Thursday, 21 January 2021 00:00

ወኵሉ ፍጥረት ተፈሥሐ በምጽአትከ (ቅዱስ ኤፍሬም)

Written by  ዲ/ን ተስፋዬ ምትኩ
 ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ እመቤታችንን ባመሰገነበት በዕለተ ሰኑይ ውዳሴ ማርያም ላይ በወልደ እግዚአብሔር ሰው መሆን ፍጥረታት በሙሉ ደስ እንዳላቸው ይናገራል፡፡ እንደሚታወቀው ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ አንድነት ሳይለይ በተለየ አካሉ ከሰማያት ወርዶ ከእመቤታችን ከቅድስት ደንግል ማርያም ሥጋና ነፍስ ነሥቶ ፍጹም ሰው የሆነው የሰው ልጆችን ለማዳን ነው፡፡ በዚህ ደስ ሊለን የሚገባን እኛ የሰው ልጆች ነን፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ግን ፍጥረት ሁሉ ደስ አለው ብሎናል፡፡ ለመሆኑ ፍጥረታት የተባሉት እነ ማን ናቸው፤ ለምንስ ደስ አላቸው ብለን ስንጠይቅ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፍጥረታት የተባሉት መላእክት፣ እንስሳትና አራዊት፣እንዲሁም ደቂቀ አዳም ናቸው። ብለው በሦስት ከፍለው አስቀምጠውልናል፡፡  ሀ. መላእክት፡-   መላእክት የሚለው ስም ግብራቸውን የሚገልጽ ነው፡፡ ቃሉ የግእዝ ሲሆን በግሪክ አንጌሎስ (Angelos)፣ በዕብራይስጡ ደግሞ መለክ፣ “Mal’ak” ከሚሉት ቃላት የአቻነት ትርጕም ያለው ነው፡፡ የተላከ (messenger) የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ በግእዙም መላእክት የሚለው ቃል፡- ለአከ፣ ተልእከ፣ ላከ፣ ተላከ ልኡክ ከሚሉ ግሶች የሚገኝ ሲሆን መላላክን፣ ማገልገልን፣ መልእከተኛ መሆንን ያመለክታል፡፡ ( ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ፲፱፻፵፰ ዓ.ም መጽሐፈ  ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ገጽ ፭፻፶፬)

 

መጽሐፍ ቅዱስም መልአክ የሚለው ቃል ተላኪ መሆኑን ያመለክታል፡፡ “ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ፦ ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ አለ” ተብሎ የተጻፈው ሐሳብ ይህን ትርጕም የሚያመለክት ነው፡፡ (የሐዋ.፲፪፥፲፩) በትንቢተ ዳንኤልም ላይ “አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ” የሚል ኀይለ ቃል እናገኛለን፡፡ (ዳን.፮፥፳፪) በእነዚህ ሁለቱ ጥቅሶች “መልአኩን ልኮ” በሚለው ሐረግ መልአክ የሚለው ቃል የሚላክ፣ መልእክተኛ የሚል ትርጕም ይሰጣል፡፡  

ከቃሉ ትርጉም ተነሥተን መላእክት የሰው ልጅን ከመከራ ሥጋና ከመከራ ነፍስ ለማዳን፣ ይልቁንም በምድር በሚገጥመው ፈተና ተስፋ ሳይቆርጥ በሃይማኖት ጸንቶ በምግባር ቀንቶ፣ በሕይወቱ ፈጣሪውን አስደስቶ ሰማያዊውን መንግሥት ለመውረስ እንዲበቃ ለማገዝ የሚላኩ ፍጥረታት ናቸው፡፡ ሐዋርያው ይህን እውነት ሲናገር ነው “ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?” ሲል የጻፈልን፡፡ (ዕብ.፩፥፲፬) 

ልበ አምላክ የተባለ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል” (መዝ.፴፫፥፯) እንዳለን ዘወትር ወደ ሰው ልጅ ይላካሉ፡፡ በመከራ የወደቁትንም እግዚአብሔር ምሕረት እንዲያደርግላቸው ይማጸናሉ፡፡ 

ቅዱሳን መላእክት እንኳንስ በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ፣ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም  ለተፈረደበት ለአዳም በኃጢአታቸው ምክንያት ሰባ ዘመን በአሕዛብ ነገሥታት እንዲቀጡ ለተፈረደባቸው ሕዝበ እስራኤልም “አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ እነዚህ ሰባ ዓመት የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?” በማለት በምልጃ ደጅ ይጠኑ እንደነበር ተጽፎልናል፡፡ (ዘካ.፩፥፲፪) እግዚአብሔርም ባለሟሎቹ ናቸውና ልመናቸውን ሰምቶ ቸል አላለም፤ ጸሎታቸውን ሰምቶ ተስፋ ሰጥቶ አስደሰታቸው እንጂ “እግዚአብሔርም ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ በመልካምና በሚያጽናና ቃል ተናገረው” እንዲል፡፡ (ዘካ.፩፥፲፫) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቅዱሳን መላእክት ከሰው ልጆች ጋር ያላቸውን ፍቅር ሲናገር “ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ሁልጊዜ በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁ” ብሏል፡፡ (ማቴ.፲፰፥፲) 

እንግዲህ ቅዱስ ኤፍሬም ስለወልደ እግዚአብሔር ሰው መሆን ሲናገር “ፍጥረት ሁሉ በመምጣትህ ደስ አለው” ብሎ ከተናገረላቸው ፍጥረታት መካከል አንዱ መሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡ ይህስ እንደምን ነው ቢሉ መላእክት ከእግዚአብሔር ተልከው ሥጋዌውን ለነቢያት ነግረዋቸው ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው ትንቢት ተናግረዋል፡፡ ይህ የተነገረው ትንቢት ተፈጽሞ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ አይተነው “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ፤ በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በምድርም ሰላም ለሰውም ልጅ በጎ ፈቃድ ሆነ” ብለን አመስግነነው በክብር ላይ ክብር፣ በጣዕም ላይ ጣዕም በጸጋ ላይ ጸጋ ተጨምሮልን እያሉ ሲመኙ ይኖሩ ነበር፡፡ ይህ ተደርጎላቸው ደስ ብሏቸው አመስግነዋልና ደስታቸው ይህ ነው፡፡ (የሰኞ ውዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ) 

በርግጥ በጌታ መወለድ ቅዱሳን መላእክት ተደስተዋል ወይ የሚለውን ለማወቅ በቤተ ልሔም የሆነውን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ “ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ። ክብር ለእግዚአብሔር በሰማያት ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ” እንዲል፡፡ (ሉቃ.፪፥፲፫-፲፬) ለመሆኑ መላእክት ስለምን ደስ አላቸው ለሚለው ጥያቄ እስካሁን ከተመለከትነው በተጨማሪ የውዳሴ ማርያም አንድታ ትርጓሜ የሚከተለውን ብሏል፡፡

መላእክት ደስ አላቸው ማለቱ ታላቅ ወንድም ለታናሽ ወንድሙ በተደረገለት ደስ እንደሚለው ያለ ደስታ ነው፡፡ መላእክትም ለሰው ተድላ ደስታ ሲደረግለት ባዩ ጊዜ ለራሳቸው እንደተደረገላቸው አድርገው ደስ ይላቸዋልና፡፡ (ዝኒ ከማሁ) “መላእክት ለሰዎች ስለተደረገው ክብር እግዚአብሔርን እንደሚያመሰግኑት ተረዳህን ይልቁንም ኃጢአት ስለተሠረየችልህ ለእኛ የተደረገውንም ክብር ለእነርሱ እንደተደረገ አድርገው ያዩታል” እንዲል፡፡ (ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈ ወርቅ ፷፮፥፴፬)

ለ.እንስሳትና አራዊት፡-

ፍጥረት ያላቸው እንስሳትና አራዊት ናቸው፡፡ ይህ እንደምን ነው ቢሉ በቤተሰብእ ልማድ ነው፤ ቤተሰብ ጌታው ሲሾምለት ሲሸለምለት ደስ እንደሚለው እነሱም ጌታቸው አዳም ከፈጣሪያቸው ጋር ሲጣላ አዝነው ነበርና በጌታ መወለድ ከጌታው ስለታረቀላቸው ደስ ብሏቸዋል፡፡ እንዲሁም ለራሳቸው በተደረገላቸው ነገር ደስ ብሏቸዋል፡፡ ቀድሞ በኖኅ ዘመን የሰው ልጆች በሠሩት ኃጢአትና በደል ምክንያት እግዚአብሔር ምድሪቱን በውኃ ሲያጠፋት ኃጢአት በደል የሌለባቸው ማለትም አእምሮ ዕውቀት ያልተሰጣቸው ጽድቅና ኩነኔም ለይተው የማያውቁና የሌለባቸው ፍጥረታት በሙሉ ከሰው ልጆች ጋር አብረው ጠፍተው ነበረና ከእንግዲህ ወዲህ ጌታችን አዳም ከፈጣሪው ጋር ከታረቀልን እኛም ሁለተኛ ጥፋት አያገኘንም ሲሉ ደስ ብሏቸዋል፡፡ (የሰኞ ውዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ)

ከእንስሳት መካከል አህያ እና ላም በጌታ መወለድ ደስታቸውን በቤተ ልሔም ዋሻ እስትንፋሳቸውን በመገበር ገልጸዋል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ነቢዩ ኢሳይያስ “በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ እስራኤል ግን አላወቀም፥ ሕዝቤም አላስተዋለም” (ኢሳ.፩፥፫) በማለት ጌታ ሕዝበ እስራኤልን የገሠጸበትን ትንቢት ሲተረጕሙ “ቤት ያለው ጎል (ግርግም) ነው ጌታ በእሷ ተወልዶባታልና አህያና በሬ ጌታ የተወለደበትን አውቀው እስትንፋሳቸውን ገብረውለታል፡፡ አይሁድ ግን በቤተ ልሔም ዋሻ በግርግም የተወለደው አምላክ ወልደ አምላክ መሆኑን አላወቁትም ብለዋል፡፡ (ትንቢተ ኢሳይያስ አንድምታ ትርጓሜ)

ሐ. ደቂቀ አዳም

ሌላኛው ፍጥረት ተብሎ የተነገረው አዳምና ልጆቹ ናቸው፡፡ ከፍ ብለን ያየናቸው እንስሳትና አራዊት “ለኃጥኣን የመጣ ለጻድቃን ይተርፋል” እንዲባል የሰው ልጅ ከፈጣሪው ጋር በመጣላቱ ምክንያት ሊመጣባቸው ካለው መዓት በመዳናቸው ምክንያት ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ በወልደ እግዚአብሔር ከሰማያት መውረድና መወለድ ትልቅ ደስታ የተደረገልን ግን እኛ የሰው ልጆች ነን፡፡  ጌታም የነሣው የመላእክትና የሌሎች ፍጥረታትን ሥጋ አይደለም፤ የሰውን ነው እንጂ፡፡ (ዕብ.፪፥፲፮) ለምን ቢሉ የበደለው፣ የወደቀው፣ ሞት የተፈረደበት፣ አዳም ነውና፡፡ 

ስለዚህ የወደቀውን ለማንሣት፣ የተፈረደበትን ነፃ ለማውጣት፣ የሞተውንም ሕያው ለማድረግ ያንኑ የአዳምን ሥጋ ተዋሕዷል፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ ምሥጢረ ተዋሕዶን ሲናገር “የቃል ገንዘቡ ለሥጋ ገንዘቡ ሆነለት፣ የሥጋም ገንዘቡ ለቃል ገንዘብ ሆነለት” (ድርሳነ ቄርሎስ ፸፰፥፫) እንዳለው እግዚአብሔር ወልድ የሰው ልጅን ሥጋና ነፍስ ነሥቶ በተዋሐደ ጊዜ  ባሕርያችን ሕያውነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነውን መለኮታዊ ባሕርይን ገንዘቡ አድርጓል፡፡ 

እንግዲህ የታመመውን የሰው ልጅ ለማዳን ከበሽተኛው አዳም የተሻለ ያልታመመ ሐኪም ፣ ወንጀል የሌለበት ዋስ ጠበቃ፣ ነቀዝ ያላበላሸው ንጹሕ የመሥዋዕት ስንዴና ፍጹም ካህን ያስፈልገን ነበረና የሕይወት መገኛ፣ የባሕርይ ሕይወት፣ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ሰው ሆኖልናል፡፡ ስለ እኛም መከራ ተቀበለ ሞተ ተቀበረ፣ የሞትንም ኃይል ሽሮ፣ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በእርሱ ሞትና ትንሣኤም ድኅነታችን ተፈጸመልን፡፡ ራሱ የመሥዋዕት በግ ራሱ የመሥዋዕቱ አሳራጊ ካህን እሱ ራሱ የመሥዋዕቱ ተቀባይና ይቅር ባይ አምላክ ሆነልን፡፡ ርቀን የነበርነውን አቀረበን፤ “አዳም ሆይ ወዴት ነህ” ብሎ በአዳም አንጻር ሲጠራን ድምፁን እንፈራና እንሸሽ የነበርን፣ በልጅነት ፍቅር የምንጠራ ሆነናል፡፡ “አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና” እንዲል፡፡ (ሮሜ ፰፥፲፭) ከልጅነት በላይ ጸጋ፣ ከአባትነት በላይ ስጦታ ደግሞ ሊኖር አይችልም፡፡ 

ይህም ሁሉ የሆነልን ወልደ እግዚአብሔር ከሰማያት ወርዶ ከእመቤታችን ሥጋና ነፍስ ነሥቶ ሰው በመሆኑ ነውና “በመምጣትህ ደቂቀ አዳም” ደስ ይላቸዋል አለን፡፡  አዎን ደስ ሊለን ይገባል፡፡  ከኀጢአት ወደ ጽድቅ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሲኦል ወደ ገነት፣ ከገሃነመ እሳት ወደ መንግሥተ ሰማያት ከባርነት ወደ ልጅነት፣ ከተገዥነት ወደ ወራሽነት የተሻገርንበት ቀን ነውና ደስ ይበለን፡፡ እርሱ ሰው ሲሆን እኛ አማልክት ዘበጸጋ ሆነናልና ደስ ይበለን፤ እርሱ በበረት ሲወለድ እኛ ወደ ንጉሡ ዙፋን ፊት ቀርበናልና ደስ ይበለን፤ እርሱ ወደ ግብፅ ሲሰደድ እኛ ወደ ርስታችን ገነት ተመልሰናልና ደስ ይበለን፤ እርሱ ሲሞት እኛ ሕያዋን ሆነናልና ደስ ይበለን፤ በትንሣኤውም ትንሣኤያችን ተረጋገጠልን፣ የበደላችን ዕዳ በሞቱ ተከፈለልን፤ የዘለዓለም ሕይወት ተስፋ ሰነቅን፤ ታዲያ ከዚህ በላይ የሚያስደስት ምን አለ? ስለዚህ ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ነገር ግን ሁለት ነገሮችን ሳንዘነጋ ነው፡፡

፩ኛ ደስታችን ፍጹም እንዲሆን ከእኛ የሚጠበቀውን ማድረግን፡- እንግዲህ በጌታ ልደትና ጥምቀት፣ ሞትና ትንሣኤ ዕዳችን ተክፍሎልን የዕዳ ደብዳቤያችን ተደምስሶልን ተስፋችን እንደለመለመ ይታወቃል፡፡ ይሁንና የእኛ ድርሻ መኖሩን መዘንጋት የለብንም፡፡ በየዓመቱ ጌታ ተወለደልን፣ ተጠመቀልን፣ ተሰቀልለን፣ ሞትንም ድል አድርጎ ተነሣልን ወዘተ እያልን በዓላትን ስናከብር፤ እንደ ሉተራውያን በቃ ድኅነታችን ተፈጽሞልናል፤ ከእኛ የሚጠበቀው ይህን ማመን ብቻ ነው እያልን አይደለም፡፡ አዎን ድኅነታችን ተፈጽሞልናል እኛ ግን ከተፈጸመልን ድኅነት ተካፋይ ለመሆን ዕለት ዕለት መትጋት ይጠበቅብናል፡፡ ይህም ጌታ እንደተወለደልን በጥምቀት ዳግመኛ በመወለድ፤ እንደተጠመቀልን ለሥርየተ ኃጢአት በመጠመቅ፣ ስቅለቱንና ትንሣኤውንም ስናስብ የተቆረሰልንን ሥጋ የፈሰሰልንም ደሙን በመቀበል እና ይህን የመሳሰሉ በጎ ምግባራት በማድረግ ሊሆን ይገባል፡፡ 

፪ኛ ደስታችን አምላካችንን ደስ በሚያሰኝ መንገድ መሆን አለበት፡- ጌታ ከኀጢአት ሊያድነን ሲወለድ እኛ ይህን ደስታ ለመግለጽ ወደ ኀጢአት አለመሄዳችን ማስተዋል ይገባናል፡፡ ደስታችን የተደረገልንን ውለታ በማሰብ ከሆነ ጌታ ራሱ “እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና” (ዮሐ.፲፫፥፲፭) እንዳለን ለሌሎች መልካም በማድረግ ደስ ይበለን፡፡ 

በክርስትና አስተምህሮ ደስታ የሚገኘው ለራሳችን በምናደርገው ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ለወንድሞቻችን በምናደርግላቸው ነው እንጂ፡፡ ብዙ በመብላትና ያለ ልክ በመጠጣት ለብሰን በማጌጥና ይህን በመሰለ ሁሉ አይደለም ደስታችን ሊሆን የሚገባው፡፡ እንደጌታችን ትምህርት የተራቡትን በማብላት የተጠሙትን በመጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ ነው እንጂ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዝናብ ያስገኘች ትንሽዋ ደመና፣ ኅብስት ያለባት መሶበ ወርቅ እየተባለች በብዙ ኅብር ከምትመሰለው ከእመቤታችን በቤተ ልሔም ዋሻ የተወለደውን ጌታ ከመላእክቱና ከእረኞቹ ጋር አብረን ማመስገን፣ ከሊቃውንቱ ጋር አብረን መዘመር፣ ይገባናል፡፡ ደስታችን ደግሞ ሰማዕያኑ መላእክትንም ደስ የሚያሰኝ ሊሆን ይገባል፡፡ እንደሚታወቀው የሰማይ ሠራዊት መላእክት ስለእኛ ደስ የሚላቸው ንስሓ ገብተን ሥጋውንና ደሙን ተቀብለን ለሰማያዊ ርስታችን ስንዘጋጅ ነው፡፡ “ንስሓ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሓ በሚገባ በአንድ ኀጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል” እንዲል፡፡ (ሉቃ.፲፭፥፯)  

በአጠቃላይ በጌታችን መወለድ መላእክት፣ እንስሳትና አራዊት እንዲሁም ደቂቀ አዳም ተደስተዋል። ዛሬም በዓሉ ለሁሉም ደስታን ያጎናጽፍ ዘንድ ብቻየን ልብላ፣ ብቻየን ልጠጣ፣ ብቻየን ላጊጥ ወዘተ ሳይሉ ያለው ለሌለው እያበላ፣ እያጠጣና እያለበሰ መከበር አለበት። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ሲሰጠን እኛም ያለንን ልናካፍል የተራቡትን ልናበላ ይገባናል። የተሰጠንን ጸጋ አጽንተን የምንኖረውና ወደከፍተኛዋ ጸጋና ክብር የምንሸጋገረው እርሱ ራሱ ከሰጠን ላይ ከጥቂቷም ቢሆን ለሌላ ስንሰጥ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ሁላችንም በሃይማኖት ጸንተን በጎ ምግባር ሠርተን ንስሓ ገብተን ሥጋውንና ደሙን ተቀብለን የመንግሥቱ ወራሾች የስሙ ቀዳሾች እንድንሆን እግዚአብሔር ይፍቀድልን አሜን።

 

Read 830 times