Friday, 16 October 2020 00:00

በኢራቅ  ሞሱል ሀገረ ስብከት ተዘርፈው የነበሩ ጥንታዊ መጻሕፍት ተመለሱ።

Written by  ካሳሁን ለምለሙ
ባለፉት በርካታ ዓመታት ኢራቅ በአሸባሪው አይኤስ ቁጥጥር ሥር በወደቀችበት ወቅት ተዘርፈው የነበሩ በርካታ የኢራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሞሱል ሀገረ ስብከት ጥንታዊ መጻሕፍት ለቤተ ክርስቲያኗ እንደተመለሱ የኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ ዘገባ ያሳያል፡፡ የተዘረፉት የኢራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ መጻሕፍት ለሞሱል ሀገረ ስብከት እንደተመለሱ ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል፡፡ እነዚህ ጥንታዊ  መጻሕፍትም የአልታአሂራአ ቤተ ክርስቲያን ንብረት የነበሩ ናቸው ተብሏል፡፡ በኢራቅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሞሱል ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኒቆዲሞስ የኒንቪህ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጎበኙበት ወቅትም ስለተዘረፉት የቤተ ክርስቲያኗ ጥንታዊ መጻሕፍትና በሞሱል ሀገረ ስብከት በአሸባሪዎች ላይ ስለሚደረገው የወንጀል ምርመራ ከሕግ ባለሙያዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡  ጉዳዩን ጉዳያችን ነው ብለው የቤተ ክርስቲያኗ ጥንታዊ መጻሕፍት ከተሰረቁበት እንዲመለሱ ላደረጉ የጸጥታ ኃይሎች ብፁዕነታቸው  ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የአካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ፍትሕን ሳያጓድል የተሰረቁ ጥንታዊ የቤተ ክርስቲያኗ መጻሕፍት ለባለቤቱ እንዲመለሱ ላደረጉት ያለሰለሰ ጥረት አክብሮታቸውን ገልጠዋል፡፡   የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፊርማ እያሰባሰበች እንደሆነ ተጠቆመ ሀግያ ሶፊያ የተባለውን ጥንታዊ የኦርቶዶክሳውያን ቤተ መቅደስ በቱርክ መንግሥት አማካይነት ወደ መስጅድነት መለወጡን አስመልክቶ በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የአሜሪካ ሀገረ ስብከት ፊርማ አሰባስቦ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሊያስገባ እንደሆነ ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ አስነብቧል፡፡ ሀገረ ስብከቱ ለጥንታዊ ቅርሶች ትኩረት እንዲሰጥ፣ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ባሕልና መብት እዲጠበቅ፣ የአናሳ መብት እዲረጋገጥ፣ የሃይማኖት ነፃነት እንዲከበርና የቱርክ መንግሥት ሆን ብሎ ታሪካዊ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ቅርሶች ከታሪክ ውጭ ከማድረግ ሥራው እንዲቆጠብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ፊርማ በማሰባሰቡ ሂደት ላይ ጠይቋል፡፡ ጉዳዩ በፍጥነት መስተካከል የማይችል ከሆነም ዓለም አቀፍ የተቃውሞ ሰልፍ ሊጠራ እንደሚችል ሀገረ ስብከቱ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል፡፡ ጥንታዊው የሀግያ ሶፊያ ካቴዴራል ቤተ ክርስቲያን ወደ መስጅድነት መቀየሩን የቱርኩ ፕሬዘደንት ርሲፕ ጣኢፕ ኢርዶጋን በ፳፻፲፪ ዓ.ም በይፋ ማወጃቸው ይታወሳል፡፡ የአርመንያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለአረፅአካህ የአምስት መቶ ሺህ ዶላር ድጋፍ አደረገች በአዘርባጃንና በአርመን መካከል እየተደረገ ባለው ጦርነት ለከፋ ችግር ለተጋለጡት የአረፅአካህ ክርስቲያኖች የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የአምስት መቶ ሺህ ዶላር ድጋፍ ማድረጓን ኦርቶዶክስ ኮግኔት ፔጅ አስታውቋል፡፡ የአርመንያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ካሪኪን ዳግማዊ  አማካይነት አምስት መቶ ሺህ ዶላር ወጪ ተደርጎ ለአርፅአካህ ድጋፍ እንደተደረገ ተገልጿል፡፡ ቅዱስነታቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ወቅት ድጋፉን እንዳስጸደቁ  ከዘገባው ለመርዳት ተችሏል፡፡  ቅዱስነታቸው የገንዘብ ድጋፉን  ከማጽደቃቸው በፊት ለሀገራቸው ሲሉ ሕይወታቸውን ላጡ አርመንያውያን ክርስቲያኖች በመላው ዓለም በጸሎት እንዲታሰቡ አሳስበዋል፡፡ በተካሄደው  ስብሰባ የተወሰነው የገንዘብ ድጋፍ ለአረፅካህ ሕዝብና የጦር ሠራዊት አባላት ድጋፍ የሚውል ይሆናል ተብሏል፡፡ የገንዘብ ድጎማው የአረፅካህ ሪፐብሊክን ወቅታዊ የጦርነት ሁኔታ ያገናዘበ እንደሆን ቅዱስነታቸው በስብሰባው ገልጠዋል፡፡ የአዘርባጃን መንግሥት በአረፅካህ ሪፐብሊክ እየወሰደ ያለውን ወታደራዊ ርምጃ በተመለከተ ቅዱስ ፓትርያርኩ ለዓለም መንግሥታት፣ ለአኅት አብያተ ክርስቲያናት፣ ለሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም ለሃይማኖት ተቋማት ኅብረት ድርጅቶች መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ የዓለም አብያተ ክርስቲያናትና የሃይማኖት ጉባኤ ተቋማት የአረፅካህ ክርስቲያኖች መብት በሚጠበቅበት ሁኔታ ላይ ጠንክረው ሊሠሩ እንደሚገባም ቅዱስነታቸው አሳስበዋል፡፡ በስብሰባው ለሀገራቸው ሲሉ ሕይወታቸው ላለፈ የጦር ሠራዊት አባላት ጸሎተ ፍትሐት እንዲካሄደ የተወሰነ ሲሆን ለአርመንያ ጦር ሠራዊት አደረጃጀትና ጥንካሬ የአህጉረ ስብከት ጥምረት በጣም ወሳኝ እንደሆነ ተነሥቷል፡፡  አርመንያ ከጥንታዊ ኦርቶዶክሳውያን ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን፤ ለመጀመያ ጊዜ ኦርቶዶክሳዊ መንግሥትን ያቋቋመች ብቸኛ የዓለማችን ሀገር ናት፡፡ በአዘርባጃን ግዛት ውስጥ የምትገኘው ኖጎሮ ካራባክህ ራስ ገዝ ሀገር ስትሆን በርካታ የአርመን ክርስቲያኖችም ይኖሩባታል፡፡ በቅርቡ በአዘርባጃንና በአርመን መካከል በተቀሰቀሰ ጦርነት ንጹሓንን ጨምሮ በርካታ ወታደሮች ለሀገራቸው ክብር ሲሉ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም ጉዳት የደረሰባቸውን የአካባቢው ኗሪዎችንና የጦር ሠራዊቱን ያማከለ የገንዘብ ድጋፍ አድርጋለች፡፡  
Read 699 times