በክብር ወደ እኔ አቀርባለሁ ማለቱ ደግሞ በተዋሐደው የአዳም ሥጋ ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ ሞትንም ድል አድርጎ በመነሣት በዚያው ሥጋ ወደ ሰማይ ዐርጎ በአባቱ ቀኝ ይቀመጣልና። የሰው ሥጋ በአብ ቀኝ የመቀመጥን ክብር የሚያገኝ መሆኑን ሲያጠይቅ ይህን ተናግሯል። “እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል” እንዲል። (ፊል.፫፥፳፩) በሌላ በኩል የአዳምን ዕዳና በደል በመስቀል ላይ በከፈለው የደም ካሳ ከደመሰሰ በኋላ በቀኙ ለተሰቀለው ሽፍታ “ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” እንዳለው፡- የሰው ልጅ ሁሉ ከዲያብሎስ ተገዥነትና ከሲኦል ባርነት ነፃ ወጥቶ በክብር ከፍ ከፍ እንዲል አደርጋለሁ ሲለን ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ አለ። (ሉቃ.፳፫፥፵፫) እንዲሁም ጌታ በመስቀል ካሳ እስከከፈለበት ጊዜ ድረስ የዲያብሎስ ባሪያዎች ተብለን እንጠራ የነበርን የሰው ልጆች ሁሉ ከካሳ በኋላ በክርስቶስ ስም ክርስቲያን በወልድ ስም ውሉደ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ ስም መንፈሳውያን ተብለን እንድንጠራ አድርጎናልና ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ አለ።
ለመሆኑ ክርስቶስ ሁሉን ወደ ራሱ የሳበበት ምሥጢር ምንድን ነው
ዕርቅን በማድረግ፡-
ጥል ባለባቸው ሁለት ሰዎች መካከል ሰላም ሲሆን ዕርቅ ሆነ ይባላል። የሰው ልጅም በአዳም ኃጢአት ምክንያት ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልቶ ለ፶፻፭፻ ዘመናት መኖሩ ይታወቃል። ሰው ከእግዚአብሔር በመጣላቱም ምክንያት፣ ሰውና መላእክት፣ ሕዝብና አሕዛብ፣ ነፍስና ሥጋ ተጣልተው ለዘመናት ኖረዋል። እነዚህ ሁሉ የታረቁት በወልደ እግዚአብሔር ሰው መሆን ነው።
እንደሚታወቀው የሰው ልጅ በነፍስም በሥጋም ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልቶ ነበር። እግዚአብሔር ግን የሰውን ነፍስና ሥጋ ከመለኮቱ ጋር አዋሐዶ ፍጹም ሰው ሆነ፤ ሥጋንም ፍጹም አምላክ አደረገው። በዚህም ዕርቀ ሰላም ሆነ። መቼም አንድ አካል ከራሱ ጋር ተጣላ እንዳይባል ሁሉ መለኮትም ከነፍስና ሥጋ ጋር ተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ሆኗልና ፍጹም ዕርቅ ሆኗል። አካል ከአካል ከተዋሐደ ባሕርይ ከባሕርይ አንድ ከሆነ ጠብ ክርክር ጥላቻና አለመስማማት አይኖርምና። ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም የክርስቶስን የማስታረቅ ሥራ የምታስተምረው በዚህ መንገድ ነው እንጂ “ክርስቶስ እርሱ ሦስተኛ ሆኖ ሌሎች ሁለት ወገኖችን አስታረቀ” ብላ አታስተምርም። ክርስቶስን ሰው ያሰኘውን የአዳምን ሥጋ፣ ሞትና መቃብር፣ መከራና ሥቃይ የተፈረደበትን የአዳምን ሥጋ “አዳም ሆይ ስለ ጥፋትህ ሞት ይገባሃል” ብሎ ከፈረደው መለኮትነቱ /እግዚአብሔርነቱ/ ጋር ማስታረቁን /መዋሐዱን/ ታስተምራለች እንጂ። ክርስቶስ የሚለውም ስም አምላክም ሰውም መሆኑን ይገልጽልናልና። ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው በሁለተኛው መልእክቱ ላይ ይህን ሲያብራራው “እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበር” ብሎ ጽፎልናል። (፪ኛ ቆሮ.፭፥፲፰-፳)
ክርስቶስ የሚለው እግዚአብሔር ወልድ ሥጋ አዳምን ከተዋሐደ በኋላ የተሰጠው ስም ነው። በሌላ አባባል እግዚአብሔር የሚለው ስም ውስጥ ክርስቶስም አለበት። እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ አስታረቀ ማለትም እግዚአብሔር በክርስቶስነቱ ከዓለም ጋር ታረቀ ማለት ነው። አንድም እግዚአብሔር ክርስቶስ ተብሎ ራሱ ከዓለም ጋር ታረቀ ማለት ነው።
ክርስቶስ ዓለምን ከራሱ ጋር ያስታረቀው ራሱ መሥዋዕት አቅራቢ /ካህን/ ራሱም መሥዋዕት /የመሥዋዕት በግ/ ራሱም መሥዋዕት ተቀባይ ምሕረት አድራጊ /ይቅርታ አድራጊ/ ሆኖ ነው እንጂ እንደ አማላጅ ሥርዓት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ሦስተኛ አካል ሆኖ መባና መሥዋዕት ይዞ በመቅረብ አይደለም። ይህም የተፈጸመው በዕለተ ዓርብ ከምድር ከፍ ከሰማይ ዝቅ ብሎ በተሰቀለ ጊዜ ነው። በዚህ አሕዛብን ወደ ራሱ ስቦ አቅርቧቸዋል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን እውነት ሲነግረን “እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፣ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና። እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ፣ በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በሐሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ” ብሏል። (ቆላ.፩፥፲፱-፳፪)
ፍቅሩን በመግለጥ
ፍቅሩን ገለጠ ስንል ሁለት ነገር ማለታችን ነው። አንደኛ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር መግለጥ ማለታችን ነው። ይህን ሲያስረዳ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “... ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና ይህም እግዚአብሔር ስለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል” ብሏል። (ሮሜ ፭፥፰) ሁለተኛው ደግሞ የፍቅርን ምንነት በተግባር በማሳየት ነው።
ከክርስቶስ መገለጥ በፊት ሕዝቡ የሚያመልኳቸው ብዙ ጣዖታት ነበሩ። በርግጥ ዛሬም አሉ። እነዚህ ጣዖታት የማይናገሩ፣ ክፉም ሆነ ደግን ማድረግ የማይችሉ፣ የማያዩ፣ የማይሰሙ፣ የማይንቀሳቀሱ የሰው እጅ ሥራዎች ሲሆኑ የጣዖታቱ ሠሪዎችና አስመላኪዎች የሆኑት ካህናተ ጣዖትና ዐላውያን ነገሥታት ግን ጣዖታቱ እንደ ተናገሩና ውሳኔ እንዳስተላለፉባቸው አድርገው ተከታዮቻቸውን በብዙ ያስጨነቋቸው ነበር። ገንዘባቸውን ሁሉ እንዲያመጡ፣ ከብቶቻቸውን ሁሉ እንዲሠው፣ ልጆቻቸውን ጭምር ለጣዖታቸው መሥዋዕት አድርገው እንዲያቀርቡ ያደርጉ ነበር። እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክና ወዳጅ መሆኑን፣ በምእመናን ሞትና መከራ የሚደሰትና አማኞች ልጆቻቸውን፣ ከብቶቻቸውን እንዲሠውለት ከመጠየቅ ይልቅ አንድያ ልጁን አሳልፎ በመስጠት በእርሱ ሞትና ትንሣኤ ዓለምን የሚያድን አምላክ መሆኑን በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ተረድተናል። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ይህን እውነት ሲናገር “የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና።” ካለ በኋላ “ፍቅር እንደዚህ ነው እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስረያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደወደድነው አይደለም” በማለት ጽፎልናል። (፩ኛ ዮሐ.፬፥፯-፲፩)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ፍጹም ፍቅር ሲናገር “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም” ብሏል። (ዮሐ.፲፭፥፲፫) በእውነቱ ለወዳጁ እንኳንስ ነፍሱን ገንዘቡን በደስታ የሚለግስ ማን ነው። ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው ደግሞ ጠላቶቹ ነበርን እንጂ ወዳጆቹም አልነበርንም። “ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ታረቅን” እንዲል። (ሮሜ ፭፥፲) እንግዲህ ከዚህ ፍቅር በላይ ስቦ የሚያቀርበን ኃይል ምን ሊሆን ይችላል? ነፍሱን ከመስጠትስ በላይ የፍቅርን ጥልቀት የሚገልጽ ምን ይገኛል?
የጥበበኞችን ጥበብ ከንቱ በማድረግ
ለሰው ልጅ ሲል ለዓለም ጥበበኞች ተገርፎ፣ ተገፎ፣ ምራቅ ተተፍቶበት፣ በጥፊ ተመትቶ፣ የአይሁድ ንጉሥ ሆይ ራስህን አድን እኛም አይተን እንመንብህ ተብሎ ተዘብቶበት፣ ተሰቅሎ የሞተውን አምላካችን ነው ብሎ መቀበል በዓለም ጥበበኞች ዘንድ ሞኝነት ነው። እኛን ክርስቲያኖችን ልዩ ከሚያድርጉንም ነገሮች አንዱ የምናመልከው ጌታ ስለ እኛ መሰቀሉንና መሞቱን ያለፍርሃት መመስከራችን ነው። ሌሎች ቤተ እምነቶች ግን ስለ አምላካቸው፣ ኃያልነት፣ ሁሉን ቻይነት፣… እንጂ ስለ ሞቱም ሆነ ስለመከራው ማውራት አይፈልጉም። እኛ የምናመልከው ጌታ ግን፣ በአምላካዊ ሥልጣኑና ኃይሉ የሚገዳደሩትን ጠላቶቹን ከመደምሰስ ይልቅ ተሸንፎ በፍቅር ማሸነፍን፣ ወዷል። ወዳጆቹ በፍቅር እንዲያክብሩትና እንዲያመሰግኑት መፍቀድ ብቻም ሳይሆን ጠላቶቹም በሰውነቱ የወደዱትን እንዲያደርጉበት የፈቀደ፣ ጠላቶችንም ከወዳጆቹ እኩል አድርጎ የወደደ ጌታ ነው ያለን። ይህን የመሰለ ጥበብ በዓለም ዘንድ የለም። ጥበበኞች ነን ለሚሉንም ይህን እውነታ ብንነግራቸው ሞኞች ይሉን ሆናል እንጂ አይረዱንም።
የዓለም ጥበበኞች የሚያምኑት የሚገዳደሯቸውን ጠላቶቻቸውን፣ ከፊታቸው ዞር እንዲሉ በማድረግ ነው። በተለይም ስሕተታቸውን እየነገረባቸው የሚያስጨንቃቸውን ገዳይ እየቀጠሩ ከምድረ ገጽ ያጠፉታል። ቢነቃባቸው ደግሞ ጠበቃ ቀጥረው ይከራከራሉ፤ ዳኛን በጉቦ እየደለሉ፣ ለሐሰት ምስክሮች ገንዘብ እየከፈሉ ንጹሕነታቸውን ያውጃሉ፤ ከኅሊና ክስ ግን አምልጠው አያውቁም። ክርስቶስ ግን ሁሉን ቻይ አምላክ ሆኖ ሳለ አንዳችም ጥፋት ሳይኖርበት፣ ከአንደበቱ ቃል ሳይወጣ፣ እጆቹንም ዘርግቶ ሳይመታ ጠላቶቹን ማጥፋት እየቻለ ያለጥፋቱ ለሚከሱት “ንጹሕ ነኝ” ብሎ ስለራሱ መከራከርን እንኳን አልወደደም። የጠላቶቹን ፈቃድ ፈጸመላቸው እንጂ፤ በሰውነቱም የወደዱትን እንዲያድርጉ ፈቀደላቸው። ጠላቶቹ የወደዱትን በማድረጋቸው ረኩ፤ ወዳጆቹ ደግሞ በሞቱ የዘለዓለም ሕይወትን አገኙ። ጠላቶቹን ከመግደል ይልቅ እንደ ጠላቶቹ ፈቃድ በመሞት ለዓለም ሁሉ ሕይወትን ከመሆን በላይ ጥበብ የት ይገኝ ይሆን? በዚህም በማስፈራራትና በመግደል የሚገዙትን የዓለም ነገሥታትን ጥበብ ከንቱነትን አሳየ፤ ስለ በጎቹ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ እረኛ መሆኑንም በማስመስከሩ በጎቹን ሁሉ ወደ ራሱ ሳበ። “እኔ ከፍ ብዬ ብሰቀል ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ” ማለቱም ለዚህ ነው።
የክርስቶስ በቤተ ልሔም ዋሻ በከብቶች በረት መወለዱ፤ በዮርዳኖስ ወንዝ በፍጡሩ በዮሐንስ እጅ መጠመቁ፣ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ መጾሙ (መራቡ መጠማቱ)፣ በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ እና በመጨረሻም በዕፀ መስቀል ተሰቅሎ መሞቱ “በዚህች ዓለም ከእኛ በላይ ጥበበኞች የሉም” በሚሉት በግሪካውያን እና፣ “ለእግዚአብሔርና ለሕጉ ከእኛ በላይ ቅርብ የሆነ ሕዝብ በዚህ ምድር የለም” በሚሉት ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ዘንድ ትልቅ ሞኝነት ነው። በጸሐፍትና በፈሪሳውያን እምነት ክርስቶስ የሚመጣው በታላቅ ዙፋን ተቀምጦ፣ አክሊል ደፍቶ፣ ካባ ደርቦና በወታደር ታጅቦ ከሮማውያን ቅኝ ግዛትና ከጭቆና ነፃ ለማውጣት ነው። እርሱ ግን በሁለት ወንበዴዎች መካከል እርቃኑን ተሰቅሎ፣ ተገፎ፣ ተገርፎ፣ ተዋርዶ፣ ሞቶና ተቀብሮ የሚያድናቸው ሆኗል። ይህን ደግሞ እንደ ዓለም ጥበብ ስንመለከት ሞኝነት ነው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲያብራራ “የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፣ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና። ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚህችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፣ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና። መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፣ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው” ብሏል። (፩ኛ ቆሮ.፩፥፲፰-፳፫)
ዛሬም መስቀሉን እንጨት፣ ጸበሉን ውኃ፣ እምነቱን አፈር፣ ታቦቱን እንጨት የሚሉ ሰዎች የዓለም ጥበበኞች ሞኞች ስለሆኑ ነው። እግዚአብሔር ግን የዓለምን ጥበብ ያፈርስ ዘንድ ዓለም በናቀው ነገር ላይ አድሮ ያድናል፤ ድንቅ ድንቅ ተአምራትንም ያደርጋል፤ ይመሰገንበታልም።
የዲያብሎስን ጥበብ በመሻር
ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ክርስቶስ ወደዚች ምድር የመጣበትን ትልቁን ዓላማ ሲያብራራ “የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ” ብሏል። (፩ኛ ዮሐ.፫፥፱) ይህ እንደምን ነው ቢሉ? ዲያብሎስ እንደ ጥበብ ተጠቅሞ አዳምንና ሔዋንን ያታለላቸው “ዕፀ በለስን” ከበላችሁ አምላክ ትሆናላችሁ” በማለት ነበር። ክርስቶስም ዲያብሎስ አዳምን የእንጨት ፍሬ በማብላት ድል በነሣው አንጻር በዕፀ መስቀል ተሰቅሎ ድል ነሥቶታል።
ዲያብሎስ አዳምንና ሔዋንን ዕፀ በለስን ከበላችሁ አምላክ ትሆናላችሁ ያለው ለሽንገላና ለማታለል ሲሆን ክርስቶስ ግን ዲያብሎስ አዳምን ለማሞኘት የተጠቀመበትን ሐሳብ በአምላካዊ ጥበቡ ወደ እውነት ቀይሮ በተዋሕዶ ሰው ሆኖ የሰውን ሥጋ አምላክ አደረገው። መለኮት በተዋሐደው ሥጋ ሞትንና መቃብርን ድል አድርጎ በመነሣት በሞትና በዲያብሎስ ላይ ሥልጣንን ሰጠን።
እንደ ዲያብሎስ ጥበብ በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው። የተረገመ ወይም ተግባሩ ርጉም የሆነ ሰው ደግሞ የተግባሩ ውጤት በሥጋው ወደ መቃብር በነፍሱም ወደ ሲኦል ወርዶ መከራ መቀበል ነው። ጌታችን ግን በዕፀ መስቀል ተሰቅሎ ሞትና መቃብርን ድል በማድረግ ነፍሳትን ከሲኦል ወደ ገነት መልሷቸዋል። ዲያብሎስ የሰውን ልጅ በማሞኘት ወደ ሞት ጎዳና ነበር የሚወስደው ክርስቶስ ግን በሞቱ ወደ ሕይወት መልሶናል። በዚህም የዲያብሎስን ጥበብ ሞኝነት እንደሆነ አሳይቶናል። ነፍሳትንም ሁሉ ወደ ራሱ ስቦ አቅርቧል።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤዛነቱ ሥራ ውጭ የፈጸማቸው ተግባራት ለአርአያነት ያከናወናቸው ናቸው። ለምሳሌ በዮርዳኖስ ከተጠመቀ በኋላ “ያመነ የተጠመቀ ይድናል” (ማር.፲፮፥፲፮) የሚል ሕግ መሥራቱ፤ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ “በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ እነርሱ እንደ ጾሙ ይታዩ ዘንድ መልካቸውን ይለውጣሉና” (ማቴ.፮፥፲፮) ብሎ ማስተማሩ፣ ቀን እያስተማረ ውሎ ሌሊት በደብረ ዘይት እየጸለየ በማደር አርአያ ከሆነ በኋላ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ” (ማቴ.፳፮፥፵፩) ብሎ ማሳሰቡ በመጨረሻም የሐዋርያትን እግር አጥቦ እኔ እንዳደረግሁላችሁ እናንተም ለሌሎች እንዲሁ አድርጉ ብሎ ትሕትናን ማስተማሩ የጌታችን ወደዚህ ምድር መምጣት ከቤዛነት በተጨማሪ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን አርአያ ሊሆነን መሆኑን የሚያስገነዝበን ነው። “እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና” እንዲል። (ዮሐ.፲፫፥፲፭)
እግዚአብሔር እኛን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ የፈጠረን ስሙን ቀድሰን ክብሩን ወርሰን ለዘለዓለም እንድንኖር ነበር። ነገር ግን ለመኖር የተፈጠርነው እኛ የተሰጠንን ነፃ ፈቃዳችንን ያለአግባብ ተጠቅመን ከሕይወት ሞትን፣ ከክብር ውርደትን፣ ከደስታ ኀዘንን መረጥን፤ ከገነት ተባርረን ወደ ሲኦል ስንወርድ እግዚአብሔር የእኛን ዕዳና በደል በራሱ ላይ አኑሮ ለኛ የሚገባንን የሞት ፍርድ ተቀብሎ እኛን ወደ ቀደመው ክብራችን ሊመልሰን የእኛን ሥጋ ተዋሕዶ ተወለደ። የሞተውም ይህንኑ ዓላማ ለመፈጸም ነው እንጂ በድንገት አሊያም በሌሎች አስገዳጅነት አይደለም። ይህንን ምሥጢር በስፋትና በጥልቀት ያስተማረው ሶርያዊው የነገረ መለኮት ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬምም በዕለተ ዓርብ ውዳሴ ማርያም ላይ “ሰውን የሚወድ እርሱ ወደ እርሱ አቀረበን ክብር ምስጋና ያለው እርሱ የእኛን ሞት ተቀብሎ የእርሱን ሕይወት ለእኛ ሰጠን” ብሏል።
አባታችን አዳም እግዚአብሔር “ዕፀ በለሰን እንዳትበላ” ብሎ የሰጠውን ትእዛዝ በማፍረሱ ደዌ ሥጋ ላይ ደዌ ነፍስን፣ ሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስን፣ ርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነመ እሳትን እንደፈረደበት የሚታወቅ ነው። ይህ ፍርድ ደግሞ ከአዳምና ከሔዋን በዘር በሩካቤ ለተወለዱ ሁሉ ስለ ደረሰ ወልደ እግዚአብሔር ከድንግል ማርያም ተወልዶ በሞቱ ሞትን ደምስሶ፣ መቃብርና ሲኦልን ድል ነሥቶ እስካዳነን ጊዜ ድረስ ሁላችንም በዚህ ፍርድ ውስጥ እንደ ነበርን ይታወቃል። በኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስትምህሮ ድኅነትም ስንል ከዚህ ሁሉ ርግማንና ፍርድ ነፃ መውጣትን ነው። ቅዱስ ኤፍሬምም “ከእኛ ርግማንን አጠፋልን፣ በመካከላችንም ሆኖ በመስቀሉ አስታረቀን በልዩ ትንሣኤውም ሰውን ዳግመኛ ወደ ገነት መለሰው” ያለው በወልደ እግዚአብሔር ሰው መሆን ያገኘነውን ድኅነት ጠቅልሎ ለመናገር ነው።
ማጠቃለያ
ክርስቶስ ከሁሉ ከፍ ያለ ሁሉን ፈጥሮ የሚገዛ እርሱ ብቻ አምላክ መሆኑን ለማስተማር በባሕር ላይ እንደ የብስ እየተራመደ፣ ማዕበሉንና ነፋሱን እየገሠጸ፣ ውኃውን ወደ ወይን እየቀየረ፣ ኮረብቶችን እንደጠቦት እያስዘለለ፣ ድንጋዮች አፍ አውጥተው እንዲናገሩና አምላክነቱን እንዲመሰክሩ እያደረገ ሁሉን ወደራሱ ስቧል። ይህም የነገረ መስቀሉ አካል ነው። ምክንያቱም ክርስቶስ ይህን በማድረጉ አይሁድ ሰንበትን ሻረ ብለው ከሰውታል። ኋላም ለሞትና ለመከራ ያደረሱት ሌላ በደል ተገኝቶበት ሳይሆን እነዚህንና መሰል ድንቅ ድንቅ ሥራዎችን ስለሠራ ብቻ ነው።
እንዲሁ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን ዕርቃኑን በተሰቀለበት ቀን ቀድሞ አማልክት ተብለው ይመለኩ የነበሩት ብርሃናውያኑ ፍጥረታት ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት የአምላካቸውን ዕርቃን ለመሸፈን ብርሃናቸውን ከልክለው የክርስቶስን አምላክነት በመናገራቸው አስቀድሞ ባለማወቅ እነዚህን ፍጥረታት ማለትም ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ያመልኩ የነበሩ አሕዛብ አምላክ እርሱ ብቻ መሆኑን አምነው ወደ ክርስቶስ ቀርበዋልና ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ አለ። ስለዚህ ጌታ በዕፀ መስቀል ላይ የተሰቀለው ሞትን በሞቱ ገድሎ ዲያብሎስንም አስሮ የዲያብሎስን ምርኮ ለመመለስ መሆኑን እናምናለን። (ሉቃ.፲፩፥፳፪) እግዚአብሔር አምላካችን ከበረከተ ስቅለቱና ከበረከተ ትንሣኤው ያድለን አሜን።