ሊቁ የተናገረውን ዘርዘር አድርገን ስንመለከት “ውእቱ ኅሊናሁ ለአብ ፍጹም ቃለ እግዚአብሔር ዘተወልደ እምኔሁ እምቅድመ ኮከበ ጽባሕ ገባሬ ኵሉ ምስለ አብ ወመንፈስ ቅዱስ ፈጣሪሁ ለሰብእ ዘህልው በኩሉ ግብር ሊቀ አበው በውስተ ሊቀ አበው ሐጋጌ ሕግ በውስተ ሕግ ፤ የአጥቢያ ኮከብ ሳይፈጠር ከሱ የተወለደ የአብ ኅሊናው ፍጹም ቃለ እግዚአብሔር እርሱ ነው ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሜ ከሆድ ወለድሁህ እንዳለ (መዝ. ፲፱፥፫) ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ሁሉን የፈጠረ በሥራ ሁሉ ያለ በአበው አለቆች ዘንድ የአበው አለቃ እርሱ ነው። ሕግን በመሥራት ጊዜ ሕግን የሠራ እርሱ ነው። ካህናትን የሚሾም ሊቀ ካህናት ነገሥታትን የሚገዛ በነቢያት አድሮ የሚናገር በመላእክት ላይ ንጉሥ እርሱ ነው። በሰው ባሕርይ ሰው የሆነ፣ ከአብ የተወለደ፣ ከባሕርይ አምላክ የተገኘ፣ የባሕርይ አምላክ የዘለዓለም ንጉሥ እርሱ ነው። ኖኅን የጠበቀው፣ አብርሃምን የመራው፣ ከያዕቆብ ጋር እንግዳ የሆነና ከዮሴፍ ጋር የተሸጠ እርሱ ነው” (ሃ.አበ.፯፥፬-፱) በማለት፡-
፩. ሕግን በመሥራት ጊዜ ሕግን የሠራ እርሱ ነው (በኦሪት)፤
፪. የአጥቢያ ኮከብ ሳይፈጠር ከሱ የተወለደ የአብ ኅሊናው ፍጹም ቃለ እግዚአብሔር እርሱ ነው (በነቢያት) (መዝ.፻፱፥፫)
፫. በሰው ባሕርይ ሰው የሆነ እርሱ ነው (በወንጌል)
በሦስቱም በኦሪት በነቢያት በወንጌል የተሰበከ ክርስቶስ እንደሆነ ቅዱስ ሄሬኔዎስ በግልጽ አስተማረ። ሦስቱን በቅደም ተከተል ከማየታችን በፊት ከስሙ ትርጓሜ እንነሣ ክርስቶስ ማለት መሲሕ ማለት ሲሆን መሲሕ ማለት ደግሞ ቅቡዕ ማለት ነው ቅቡዕ ማለትም ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ሆኖ የተዋሐደ ማለት ነው ስለዚህ አምላክ ሰው ሲሆን የወጣለት ስም ነው።
፩. በኦሪት እንዴት ተሰበከ?
ለሰው ልጅ የተሰጠው ተስፋ (በኋላ በክርስቶስ ፍጻሜ ያገኘው) ከዘመነ ኦሪት በፊት ከአዳም ጀምሮ ለነበሩ አባቶች የተናገረውን በኦሪቱ ላይ ተገልጾ እናገኘዋለን። ‹‹በአንተና በሴቲቱ መካከል በዘርህና በዘሩ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ። ራስህን ይቀጠቅጣል አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ›› (ዘፍ.፫፥፲፭) ብሎታል። ይህውም ‹‹ባንተና በሴቲቱ›› ማለት በእባብና በሔዋን ጠላትነት አደርጋለሁ ብሎ በሔዋንና በዲያብሎስ መካከል የሚሆነውን ታላቅ ጸብና ክርክር ለአዳም ነግሮታል። እግዚአብሔር እንዲህ ማለቱ ሔዋን ከዲያብሎስ ጋር ተጣልታ ድል የምትነሳው ሆኖ አይደለም። ከሔዋን ባሕርይ ከተገኘች ዳግማዊት ሔዋን ከምትባል ከቅድስት ድንግል ማርያም የዲያብሎስን ምክር የሚያፈርስ፣ ኃይሉን የሚያደክም፣ መርዙን የሚያጠፋ ቤዛ ኩሉ ዓለም ክርስቶስ የመወለዱን ነገር መናገሩ ነው።
እንዲሁም ‹‹በዘርህ እና በዘሯ መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ›› በማለትም የዲያብሎስ የግብር ልጅ በተባሉት ዲያብሎስ ክፉ ሥራውን በሠራባቸው በአይሁድ መካከል እና ከሔዋን ባሕርይ ከተገኘ ከዳግማዊት ሔዋን ከድንግል ማርያም በድንግልና በተወለደው ልጇ በክርስቶስ መካከል ፀብና ክርክር እንደሚሆን አስቀድሞ ገለጠ ።
ይህውም ኃጢአት በመሥራት የተጎዱ አዳምና ሔዋን ሲሆኑ ተስፋውም የእነርሱ ሲሆን ሔዋንን ብቻ ለይቶ ‹‹በዘርዋ›› ተስፋውን የሰጠበት ምክንያት የእግዚአብሔር ልጅ አካላዊ ቃል ክርስቶስ ተወልዶ የሚያድናቸው ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት እንደተወለደው ሁሉ ድኅረ ዓለም ደግሞ ያለ አባት ከዳግሚት ሔዋን ከድንግል ማርያም ብቻ በድንግልና ተወልዶ ነውና ለሔዋን ብቻ ሰጥቶ ተስፋውን ገልጾላታል። አካላዊ ቃል ለአዳም በሰጠው ተስፋ መሠረት ከሔዋን ዘር ይወለድ ዘንድ ስላለው ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር ‹‹እንግዲህ ሕግ ምንድን ነው ? ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ›› (ገላ.፫፥፲፱) በማለት የሰጠውን ተስፋ አጉልቶ ከተናገረ በኋላ በሰጠው ተስፋ መሠረት ከቅድስት ድንግል ማርያም የመወለዱን ነገር ሲገልጽ ‹‹ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ከሴትም ተወለደ›› (ገላ. ፬፥፬) ሲል ገልጾአል። “እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ሰኮናውን ትነድፋለህ” በማለት የተናገረው ሊፈጸም አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ሰው በሆነ ጊዜ ዲያብሎስ በገዳመ ቆሮንቶስ በአካል በመምጣትና በመፈተን ከዚያም በልበ አይሁድ አድሮ ሰኮና ትምህርቱንና ሰኮና ተአምራቱን በመቃወም በመስቀል ሲያሰቅለው ጌታ በመስቀል ተሰቅሎ በመስቀሉ የእባቡን የዲያብሎስን ራስ ቀጥቅጦ ድል በመንሳት ዓለምን አድኖ ለአዳምና ለሔዋን የሰጠውን የተስፋ ቃሉን ፈጽሞታል ።
ቅዱስ ዳዊት በመንፈሰ እግዚአብሔር ተመርቶ ‹‹እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ አንተ ባሕርን በኃይልህ አጸናሃት አንተ የእባቦችን ራስ በውኃ ወስጥ ሰበርህ አንተም የዘንዶውን ራስ ቀጠቀጥኽ›› (መዝ. ፸፫፥፲፪-፲፬) በማለት ለአዳም ተስፋ በሰጠው መሠረት በመስቀሉ ዲያብሎስንና ሠራዊቱን ድል የማድረጉን ነገር ተናገሯል።
መሲህ ክርስቶስ ከአብርሃም ወገን እንደሚወለድ እንዲህ ተበሎ ተገልጾአል። ‹‹የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ፤ ቃሌን ሰምተሃልና›› (ዘፍ. ፳፪፥፲፰) ይላል። እንዲህ ተብሎ የተነገረውን ፍጻሜ ‹‹የዳዊት ለጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ መጽሓፍ›› (ማቴ.፩፥፩) ተብሎ በወንጌል የተገለጸ ሲሆን ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጳውሎስ “እነርሱም አባቶቻችን ናቸው፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ ተወለደ፤ እርሱም ከሁሉ በላይ የሆነ ለዘለዓለም ቡሩክ አምላክ ነው›› (ሮሜ ፱፥፭) በማለት አስረደቷል።
ክርስቶስ ከአብርሃም ዘር ከነገደ ይሁዳ እንደሚወለድ እንደሚወለድ ብቻ ሳይሆን ተወልዶ የሚያከናውናቸው ተግባራትም ተገልጸዋል። ይህን አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ “መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም፤ ምስፍናም ከአብራኩ ለእርሱ የሚጠብቀውን እስኪያገኝ ድረስ፤ የአሕዛብ ተስፋቸው እርሱ ነውና፤ አህያይቱን በወይን ግንድ ያስራል፤ የአህያይቱንም ግልገል በወይን ሐረግ፤ ልብሱን በወይን ያጥባል፤ መጎናጸፊያውንም በዘለላው ደም።” (ዘፍ. ፵፱፥፲-፲፩) በማለት ከአይሁድ ዘር መወለዱን ብቻ ሳይሆን በውርንጫ የተመሰሉ አሕዛብን በአህያይቱ ግልገል የተመሰሉ እስራኤል ዘሥጋን በማየ ገቦው (ከጎኑ በሚፈሰው ውኃ ) ልጅነትን በመስጠት ማለትም ‹‹ልብሱን በወይን ያጥባል›› በማለት ልጅነትን ‹‹መጎናጸፊያውንም በወይን ደም›› በማለት በሥጋውና በደሙ ሕዝብንና አሕዛብን እንደሚያከብር ተገለጸ። ፍጻሜውንም ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ጌታችን ከአይሁድ ነገድ እንደወጣ የተገለጠ ነውና›› (ዕብ. ፪፥፲፬) በማለት ገልጾታል እስራኤል ዘሥጋም በምድረ በዳ ሲጋዙ በበረሃ ውስጥ ከዐለት ያፈለቀው ውሃ ክርስቶስን የሚገልጽ ነው። ሙሴም እጁን ዘርግቶ ድንጋዩን ሁለት ጊዜ በበትሩ መታው ከዚህም ውኃ ወጣ ማኅበሩም ከብቶቻቸውም ጠጡ (ዘኁ. ፳፥፲፩) ፤ (ዘፀ. ፲፯፥፩) ተብሎ የተገለጸው ለክርስቶስ እንደሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ይከተላቸው ከነበረው ከመንፈሳዊ ዓለት ጠጥተዋልና ያም ዐለት ክርስቶስ ነበር›› (፩ቆሮ.፲፥፬) ሕዝቡም አሕዛቡም ጠጥቶ የሚረካበት ውኃ የፈለቀበት ዐለት ክርስቶስ እንደሆነ ነገረን።
፪. ክርስቶስ በነቢያት አስተምሮ
ቅዱሳን ነቢያት በመንፈሰ እግዚአብሔር ተቃኝተው አምላካችን ከእመቤታችን እንደሚጸነስ፣ እንደሚወለድ፣ እንደሚሰደድ፣ በዮርዳኖስ እንደሚጠመቅ፣ ወንጌልን ዙሮ እንደሚያስተምር፣ መከራን እንደሚቀበል፣ እንደሚሰቀል፣ እንደሚሞት፣ እንደሚነሣ፣ እንደሚያርግ፣ ዳግም እንደሚመጣ በሰፊው አስተምረዋል። የእግዚአብሔር ልጅ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ ደረሶ ሥጋን አልተዋሐደም ፤ አስቀድሞም በነቢያት አድሮ ትንቢትን አናግሯል ፤ ሱባኤንም አስቆጥሯል የሥጋዌውም ምስክር ቀደምት ነቢያት ናቸው። በመሆኑም የነቢያትን ትምህርት ማወቅ ምሥጢረ ሥጋዌን በትክክል ለመረዳት እጅግ አስፈላጊ ነው። እንዲህ ከሆነ ነቢያት ስለክርስቶስ ከአስተማሩት የተወሰኑትን እንመልከት።
ልዑለ ቃል ኢሳይያስ የሰው ልጅ ከነፍስ መቅሰፍት የሚድንበትን ምልክት “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች” (ኢሳ. ፯፥፲፬) ብሎ የገለጸው እመቤታችን በድንግልና ጸንሳ መውለዷን ለማስረዳት ነው። ይህንም ‹‹ሕፃን ተወልዶልናልና ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል›› (ኢሳ. ፱፥፮) በማለት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ገና ሳይወለድ እንደተወለደ አድርጎ በመግለጽ ደረቅ ሐዲስ የሚባለውን ትምህርት አስተማረን። ይኸውም የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራልና የተባለለትና ሥልጣን የባሕርይ የሆነለት ሕፃን መስቀልን በጫንቃው ተሸክሞ አጋንትን ከሰው ልቡና በማውጣትና በማሳደድ ለዓለም ሰላምን ሰጠ።
ነቢየ እግዚአብሔር ሕዝቅየልም በኅቱም ድንግልና የመወለዱን ነገር እንዲህ ብሎ ገልጾታል ‹‹እግዚአብሔር ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል›› (ሕዝ. ፵፬፥፪) በማለት አምልቶና አስፍቶ የተናገረው (ማቴ. ፩፥፳፪-፳፫) ተፈጽሟል። ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም ‹‹እነሆ በኤፍራታ ሰማነው በዱር ውስጥም አገኘነው›› (መዝ. ፻፴፩፥፮) በማለት በዱር ተጥሎ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግዕዘ ሕፃናት ሲያለቅስ ሰማነው ሲል ያልተፈጸመው እንደተፈጸመ ሆኖ ተገልጾለት ስለመሲህ ክርስቶስ ሰብኮልናል። ስለዚህ ነቢያት አምልተውና አስፍተው የተናገሩት ትንቢት የመሰሉት ምሳሌ ማለትም በሐመልማልና ነበልባል አምሳል፣ በጠልና በፀምር፣ በቆመ ድንጋይና በሚያስፈራ አንበሳ አምሳል መስለው የተናገሩት መድኅን ክርስቶስን የሚሰብክ ነው። ስለዚህ ታላቁ ቅዱስ አባት ሄሬኔዎስ ‹‹ኦሪት ነቢያት ወንጌል ክርስቶስን አስተማሩ›› በማለት ሦስቱንም በማሰናሰል የተናገረው በተለይ ከወንጌል በፊት የነበሩት ኦሪትና ነቢያት በወንጌል የሚፈጸመውን በሰፊው እንደገለጹና ወንጌል ዳግም አካሉ የተገለጸባት ስለሆነች ቀጥሎ እንመልከት።
፫. ክርስቶስ በወንጌል
የሰው ልጅ በመጀመሪያ ትእዛዘ እግዚአብሔርን በመጣሱና በሕገ ልቡና መተዳደር ቢያቅተው በሙሴ አድሮ ሕገ ኦሪን በደብረ ሲና ሠርቶ እርሱ እንዲቀርብ እስራኤል ዘሥጋ እንዲመሩበትና ከሙሴም ቀጥሎ ነቢያትን በመሾም በእነርሱ እንዲማሩ እንዲገሠጹና ተስፋውን እንዲጠባበቁ ቢናገራቸውም በሕጉ መኖር እና ሕጉን መጠበቅ ትእዛዙን መፈጸም አልቻሉም ነበር። ስለዚህ ከሦስቱ ቅዱስ አንዱ ቅዱስ ወልደ እግዚአብሔር በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ወደዚህ ዓለም መጣ፤ አምላክ ሰው ሆነ ሰው አምላክ ሆነ፤ ሕገ ወንጌልንም ሠራ። በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የሠራት ሕገ ወንጌል ስለ ክርስቶስ ምን መሰከረች? የሰው ልጅስ ክርስቶስን እንዴት ተቀበለው? የሚሉትን ጥያቄዎች አንሥተን መመልከት ተገቢ ነው።
ወንጌልን የሠራልን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለራሱ ሲናገር “እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ። (ዮሐ. ፮፥፵፰)፤ መልካም እረኛ እኔ ነኝ። (ዮሐ. ፲፥፲፩)፤ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ። (ዮሐ.፰፥፲፪)፤ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ። (ዮሐ. ፲፥፴፮)፤ እኔና አብ አንድ ነን። (ዮሐ.፲፥፴)፤ ትንሣኤ እና ሕይወት እኔ ነኝ። (ዮሐ.፲፩፥፳፭፤ “የእውነትና የሕይወት መንገድ እኔ ነኝ።” (ዮሐ.፲፬፥፮)፤ እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተ ቅርንጫፎች ናችሁ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የማትኖር እኔም በእርሱ እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል፤ ይደርቅማል (ዮሐ.፲፭፥፭-፮) በማለት ስለራሱ አስተማረን።
በተለይም ‹‹ነኝ›› ‹‹እኔ ነኝ›› በማለት በማስረገጥ ስለርሱ ካስተማረ በኋላም እኔ የወይን ግንድ ነኝ ብሎ እናንተ ቅርንጫፎች ናችሁ በማለት እና ያለ እርሱ መኖር እንደማንችል ፍሬ ምግባር ማፍራት እንደማይቻለን እና ከወይን ግንድ የተለየ ቅርንጫፍ እንደሚደርቅ ሁሉ እኛ የሰው ልጆችም ከሱ ከተለየን ምንም ዓይነት ሕይወት እንደማይኖረን በእኔ የማይኖር ቢሆን እንደ ቅርንጫፍ ወደ ውጭ ይጣላል፤ ይደርቅማል በማለት ነገረን። ስለሆነም የወይን ቅርንጫፍ የተባሉ ሐዋርያት፣ ሰብአ አርድእት፣ ሰማዕታት፣ ሊቃውንት፣…..በአላውያን አደባባይ ሳይፈሩና ሳያፍሩ ስሙ ሕይወት መድኃኒት ካለው ከክርስቶስ መከራ መስቀሉን ተሸክመው የራሳቸውን ፈቃድ ሳይሆን የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም ክርስቶስን ሰበኩ ስለ ጽድቅ ብለው በዚች ዓለም እንየተንከራተቱ ኖሩ።
ያልተቀበሉት እነማን ናቸው?
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኦሪትም በነቢያትም በወንጌልም ቢሰበክም በአንጻሩ ደግሞ ያልተቀበሉትም ነበሩ። ከወይኑ ግንድ የተለዩት የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም ‹‹እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ አልተቀበላችሁኝም›› (ዮሐ. ፭፥፵፫) በማለት እንደገለጸው የሰው ልጅ በመንጸፈ ደይን መውደቁን በእግረ አጋንንት መጠቅጠቁን አይቶ፣ ልዑል ባሕርዩን ዝቅ አድርጎ ይህን ዓለም ሊያድን መጣ። እነርሱ ግን አልተቀበሉትም ቅዱስ ዮሐንስም ይህን ሲገልጽ ‹‹የእርሱ ወደ ሆነው መጣ የገዛ ወገኖቹም አልተቀሉትም›› (ዮሐ.፩፥፲፩) ብሎ ገልጾታል። ይህንም አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራትን እያደረገ፣ አጋንንትን ከሰው ልቡና እያስወጣ፣ ድውይ እየፈወሰ፣ ለምፃም እያነፃና ኅብስት አበርክቶ እየመገበ ቢያስተምራቸው ትምህርቱን አንቀበልም አምላክነቱን አናምንም አሉ። እነዚህም ጸሐፍት ፈሪሳውያን እንዲሁም ከነሱ በኋላ እስከ ዓለም ፍፃሜ የሚነሡት ሲሆኑ እንዲህ ይላቸዋል ‹‹እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ከአንዱም ከእግዚአአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ? እኔ በአብ ዘንድ የምከሳችሁ አይምሰላችሁ ። የሚከሳችሁ አለ እርሱም ተስፋ የምታደርጉት ሙሴ ነው ሙሴንስ ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር እርሱ ስለእኔ ጽፏልና መጻሕፍትን ካላመንችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ›› (ዮሐ. ፭፥፵፬-፵፮) ቤተ አይሁድ ሙሴም ስለ እነርሱ ጽፎላቸው ባለቤቱ ክርስቶስም እያስተማራቸው ስለራሳቸው ዝናና ክብር ብለው አንቀበልም አሉት።
በተቀራኒው አሕዛብ ግን ስለ ክርስቶስ አንድም ነገር ያልሰሙ ስለ እግዚአብሔር አንዳች ነገር የማያውቁ ተአምራቱን ያላዩ በፍልስፍና መጻሕፍቶቻቸው በገጣሚዎቻቸው በጥበበኞቻቸው ስለክርስቶስ አንዲትም መስመር ያልተጻፈላቸው ሆነው ሳለ አመኑት፤ ወደዱት፤ ተቀበሉትም፤ ክብርንም አገኙ ። ‹‹ቀራጮችና አመንዝሮች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሟችኋል›› (ማቴ.፳፩፥፴፩) በማለት የገሠጻቸው ለዚህ ነው። የስሙን ዝና ተሸክመው ቤተ አይሁድ ስለራሳቸው ክብር ሲሉ ለመቀበል ወደኋላ ሲሉ አሕዛብ ግን ምንም ዓይነት ዝና ሳይኖራቸው ስሙ ሕይወት መድኃኒት ነው ብለው አምነው ከበሩበት ቤተ አይሁድ ቢንቁትም እንኳን ‹‹ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ›› (መዝ.፻፲፯፥፳፪) እንደተባለ ክርስቶስ የማእዘን ራስ ሆኗል።
ስለዚህ ቅዱስ ሄሬኔዎስ እንዳለው ኦሪት ‹‹ነቢያት ወንጌል ክርስቶስን አስተማሩ›› ነገር ግን አይሁድ ግን ኦሪትን ነቢያትን በጆሮአቸው ሰምተው ወንጌል በአካል ተሰብኮላቸው እነርሱ ግን እያዩ የማያዩ እየሰሙ የማይሰሙ ዝንጉአነ አእምሮ ሆነዋል። ይህንም ማኅቶተ ቤተ ክርስቲያን ቀዱስ ጳውሎስ ሲገልጸው ‹‹የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውን ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም የማያምኑም ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና›› (ሮሜ ፲፥፫-፬) በማለት እነዚህ የራሳቸውን ጽድቅ የሚያቆሙ ለራሳቸው ዝና የሚሞቱ ሕግ እናከብራለን እያሉ የሕግ ፍጻሜ ክርስቶስን ግን መቀበል ያቃታቸው እንደሆኑ ያስረዳናል። ሐዋርያው አያይዞም ‹‹እንግዲህ ምን እንላለን? ጽድቅ ያልተከተሉ አሕዛብ ጽድቅን አገኙ እርሱ ግን ከእምነት የሆነ ጽድቅ ነው እስራኤል ግን የጽድቅን ሕግ እየተከተሉ ወደ ሕግ አልደረሱም›› (ሮሜ ፱፥፴-፴፩) በማለት አስረዳን። በጣም የሚያሳዝኑት የጽድቅን ሕግ እየተከተሉ ወደ እምነት ማደግ አለመቻላቸውና እያደሩ እየቀጨጩ መሄዳቸው ነው። እንዲሁም መስቀል ላይ በደሙ ፈሳሽነት የገለጸውን ፍጹም የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እምቢ አሻፈረኝ ማለታቸው በተነገረላቸው ተስፋ መጠቀም አለመቻላቸው ነው።
ለሕዝብም ለአሕዛብም የሚበቃውን ክርስቶስን አልተመለከቱም ይልቁንም በግዝረት የሚያምኑ አይሁድ ‹‹ከኃጢአተኞች ጋር ይበላል›› ብለው ክርስቶስን ተቃወሙት ምሥጢሩ ባይረዳችው ነው እንጂ ቢረዳቸውማ ‹‹በስውር ከአይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው መገረዝም በመንፈስ የማድረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሓፍ አይደለም›› (ሮሜ ፪፥፳፱) ተብሏል። ግዝረት ማለት ይህ ነው ታዲያ ይኽን መቀበል ካቃታቸው የአይሁዳዊነት ብልጫው ምንድን ነው?›› ስለዚህ እኛም በሕይወተ ሥጋ እያለን ክርስቶስን በሥራው ልንከተለው ይገባል። ይህ ካልሆነ እነርሱ የአይሁዳዊነት ብልጫው ምንድን ነው? ተብለው እንደተጠየቁ እኛም የክርስትና ብልጫው ምንድን ነው ተብለን እንጠየቃለን?።
ሳንፈልገው የፈለገን፣ ሳንወደው የወደደን፣ ስንገፋው ያልገፋን፣ ስንርቀው ያልራቀን አምላካችን ለእኛ የከፈለውን ዋጋ ማስታወስ ተገቢ ነው ሊቁ ‹‹ኦሪት ነቢያት ወንጌልም ክርስቶስን አስተማሩ›› አለ ኦሪትና ነቢያት አስቀድመው ክርስቶስ ለእኛ የከፈለውን ዋጋ አስተማረች ያውም በክርስቶስ ወርቀ ደም መገዛታችን ነው። (፩ ጴጥ. ፩፥፲፱) ታዲያ እርሱ ይህን ዋጋ ለመክፈል ወደሰው ልጅ ሲመጣ ለራሱ የሚሆን ማደሪያ አልነበረውም ይህንም ‹‹ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይ ወፎች መስፈሪያ አላቸው ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም›› (ማቴ.፰፥፳) በማለት መድኅነ ዓለም ክርስቶስ ተናግሯል።
ፍጥረታት እያንዳንዳቸው እንደ አቅማቸው የራሳቸው የሆነ ማረፊያ አላቸው። ለሰው ልጅ (ክርስቶስ) ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም ሲባል ሰዎች ራሳቸውን የሚያስጠጉበት የሳር ጎጆ አጣ ማለት አይደለም ለምን ቢባል ቀን በምኩራብ ያስተምራል ሌሊት በደብረ ዘይት ዋሻ ሲጸልይ ያድራል አጣ የተባለው የሰው ልቡና ነው የሰው ልቡና ለማደሪያ ቢመርጠውም ሰው ግን ልቡናውን በኃጢአት ቆልፎ አላሳድርም አለ አንደዶቹም ተአምራትን ሲያደርግ እባክህ ከዚህ አልፈህ ሂድልን ይሉ ነበር ‹‹ከአገራቸው እንዲሄድላቸው ለመኑት (ማቴ. ፰፥፴፬) ይህም የሆነው የሰው ልጅ ከመክፋቱና የሚፈልገውን አምላክ አለመፈለጉ ነው።
ይህ ካልሆነ ግን በሥጋ የተገለጠው፣ በመንፈስ የጸደቀው፣ ለመላእክት የታየውን፣ በአህዛብ የተሰበከውን፣ በዓለም የታመነውን፣ በክብር ያረገውን፣ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚሰጠውን ክብር ማግኘት አይቻልም። መሐሪነቱን እያሰብን ወደ እርሱ መቅረብ ይገባል። “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ” የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው።
ቅዱስ ጳውሎስም አምላኬ መከራውን የተቀበለው ለእኔ ነው በማለት መከራ ሳይበግረው እስከ ፅንፈ ምድር ድረስ ክርስቶስን ሰበከ ስለዚህ ኦሪት ነቢያት ወንወጌል ክርሰቶስን ሰብከውላቸው ያላመኑ አይሁድ ከክብር እንደራቁ አሕዛብ ግን በማመናቸው በክብሩ እንደተጎናጸፉ ሁሉ በእኛም ላይ የአምላካችን የክብሩ ሙላት በላያችን ሞልቶ የሚፈሰው ወደ እርሱ መቅረብ ስንችል ነው። ወደ እርሱ የምንቀርበው በኑሮአችን፣ በቤተሰብ፣ በባሀል፣ በአለባበስ፣ በትዕግሥት፣ በፍቅር፣ በፈተና፣ በመከራ፣ ሲመቸን ሳይመቸን፣ በጊዜውም አለጊዜውም ሰንደክም ስንበረታ፤ ክርስቶስን የምንሰብከው በግድ አይደለም ። ነፃ ፍቃድ ለሁላችን ያለዋጋ ተሰጥቶናል ይህን ነፃ ፈቃዳችን ተጠቅመን የአምለካችንን ምሕረት አጋዥ አድርገነው ሁሉን ነገር ማድረግ የምንችለው። ይህንንም ለማድረግ፣ ልጅነታችንን ለመጠበቅ፣ በንስሐ ሕይወት ለመኖር፣ ልምላሜ ሃይማኖት፣ ፍሬ ምግባር ሁልጊዜ ከእኛ እንዳይጠፋ በወይኑ ግንድ በክርስቶስ መኖር ይጠበቅብናል። በዚህ ሁሉ የእግዚአብሔር ቸርነቱ ይጠብቀን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን !!