ናጎርኖ-ካራባኽ (Nagorno-Karabakh) በአርመንና በአዘርባጃን መካከል ለተከሰተው ጦርነት ምክንያት የሆነች አካባቢ ናት።
አካባቢው በአዘርባጃን የአስተዳደር ወሰን ሥር ያለ ሲሆን፡ የሚኖሩበት ግን አርመናውያን ክርስቲያኖች ናቸው። በዚህ አካባቢ ላይ ውጥረትን ያነገሠው ቆየት ያለው ግጭት የተፈጠረው፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ‹‹እኛ ዝርያችን አርመን፣ እምነታችንም ክርስትና ነውና ከማትመስለን ከአዘርባጃን ጋር አንኖርም›› በማለት የፈጠሩት እንቅስቃሴ ነበር። በዚህም ምክንያት ከ1981 ዓ.ም. አካባቢ ጀምሮ በኹለቱ ሀገራት መካከል ከፍተኛ ውጥረት ተከሰተ። በቀጣዮቹ ዓመታትም በአውዳሚ ጦርነት እርስ በእርሳቸው ተዋግተው ከባድ ዋጋን ከፈሉ።
ከዚህ በኋላ የአካባቢው አማጽያን ራሳቸውን ‹‹የአርትሳክ ሪፐብሊክ (Republic of Artsak)›› በማለት ሰይመው ለአዘርባጃን መንግሥት ያላቸውን እምቢተኝነት ገፉበት። የናጎርኖ-ካራባኽ አማጽያን የሚባሉት እነዚህ ኃይሎች ዋና ዓላማቸው ከአርመኖች ጋር መዋሐድ ነበር።
ከሰሙኑ እንደ አዲስ ያገረሸው ጦርነትም፡ የአዘርባጃን የራስ ገዝ ግዛቱን በኃይል ጠቅልላ ለመያዝ ያደረገችው ጥረት ነበር። በዚህም የራስ ገዙ ጦር የአዘርባጃንን ጥቃት ለመመከት የሚያደርገውን ጥረት የአርመን ጦር ሙሉ በሙሉ ስለ ደገፈው፡ ሁለቱ ሀገራት ወደ ሙሉ ጦርነት ለመግባት ተገድደዋል። አዘርባጃን ‹‹በግዛቴ ውስጥ በማያገባት ገብታ ወረራ ፈጽማብኛለች›› በማለት አርመንን ስትከስ፤ አርመንም ‹‹በናጎርኖ-ካራባክ ግዛት ውስጥ በሚገኙ አርመናውያን ላይ ከፍተኛ ጭቆናና በኃይል የመያዝ ግፍን እየፈጸመች ነው›› ስትል አዘርባጃንን ትከሳለች።
በናጎርኖ ካራባክ የሚገኘው በአርመን ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ሥር ያለው የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ባለፈው የፈረንጆቹ ወር በከባድ መሣሪያ ሊመታ የቻለውም በዚህ ሰሞንኛ ግጭት ምክንያት ነው። አርመን እንደ ገለጸችው፡- ይህ ጋዛንቼትሶትስ ካቴድራል (Ghazanchetsots Cathedral) በመባልም የሚታወቀው ይህ የመድኃኔዓለም ካቴድራል፡ በመጀመሪያ ጉልላቱ በከባድ መሣሪያ ተመታና በከፊል ፈረሰ። የውስጥ አካሉም በዚህ ጥቃት ጉዳት ደረሰበት። ሌሎች ዘገባዎችም አያይዘው ሕፃናትና ጎልማሶች በካቴድራሉ ውስጥ ተጠልለው እንደ ነበር ይገልጹና፡ በመጀመሪያው ጥቃት ማንም የተጎዳ እንዳልነበር ያክላሉ።
ከብዙ ሰዓታት በኋላ ካቴድራሉ በድጋሚ ተመታ፤ በውስጡ የነበሩት ሁለት ራሺያውያን ጋዜጠኞችም በጥቃቱ ቆሰሉ። የአርመን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ‹‹ጥቃቱ አውሬአዊ ወንጀልና ለሰው ልጅም ትልቅ ተግዳሮት ነው›› ሲሉ የገለጹ ሲሆን፡ የሃይማኖት ተቋማትን ዒላማ ማድረግ የጦርነት ወንጀል መሆኑንም አክለው ተናግረዋል። ሆኖም አዘርባጃን ታሪካዊ፣ ባሕላዊና በተለይም ሃይማኖታዊ ሕንጻዎችንና ሐውልቶችን ዒላማ እንደማታደርግ በመከላከያ ሚኒስትሯ በኩል በመግለጽ ጥቃቱን ክዳለች።
በጥቃቱ ጊዜ እጅግ ተጨንቀው እንደ ነበር የገለጹት አባ እንድርያስ የተባሉ የካቴድራሉ ካህን ‹‹የውቡ ካቴድራላችን ግድግዳዎች የመፍረሳቸው ሕመም ይሰማኛል፤ ዛሬ እዚህ እየተከሰተ ስላለው ነገርና እናት መሬታቸውን እየጠበቁ ልጆቻችን እየሞቱ ዓለም ዝም የማለቷ ሕመምም ይሰማኛል›› ሲሉ መሪር ኀዘናቸውን ገልጸዋል።
ሹሻ በተባለችው የግዛቱ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ይህ ካቴድራል በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን የታነጸ ሲሆን፡ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1920ዓ.ም. አካባቢ በዘር ምክንያት በተነሣ ግጭት ጉዳት ደርሶበት የነበረ ሲሆን፡ በ1980ዎቹ ከነበሩት ግጭቶች በኋላም ታድሶ ነበር።
የሁለቱ ሀገራት ግጭትና በካቴድራሉ ላይ የደረሰውም ጉዳት፡ ጦርነት እጅግ አውዳሚና ክፉ መሆኑን የሚያስተምር ነው። (ምንጭ፡- AP, AFP, Reuters)