትቀውም፤ ትቆማለች” ማለት ለፍጡራን ሁሉ ይልቁንም በአማላጅነቷ ለሚያምኑ በቃል ኪዳኗ ለሚማፀኑ አማላጅነቷን አስረጂ ነው። “ትነብር፤ ትቀመጣለች” ማለት ደግሞ ከዚህ ዓለም ድካመ ሥጋ በዕርገት ማረፏን የተሰጣትን ፍጹም ክብር የሚያስረዳ ነው። መቆም ተልእኮን፣ መቀመጥ ደግሞ ክብርን ገላጭ ነው። በቀኝህ ትቀመጣለች የሚለው ቅዱስ ያሬድ በዝማሬው ካነሣው ሐሳብ ጋር አንድ ነው። “ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ፤ ከልጇ ጋር በዚያ ተቀመጠች” ይላል በዚያ ያለው በመንግሥተ ሰማያት ነው እርሷ በወራሽነት ልጇ በምልዓት ይኖሩባታልና ነው::
የመጀመሪያዋ የገነት ኗሪ ከቀዳማዊው አዳም ጋር ሔዋን ነበረች። የመንግሥተ ሰማያት ጀማሪ ደግሞ ከዳግማይ አዳም ክርስቶስ ጋር ዳግሚት ሔዋን እመቤታችን ናት። “ይቤ ቅዱስ ማሪ ኤፍሬም አፈበረከት ወመምህር ሦርያዊ በእንተ እግዝእትነ ማርያም ድንግል ወትረ በኩሉ ጊዜ እምአመ ልደታ እስከ አመ እረፍታ ወፍልሰታ፤ አፈ በረከት የሦርያው መምህር ቅዱስ ኤፍሬም ዘወትር ድንግል ስለሆነች ስለእመቤታችን ከልደቷ እስከእረፍቷ እና ፍልሰቷ በተናገረበት ድርሳኑ እንዲህ አለ::” ( ሃ.አበ. ፵፯፥፩)
ይህ ፍልሰት የሥጋ ብቻ አይደለም ነፍስና ሥጋዋ ተዋሕደው እንደ ልጇ ትንሣኤ እና ዕርገት ነው እንጂ። (ሰላም ለፍልሰተ ሥጋኪ ምስለ ነፍስኪ ኢመዋቲ በተሰናዕዎ አሐቲ፤ ከማትሞት ነፍስሽ ጋር በአንዲት መስማማት ለተደረገ ለስጋሽ ፍልሰት ሰላም እላለሁ) ፤ “ሰላም ለዕርገተ ሥጋኪ ዘተወጥነ ቦቱ:: ዕርገተ ቅዱሳን ሰብእ ዘበኀቤኪ ተአኲቱ፤ በአንቺ ዘንድ የተመሰገኑ የቅዱሳን ሰዎች ዕርገት ለተጀመረበት ለሥጋሽ እርገት ሰላም እላለሁ:: (መልክአ ፍልሰታ) ተብሎ እንደተገለጸው ፍልሰቷ ነፍስና ሥጋዋ ተዋሕዶ ዳግም ትንሣኤን ሳይጠብቅ መንግሠተ ሰማያትን መውረሷን የሚያመለክት ነው።
ከፍጡራን የሞት እና የውርደት ጀማሪ ሔዋን ስትሆን የትንሣኤና የዕርገት ጀማሪ እመቤታችን ናት:: ልጇን መስለን እርሷን ተከትለን ሁላችን እንደምንነሣና እንደምናርግ የታወቀ ነው:: ተስፋ ምናደርገው ትንሣኤ ዘጉባኤ ለሁላችን አለ። ጸሎታችን የእምነት መግለጫችንም ይህ ነው “የሙታንን መነሣት ተስፋ እናደርጋለን የሚመጣውንም ሕይወት ለዘለዓለሙ” ለዘለዓለሙ የሚመጣው ሕይወት በትንሣኤ የምናገኘው በዕርገት የምናረጋግጠው አይደለምን? ይህም አምላካችን የሰጠን የተስፋ ፍጻሜ ነው:: “በአባቴ ቤት ብዙ ማደሪያና ማረፊያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ኖሮ ቦታ ላዘጋጅላችሁ እሄዳለሁና እላችሁ ነበር። ከሄድሁና ቦታ ካዘጋጀሁላችሁም ዳግመኛ እመጣለሁ፤ እናንተ እኔ ባለሁበት ትኖሩ ዘንድ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።” (ዮሐ. ፲፬÷፪) በማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው ጽኑእ ተስፋ ለዘለዓለም የጸና ምእመናንም ይህን ተስፋ ሰንቀው ሃይማኖታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ የሚያደርጋቸው ነው።
ይህ ለሰው የተሰጠው ተስፋ ማለትም መንግሥተ ሰማያትን ወርሶ መኖር አስቀድሞ የተሰጠው ለእመቤታችን ነው ኋላ ለሁላችን ይሆናል:: “ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤ ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን። ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ።” (፩ኛ ተሰ. ፬ ÷፲፮-፲፰) ተብሎ እንደተነገረው።
ባጠቃላይ “ተለዐለት እምድር በስብሐት ውስተ ሰማያት ወበህየ ነበረት፤ በክብር በምስጋና ከምድር ወደሰማይ ዐረገች በዚያም ተቀመጠች” በማለት ቅዱስ ያሬድ የገለጸው እመቤታችን ድንግል ማርያም እንደልጇ እንደወዳጇ በይባቤ መላእክት በክብር፣ በምስጋና ከሙታን ተለይታ መነሣቷን፣ እንዲሁም ወደሰማይ ማረጓን፣ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ፣ ድካም፣ እንግልት ማረፏን፣ በክብር መንግሥተ ሰማያትን መውረሷን የሚያስረዳን ነው። እንደ ልጇ ትንሣኤና ዕርገት የእርሷንም ትንሣኤና ዕርገት በማመን ከትንሣኤዋና ከዕርገቷ በረከትን እንዲያሳትፈን እግዚአብሔር ይፍቀድልን፤ የእመቤታችን ቃል ኪዳን ረድኤት ይደረግልን አሜን !!