Wednesday, 07 April 2021 00:00

ነገረ ምጽአት

Written by  በመ/ሐ ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ
የሰው ልጅ የመጀመሪያ ተስፋ የወልደ እግዚአብሔር አካላዊ ቃል ቀዳማዊ ምጽአቱ ነው። ይህም ማለት እግዚአብሔር ለሰው የሰጠውን ተስፋ ለመፈጸም ልኡካነ ቃል ነቢያትን አስነሥቶ በሥጋ እንደሚመጣ አናገረ፤ ነቢያት የወልደ እግዚአብሔርን መምጣት በብዙ ኅብረ ትንቢት እና ኅብረ ምሳሌ አስተማሩ፤ ስለቀዳማዊ ምጽአቱ ትንቢት ተናገሩ፤ ሱባኤ ቆጠሩ፤ የሰው ልጅ ልቡና የፈጣሪውን መምጣት በተስፋ ሰነቀ። በምጽአቱ የሚያገኘውን ድኅነት በተስፋ ጠበቀ። የተናገረውን የማያስቀር የማያደርገውን የማይናገር አምላክ ዘመኑ ሲደርስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በብሥራተ መልአክ ተወለደ፤ ይህ የመጀመሪያ ምጽአት ይባላል። ‹‹ዘመኑ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ከሴትም ተወለደ›› እንዲል ገላ.፬፥፬። ይህ አመጣጥ የዓለምን ገጽታ የቀየረ ለዘመናት በሰው ልጅ ላይ ጸንቶ የነበረውን መርገም የሻረ ከገነት ተሰዶ የነበረውን የሰው ልጅ ወደገነት የመለሰ የአረጀውን ዓለም ያደሰ የረከሰውን የሰው ልጅ ሕይወት የቀደሰ ልጅነትን በሃይማኖት የሰጠ መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን ያጠፋ  ሞትን የገደለ የሰው ልጆችን ክብር የገለጠ ምጽአት ነው። በዚህ ግሩም ትሕትናውን አሳይቶ አምላክ በሥጋ በተገለጠበት ቀዳማዊ ምጽአቱ ሰው ሆኖ በመወለዱ ዓለም ያገኘውን ሕይወት መዘርዘር ያገኘውን ጸጋ መናገር በቁጥር የሚወሰን ስላልሆነ ይህን ያህል ነው ማለት አንችልም። እንዲያው በጥቅሉ የሰው ልጅ ከሞት ባርነት ከኃጢአት ተገዥነት በመቃብር ፈርሶ በስብሶ ከመቅረት ነጻ የወጣው በቀዳማዊው ምጽአተ ወልደ እግዚአብሔር ነው። 

 

የሰው ልጅ ፍቅር ስቦት ሰውን መውደዱ አገብሮት አምላክ ወዶ ፈቅዶ ሰው ሆኖ መጥቶ የሰውን ሁሉ መከራ ተቀብሎ አዳነን። ‹‹ነሥአ ደዌነ ወጾረ ሕማመነ፣ ደዌያችን ወሰደ ሕማማችን ተሸከመ በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን›› (ኢሳ.፶፫ ፥፮) እንዲል::

ደዌ ሥጋን በተአምራት ደዌ ነፍስን በትምህርት ቀጣልን የደዌ የሕማማት ምንጭ የነበሩ አጋንንትን ድል ነሣልን። ሞታችንን ሞቶ የእርሱን ሕይወት ለእኛ ሰጠን ‹‹ዘዚኣነ ሞተ ነሥአ ወእንቲኣሁ ሕይወተ ወሀበነ፤ የእኛን ሞት ወስዶ የእሱን ሕይወት ለእኛ ሰጠን›› (እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ) በዚህ መንገድ ወገኖቹ አደረገን በሐዲስ ተፈጥሮ እንደገና ፈጠረን ከብሉይ ሰውነት አውጥቶ በሐዲስ ሰውነት አጽንቶ ሐዲስ ሕግ ሠራልን በቅዱስ ኑሮ መመላለስ እንችል ዘንድ በቅዱስ ቃሉ ‹‹ንዑ ትልውኒ፤ ኑ ተከተሉኝ›› ብሎ ጠራን ‹‹እናንተ ሸክም የከበደባችሁ ወደእኔ ኑ እኔ አሳርፋችኋለሁ›› (ማቴ.፲፩፥፳፰) ብሎ ሸክም የከበደበትን ዓለም ወደ እርሱ ወደ ሠርጉ ቤት ጠራው ቅዱስ ኑሮን ለሰው ልጅ አስተማረ ‹‹እኔ የዋህ ነኝ ከእኔ ተማሩ ለነፍሳችሁ ዕረፍትን ታገኛላችሁ›› በማለት አስተማረ። (ማቴ.፲፩፥፳፰-፳፱)  

ጌታችን በመጀመሪያው ምጽአቱ እንዴት መኖር እንደሚገባን ለሰው ልጆች ሁሉ አስተማረን እንድንከተለውም ፍለጋውን ተወልን ‹‹ፍለጋውን እንከተል ዘንድ ምልክቱን ተወልን›› (፩ኛ ጴጥ.፪፥፳፪) እንዲል። በዚህ መንገድ እርሱን ተከትለንና መስለነው እንድንኖር መኖሪያ ቤት ቤተ ክርስቲያንን መመሪያ ሕግ የፍቅርና የትሩፋት ሕግ ወንጌልን ሰጠን የሚመሩ ሐዋርያትን፣ ጳጳሳትን፣ ሊቃውንትን የምንበላውን ቅዱስ ሥጋና የምንጠጣውን ክቡር ደሙን በነጻ ያለ ዋጋ በቸርነቱ አድሎን ይህን አድርጎ ዳግመኛ እንደሚመጣ ነግሮን ወደ ሰማያት ዐረገ በአባቱ ቀኝ (ዕሪና) ተቀመጠ። 

ስለዚህ አሁን የሰው ልጅ የሚጠብቀው የወልደ እግዚአብሔርን ዳግም ምጽአት ነው። ይህም የሁሉም ፍጻሜ የሚሆንበት ወልደ እግዚአብሔር በቀዳማዊ ምጽአቱ መጥቶ በሰጠው ሕግ በአስተማረው ትምህርት መሠረት ለሠራነው መልካምም ሆነ ክፉ ሥራ ዋጋ  ለመስጠት እንደ ቀድሞው ለትምህርት ሳይሆን እንደየሥራችን ለመክፈል ይመጣል። ይህ የጌታችን ዳግም መምጣት የሁሉ ፍጻሜ ነው የሚታየው ዓለም ያልፍበታል የሚመጣው ዘለዓለማዊ ዓለም ይገለጥበታል ቀዳማዊ ምጽአቱ ዘር ደኃራዊ ምጽአቱ መከር ነው በዘር ጊዜ ገበሬ መከራ እንደሚበዛበት ጌታችን በመጀመያው ምጽአቱ ለመከራ ነው የመጣው። በትሑት ሰብእና በመገለጡ ይህ ዓለም ንቆታል፤ አቃሎታል፤ መዘባበቻም አድርጎታል። ‹‹ጋኔን አለበት ለምን ታደምጡታላችሁ?››፤ በብኤልዘቡል ያወፅኦሙ ለአጋንንት አጋንንትን በብኤልዘቡል በአጋንንት አለቃ ነው የሚያወጣቸው›› ዮሐ.፲፥፳፤ ማቴ.፲፪፥፳፬። እየተባለ ተዘበተበት። ይህን ሁሉ ጽርፈት በትሕትና ተቀብሏል። በቀዳማዊ ምጽአቱ ኃጢአተኛውን ዓለም በንስሓ ሊጠራ ነው የመጣው ። ‹‹ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም ኃጥኣንን ለንስሓ ልጠራ መጣሁ እንጂ›› ማቴ.፱፥፲፫ እንዲል።

አሁን ዳግመኛ የሚመጣው ግን እንደቀድሞው ዓለምን በትሕትና ለመጥራት ሳይሆን የመከር ጊዜ ነውና ስንዴውን ከገለባው፣ ገለባውን ከፍሬው፣ እንክርዳዱን ከስንዴው፣ ስንዴውን ከእንክርዳዱ፣ ወዘተ ለይቶ ስንዴውን በጎተራው ሰብስቦ እንክርዳዱን እና ገለባውን በእሳት ሊያቃጥል ነው። መከር እንደዚያ ነውና ‹‹እንክርዳዱን ስትነቅሉ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉ አይሆንም ተውአቸው እስከ መከር አብረው ይደጉ በመከር ጊዜ አጫጆችን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በየነዶውም አስራችሁ በእሳት አቃጥሉት ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ እላለሁ አለ›› (ማቴ.፲፫፥፳፱-፴) እንዲል።

ከላይ ያየነው በሰም አነጋገር የተገለጠው የጌታችን ትምህርት እንክርዳድ በሚል የገለጣቸው የንስሓ፣ የመልካም ሥራ ፍሬ የሌላቸውን ኃጥኣንን ነው። ለመሥዋዕት በተመረጠው ስንዴ   የመሰላቸው ደግሞ ጻድቃንን ነው። እሳት የተባለው ለዲያብሎስ እና ለሠራዊቱ የተዘጋጀው የዲያብሎስ የግብር ልጆች ዲያብሎስን መስለው ተከትለው የሚገቡበት ገሃነመ እሳት ነው። ጎተራ የተባለው ደግሞ ስንዴ በሚል ስም የተገለጡት ጻድቃን የሚወርሱት መንግሥተ ሰማያት ነው። ስለዚህ የጌታ ዳግም ምጽአት ለኃጥኣን መከራን ለጻድቃን ደስታን የሚያጐናጽፍ ነው። 

ከላይ በምሳሌ የገለጠውን በግልጽ እንዲህ በማለት ተርጉሞታል። ‹‹እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው መልካምን ዘር የዘራው የሰው ልጅ (ክርስቶስ) ነው፤ እርሻውም ዓለም (ሰው) ነው፤ መልካም ዘር የተባሉ የመንግሥት (የወንጌል) ልጆች እንክርዳዱም የክፉ ልጆች ናቸው የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው። መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው አጫጆች መላእክት ናቸው። እንግዲህ እንክርዳዱ ተለቅሞ እንደሚቃጠል በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ (ክርስቶስ) መላእክቱን ይልካል ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሏቸዋል። በዚያ ለቅሶና ጥር ማፋጨት ይሆናል። በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ›› እንዲል ማቴ.፲፫፥፴፯-፵፫።

ከላይ ባነበብነው መሠረት ለኃጥኣን ፍዳቸውን ለጻድቃን ዋጋቸውን (ክብራቸውን) ለመስጠት ይመጣል እንዲህ ከሆነ የእንክርዳድነትን ጠባይ አስወግደንና ተዘጋጅተን ንስሓ ለመቀበል መትጋት አለብን ማለት ነው። በዚህ ጊዜ ጌታ የዘራውን ንጹሕ ዘር ይሰበስባል ዲያብሎስም የዘራውን እንክርዳድ ይለቅማል የኔ ሕይወት የትኛው ላይ ይሆን ብለን ራሳችን ግብራችንን መመርመር አለብን። 

፩. ዳግም ምጽአት በነቢያት 

ቅዱሳን ነቢያት ዋናው የተልዕኳቸው ማእከል የቀዳማዊ ምጽአቱን በተስፋ ትንቢት ለሰው ልጆች ማወጅ ነው። እንዲሁም ይመጣል ብለው በትንቢት የተናገሩለት አምላክ እንደሚመጣ ወደ ሰማያት በክብር እንደሚያርግ ዳግም ለፍርድ እንደሚመጣ የወጉት ሁሉ እንደሚያዩት ለእያንዳንዱ ዋጋውን እንደሚከፍል አስተምረዋል በጥቂቱ እንመልከት። 

የእግዚአብሔር ሰው ሄኖክ ‹‹እግዚአብሔር ይፈርድ ዘንድ ቅዱሳን መላእክትን አስከትሎ ይመጣል ለሁሉ እንደየሥራው ይከፍለዋል ስለ ሠሩት ኃጢአታቸው ኃጥኣንን ይዘልፋቸዋል በእርሱ ላይ የማይገባ ነገር የተናገሩትን ሁሉ›› (ሄኖ.1፥9) በማለት ተናግሯል። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም ‹‹እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል መጥቶም ዝም አይልም እሳት በፊቱ ይነዳል ከላይ ሰማይን ይጠራታል በሕዝቡ ይፈርድ ዘንድም ምድርንም ይጠራታል›› መዝ.፵፱፥፪ በማለት አስረዳቷል። ይህ ማለት ሰማይ ልዑላኑን መኳንንትን መሳፍንትን የምድር ገዥዎችን የሚመለከት ሲሆን ምድር ያላቸው ደግሞ ትሑታንን ነው። እነዚሀን ሁሉ በዳግም ምጽአቱ ለፍርድ በፊቱ ያቆማቸዋል። 

የእግዚአብሔር ነቢይ ዘካርያስ ‹‹በዚያም ጊዜ (ቀን) እግሮቹ በኢየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ተራራ ይቆማሉ›› (ዘካ.፲፬፥፬) በማለት ተናግሯል። ነቢዩ ዘካርያስ ምጽአቱ የሚደረግበት የምጽአቱ ምሥጢር መገለጫ ደብረ ዘይት የተባለው ተራራ መሆኑን ጭምር ገልጧል። ይኸውም ጌታችን በማቴዎስ ወንጌል ፳፬፥፫ ጀምሮ በደብረ ዘይት ምሥጢረ ምጽአቱን ሲያስተምር ምጽአቱ የሚከናወነው በዚያ ሥፍራ መሆኑን ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯል። ስለዚህ ዳግም ምጽአቱ በነቢያት ትንቢት ተነግሯል ማለት ነው። አምላክ ሰው ሆኖ ከአከናወነው ነቢያት ያልተናገሩት ምን አለ? እግዚአብሔር ገልጦላቸው ተናገሩ፤ የተናገሩትንም አምላክ ሰው ሆኖ ፈጸመው። ከተናገሩት መካከል ያልተፈጸመው ገና የሚፈጸም የምንጠብቀው ተስፋ የምናደርገው ዳግም ምጽአቱ ነው። ይህም የሁሉ ፍጻሜ የዓለም መጨረሻ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ የአዲሱ ሕይወት መጀመሪያ ነው። 

ያን ጊዜ ጻድቁ (እውነተኛው) መከራ በአጸኑበትና ድካሙን በካዱ ነገሩን በናቁ ሰዎች ፊት በብዙ መገለጥ ይቆማል በግርማ እና በክፉ ማስፈራራት ሆኖ ባዩት ጊዜ ይታወካሉ። ድንቅ ስለሚሆን ደኅንነቱ ይደነቃሉ እየተጸጸቱና በተጨነቀ መንፈስ እየጮኹ እርስ በእርሳቸው ይናገራሉ እንዲህም ይላሉ ‹‹ቀድሞ በእኛ በሰነፎች ዘንድ መሳለቂያ መሽሟጠጫ የሆነው ሥራውን ስንፍና፣ ሞቱንም የተናቀ ያደረግንበት ይህ ነውን? እንዴት የእግዚአብሔር ልጅ ሆነ? ርስቱስ እንዴት ለቅዱሳን ሆነች? ስለዚህ ከቀና መንገድ ወጥተን ስተናል፤ የጽድቅ ብርሃንም አልተገለጠልንም፤ ፀሐይ አልወጣልንም፤ በደልን እና ጥፋትን በመንገዳችን ሞላን፤ በምድረ በዳም ሄድን የእግዚብሔርን መንግሥት አላወቅንም፤ ትዕቢት ምን ጠቀመን? ከትዕቢት ጋር ያለ ባለጠግነትስ ምን አመጣልን? ይህ ሁሉ እንደ ጥላ ኃላፊ ነው›› ጥበ.፭፥፩-፬። 

፪.ዳግም  ምጽአት በሐዋርያት 

የነገረ ምጽአት ትምህርት ምንጩ ቀዳማዊው ምጽአቱ ነው ይህን ቀዳማዊ ምጽአት ቅዱሳን ሐዋርያት በዐይናቸው አይተዋል፤ የቃሉን ትምህርት በጆሯቸው ሰምተዋል፤ በእጃቸው ዳሰውታል፤ ከዋለበት እየዋሉ ካደረበት እያደሩ የእጁን ተአምራት እያዩ ለጌታችን ከአቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል ነገረ ምጽአት፣ የዓለም መጨረሻ፣ ምልክቶቹ ተጠቃሾች ናቸው። የነገረ ምጽአት ትምህርት በቅዱሳን ሐዋርያት ጠያቂነት በጌታችን መልስ ሰጭነት የተሰጠ ምሥጢራዊ ትምህርት ነው። 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ድንቅ የመምጣቱን ምሥጢር አስተምሯቸዋል እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ጽፈው አቆይተውልናል ጥቂቶችን እንመልከት። ‹‹ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ መልሶ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ እንግዲህ ዋጋችን ምን ይሆን›› አለው ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ የተከተላችሁኝ እናንተ በዳግም ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ እናንተም በዐሥራ ሁለቱ ዙፋን ትቀመጣላችሁ በዐሥራ ሁለቱም ነገደ እስራኤል ትፈርዳላችሁ›› ማቴ.፲፱፥፳፮ በዚህ ጥያቄ ጌታችን በዳግም ምጽአቱ ቅዱሳን ሐዋርያት የሚያገኙትን ዋጋ እና ከፍ ያለ ክብር ያስተማረበት ነው። ይህን ምጽአት እየናፈቁ በትጋት እንዲያገለግሉት አስተምሯቸዋል። 

ቅዱሳን ሐዋርያት የነቢያትን ትንቢት የተረጎሙ በቀዳማዊ ምጽአቱ ነቢያት ለዘመናት ሊያዩት የተመኙትን ያዩ ነቢያት ሊሰሙት የወደዱትን የሰሙ፣ ፈጣሪያቸውን በእግር ተከትለው በግብር መስለው የእጁን ተአምራት ያዩ፣ የቃሉን ትምህርት የሰሙ፣ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የከበሩ፣ የጨለማውን ዓለም በወንጌል ብርሃንነት ያበሩ፣ ክርስቶስን መስለው ሰማዕትነትን ያስተማሩ፣ በዓለም ዳርቻ የተበተኑትን የሰው ልጆች በወንጌል መረብነት የሰበሰቡ ናቸው። በመሆኑም ሐዋርያት ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጠይቀው ባገኙት መሠረት ሁላችን ዝግጅት እንድናደርግና በተስፋ እንድንጠብቀው ጽፈውልናል። ለምሳሌ፡-

የሐዋርያት አለቃ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹የእግዚአብሔርን የመምጣት ቀን ተስፋ እያደረጋችሁ በተቀደሰ ኑሮ ለመኖር ቸኩሉ›› 2ኛ ጴጥ.፫፥፲፩። በማለት በቀዳማዊ ምጽአቱ የተቀበልነውን የጸጋ ልጅነት፣ ድኅነት፣ ነጻነት ወዘተ አጽንተን በተቀደሰ አኗኗር እንድንኖር አስረድቶናል። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ''የሰው ሁሉ ተስፋ የወልደ እግዚአብሔርን መምጣት ይጠብቃልና'' (ሮሜ. ፰፥፲፱) በማለት በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች  የእግዚአብሔርን አመጣጥ  አስረድቷል። በመሆኑም ሐዋርያው እንደነገረን የዓለም ተስፋ የእግዚአብሔር መምጣት ነው ሌላ ተስፋ የለውም። በቀዳማዊ ምጽአቱ የተሰጡ የድኅነት ተስፋዎች ሁሉ የሚጠናቀቁትና የሚረጋገጡት በእግዚአብሔር ዳግም መምጣት ነው።

ሐዋርያት ከጌታ ባገኙት ትምህርት የነገረ ምጽአትን ጉዳይ በዝርዝር አስረድተዋል። ስለነገረ ምጽአት የነገሩንም በሃይማኖት ጸንተን በንጽሕና በቅድስና እንድንኖር ነው። ከገቡ የማይወጡበት፣ ከአገኙ የማያጡት ዘለዓለማዊ ደስታ አለና ያን ተስፋ አድርገን ለመልካም ሥራ እንድንቸኩል ለማድረግ በምልዓት አስረድተውናል። የአባቶቻችንን መልካም ትምህርት ጠብቆ የማያልፈውን ሕይወት ተስፋ እያደረጉ በቅድስና በንጽሕና በንስሓ ሕይወት እየተመላለሱ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እየተቀበሉ መኖር ከእኛ የሚጠበቅ ተግባር ነው።

፫.የምጽአቱ ምልክቶች 

ሀ.የብዙዎች ሐሰተኞች መነሣት ብዙዎችን ማሳታቸው፡- ጌታችን መድኃኒታችን ሲየሱስ ክርስቶስ ይህን ሲገልጥ ‹‹ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉ›› ማቴ.፳፬፥፬ ብሏል። አሁን እንደምናስተውለው ብዙ ሐሰተኞች እንደ አሸን ፈልተው የሐሰት ትምህርት እያስተማሩ ብዙዎችን ከእውነተኛው የክርስትና መንገድ እያወጡ ይገኛሉ። ነቢይ ነኝ፣ ሐዋርያ ነኝ ተአምራት አደርጋለሁ በሚል ውሸት ብዙዎችን እያታለሉ ነው። እውነትን በሚጠሉ ሰዎች ድጋፍ ለቁጥር በሚያታክቱ የግንኙነት መስመሮች (ቻናሎች) ዓለምን እያደናቆሩት ይገኛሉ። እነዚህ የዳግም ምጽአትን መቅረብ የሚያሳዩ ናቸው። ‹‹እንዳያስቷችሁ ተጠንቀቁ›› ተብለናልና እንጠንቀቅ። 

ለ. ጦርነት፡- በሁለተኛ ደረጃ ምልክት ሆኖ የተጠቀሰው ጦርነት ነው። አሁን ዓለማችን ዕለት ከዕለት ጆሮአችንን የሚያድነቁረን የጦርነት ወሬ ነው። አሁን ዓለም ዓለምን የሚያጠፉ የጦር መሣሪያ (ኒኩለር) አመረትኩ ተምዘግዛጊ ሚሳኤል በስውር የሚበር የጦር ጀት አለኝ ነው ዜናዋ ይህም ዓለም ለጥፋት እየቀረበች መሆኑን አመልካች ነው። ‹‹ጦርንም የጦርነትንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ ግድ ነው ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ አትደንግጡ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል።›› እንዲል። ማቴ.፳፬፥፮ 

ሐ. በሽታ፡- ከረኃብም ላይ በሽታ የምድር መናወጥ ይህን የመሳሰሉት ሁሉ የዳግም ምጽአትን አዋጅ እየመረረንም ቢሆን የሚያውጁ ናቸው። በተለይ አሁን ዓለምን ሥጋት ላይ የጣለው የኮረና ቫይረስ ለዚህ ዋና ማሳያ ነው። ዓለም ታሟል ፈውሱ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነው። ‹‹ረኃብ፣ ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ሥፍራ ይሆናል›› እንዲል። ማቴ.፳፬፥፪

መ. የክርስቲያኖች ለመከራ ተላልፎ መሰጠት፡- አሁን ዓለማችን እንደፋሽን የተያያዘችው ተግባሯ ክርስቲያኖችን መግደል፣ ማፈናቀል፣ ማሳደድ፣ ማንገላታት፣ ማዘረፍና አብያተ ክርስቲያናትን ማቃጠል ለክርስቲያኖች ፍትሕ አለመስጠት የዚሁ የዳግም ምጽአት ምልክት አንዱ አካል ወይም ማሳያ ነው። በዚህ ሁኔታ በተለይም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት እየደረሰ ያለው መከራ ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሀቅ ነው። ‹‹በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል ይገድሏችኁማል፤ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ በዚያ ጊዜ ብዙዎች ሃይማኖታቸውን ይለውጣሉ፤ እርስ በእርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ›› ማቴ.፳፬፥፱ እንዲል። 

ረ. የፍቅር መጥፋትና የዐመፃ ብዛት፡- እነዚህን ሁሉ የሚያደርገው የፍቅር መጥፋት የዐመፃ እና የዐመፀኞች መብዛት ነው። ይህም የምጽአት ምልክት እንደሆነ ጌታችን አስተምሯል። አሁን መቸም ፍቅር አለ ብሎ መናገር ይከብዳል። አለም ካልን በጥቅም ላይ የተመሠረተ ነው ይህ ደግሞ ፍቅርን ሳይሆን ዐመፃን የሚያነግሥ ነው። ‹‹ከዐመፅም ብዛት የተነሣ የብዙዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች እስከ መጨረሻ የሚፀና እርሱ ይድናል ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል ይሰበካል በዚያን ጊዜ መጨሻው ይመጣል›› እንዲል ማቴ.፳፬.፲፪። 

፬. የመምጫው ሰዓት 

ከላይ የተዘረዘሩት ምልክቶች በትክክል ሰዓቱን ለይተው በዚህ ጊዜ ነው የሚሉ አይደሉም። ምክንያቱም የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ድንገት የሚሆን ነውና። ‹‹በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል በዚያን ጊዜ የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ የሰው ልጅንም በኀይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል መላእክቱንም ከታላቅ የመለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል ከሰማያት ዳርቻ እስከ ዳርቻዋ ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ›› ማቴ.፳፬.፴፤ ‹‹በኖኅ ዘመን እንደሆነ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናል›› ማቴ.፳፬፥፴፯ ማለት ቀንዋን እና ሰዓቷን የሚያውቅ የለም ተዘጋጅቶ መጠበቅ ብቻ ነው። ነገር ግን በዕለተ ዕርገቱ ለቅዱሳን ሐዋርያት በመላእክት አንደበት ‹‹ይህ ከእናንተ ዘንድ ወደ ሰማይ ያረገው ኢየሱስ ነው ሲያርግ እንዳያችሁት ዳግመኛ ይመጣል›› ተብሎ ተነግሯልና በግልጥ ይመጣል። ሐዋ.፩፥፱-፲፩ ወንጌላዊው ዮሐንስ በራእዩ ‹‹እነሆ በሰማይ ደመና ይመጣል፤ ዐይን ሁላ ታየዋለች እነዚያም የወጉትም ይመለከቱታል፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ስለእርሱ ያለቅሳሉ›› በማለት እንደተናገረው እየታየ በግልጥ ይመጣል። ራዕ.፩፥፯። 

በዚህ መልኩ መጥቶ ዓለምን እንደ ሸማ ጠቅልሎ ያሳልፋታል ይህን ጊዜ ምድር የተቀበለችውን አደራ ታስረክባለች። ሙታን ይነሣሉ፤ የተዘራው ዘር ፈርሶ በስብሶ ተነሥቶ እንዲያፈራ አውሬ የበላው፣ ነፋስ የበተነው፣ ውኃ የወሰደው፣ በልዩ ልዩ ሞት በነፍስ ወደገነት ወይም ወደ ሲዖል የተወሰደውና በሥጋ በመቃብር ውስጥ ያረፈው ሁሉ ይነሣል።  ‹‹በመጀመሪያ የአዋጅ ቃል በልዩ ልዩ ሞት የሞተው አውሬ የበላው ውኃ የወሰደው የፈረሰው የበሰበሰው የሰው አካል ራስ ካለበት ይሰበሰባል። በሁለተኛው አዋጅ የተኛህ ንቃ በሚለው ያለ መንቀሳቀስ ትኩስ በድን ይሆናል። በሦስተኛው አዋጅ ጻድቃንም ኃጥኣንም ከዓለም የተከተላቸው ሥራቸውን ይዘው ይነሣሉ።›› (ቅዳሴ ያዕቆብ ዘሥሩግ) ምድር ይህን አደራዋን  ካስረከበች በኋላ ታልፋለች። የማያልፈው ዘለዓለማዊውን ርስት ለማውረስ ጻድቁን በቀኙ ኃጥኡን በግራው የሚያቆመው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 

ይህ በጌታችን ምጽአት የሚደረገውን ትንሣኤ ሙታንን ተከትሎ የዘለዓለም ሕይወት ለጻድቃን የዘለዓለም ኵነኔ ለኃኣን የሰጣል። ‹‹በመቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል መልካም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉ ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ እና በዚህ አታድንቁ››  ዮሐ. ፭፥፳፰ ከዚህ ትንሣኤ በመቀጠል የዘለዓለም ፍርድ የሰጣል። 

፭.የዘለዓለም ፍርድ 

የሰው ልጅ በክብሩ በመጣ ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክት ሁሉ ያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣሉ አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ እረኛም በጎችን ከፍየሎች እንደሚለይ ይለያያቸዋል። በጐችን በቀኙ ፍየሎችን በግራው ያቆማቸዋል ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል ‹‹እናንተ የአባቴ ቡሩካን ኑ ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ ተርቤ አብልታችሁኛልና ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና ታርዤ አልብሳችሁኛልና ታምሜ ጠይቃችሁኛልና ታስሬ ወደኔ መጥታችኋልና ጻድቃንም መልሰው ይሉታል ጌታ ሆይ ተርበህ አይተንህ መቼ አበላንህ? ተጠምተህስ መቼ አጠጣንህ? እንግዳ ሆነህስ መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታስረህ አይተንህ መቼ ጠየቅንህ? ታርዘህ መቼ አለበስንህ? ወይስ ታስረህ ታመህ መቼ ወደ አንተ መጣን ይሉታል። 

ንጉሡም እውነት እላችኋለሁ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ ማድረጋችሁ ለእኔ ማድረጋችሁ ነው›› ይላቸዋል። በግራ ያሉትን ደግሞ ‹‹ብራብ አላበላችሁኝም ብጠማ አላጠጣችሁኝም ብታረዝ አላለበሳችሁኝም … እነርሱም ደግሞ መልሰው ጌታ ሆይ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ  ታመህ ወይስ ታርዘህ  መቼ አይተንህ አላገለገልንህም? ይሉታል። ያን ጊዜ እውነት እላችኋለሁ ከሁሉ  ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ አለማድረጋችሁ ለእኔ ደግሞ አለማድረጋችሁ ነው›› ብሎ ይመልስላቸዋል። ከዚያም ኃጥኣን ወደ ዘለዓለም ቅጣት ጻድቃን ግን ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሄዳሉ። ማቴ.፳፭፥፴፩-፵፮ ከዚህ በኋላ የሁሉም ፍጻሜ ይሆናል መንግሥተ ሰማያት ለጻድቃን ገሃነመ እሳት ለኃጥአን ይሰጣቸዋል እንደየሥራቸው ያገኛሉ። ‹‹እነሆ በቶሎ እመጣለሁ ለእያንዳንዱ እንደየሥራው መጠን እከፍለው ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ›› እንዲል። ራእ. ፳፪፥፲፪

በአጠቃላይ የነገረ ምጽአት ጉዳይ ከላይ በሰፊው በተገለጸው መንገድ እንደሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። የመምጫው ጊዜ እንደቀረበ የሚያስታውሱ ምልክቶችን ተነገረን እንጂ ሰዓቷን በትክክል አልተነገረንም። በዚህ ፈንታ ግን ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ተብለናል። ስለዚህ ዋጋን ለመቀበል በቅዱስ ኑሮ ለመኖር መቸኮል ያስፈልጋል ''የእግዚአብሔርን የመምጣት ቀን ተስፋ እያደረጋችሁ በተቀደሰ ኑሮ ለመኖር ቸኩሉ'' ተብለናልና በሃይማኖት ጸንተን መልካም ሥራ ሠርተን እግዚአብሔር አምላካችን በክብር በመጣ ጊዜ በቀኙ ከሚቆሙት እድል ፈንታችንን ጽዋዕ ተረታችንን ያደርግልን ዘንድ መልካም ፈቃዱ ይሁንልን አሜን።   

 

Read 2135 times