Friday, 04 September 2020 00:00

  የቱርክ መንግሥት  የሀግያ ሶፊያን ቤተ መቅደስ ወደ መስጅድነት መቀየሩን ተከትሎ ዐሥራ አራት የአውሮፓ ሀገራት ድርጊቱን እንዲያወግዙ ጥሪ ቀረበላቸው

Written by  ካሳሁን ለምለሙ

Overview

የቱርክ መንግሥት ታላቁንና ጥንታዊውን የሀግያ ሶፊያ ቤተ መቅደስ ወደ መስጅድነት መቀየሩን ተከትሎ ዐሥራ አራቱ የአውሮፓ ሀገራት መንግሥታት ድርጊተን እንዲያወግዙ የግሪኳ ፕሬዘዳንት ካተሪና ሳከላሮፖውሎው (Katerina Sakellarouplou) ጥሪ እንዳቀረቡላቸው ኦርቶዶክስ ታይምስ ዘግቧል፡፡ ፕሬዘዳንቷ ለዐሥራ አራት አውሮፓ ሀገራት መንግሥታት ደብዳቤ የጻፉ ሲሆን በደብዳቤያቸውም ጥንታዊውና  በአውሮፓ የቀደመ ታሪክ ትልቅ ቦታ ያለውን የሀግያ ሶፊያ ቤተ መቅደስ ወደ መስጅድነት የመቀየር የቱርክ መንግሥት ውሳኔን እንዲታገሉና እንዲያወግዙት አሳስበዋል፡፡  ታላቁ የሀግያ ሶፊያ ቤተ መቅደስ የአውሮፓውያንን የጋራ ማንነት፤ እሴትና ልዩነት ለወደፊቱ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው ያሉ ሲሆን ፕሬዘዳንቷ ቤተ መቅደሱ የአውሮፓውያን የጋራ   ታሪካዊ ቅርስ፣ ልዩ ጥበብና እምነትን ያጣመረ እንደሆነም ገልጠዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ቤተ መቅደሱ እንደ እ.ኤ.አ. ፲፱፻፸፪ ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፤ ሳይንስና ባህል ድርጅት የዓለም ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በመሆኑም የቱርክ መንግሥት ቤተ መቅደሱን የመቻቻል፣ የሰላም፣ የአብሮ መኖር፣ በባህሎችና በሃይማኖት ተቋማት መካከል የመነጋገሪያ ምልክት ሆኖ እንዲቀጥል ከማድረግ ይልቅ የግጭት፣ ያለመቻቻል፣ የመገፋፋትና የጥርጣሬ ምልክት እንዲሆን ማድረጉ እንዳስከፋቸው ፕሬዘዳንቷ ተናግረዋል፡፡ 

 

መንግሥታቸው ድምፁን በማሰማት የቱርክን መንግሥት ድርጊት ማውገዙን እንደሚቀጥል ያስታወቁት ፕሬዘዳንቷ የቱርክ መንግሥት ጉዳዩን መልሶ እስኪያጤነውና ውሳኔውን እስኪያስተካክል ድረስ ማውገዛቸውንም እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡ ታላቁ የሀግያ ሶፊያ ቤተ መቅደስ ወደቀደመ ክብሩና ማንነቱ እስካልተመለሰ ድረስ ጥሪ የቀረበላቸው አሥራ አራቱ የአውሮፓ ሀገራት መንግሥታትም ማውገዛቸውንና ድምፃቸውን ማሰማታቸውን እንዲቀጥሉ ፕሬዝዳንቷ አሳስበዋል፡፡ 

ቡልጋሪያ፣ ኦስትሪያ፣ ጀርመን፣ ኢስቶኒያ፣ አየርላንድ፣ ላቲቪያ፣ ክሮሺያ፣ ጣሊያን፤ ማልታ፣ ሀንጋሪ፣ ፓላንድ፣ ፓርቹጋል ፣ስሎቫኒያ እና ፊንላንድ ፕሬዝዳንቷ በጻፉላቸው ደብዳቤ የሀግ ሶፊያን ቤተ መቅደስ በተመለከተ የቱርክን መንግሥት እንዲያወግዙ ጥሪ የቀረበላቸው የአውሮፓ ሀገራት መንግሥታት ናቸው፡፡ 

 

 የኢራቁ ፕሬዘዳንት ለክርስቲያኖች አስቸኳይ ጥሪ አቀረቡ

በመካከለኛው ምሥራቅ የምትገኘው የዐረቡ ዓለም ፈርጥ ኢራቅ ቀላል ለማይባሉ ዓመታት በእስላማዊው የሽብር ቡድን (አይኤስ አይኤስ) ስትታመስ መቆይቷ ይታወቃል፡፡ ሀገሪቱ እስላማዊው የሽብር ቡድን እያደረሰባት ካለው ጥቃት ለመዳን ለበርካታ ዓመታት ያለ የሌለ ኃይሏን አሟጣ ስትለፋም ኖራለች፡፡ የሽብር ቡድኑን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከግዛቶቿ ለማስወጣት ያላሰለሰ ጥረት ስታደርግ የቆየች ቢሆንም እንዳሰበችው ሳይሆን ቀርቶ ቀላል የማይባል ዋጋ አስከፍሏታል፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ ዜጎቿን በስደትና በሞት ተነጥቃለች፡፡ በርካታ የሀገሪቱ ግዛቶችም እንዳለሆነ ሆነው ወድመዋል፡፡ በወቅቱ ታዲያ እስላማዊው የሽብር ቡድን  በሀገሪቱ የሚኖሩ ክርስቲያኖችን ዓይናችሁን ለአፈር ብሎ ያሳድዳቸውና ይገድላቸው ነበር፡፡ የማምለኪያ ሥፍራቸውንም ያወድምባቸው ነበር፡፡ ክርስቲያኖቹ ከሕይወት መሥዋዕትነት ጀምሮ ለዘመና እሰካፈሩት ሀበትና ንብረት ድረስ ለእስላማዊ የሽብር ቡድን ገብረዋል፡፡ በሕይወት የተረፉት ክርስቲያኖች ደግሞ “ከመሞት መሰንበት ይሻላል” ብለው ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡ 

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የሰላም አየር በሀገሪቱ ላይ መንፈስ ጀምሯል፡፡ ይህንን የሰላም አየር መኖሩን የረጋገጡት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ታድያ በፀጥታ ችግር ምክንያት ሀገራቸውን ጥለው የተሰደዱትን ክርስቲያን ዜጎቻቸውን “እባካችሁን በአስቸኳይ ወደ ተውልድ ሀገራችሁ ተመለሱ” የሚል የመማጸኛ መልእክት እንዳስተላለፉ ከኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ከተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አልካዚሚ በስደት ያሉ ክርስቲያን ዜጎቻቸውን “የሀገሪቱ ልጆች በመሆናችሁ እባካችሁ ወደ እናት ሀገራችሁ ተመለሱ” በማለት ተማጽነዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢራቃውያን ክርስቲያኖች አስቸኳይ የሆነውን ጥሪ ካቀረቡ በኋላ ከሮማን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር በኢራቃውያን ክርስቲያኖች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ዙሪያም በሰፊው መክረዋል ይላል ዘገባው፡፡ 

በሀገራቸው መንግሥት በኩል ጥሪ የተደረገላቸው በየዓለማቱ የሚገኙ ኢራቃውያን ክርስቲያኖች የመንግሥታቸውን ጥሪ በደስታ ተቀብለው ወደሀገራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተሰበረ ልብ ውስጥ ሆነው ኢራቅ የሁሉም ሀገር እንደሆነችና በተለይም ክርስቲያኖች የሀገሪቱ ቀደምት ዜጎች እንደሆኑ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ የበለጸገችውንና ያደገችውን የወደፊቷን ኢራቅ ለመገንባት የክርስቲያኖች ሚና በሀገራቸው ላይ የጎላ እንደሆነ ያነሡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢራቅ ያለ ክርስቱያን ልጆቿ ካሰበችው ልትደርስ እንደማትችልም አስምረው ተናግረዋል፡፡ 

ክርስቲያን ዜጎቻቸውን ቁርጠኛ ሆኖ ለመደገፍና ችግሮቻቸውን ለመፋታት መንግሥታቸው ዝግጁ እንደሆነ ፕሬዳንቱ ያስረዱት ሲሆን ክርስቲያኖች ወደ እናት ሀገራቸው ኢራቅ ተመልሰው መጥተው በሀገሪቱ መልሶ ግንባታ ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጋብዘዋል፡፡ የሙስጠፋ አልከዚሚ መንግሥት ክርስቲያን ዜጎቹ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የሚያደርገውን ውትወታ ተከትሎ የተወሰኑት ወደሀገራቸው ለመመለስ ፍላጎት ቢያሳዩም አንዳንዶች ግን እስላማዊ የሽብር ቡድን ከዚህ ቀደም ያደረሰባቸውን ሥቃይና ግድያ በማስታውስ አሁንም ደረስ የፀጥታ ችግር ይኖራል በማለት ወደ ሀገራችው ለመመለስ ፍላጎት እያሳዩ እንዳልሆነ ታውቋል፡፡

 

 

Read 463 times