Friday, 06 November 2020 00:00

ወለርሑቃን ፈውሰ ወጥዕምተ ገብራ “ሰቈቃወ ድንግል”

Written by  ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን

Overview

የቃሉ ተናጋሪ አባ ጽጌ ድንግል ነው። ቃሉን የተናገረውም የቅድስት ድንግል ማርያምን ስደቷን፣ በስደቷ ጊዜም የደረሰባትን መከራና ኃዘን አምልቶና አስፍቶ በገለጸበትና በኅቱም ድንግልና ፀንሳ በኅቱም ድንግልና አምላክን የወለደች ድንግል ማርያምንም ባመሰገነበት ክፍሉ ነው። ሙሉ ቃሉን እንደሚከተለው እንመልከተው። “ሰሚዖ ሕፃን ለእሙ ገአራ፤ ባረከ ኰኵሐ ወአንቅዐ ማየ እምታሕተ እግራ፤ ወእምኔሁ ለጽምዓ ትስተይ አመራ፤ ከመ ኢይስተይዋ ሰብአ ሀገር ለይእቲ ማይ አምረራ፤ ወለርሑቃን ፈውሰ ወጥዕምተ ገብራ፤  ሕፃኑ የእናቱን ጩኸት (ለቅሶ) ሰምቶ፤ ዐለቱን ባርኮ ከቆመችበት ቦታ ውኃ አፈለቀ፤ ከውኃውም ትጠጣ ዘንድ አመለከታት፤ የዚያች ሀገር ሰዎች እንዳይጠጧት ያችን ምንጭ አመረራት፤ ከሩቅ  ለመጡት ግን መድኃኒት የጣፈጠችም አደረጋት።” (ሰቈቃወ ድንግል) ይህ ኀይለ ቃል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ጋር በተሰደደች ጊዜ የደረሰባትን መከራና ሁሉን የሚችለው አምላክ ወልደ አምላክ የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ካደረጋቸው ተአምራት መካከል አንዱን የሚያስታውሰን ነው። በማቴዎስ ወንጌል ተጽፎ እንደምናነበው ሰብአ ሰገል እጅ መንሻ ይዘው “የተወለደው የአይሁድን ንጉሥ የት አለ” እያሉ ሲመጡ በዘመኑ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስ በቅንዐት ተነሳሳና ሊገድለው ፈለገ። በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ ነገረውና በሌሊት እናቱንና ሕፃኑን ይዞ ወደ ግብፅ ሸሸ። ወንጌላዊው ማቴዎስ ይህን ታሪክ “እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይሻዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ምድረ ገብፅ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ኑር አለው። እርሱም በሌሊት ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ ግብፅ ሄደ።” (ማቴ.፪፥፲፫-፲፬) በማለት እንደጻፈው ሁሉን የሚችል ፣ ሁሉ የእርሱ የሆነ አምላክ ጠላት ተነሣበትና ስደተኛ ሆነ።  ሰው ከሀገሩ ወጥቶ ስደተኛ ሲሆን ስንቁ ያልቃል፤ ይራባል፤ ይጠማል፤ የሚሰጠው ሊያገኝም ላያገኝም ይችላል። መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስም በሄሮድስ ላይ አድሮ በጠላትነት እንዲነሣሣ ያደረገ ሰይጣን በሰዎች ላይ እያደረ የሚያዝንላቸው አጥተው ስለነበረ ተራበ፤ ተጠማ፣ ዐለት ሰንጥቆ ውኃ አፍልቆ የሚያጠጣው አምላክ በተዋሐደው ሥጋ ተጠማና አለቀሰ። የልጇን ልቅሶ ስትሰማ እናቱም ምርር ብላ አለቀሰች። ሁሉን የሚችል አምላክ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ቢወሰንም አምላክ ወልደ አምላክ መሆኑን ሲያስረዳ፣ ዐለቱን ባርኮ ውኃ አፈለቀ።  ማፍለቁ ብቻ ሳይሆን ያፈለቀው ውኃ ለስደተኞች የሚጥምና የሚጣፍጥ በአካባቢው ላሉትና በክፋት ለተሞሉት ሰዎች ደግሞ የሚመር ሁለት ዓይነተ ጣዕም ያለው ውኃ ሆነ። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ይህን ምሥጢር የገለጸለት ደግ አባት አባ ጽጌ ድንግልም  ከእግዚአብአብሔር ሁሉን ቻይነት አንጻር የማያስደንቅ ቢሆንም ከፍጡራን ባሕርይና ችሎታ አንጻር ግን እንዲህ እጅግ የሚያስደንቀውን ምሥጢር ገለጸልን። ሰዎች እርሱ የሰጣቸውን ውኃ ሲከለክሉት እርሱ ግን ከአንድ ምንጭ ተገኝቶ ለአንዱ ጣፋጭ ለሌላው መራራ የሆነ ተአምረኛ ውኃ አፈለቀ። ይህ እጀግ የሚያስደንቅና ልዩ የሆነ ምሥጢር ያን ጊዜ እንደ አዲስ የተጀመረ ሳይሆን ጥንትም ሀልወቱን፣ መግቦቱን፣ አምላካዊ ጥበቃውን ሲገልጽበት የኖረ፣ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ የሚኖርም ነው። ለማሳያ የሚሆነን ታሪክ እንመለከታለን። እስራኤላውያን በግብፅ ባርነት በከፋ አገዛዝ ሁለት መቶ ዐሥራ አምስት ዓመታት ያህል ኖረዋል። የገዢዎቻቸው ጭካኔ ልኩን ሲያልፍና እነርሱም አብዝተው ሲጮኹ ጩኸታቸውን ሰምቶ በሙሴ አማካኝነት ከግብፅ ምድር አውጥቷቸዋል። በጉዟቸውም ጊዜ መና ከሰማይ እያወረደ ሲመግባቸው፣ ውኃ ከዐለት ላይ እያፈለቀ ሲያጠጣቸው የነበረ መሆኑ የእስራኤልን ታሪክ የጻፈለን ሊቀ ነቢያት ሙሴ መዝግቦት እናገኛለን። በመጽሐፍ ቅዱስም “ሙሴም የእስራኤልን ልጆች ከኤርትራ ባሕር አውጥቶ ወደ ሱር ምድረ በዳ ወሰዳቸው። በምድረ በዳም ሦስት ቀን ተጓዙ፤ ይጠጡም ዘንድ ውኃ አላገኙም። ወደ ማራም በመጡ ጊዜ ከማራም ውኃ ሊጠጡ አልቻሉም፤ ውኃው መራራ ነበርና፤ ስለዚህ የዚያ ስፍራ ስም “መሪር” ተብሎ ተጠራ። ሕዝቡሙ “ምን እንጠጣለን?” ብለው በሙሴ ላይ አንጎራጎሩ። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔርም እንጨትን አሳየው፤ በውኃውም ላይ ጣለው፤ ውኃውም ጣፈጠ። በዚያም ሥርዐትንና ፍርድን አደረገላቸው፤ በዚያም ፈተናቸው። እርሱም “አንተ የአምላክህን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ በፊቱም መልካምን ብታደርግ ትእዛዙንም ብታደምጥ ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቅ በግብፀውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና” አለ።” (ዘፀ.፲፭፥፳፪-፳፮) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቦ እንደምናነበው በዚህ ጥቅስም እንደተመለከትነው በወቅቱ መራራ የነበረው ውኃ በሙሴ ጸሎትና ልመና አማካኝነት በእግዚአብሔር ቸርነት ጣፍጦላቸው ጠጥተዋል። በጊዜው መጠጣታቸው ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም የሕይወታቸው መመሪያ የሚሆናቸውን አምላካዊ ቃል በሙሴ አማካኝነት አስተላልፏል። እርሱም “አንተ የአምላክህን ቃል አጥብቀህ ብትሰማ በፊቱም መልካምን ብታደርግ ትእዛዙንም ብታደምጥ ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቅ በግብፀውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም፤ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና” አለ።” እንዲል። እስራኤላውያን ሕጉን ጠብቀው፣ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው፣ እንደሥርዓቱ ቢጓዙ በግብፅ ላይ የወረደው መቅሰፍት እንደማይደርስባቸው እንደተነገራቸው ሁሉ ዛሬም በሃይማኖት ጸንተን በጎ ምግባር እየሠራን የተፈቀደልንን እያደረግን ያልተፈቀደልንን እየተውን ብንኖር አምላካዊ ጥበቃው ሳይለየን እንደምንኖር ያስረዳናል።  በወቅቱ መራራ የነበረውን ውኃ አጣፍጦ እንዳጠጣቸው ሁሉ በሙሴ ጸሎት በእግዚአብሔር ቸርነት ለእስራኤል ከዐለት ላይ ውኃ ፈልቆላቸው ጠጥተዋል። (ዘፀ.፲፯፥፩-፯) እግዚአብሔር ያለውን ማጣፈጥ ብቻ ሳይሆን ከሌለበት ማምጣትና መስጠትም እንደሚችል እንረዳለን። የእግዚአብሔር ቸርነት ካልተከተለን በቀር ከዐለት ላይ ውኃ ማፍለቅ አይቻለንም። እርሱ ግን የማንም ረዳት ሳያስፈልገው ከዐለት ላይ ውኃ ማፍለቅ ይቻለዋል። የኤርትራን ባሕር ከፍሎ እስራኤላውያንን ማሻገር፣ ግብፃውያንን ደግሞ በባሕር ተሰጥመው እንዲቀሩ ማድረግ ችሏል። አሁንም ሁሉን ማድረግ ይችላል። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ዕብን ዘመነንዋ ነደቅት ወይእቲ ኮነት ውስተ ርእሰ ማዕዘንት፤ ግንበኞች የናቋት ድንጋይ እርሷ የማዕዘን ራስ ሆነች።” (መዝ.፻፲፯፥፳፪) በማለት የተናገረውን መተርጉማኑ የተናቀች ደንጊያ የተባለችው ዕብነ ሙሴ እንደሆነች አስረድተዋል። ይቺ ዕብነ ሙሴ  ዐሥራ ሁለት ምንጭ ያላት ለዐሥራ ሁለቱም ነገደ እስራኤል እያፈለቀች የምታጠጣ፣ በፊት በኋላ በቀኝ በግራ ሁና ከለላ የምትሆን፣ ጠላት ሲመጣ ረግረግ እየሆነች የምታሰጥም፣ ቀን እንደደመና እየሆነች ከቀን ሐሩር የምትከላከልላቸው፣ ሌሊት የብርሃን ዐምድ እየሆነች የምትመራቸው እንደነበረች በትርጓሜ አስረድተዋል። (መዝ.፻፲፯፥፳፪ አንድምታ ትርጓሜ) ለእስራኤል የተደረገውን ድንቅ ተአምር ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “ሁሉም ያን መንፈሳዊ ምግብ ተመገቡ። ሁሉም ያን መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይኸውም በኋላቸው ከሚሄደው ከመንፈሳዊ ዐለት የጠጡት ነው፤ ያም ዐለት ክርስቶስ ነበረ።” (፩ቆሮ.፲፥፫-፬) በማለት ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከው መልእክቱ አስረድቷል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይከተላቸው የነበረ መንፈሳዊ ዐለት በማለት የገለጸውን ይህም ዐለት ክርስቶስ ነበረ በማለት ተርጕሞታል።  ሁሉን የሚችለው አምላክ ዐለቱን የውኃ መፍለቂያ ምንጭ አድርጎ የተጠማውን ያጠጣበታል፤ የተራበውን ኅብስተ መና አድርጎ ይመግብበታል፤ ለጠላት መከላከያ መሣሪያም ያደርገዋል። ይሁን እንጂ መለስ ብለን በታሪክ እንደምናስታውሰው ይህ ሁሉ የቸርነት ሥራ ለክፉዎች  አይመችም ነበር። አንዲ ሲድንበት ሌላው ሲጠፋበት ኖሯል። በስደቱ ወቅት ያደረገው ተአምርም የሚያስረዳን እንዲህ ያለውን ጉዳይ ነው። ዛሬም ለአንዱ መራራ ለሌው ጣፋጭ የሚሆን ብዙ ነገር አለ። በእርግጥ መራራም ሆነ ጣፋጭ የሚሆነው ተቀባዩ ለዚያ ነገር ከመብቃትና ካለመብቃት፣ ወዶ ፈቅዶ ከመቀበልና ካለመቀበል፣ ለሚሰጠው ነገር አስፈላጊውን ዝግጅት ከማድረግና ካለማድረግ ወዘተ የሚመጣ ነው እንጂ ስጦታው በተፈጥሮው መራራ ሆኖ አይደለም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ክፉ ነገር አይሰጥም። ሰዎች ግን በአጠቃቀም ስሕተት በመድኃኒቱም ይሞቱበታል። ይህን በተመለከተ የተወሰኑትን እንጥቀስ፡- ፩. የእግዚአብሔር ቃል ከላይ እነምደተገለጸው የእግዚአብሔር ቃል የሚመር ሆኖ አይደለም። ከአቀባበል መለያየት የተነሣ ግን የመረራቸው፣ አሁንም የሚመራቸው አሉ፤ ወደፊትም ይኖራሉ። የጣፈጣቸውም ነበሩ፤ ዛሬም አሉ ወደፊትም ይኖራሉ። የሚጣፍጣቸውንም ሆነ የሚመራቸውን እንመልከት። ሀ. የሚጣፍጣቸው ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ጥዑም ለጕርዔየ ነቢብከ እምዓር ወሦከር ጥዕመኒ ለአፉየ፤ ቃልህ ለጕረሮዬ ጣፋጭ ነው፤ ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ” (መዝ.፻፲፯፥፻፫) በማለት እንደገለጸው የእግዚአብሔር ቃል የሚጣፍጥ ለሕይወትም መሠረት ነው። ለዚህም ነው “ቃልህ ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው” ካለ በኋላ በምድር ላይ ጣፋጭ ከሚባለው “ከማርና ከወለላ ይልቅ ጣፈጠኝ” በማለት እኛ ልንረዳውና ልንገነዘበው በምንችለው አገላለጽ ነገረን። የቃሉን ጣፋጭነትና መድኃኒትነት የተረዳው የመቶ አለቃው “በቃልህ እዘዝ፤  ልጄም ይድናል” (ማቴ.፰፥፰) በማለት ፍጹም የሆነ ሃይማኖቱን ገለጠ። መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ጊዜም ቃሉ የሚጣፍጣቸው በርካታ ሰዎች ነበሩ። በቅዱስ ወንጌል “በየምኵራቦቻቸውም ሁሉ ያስተምራቸው ነበር፤ ትምህርቱንም ያደንቁ ነበር፤ ሁሉም ያመሰግኑት ነበር።” (ሉቃ.፬፥፲፭) ተብሎ ተጽፎ እናነባለን። እንዲሁም በቅዱስ ወንጌል “ወደ ገሊላ ከተማም ወደ ቅፍርናሆምም ወረደ፤ በሰንበትም ያስተምራቸው ነበር። አነጋገሩም በትእዛዝ ነበርና ትምህርቱን ያደንቁ በር።” (ሉቃ.፬፥፴፩) ተብሎ ተጽፎ እናገኛለን። ይህ ሁሉ የሚያስረዳን ቃሉን በደስታ የተቀበሉት እንዳሉ ነው። በመሆኑም “ወለርሑቃን ፈውሰ ወጥዕምተ ገብራ” እንደተባለው ቃሉን ለሚሹት፣ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ፈልገው ሲለምኑት ለኖሩት ለአበው ቀደምት፣ ለነቢያት፣ ለቅዱሳን ጣፋጭ አደረጋት። እንዲሁም ከአሕዛብ ወገን ለሆኑት፣ ከሩቅ ለመጡት፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ላልተባሉት ጣፋጭ አደረጋት።  በሌላ አገላለጽ ትንቢት ለተነገረላቸው ሱባኤ ለተቈጠረላቸው ወገኖቹ ለተባሉት እስራኤላውያን መራራ አደረጋት። ማለት እንዳይቀበሉት ዐይነ ልቡናቸው ታወረ። “ወደ ወገኖቹ መጣ፤ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው። እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ግብር ወይም ከወንድና ከሴት ፈቃድ አልተወለዱም” (ዮሐ.፩፥፲፩-፲፫) እንዲል የተቀበሉት እንዳሉ ሁሉ ያልተቀበሉትም እንደነበሩ ልንገነዘብ ይገባል።  ለ. የሚመራቸው በዚህ አገላለጽ አምነው ባለመቀበላቸው አለመጠቀማቸውንና መጎዳታቸውን ለማስረዳት ነው። በመሆኑም ከአብርሃም ዘር በመወለዳቸው የሚመኩትን አይሁድን “እውነት እውነት እላችኋለሁ የአብርሃም ልጆች ብትሆኑስ የአብርሃምን ሥራ በሠራችሁ ነበር)” (ዮሐ.፰፥፴፱) በማለት መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የወቀሳቸው እውነተኛውን ቃሉን ሲነግራቸው ማመን ባለመቻላቸው ነበር። ቃሉን አምነው ከመቀበል ይልቅ ሊገድሉት ይሹ ነበር። በእውነት መንገድ ለማይጓዝ፣ እውነትን ገንዘብ የማያደርግ አካል ምንጊዜም ቢሆን እውነት ይመረዋል። እውነቱን ስለነገራቸው ስለኃጢአታቸውም ስለዘለፋቸው ጋኔን አድሮበታል ይሉትም ነበር። “አይሁድም አንተ ሳምራዊ እንደሆንህ ጋኔንም እንዳለብህ መናገራችን በሚገባ አይደለምን? ብለው ጠየቁት” (ዮሐ.፰፥፵፰) እንዲል።   ቃሉ ሕይወት መድኃኒት ሲሆን በሚገባ ባለመቀበላቸውና የሕይወታቸው መመሪያም ባለማድረጋቸው የተነሣ ተፈርዶባቸዋል። በዕለተ ምጽአትም መፈራረጃ ይሆንባቸዋል። ይህን አስመልክቶ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “አመ ይመጽእ ንጉሥ በግርማ መንግሥት ኵነኔ ድልው ቅድሜሁ ነፍስ ትርእድ ወመጻሕፍት ይትከሠታ ለስምዕ፤ ንጉሡ በግርማ መንግሥት በክበበ ትስብእት በመጣ ጊዜ ፍርዱ በፊቱ ነው፤ ነፍስ ትንቀጠቀጣለች መጻሕፍትም ለምስክርነት ይረቀርባሉ” (ጾመ ድጓ ዘደብረ ዘይት) በማለት ያስረዳናል። ቃሉን ሰምተው አለመጠቀማቸው ለፍርድ ይሆንባቸዋል። ፪.ሥርዐቱ ሕጉን ጠብቀው፣ እንደ ሥርዓቱ ተጉዘው ሰማያዊውን ርስት ለመውረስ ለሚመኙት እግዚአብሔር ያስቀመጠልን ሕግና ሥርዓት የሚመች፣ የሚጥም ነው። ነገር ግን መሠረታዊ ዓላማቸው ይህ ላልሆነው፣ ጽድቁን ቢያስቡም ያለመከራ ለሥጋዊ ምኞታቸው ቅድሚያ በመስጠት ለመጽደቅ ለሚያስቡት ሕጉና ሥርዓቱ ላይመቻቸው ይችላል። ሕግና ሥርዓት ለእውነተኛ ሰው አይጎራብጥም፤ የሚጎራብጠው እውነትን መከተል ለማይፈልግ፣ ከእውነት ጎዳና አፈንግጦ በራሱ ሐሳብና ምኞት ለሚጓዝ ግን አይመችም። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን ነው” (መዝ.፻፲፰፥፻፭) በማለት የገለጸው ለእውነተኞች የእግዚአብሔር ሕግ የሕይወት መሠረት ስለሆነ ነው። በአንጻሩ በሕግ መኖር ለማይፈልግ ግን ይመረዋል፤ ይጠፋበታልም። ፫. መንፈሳዊ ተጋድሎ  ሰው በልዩ ልዩ ምክንያቶች አብሮት ከሚኖረውም ሆነ ከማይኖረው ጋር ይጋጫል፣ ይጋደላል። ለምድራዊ ርስት፣ ለምድራዊ ሀብት ንብረት ብሎ የሚጛደል ይኖራል። ለመንፈሳዊው ርስት ብሎ ደግሞ ከሚታየውም ከማይታየውም ጋር ይጋደላል። ምድራዊውን ርስት ፈጽሞ አያስፈልግም ባይባልም ሰማያዊውንነ ርስት አስቦ የሚታየውን ዓለም በማይታየው ዓለም ለውጦ የሚያደርጉት ተጋድሎ መንፈሳዊ ተጋድሎ ተብሎ ይጠራል። ይህ መንፈሳዊ ተጋድሎ የሚጥማቸውም የማይጥማቸውም  አካላት አሉ።  ሀ.የሚጣፍጣቸው ቅዱሳን አባቶቻችን እውነተኛውንና መንፈሳዊውን ተጋድሎ በተግባር ፈጽመው አሳይተውናል። እየጣፈጣቸውም ተቀብለውት አልፈዋል። በሃይማኖት ጸንተው የሚቀበሉት መከራ ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያስገኝ ክብርን የሚያጎናጽፍ በመሆኑ ይጣፍጣል። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከው መልእክቱ “ስለዚህም ቢሆን  በብዙ ራእይ እንዳልታበይ ሰውነቴን የሚወጋ እርሱም የሚጎስመኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ። ስለዚህም ከእኔ ያርቀው ዘንድ ጌታዬን ሦስት ጊዜ ማለድሁት። እርሱም ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይልስ በደዌ ያልቃል አለኝ፤ የክርስቶስም ኃይል በእኔ ላይ ያድር ዘንድ በመከራዬ ልመካ ወደድሁ። ስለዚህም ስለ ክርስቶስ መከራ መቀበልን፣ መሰደብን፣ መጨነቅን፣ መሰደድን፣ መቸገርንም ወደድሁ፤ መከራ በተቀበልሁ ጊዜ ወዲያውኑ እበረታለሁና። (፪ቆሮ ፲፪፥፰) በማለት በእርሱ ላይ ያደረው ደዌ በፈቃደ እግዚአብሔር እንደሆነና ለምንም እንደተሰጠው ሲናገር በመከራው (በደዌው) ምክንያት የሚያገኘው ጸጋ እንዳለ ያስረዳል። ስለዚህ ጸጋ የሚያስገኝ  መከራ ይጣፍጣል። በሃይማኖት ጸንተን ምግባራችንን አቅንተን እየኖርን የሚመጣብን ቅጣት ክብር የሚያሰጥ ነው። ሐዋርያው ያዕቆብ “በመከራ የሚታገሥ ሰው ብፁዕ ነው፤ ተፈትኖ እግዚአብሔር ለሚወዱት ተስፋ ያደረገላቸውን የሕይወት አክሊል ይቀበላልና።” (ያዕ.፩፥፲፪) በማለት እንዳስተማረን መከራችን፣ ተጋድሏችን ሰማያዊ ክብርን የሚያሰጥ፣ ዘለዓለማዊ ደስታን የሚያጎናጽፍ ነው። ስለዚህ እንደዚህ ያለውን ተጋድሎ ባንጋደል ሰማያዊው ክብር ይቀርብናል። ይህ መንፈሳዊ ተጋድሎ  የማያልፈውን፣ የማይጠፋውን፣ ዘለዓለማዊ ክብር የሚያሰጠን ስለሆነ በዚህ መንፈሳዊ ተጋድሎ አለመጽናታችን የምናስበውንና የምንመኘውን ክብር እንዳናገኝ ያደርገናል። ሊቁ ቅዱስ ያሬድ “ሞዕዎ ለእኩይ ኅሊና በእምነቶሙ እስመ ሠናየ ገድለ ተጋደሉ፤ መልካሙን ገድል ተጋድለዋልና በእምነታቸው ክፉውን ሐሳብ ድል አደረጉት” በማለት እንደገለጸው ይህ መንፈሳዊ ተጋድሎ ክፉውን ሐሳብ ድል የምናደርግበት ነውና እጅግ ይጥማል። ቅዱሳኑም ሰማያዊውን ዓለም እያሰቡ ተጋድሎውን ሳይሳቀቁት ይልቁንም እየጣፈጣቸውና እየተመቻቸው መከራውን በመቀበላቸውም እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ተግባራዊ ክርስትናን አሳይተውናል። ለ.የሚመራቸው፡- ከላይ የተገለጸው መንፈሳዊ ተጋድሎ ለእነ ቅዱስ ጳውሎስ እንደጣማቸው ለነዴማስ አልጣማቸውም። እነ ቅዱስ ጳውሎስ “አማን መነኑ ሰማዕት ጣዕማ ለዛ ዓለም ወከዐዉ ደሞሙ በእንተ እግዚአብሔር ወተዐገሡ ሞተ መሪረ በእንተ መንግሥተ ሰማያት፤ ሰማዕታት በእውነት የዚችን ዓለም ጣዕም ናቁ ስለ እግዚአብሔር ደማቸውን  አፈሰሱ፣ ስለመንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሡ” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) እንደተባለው በመከራው ሲደሰቱ እነዴማስ ግን እንዲህ ዓይነቱን ሕይወት ሳይሆን የተሰሎንቄን ከተማ መረጡ። ስለዚህ በመልካም ተጋድሎ መንግሥተ ሰማያትን መውረስ መቻልን፣ ወይም መንፈሳዊውን ተጋድሎ በጸጋ መቀበልንና በሕይወት መተርጎምን ከሩቅ ለመጡት ጣፋጭ ለቅርብ ሰዎች ግን መራራ አደረገው ማለት በተጋድሎ ሰማያዊውን ዓለም እንደሚወርሱ የተሰበከላቸው የእግዚአብሔር ሕዝቦች የተባሉት እስራኤል ጸንተው መቀበል ሲያቅታቸው ከአሕዛብ ወገን የነበሩት ግን አምነው መልካሙን ተጋድሎ ተጋድለው ይህ ዓይነት ሕይወትም ጣፍጧቸው እንደተጠቀሙበት ለመግለጽ ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ስብከቱ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ቀራጮችና አመንዝሮች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሟችኋል” (ማቴ.፳፩፥፴፩) በማለት የተናገረው ትንቢቱ የተነገረላቸው ሱባኤው የተቈጠረላቸው አምነው መቀበል ሲቸገሩ ትንቢት ያልተነገረላቸው ሱባዔ ያልተቈጠረላቸው አሕዛብ አምነው በመቀበላቸው ለክብር መብቃታቸውን ያስረዳናል። ፬. ንስሓው ንስሓ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚታረቅበት፣ ከቅዱሳን ኅብረት አንድ የሚሆንበት ታላቅ ስጦታ ነው። የመልካም አባት ስጦታ፣ የፍቅር ስጦታ እየተባለም በሊቃውንት ዘንድ ይነገራል። ይህን ታላቅ ስጦታ ተረድተውት ለሚጠቀሙበት የሚጣፍጥ ነው። ለማይጠቀሙበት ግን ፍርድን ያስከትላል። ኃጢአታቸውን እያሰቡ ያለቀሱት፣ ዘመናቸውን በአግባቡ የተጠቀሙትን ለምሳሌ ብንጠቅስ አዳም፣ ዳዊት፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ በቀኝ የተሰቀለው ሽፍታ እናገኛለን። ይሁን እንጂ የንስሓ ዕድሜ ተሰጥቷቸው ያልተጠቀሙበት ደግሞ እንደ ይሁዳና ሌሎችም የይሁዳን መንገድ የተከተሉትን መጥቀስ ይቻላል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃሉን አምነው ባለመቀበላቸውና ንስሓም ባለመግባታቸው እንዲህ ይወቅሳቸው ነበር። “ኮራዚ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ ወዮልሽ በእናንተ የተደረገ አምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው አስቀድመው ንስሓ በገቡ ነበር። ነገር ግን እላችኋለሁ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ጢሮስና ሲዶና ዕረፍትን ያገኛሉ። ቅፍርናሆም አንቺም እስከ ሰማይ ከፍ ከፍ ብትዪ እስከ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺም የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን እስከ ዛሬ በኖረች ነበር። ነገር ግን እልሻለሁ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ የሰዶም ምድር ዕረፍትን ታገኛለች።” (ማቴ.፲፩፥፳፩-፳፬)  ይህ ኀይለ ምንባብ የሚያስረደሳን መድኅነ ዓለም ክርስቶስ በአካል ተገልጦ ቢያስተምራቸው አንመለስም ብለው የንስሓ ሕይወትን ገንዘብ አለማድረጋቸውን ነው። አባ ጽጌ ድንግም “ለሀገሩ ሰዎች መራራ አደረጋት” ብሎ የገለጸው እንዲህ ያለውን በቅርብ የተገኘ ጸጋ በአግባቡ አለመጠቀምን ሲያስረዳን ነው። ፭. ሥጋ ወደሙ በሰው ልጅ ሕይወት የሚገድልም የሚያድንም ምግብ አለ። አዳም ከአንዲት ዕፀ በለስ በቀር በገነት ያለው ሁሉ ሲፈቀድለት ዕፀ በለስን ግን ተከልክሏል። የተፈቀደለት ነገር በሕይወት እንዲኖር የሚያስችለው ሲሆን የተከለከለው ግን ሞትን የሚያመጣበት ነበር። የተፈቀደለት ነገርና የተከለከለው ዕፀ በለስ እንዳለ ሆኖ ብላም አትብላም የሚል ትእዛዝ ያልተላለፈበት ዕፀ ሕይወትም ነበረ። አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስን ሲበላ ሞት ተፈረደበትና ዕፀ ሕይወትን ተከለከለ። “አሁንም እጁን እንዳይዘረጋ ደግሞም ከሕይወት ዛፍ ወስዶ እንዳይበላ ለዘለዓለምም ሕያው ሆኖ እንዳይኖር ስለዚህ የተገኘባትን መሬት ያርስ ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ደስታ ከሚገኝባት ገነት አስወጣው” (ዘፍ.፫፥፳፪-፳፫) እንዲል። አዳም አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስን በመብላቱ ዕፀ ሕይወትን ተከለከለው። በአዳም ሕይወት ዕፀ በለስ የሚገድል ዕፀ ሕይወት ደግሞ ዘለዓለማዊ ሕይወትን የሚያስገኝ ነበር። በሐዲስ ኪዳን ላለን ምእመናን በዕፀ ሕይወት ፈንታ የታደለን ሥጋ ወደሙ ነው። ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችን ቅድስት ማርያምን ባመሰገነበት በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ “ ከፈለነ ንብላዕ እም ዕፀ ሕይወት ዘውእቱ ሥጋሁ ለክርስቶስ ወደሙ ክቡር በእንተ ፍቅረ ዚአነ፤ ከሕይወት እንጨት እንበላ ዘንድ አደለን ይኸውም ሰውን ስለመውደዱ ያደለን ሥውና ደሙ ነው” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) በማለት እንደገለጸው ሕይወትን የሚሰጠን ዘለዓለማዊ ሕይወትን ገንዘብ አድርገን እንድንኖር የተሰጠን ሥጋውና ደሙ ነው።  የተለያዩ ነገሮች የተለያየ ጠባይና ተፈጥሮ መኖራቸው ላያስደንቅ ይችላል። ዕፀ በለስና ዕፀ ሕይወት የሞትና የሕይወት እንጨት መሆናቸው ብዙ ላይገርመን ይችላል። ነገር ግን አንዱ ዕፀ ሕይወት ለአንዱ ሕይወትን የሚያድል ለሌላው ደግሞ ሞትን የሚያመጣ መሆኑ የረቀቀ ምሥጢር። ሥጋ ወደሙ ሕይወትን የሚያድላቸው እንዳሉ ሁሉ  ሞትን የሚያመጣባቸው ወገኖች አሉ። እነርሱ እንማን ናቸው? የሚለውን እንመለከታለን። ሀ. የሚጣፍጣቸው፡- ፈቅደውና ወደው ንስሓ ገብተው የሚችሉትን ዝግጅት አድርገው ለሚቀበሉት ሕይወት መድኃኒት ነው። ሊቁ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው “እሳት ማሕየዊ ለርቱዓነ ልብ ለእለ ይገብሩ ፈቃዶ፤ ፈቃዱን ለሚፈጽሙ የሚያድን እሳት ነው” (ቅዳሴ ማርያም) በማለት እንደገለጸው በእግዚአብሔር ፈቃድ ለሚመላለሱት እንድንበታለን ብለው አምነው ለሚቀበሉት ሕይወት መድኃኒት ነው። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውንና ደሙን አስፈላጊ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን ያለዚያ ሰማያዊ መንግሥትን መውረስ እንደማይቻልም አስተምሮናል። “እውነት እውነት እላችኋለሁ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ የዘለዓለም ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው፤ እኔም በኋለኛይቱ ቀን አነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛመጠጥ ነውና” (ዮሐ.፮፥፶፫-፶፭) ለ. የሚመራቸው ሥጋዬን ብሉ ደሜን ጠጡ ብሎ ሲያስተምር በእምነት መቀበል የተቸገሩት አይሁድ “ይህ እንበላ ዘንድ ሥጋውን ሊሰጠን እንዴት ይችላል? ብለው እርስ በእርሳቸው ተከራከሩ” (ዮሐ.፮፥፶፪) በእርግጥም አምነው ለማይቀበሉት፣ ሳይገባቸው ለሚቀበሉት የማይቻል ነው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከላቸው መልእክቱ “አሁንም ሳይገባው ይህን ኅብስት የበላ ይህንም ጽዋ የጠጣ የጌታችን ሥጋውና ደሙ ስለሆነ ዕዳ አለበት” (፩ቆሮ.፲፫፥፳፯) በማለት ሳያምኑበትና ያድነኛል ሳይሉ ንስሓም ሳይገቡ ለሚቀበሉት ዕዳ እንደሚሆናቸው፣ እንደማይመቻቸው ያስረዳል። ሊቁ አባ ሕርያቆስም መድኃኒትነቱን ብቻ ሳይሆን የሚያጠፋ መሆኑንም  “እሳት በላዒ ለአማጽያን ለእለ ይክህዱ ስሞ” ስሙን ለሚክዱት ለአመጸኞች የሚባላ እሳት ነው። በማለት ከማን አንሼ ብለው፣ እገሌ ሲቈርብ አየን ብለው የሚቀበሉት እንዳልሆነ በእንደዚህ ያለ ሁኔታ ላይ ሆነው ቢቀበሉት ደግሞ መፈራረጃ እንደሚሆን አስረድቷል። በአጠቃላይ በማይመረመር ጥበቡና በልዩ ፍቅሩ የፈጠረን እግዚአብሔር አምላካችን የሚሰጠን ሁሉ መልካም ነው። ይሁን እንጂ የተሰጠንን ነገር በአግባቡ ባለመጠቀማችን ስንጎዳበት እንስተዋላለን። አንዳንዶቹ በቤቱ እየኖሩ፣ በክህነት አገልግሎት እየተመላለሱ፣ ግን ለቤቱ የሚገባና የሚመች አገልግሎት ባለመፈጸማቸው ሲጠፉበት ይስተዋላሉ። በአንጻሩ ደግሞ ከውጭ ሆነው እግዚአብሔርን በመፍራትና በመንቀጥቀጥ የሚኖሩ ግን ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው መንፈሳዊ ማንነታቸው የማይገለጥ በርካታ ሰዎች አሉ። ለዚህ ነው “ከሩቅ ለመጡት የሚጣፍጥ ለሀገሩ ሰዎች ደግሞ መራራ አደረጋት” በማለት አባ ጽጌ ድንግል የገለጸልን። በቤቱ ኖረን ለቤቱም የሚገባውን ክብር በመስጠት አገልግሎታችንን ፈጽመን ሰማያዊውን ዓለም እንዲያወርሰን እግዚአብሔር ይፍቀድልን አሜን። 
Read 748 times