Friday, 04 December 2020 00:00

ጾመ ነቢያት በዓለም ማዕዘናት

Written by  ዲ/ን ኅሊና በለጠ
ከኅዳር 15 ጀምሮ የሚገባውን የነቢያት ጾምን መጾም፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ የሚታወቅ ሥርዓት አይደለም። ሁሉም የኦርቶዶክስና የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ይህንን ጾም ይጾሙታል። ጾሙን የሚጾሙት ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ይህን ጾም ለመጾማቸው እንደ ዋና መሠረት የሚጠቅሱት ለጾሙ ፋሲካ የሆነውን የክርስቶስን ልደት በጾም ተዘጋጅቶ መቀበልን ነው። አብዛኞቹ ‹‹Nativity Fast›› ይሉታል፤ ‹‹ጾመ ልደት›› እንደ ማለት ነው። የቅዱስ ፊሊጶስ በዓል ከተከበረ በኋላ በመግባቱም ‹‹ጾመ ፊሊጶስ›› ተብሎ መጠራቱም የተለመደ ነው። በተለያየ አጠራር ብንጠራውም፡ ነቢያት የጌታችንን መውረዱንና መወለዱን ተስፋ በማድረግ አስቀድመው የጾሙት ጾም በመሆኑ በእኛ ቤተ ክርስቲያን ስያሜው ‹‹ጾመ ነቢያት›› መባሉ የሚታወቅ እውነታ ነው። የባይዛንታይን አብያተ ክርስቲያናት ከኅዳር ፮ (Nov. 15) እስከ ታኅሣሥ ፲፭ (Dec. 24) በመጾም ልደተ እግዚእን በታኅሣሥ ፲፮ (Dec. 25) ያከብራሉ። የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ አንዳንዶቹ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ግን ጾሙን ኅዳር ፲፱ (Nov. 28) ይጀምራሉ። የኅዳር ፲፱ ስንክሳርም ‹‹ወበዛቲ ዕለት ኮነ ጥንተ ጾመ ስብከተ ጌና ዘሮም ወአፍርንጊ ወሶርያ ወአርማንያ ዘእንበለ ግብጽ ወኢትዮጵያ ወኖባ - በዚችም ዕለት የሮም፣ የአፍርንጊ፣ የሶርያ፣ የአርማንያ ክርስቲያን ከግብጽ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከኖባ በቀር የስብከተ ጌና ጾምን የሚጀምሩበት ነው›› ብሎ የተጠቀሱት አብያተ ክርስቲያናት ጾሙን በኅዳር ፲፱ የሚጀምሩ መሆናቸውን ያስረዳል። አስቀድመን በጽሑፉ መጀመሪያ እንደ ገለጽነው ይህን የተመለከተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ጾሙ በኅዳር ፲፭ እንዲጀመር ያዛል።

 

ጾሙን የሚጾሙት ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ጸሎት፣ ንስሐና ምጽዋት አብረው በስፋት እንዲተገበሩ ያዛሉ። እንዲህ ከሆነም የልደተ ክርስቶስን ሱታፌና በረከት ለማግኘት ይበልጥ መዘጋጀት እንደሚቻል ይሰብካሉ። ከማንኛውም ሥጋ፣ ከወተት፣ ከዓሣ፣ ከቅባትና ከእነዚህ ውጤቶች ሁሉ መጾም እንደሚገባ ሁሉም ቢመክሩም፤ አንዳንዶቹ ወይን መጠጣትንም ከሰንበታት በስተቀር አይፈቅዱም። ዓሣና ዘይቶችን/ቅባቶችን በሰንበታት የሚፈቅዱም አሉ። ይህን በመሰለው ነገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትኅርምታዊ ምሳሌነት ለሁሉም ጎልቶ መነገር የሚችል ነው። የሚከለከሉት ነገሮች ሁሉ ሙሉ ጾሙ እስኪፈጸም የሚከለከሉ ናቸውና። አንዳንዶቹ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የወይን መጠጥን መከልከላቸው ግን የእነርሱም የትኅርምት ሥርዓት ቀላል እንዳልሆነ የሚያስተምር ነው።

የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት በሰንበት ብቻ ሳይሆን፡ በጾሙ ውስጥ በሚያከብሯቸው በተወሰኑ በዓላትም ዓሣን፣ ወይንንና ዘይትን/ቅባትን ይፈቅዳሉ። እነዚህ የሚያከብሯቸው በዓላትም የወንጌላዊው ማቴዎስ ኅዳር ፯ (Nov. 16)፣ የሐዋርያው እንድርያስ ኅዳር ፳፩ (Nov. 30)፣ የሰማዕቷ ቅድስት ባርባራ ኅዳር ፳፭ (Dec. 4)፣ የገባሬ መንክራት ኒቆላዎስ ኅዳር ፳፯ (Dec. 6)፣ የአግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ ታኅሣሥ ፲፩ (Dec. 20) እና የሌሎች የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ‹‹ቅዱሳን›› ናቸው። (የተጠቀሱት የቅዱሳኑ የመታሰቢያ ዕለታት በኦሪየንታል ኦርቶዶክስና በምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ቅዱሳኑ የሚታሰቡባቸው ናቸው። የግዴታ እኛ ቅዱሳኑን ከምናስብባቸው ቀናት ጋር አንድ ላይሆኑ ይችላሉ።) በአብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ በማዕርጋተ አጽዋም የጾመ ነቢያት ደረጃ ከዐቢይ ጾምና ከጾመ ፍልሠታ ቀጥሎ የሚገኝ ነው። ትኅርምቱም በዚያው ልክ ነው።

የቅብጥ ቤተ ክርስቲያን እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሁሉ የስምዖን ጫማ ሰፊውን ታሪክ በማሰብ በጾሙ ላይ ሦስት ቀናትን ጨምራ ትጾማለች። ይህን የነቢያት ጾም በሌላ አጠራር ‹‹ጾመ ምጽአት (Advent Fast)›› ብለው የሚጠሩና የክርስቶስን የመጀመሪያ ‹‹ምጽአት›› የሚያስቡም ብዙ ናቸው። ከነዚህ መካከል የአርመን ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ጾሙን በኅዳር ፲ (Nov. 19) ‹‹ጾመ ምጽአት›› ብላ ትጀምርና ታኅሣሥ ፳፰ (Jan. 6) የክርስቶስን ልደት ከማክበሯ በፊት ያለውን አንድ ሳምንት ‹‹ጾመ ልደት (Nativity Fast)›› ብላ ትጾማለች። (ምንጭ፡- www.oca.org, www.goarch.org, www.orthodoxwiki.org, www.stjohnsarmenianchurch.org)::

ጥንታዊ መሠረት ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ይህን ጾም መጾማቸው፡ ጾሙ ሐዋርያዊ መሠረት ያለው መሆኑን የሚመሰክር ነው። ይህም ከአምስት መቶ ዓመታት የዘለለ ታሪክ ለሌላቸውና ጾሙን ለማይጾሙት እንደ ፕሮቴስታንት ላሉት ቤተ እምነቶች ትምህርት መሆን የሚችል ነው።

 

Read 717 times