Saturday, 02 January 2021 00:00

ወኮነ ሰማይ ዓለመ ወዓለምሂ ሰማየ (ሃ.አበ. ዘሳዊሮስ ፹፭፥፴፯)

Written by  ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
የምሥጢረ ሥጋዌ ነገር እጅግ የሚረቅ፣ የሚደንቅ፣ ከኅሊና በላይ የሆነ ነው። ሊቃውንቱንም እጅግ እያስደነቃቸው በተቻላቸው መጠን ለመግለጽ ይሞክሩና ከኅሊናቸው በላይ ሲሆን ዕፁብ ድንቅ እያሉት ያልፋሉ። ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት ውዳሴው “ኦ ዝ መንክር ልደተ  አምላክ እማርያም ቅድስት ድንግል አግመረቶ ለቃል ኢቀደሞ ዘርዕ ለልደቱ፤ ልዩ ከሆነች ድንግል ማርያም ይህ የአምላክ መወለድ ምን ይደንቅ፣ ቃልን ወሰነችው ልደቱንም ዘር አልቀደመውም” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) በማለት በኅሊናው ላይ የተፈጠረውን አግራሞት ይገልጻል። እንዲህ ያለው ልዩ ምሥጢር የተገለጸለትና በአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ሁኖ የኖረው ሊቁ ቅዱስ ሳዊሮስም “ወኮነ ሰማይ ዓለመ ወዓለምሂ ሰማየ፤ ሰማይ ዓለምን ሆነ ዓለምም ሰማይን ሆነ” በማለት ተናገረ። እስኪ ምን ማለት እንደሆነ የተወሰነውን ምንባብ ጠቅሰን ዘርዘር አድርገን እንመልከተው። “ወኮነ ሰማይ ዓለመ ወዓለምሂ ሰማየ፤ ወኮነ እግዚአብሔር ሰብአ በታሕቱ፤ ወረሰዮ ለሰብእ ውስተ አርያም በላዕሉ። ወስብሐተኒ ዘውስተ ሰማይ ኮነ ዲበ ምድር፤ ዘሀሎ በሕጽነ አቡሁ ኮነ በሕፅነ ማርያም፤ ወለዘወለዶ እግዚአብሔር አብ በምሥጢር ዘኢይትረከብ እንበለ መንጸፈ አንስት፤ ወለደቶ ማርያም በሥጋ በምሥጢር ዘኢይትረከብ እንበለ ሩካቤ ተባዕት፤ ሰማይ ዓለም ሆነ ዓለምም ሰማይን ሆነ፤ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ በዚህ ዓለም ተገኘ ሰውንም በላይ በአርያም አደረገው፤ በሰማይ የሚቀርበው ምስጋና በዚህ ዓለም ተደረገ (መላእክትና ደቂቀ አዳም በአንድ ቦታ ተገልጠው አመሰገኑ) ። በአብ እሪና ያለ እርሱ በእመቤታችን ክንድ ተይዞ ታየ። እግዚአብሔር አብ በማይመረመር ምሥጢር ያለ እናት የወለደውን ማርያም በማይመረመር ምሥጢር ያለ ዘርዐ ብእሲ በሥጋ ወለደችው።” (ሃ.አበ. ዘሳዊሮስ ፹፭፥፴፯) ከዚህ ምንባብ በርከት ያሉ  ነጥቦችን ማንሣት ቢቻልም። ጉዳዩ ሰፊ በመሆኑ በዚህ ጽሑፍ የተወሰኑትን ብቻ እንደሚከተለው እንመለከታለን። ፩. አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ  ሊቁ የአምላክን ሰው መሆን የሰውን አምላክ መሆን “ወኮነ እግዚአብሔር ሰብአ በታሕቱ፤ ወረሰዮ ለሰብእ ውስተ አርያም በላዕሉ፤ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ በዚህ ዓለም ተገኘ ሰውንም በላይ በአርያም አደረገው” በማለት ገለጸልን። እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ለማዳን ሰው ሆነ፤ አምላክ ሰው በሆነ ጊዜ ሰውም አምላክ ሆነ። ጥንት እግዚአብሔር የእርሱን የባሕርይ አምላክነት፣ ገዢነት፤ ልጅነት ወዘተ በጸጋ አድሎት፣ ፍጥረቱን ሁሉ እንዲገዛ ፈቀደለት። ግን አታድርግ የተባለውን ሲያደርግ የተሰጠውን ጸጋ ሁሉ ተነጠቀ። ይህ የተነጠቀው ጸጋ ይመለስለት ዘንድ አምላክ ሰው ሆነ።  የሰው ልጅ ይድን ዘንድ አምላክ ሰው መሆኑን አስመልክቶ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ መጽሐፈ ምሥጢር በተሰኘ መጽሐፉ የሚከተለውን ይነግረናል። “ባለመድኃኒቱ በድውዮች ሴት ልጅ አደረ ከእርሷም ምድራዊት ሥጋን ተዋሐደ ለድውዮችም ፈውስ በሚሆን ገንዘብ ከመለኮቱ ጋር ገንዘብ አደረገው። ባለመድኃኒት ከሰማየ ሰማያት መጥቷልና የፈውስ እንጨትም በዳዊት ቤት ተገኘ። መለኮት ከሥጋ ጋር ሳይዋሐድ ፈውስ እንደማይሆን ባለመድኃኒቱ አወቀ።  ስለዚህ ራሱን ሰው ለመሆን ሰጠ።” (መጽሐፈ ምሥጢር ፳፥፯) ሁሉን የሚያድን አምላክ ለሰው ልጅ መድኃኒት ያደረገው ራሱ ሰው መሆንን ነበር። በመሆኑም አምላክ ሰው ሲሆን ሰውም አምላክ ሆነ። ሊቁም የነገረን ይህን ነው።  ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ቅድስት ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት ውዳሴ ማርያም “ወኮነ ሰብአ ከማነ ዘእንበለ ኀጢአት ባሕቲታ፤ ከኀጢአት ብቻ በቀር እንደኛ ሰው ሆነ።” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) በማለት የተናገረውን መተርጕማኑ “ባሕርያችንን እንደተዋሐደ ሲናገር እንደኛ ሰው ሆነ አለ። ከግብራችን እንደለየው ሲናገር ደግሞ ከኀጢአት ብቻ በቀር አለ” በማለት አብራርተውታል። ሰው የሚባለው አራቱ ባሕርያተ ሥጋና ሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ በተዋሕዶ አንድ ሆነው ነውና። አምላክ ሰው ሲሆን ሰው አምላክ ሲሆን ባሕርየ ሥጋን ባሕርየ ነፍስን ሲነሣ ሥጋም ባሕርየ መለኮትን ገንዘብ ሲያደርግ ረቂቁ መለኮት ገዘፈ ግዙፉ ሥጋ ረቀቀ፤ ውሱኑ ሥጋ መላ ምሉእ መለኮት ተወሰነ። አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ ማለት ይህ ነው። ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ይህን ልዩ ምሥጢር “ኑ ይህን ድንቅ ምሥጢር እዩ ሰው የማይሆን ሰው ሆነ ዘመን የማይቆጠርለት ዘመን ተቆጠረለት የማይታይ ታየ የማይታወቅ ታወቀ።” (ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ) በማለት ከአድናቆት ጋር ያስረዳል። ስለዚህ ሰማይ ዓለምን ሆነ ዓለምም ሰማይን ሆነ” ማለት ልዑለ ባሕርይ ሰማያዊ አምላክ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ሰው ሆነ፤ በዚህ ዓለም ተገለጠና ለሰው ሁሉ ታየ፤ ምድራዊው ሰው በተዋሕዶ የመለኮትን ገንዘብ ገንዘብ አድርጎ ሰማያዊ አምላክ ሆነ ማለት ነው። ይህ ምሥጢር በተዋሕዶ የተፈጸመ መሆኑን ሲያስረዳ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ “በእንተ ሥጋ ወነፍስ ዐፅም ወደም ፀጕር ወአሥራው ዘነሣእከ እምኔሃ ወረሰይኮን አሐደ ምስለ መለኮትከ ዘእንበለ ፍልጠት ወኢውላጤ ዘእንበለ ቱስሕት ወኢቡአዴ በከመ መሐሩነ አበው፤ ከእርሷ የነሣሃቸውን ሥጋና ነፍስ፣ አጥንትና ደም፣ የሰውነት ክፍሎችም አባቶቻችን እንዳስተማሩን ያለመለየት፣ ያለመለወጥ፣ ያለመጨመር፣ በተዋሕዶ ከመለኮትህ ጋር አንድ አደረግሃቸው። (መጽሐፈ ሰዓታት) በማለት ያስረዳል። ፪. አብ የወለደውን ድንግል ማርያም ወለደችው  ሊቁ ከላይ በገለጽነው ምንባብ ከሚናገራቸው ነጥቦች መካከል አንዱ አብ የወለደውን ድንግል ማርያም ወለደችው የሚለው ነው። ይህን ሲገልጽ “ወለዘወለዶ እግዚአብሔር አብ በምሥጢር ዘኢይትረከብ እንበለ መንጸፈ አንስት፤  ወለደቶ ማርያም በሥጋ በምሥጢር ዘኢይትረከብ እንበለ ሩካቤ ተባዕት፤ በማይመረመር ግብር አብ ያለ እናት የወለደው እርሱን፤  በማይመረመር ተዋሕዶ እመቤታችን ያለ አባት ወለደችው” በማለት ልደቱን ብቻ ሳይሆን  ልደቱ የማይመረመር እና ረቂቅ ምሥጢር እንደሆነም ይነግረናል። የሰውን ልጅ ለማዳን ከቅድስት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና የተወለደው ወልድ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት የተወለደው ነው። ይህን በተመለከተ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ወለድኩከ እምከርሥ እምቅድመ ኮከበ ጽባሕ፤ ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ” (መዝ.፻፱፥፫) በማለት ነገረን። መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞንም “ተራሮች ሳይመሠረቱ ከኮረብቶች በፊት ወለደኝ፤ እግዚአብሔር ከሰማይ በታች የሚታደርባቸውን ሀገሮችንና ዳርቻዎችን ሳይፈጥር ሰማዮችን በዘረጋ ጊዜ አብሬው ነበርሁ። ዙፋኑን በነፋሳት ላይ ባጸና ጊዜ፣ የቀላያትን ምንጮች ባጸና ጊዜ፣ ለባሕርም ዳርቻን በወሰነ ጊዜ ውኃ ከትእዛዙ እንዳያልፍ የምድርን መሠረት ባጸና ጊዜ እኔ ከእርሱ ጋር እሠራ ነበር” (ምሳ.፰፥፳፭-፴) በማለት ቅድመ ዓለም መወለዱን፣ እንዲሁም በአንዲት ሥልጣን ከባሕርይ አባቱ ጋር ዓለምን የፈጠረ መሆኑን ያስረዳናል። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ምእመናን በላከው መልእክቱ “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዐይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ” (ዕብ.፩፥፩) በማለት እንደነገረን ጥንት በአበው ምሳሌ ሲያስተምር በነቢያት ትንቢት ሲያናግር የነበረው አምላክ በኋላም በሐዋርያት እንደተመሰከረለት ሊቃውንቱም አምልተውና አስፍተው አስረዱን። ረቂቁን ምሥጢር እግዚአብሔር በገለጸላቸው መጠን ገለጹልን። ቅድመ ዓለም ከአብ ያለእናት የተወለደው ድኅረ ዓለም ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት መወለዱን ወልደ አብ ወልደ ማርያም መሆኑን አባቶቻችን ሊቃውንት በስፋት ገልጸው ነገሩን።   የተዋሕዶ መዶሻ እየተባለ የሚጠራው ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስ “ወልድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማይመረመር ተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነውና ቀዳማዊ ሲሆን ከዘመናት አስቀድሞ ከአብ የተወለደ ነው፤ ዳግመኛም ከድንግል በሥጋ የተወለደ ነው ተብሎ ስለ እርሱ እንዲህ ይነገራል።” (ሃ.አበ.ምዕ ፸፫ ክፍል ፲፩ ቁ. ፬) በማለት ያስረዳል።  ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ “በምድራዊ ልደቱ አባት አለው አትበሉ፤ በሰማያዊ ልደቱም እናት አለችው አትበሉ፤ እርሱ በምድር አባት የሌለው ነው፤ በሰማይም እናት የሌለችው ነው።” በማለት ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት ድኅረ ዓለም ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት መወለዱን አስረዳን። ሊቁ እንዲሁ ተወለደ በሚል ቃል ብቻ አይደለም የገለጸው በሰማይ እናት አትፈልጉለት፣  በምድር ደግሞ አባት አትፈልጉለት በማለት በውስጣችንም ሊነሣ የሚችለውን ጥያቄ ግሩም የሆነ መልስ በመስጠት መጨነቅም እንደሌለብን ያስረዳል። አንድ ሰው ተወልዶ እስኪያድግ ድረስ ጡት እያጠባች የምታሳድገው እናት፣ ከእናቱ ጋር እየተንከባከበ የአባት ፍቅር ሰጥቶ የሚለብሰውንና  የሚጎርሰውን እያዘጋጀ የሚያሳድገው አባት ይፈልጋል። ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ለሰማያዊ ልደቱ እናት ለምድራዊ ልደቱ አባት እንደማያስፈልገው ሊቁ ጎርጎርዮስ “በሰማያዊ ልደቱ ጡት አጥብታ በወተት የምታሳድገው እናት አትሹለት፤ በሰማያዊ ልደቱ እናት የለችውምና መለኮቱን ከትስብእቱ ልዩ ነው አትበሉ፤ መለየት በሌለበት በእርሱ ክፉ መለየት እንዳይመጣ። (ሃ.አበ ምዕ.፴፭ ክፍል ፪ ከ፲፮-፲፰)  በማለት ምሥጢረ ሥጋዌን በአግባቡ እንድንረዳ አምልቶና አስፍቶ ይነግረናል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድራዊ ልደቱ የወለደችው እናት ቅድስት ድንግል ማርያም ጡት አጥብታ አሳደገችው። ይህን አስመልክቶ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ “ሰብእ ወእንስሳ ወኵሉ ዘሥጋ ያስተበፅዑኪ እስመ ለዘይሴስዮሙ በሐሊበ አጥባትኪ ሐፀንኪዮ፤ ሰው እንስሳና ሥጋዊ ፍጥረት ሁሉ ያመሰግኑሻል። የሚመግባቸውን በጡትሽ ወተት አሳድገሽዋልና” (አርጋኖን ዘሰኑይ) በማለት ቅድስት ድንግል ማርያምን ፍጥረታት ሁሉ እንደሚያመሰግኗት ከገለጸ በኋላ ለምን እንደሚያመሰግኗት ምክንያቱን ሲያብራራ ደግሞ ፍጥረታትን ሁሉ የሚመግበውን አምላክ ጡቷን አጥብታ በማሳደጓ እንደሆነ ያስረዳል። ከዚህ ላይ ከርእሰ ጉዳዩ አንጻር ልብ እንዲባል የሚፈለገው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋዊ ልደቱ ጡት አጥብታ ያሳደገችው መሆንዋን እንድንረዳው ነው። ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም “በኪሩቤልና በሱራፌል ላይ የሚኖረውን ጌታን በመሀል እጅሽ ይዘሽዋልና በቸርነቱ ብዛት ሥጋዊ ፍጥረትን ሁሉ የሚመግብ እርሱ ጡትሽን ይዞ ጠባ” (ውዳሴ ማርያም ዘዓርብ) ብሎ እንደገለጸው በምድራዊ ልደቱ የእናቱን የድንግል ማርያምን ጡት ጠባ። ለምድራዊ ልደቱ አጥብታ ያሳደገችው እናት ቅድስት ድንግል ማርያም እንዳለች ሁሉ ለሰማያዊ ልደቱ ግን እንዲህ የምታጠባውና የምታሳድገው እናት አትሹለት በማለት ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስና ሌሎችም ሊቃውንት ነገረ ክርስቶስን አምልተውና አስፍተው ይነግሩናል።  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት ድኅረ ዓለም ደግሞ ከድንግል ማርያም ያለ አባት በመወለዱ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ተብሎ ይጠራል። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ድጓ በተሰኘው መጽሐፉ “ወይቤላ እግዚአብሔር ለማርያም አዝማንየ አዝማንኪ አምጣንየ አምጣንኪ ማርያም ሐቀፍኪዮ ወአነ ዮም ወለድክዎ፤ እግዚአብሔር ማርያምን ዘመኔ ዘመንሽ መጠኔ መጠነሽ ነው፤ አንቺ ታቀፍሽው እኔም ዛሬ ወለድሁት” (ድጓ ዘልደት) በማለት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና ፀንሳ በኅቱም ድንግልና የወለደችው በእቅፏም የታቀፈችው ቅድመ ዓለም ከአብ ያለእናት የተወለደ ወልደ አብ ወልደ ማርያም መሆኑን ያስረዳናል።  ሊቁ በአንቀጸ ብርሃን ድርሰቱ ደግሞ “ወመሀረነ ወልድከ እግዚእነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ አንተ ባሕቲትከ አቡሁ ሎቱ ወውእቱ ባሕቲቱ ወልድ ለከ ከመዝ ነአምን ዘአልቦቱ እም በሰማያት ወአብ በዲበ ምድር እንዘ አልቦ ዘየአምር ምጽአቶ ዘእንበለ አቡሁ ባሕቲቱ ወጰራቅሊጦስ  መንፈሰ ጽድቅ፤ ልጅህ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንተ ብቻ አባቱ እንደሆንህ፣ እርሱ ብቻም ልጅህ እንደሆነ አስተማረን። አመጣጡን ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ብቻ በቀር ማንም የሚያውቅ እንደሌለ፤ በሰማይ እናት እንደሌለችው በምድር አባት እንደሌለው እናምናለን።” (አንቀጸ ብርሃን) በማለት የአብ ልጅ የማርያም ልጅ የማርያም ልጅ የአብ ልጅ መሆኑን፣ አብ ያለእናት መውለዱን በሰማይ እናት እንደሌለችው በማለት፣ ድንግል ማርያም ያለ አባት እንደወለደችው ደግሞ በምድርም አባት እንደሌለው እናምናለን በማለት ያስረዳል። ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅድስት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና እንደወለደችውና ምድራዊ አባት እንደሌለው ሲያስረዳን “ሶበ ተወልደ እምድንግል ዐቀበ ድንግልናሃ እንበለ ሙስና፤ ከድንገል በተወለደ ጊዜ ድንግልናዋን ያለ መለወጥ አጸናው። (ሃ.አበ.ምዕ.፷፯ ክፍል፲፩ ቍ.፫) በማለት ከድንግል መወለዱን ብቻም ሳይሆን ሲወለድም ማኅተመ ድንግልናዋን  እንዳልለወጠው ይናገራል። በሰው ባሕርይ በመጀመሪያ ድንግሊቱ ልትወልድ አትችልም በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከወለደች በኋላ ድንግል ተብላ ልትጠራ አትችልም። ድንግል ማርያም ግን ከመውለዷ በፊት፣ በወለደችውም ጊዜ ከወለደችውም በኋላ ድንግል ናት። ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ የሚነግረን ይህን ነው። ፫. በአብ እሪና ያለ እርሱ በእመቤታችን ክንድ ተይዞ ታየ።  ይህን ዓለም ለማዳን ወዶና ፈቅዶ ወደዚህ ዓለማ የመጣው ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ቅድመ ዓለም በአብ እሪና የነበረ ዛሬም ያለ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር አምላክ ነው። ይህ ቅድመ ዓለም በአብ እሪና የነበረው፣ ዛሬም ያለው በተለየ አካሉ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ተወለደ። ስለዚህ ረቂቁ አምላክ በአብ እሪና እንዳለ በድንግል ማርያም ክንድ ተይዞ ታየ። የጌታ ወዳጅ የተባለውና ወንጌላዊው ዮሐንስ “ስለሕይወት ቃል ከመጀመሪያ የነበረውንና የሰማነውን በዐይናችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን። (፩ዮሐ. ፩፥፩) በማለት ቅድመ ዓለም የነበረ መሆኑን፣ ሥጋ ማርያምን ገንዘብ አድርጎ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ መገለጡን በዐይናችን ያየነውን በእጆቻችን የዳሰስነውን የሕይወት ቃል እንነግራችኋለን በማለት አስረዳን።  ወንጌላዊው ዮሐንስ የጌታን ነገረ ሥጋዌ አምልቶና አስፍቶ በጻፈበት በቅዱስ ወንጌል “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህም በመጀመሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ሁሉ በእርሱ ሆነ። (ዮሐ. ፩፥፩) ይለንና ይህ ቅድመ ዓለም የነበረው ዓለምን የፈጠረው አካላዊ ቃል ሥጋ ማርያምን ነሥቶ ተዋሕዶ ወደዚህ ዓለም መምጣቱንና መገለጡን ሲያስረዳን “ቃል ሥጋ ሆነ።” (ዮሐ.፩፥፲፬) በማለት ነገረን። ስለዚህ በአብ እሪና ያለው አካላዊ ቃል የእኛን አካልና ባሕርይ ገንዘብ አድርጎ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ረቂቁ ሲገዝፍ፣ ሥውሩ ሲገለጥ በድንግል ማርያም ክንድ ተይዞ ታየ። “ዘሀሎ በሕጽነ አቡሁ ኮነ በሕፅነ ማርያም ፤ በአብ እሪና ያለ እርሱ በእመቤታችን ክንድ ተይዞ ታየ።” ያለው ለዚህ ነው። ፬. መላእክትና ደቂቀ አዳም በአንድ ቦታ ተገልጠው አመሰገኑ፡-  ሊቁ “ወስብሐተኒ ዘውስተ ሰማይ ኮነ ዲበ ምድር፤ በሰማይ የሚመሰገነውም ምስጋና በምድር ተደረገ።” በማለት በምሥጢረ ሥጋዌ ጊዜ ከተከናወኑት ተግባራት መካከል ሰውና መላእክት አንድ ላይ መዘመር መቻላቸውን ገለጸልን። በጸሎተ ሠለስቱ ደቂቅ “የጌታ ፍጥረቶች ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል” (ዳን.፫፥፴፭) ተብሎ እንደተጻፈ እግዚአብሔር ባወቀ ሳያመሰግን የሚውል የሚያድር ፍጥረት የለም። ይልቁንም ስሙን ቀድሰው ክብሩን ወርሰው ሕያዋን ሁነው ይኖሩ ዘንድ የተፈጠሩ ፍጥረታት ደግሞ ያለማቋረጥ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል። ማክሰኞ በሚጸለየው የሊጦን ጸሎት “ዘኪያከ ያንቀዐዱ ኵሉ ዘበሰማይ ወዘበምድር ዘፈጠርከ ለስምከ ይሰብሑ ወያእኩቱ፤ ስምህን ያመሰግኑ ዘንድ የፈጠርሃቸው ፍጥረታት ሁሉ በሰማይም በምድርም ወዳንተ ያንጋጥጣሉ” (ሊጦን ዘሠሉስ) ተብሎ እንደተጻፈ ሥራቸው እግዚአብሔርን ማመስገን የሆነላቸው ፍጥረታት ዕለት ዕለት እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል። እነዚህም መላእክትና የሰው ልጆች ናቸው። መላእክትና የሰው ልጅ ጥንቱንም ሲፈጠሩ እግዚአብሔርን ስሙን ቀድሰው ክብሩን ወርሰው እንዲኖሩ ነው። ይህን በተመለከተ በመጽሐፍ “ረቂቅ የምትሆን አንተ ከእሳት ነበልባልና ከነፋስ የፈጠረህን ፈጣሪ ነኝ በማለት በታበይህ ጊዜ አንተም በተመካህ ጊዜ እግዚአብሔር ክፉ ሥራህን ተመለከተ፤ ሳያጓድል ስሙን ያመሰግን ዘንድ በአንተ ፋንታ የሚያመሰግን አዳምን ፈጠረው።” (፫መቃ.፪፥፲-፲፩) ተብሎ ተመዝግቧል። እንዲሁም “ምስጋናው በአንተ ጉድለት ይመላ ዘንድ በእጁ በፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ላይ ሾመው። የመሬታዊውም ምስጋና ከሰማያውያኑ ምስጋና ጋር ተጨመረ፤ ምስጋናቸውም እኩል ሆነ” (፫መቃ.፬፥፲፩) የሚል ምንባብ እናገኛለን። ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች መላእክትም ሆኑ የሰው ልጅ የተፈጠሩት ስሙን ቀድሰው ክብሩን ወርሰው ሊኖሩ እንደሆነ ነው። እግዚአብሔር አመስጋኝ ጎድሎት፣ የሚያመሰግነው መፍጠር ግድ ሆኖበት አይደለም። የክብሩ መገለጫ ይሆን ዘንድ ይህን ዓለም እንዴት እንደወደደው ይልቁንም ለሰው ልጅ ያለውን ጥልቅ ፍቅር እንረዳ ዘንድ ነው እንጂ። ዛሬም አመስጋኙ ለራሱ ይከብራል እንጂ እግዚአብሔር ባያመሰግኑት የሚጎድልበት ቢያመሰግኑት ደግሞ የሚጨመርለት ነገር ኑሮ አይደለም። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ዓለም ያድን ዘንድ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ መላእክት ከሰው ልጅ ጋር አመስግነዋል። አዳም አትብላ የተባለውን በልቶ ከእግዚአብሔር ጋር ሲጣላ ከመላእክት ጋርም ተጣላ፣ አንድነቱን አጣ። በክርስቶስ መወለድ የሰው ልጅ ካገኛቸው ጸጋዎች አንዱ ከመላእክት ጋር በአንድነት እግዚአብሔርን ማመስገን መቻል ነው። ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ በሃይማኖተ አበው “ወረሰዮ ድልወ ይትቀነይ ሎቱ ወይትለአኮ ከመ መላእክት እንዘ ሀሎ ውስተ ምድር በምግባር ሠናይ ወበሃይማኖት ርትዕት ዘሥላሴ ቅድስት፤ በዚህ ዓለም ሳለ በበጎ ምግባር ሥላሴንም በማመን እንደ መላእክት ያገለግለው ዘንድ ለእርሱም ይገዛለት ዘንድ የበቃ አደረገው” “ሃ.አበ. ፳፰፥፴፭) በማለት እንደገለጸው ሰውና  መላእክት ዋናው የተፈጠሩለት ዓላማ እግዚአብሔርን አመስግነው ክብሩን ወርሰው ለመኖር ነው። ስለዚህ መላእክት ከሰው ጋር ማመስገን ቻሉ።  ይህን በተመለከተ በቅዱስ ወንጌል “ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ ሠራዊት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ፤ ክብር ለእግዚአብሔር በሰማያት ሰላምም በምድር ለሰው ልጅም በጎ ፈቃድ ሆነ ይሉ ነበር” (ሉቃ.፪፥፲፫-፲፬) ተብሎ መላእክት በክርስቶስ ልደት ከሰው ልጅ ጋር ያመሰገኑት ምስጋና ተመዝግቦልን እናገኛለን። ሊቁ ቅዱስ ያሬድም “ዮም አሐደ መርኤተ ኮኑ መላእክት ወሰብእ ከመ ይሰብሕዎ ለክርስቶስ በቃለ አሚን፤ ዛሬ መላእክትና ሰው ሃይማኖታዊት በሆነች ቃል ክርስቶስን ያመሰግኑት ዘንድ አንድ ሆኑ።” (ድጓ ዘፋሲካ) በማለት አስረዳን። ስለዚህ ከሊቁ አገላለጽ የምንረዳው በብዙ መንገድ የተገለጸውና መጻሕፍት አምልተውና አስፍተው የሚነግሩን የሰው ልጅ ከመላእክት ጋር ማመስገናቸውን ነው። በአጠቃላይ “ወኮነ ሰማይ ዓለመ ወዓለምሂ ሰማየ፤ ሰማይ ዓለምን ሆነ ዓለምም ሰማይን ሆነ” ማለት አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ፤  አብ ቅድመ ዓለም ያለ እናት የወለደውን ድንግል ማርያም ያለ አባት ወለደችው፤ በአብ ዕሪና ያለ በድንግል ማርያም እቅፍ ተይዞ ታየ፤ ሰማያውያን መላእክት ከምድራውያኑ የሰው ልጆች ጋር አመሰገኑ፤ በሰማይ የሚነገረው የመላእክት ምስጋና በምድር፣ በምድር የሚነገረው የሰው ልጅ ምስጋና በሰማይ ተነገረ፤ የሚለውና ከላይ በሰፊው እየተነተነው የመጣነውን የሚያስረዳን ነው። ከበረከተ ልደቱ ያሳትፈን አሜን።  
Read 1049 times