Friday, 06 November 2020 00:00

‹‹በኢትዮጵያ ‹መምህር ነበርኩ› ከምል ይልቅ ‹ተማሪ ነበርኩ› ብል ይቀለኛል… እባካችሁ ቤተ ክርስቲያን የኹሉም ናትና ከአንድ ብሔር ጋር ብቻ አታያይዟት›› ዶ/ር ጆሲ ጄኮብ

Written by  ዲ/ን ኅሊና በለጠ
ዶክተር ጆሲ ጄኮብ (ቀሲስ) በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ውስጥ ለአሥራ ስድስት ዓመታት ያስተማሩ የሕንድ የማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካህንና መምህር ናቸው። መምህሩ ከኮሌጁ የመምህርነት አገልግሎታቸው በተጨማሪ እዚህ በቆዩባቸው ዓመታት በሁለቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠነክርም በትጋት ሠርተዋል። ታዲያ ይህን ቆያታቸውን እና በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በማስመልከት Orthodoxy Cognate Page የተባለ ሚዲያ አጭር ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸው ነበር። ዶክተሩ በቃለመጠይቁ ላይ በመንፈሳዊ ኮሌጁ የነበራቸውን የአሥራ ስድስት ዓመት ቆይታ እንዲህ ሲሉ ገልጸውታል፡- ‹‹ከሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ነገረ መለኮትን እንዳስተምር ወደ ኢትዮጵያ የተላኩት ጥቅምት ፳፰፣ ፲፱፻፺፮ ዓ.ም. ነበር። በዚያም ለ፲፮ ዓመታት ያክል ቆይቼ ወደ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተመለስኩት በ፳፻፲፩ ዓ.ም. ነበር። በዚህም ብዙ ልምዶችን አግኝቼበታለሁ። ከተለያዩ ቦታዎች፣ ከተለያዩ የሥራ ዘርፎች፣ ከተለያዩ የሕይወት ዳራዎች ከሚመጡ ከብዙ ሰዎች ጋር ተገናኝቼአለሁ። ብዙ ተምሬአለሁ። እንደውም በኢትዮጵያ ‹መምህር ነበርኩ› ከምል ይልቅ ‹ተማሪ ነበርኩ› ብል ይቀለኛል።›› የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በተመለከተም ‹‹ውብ ነው›› ሲሉ ገልጸዋል፤ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነገረ መለኮት ውብ ነው። ነገር ግን በዓለም ላይ ብዙም አልታወቀም። ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኒቱ መጻሕፍት የተጻፉት በሀገር ውስጥ ቋንቋ፡ በተለይም በግእዝ ነው እንጂ በውጪ ቋንቋዎች አይደለም። ግእዝ በተለይም ከ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ የመነጋገሪያ ቋንቋ አልነበረም። ብዙ የቤተ ክርስቲያኒቱ መጻሕፍት የሚገኙት ግን አሁንም በግእዝ ነው። ባሕሉ ራሱ የግእዝ ባሕል ነው።›› በቅድስት ሥላሴ በሚያስተምሩበት ጊዜ በኮሌጁ ማኅበረሰብ ‹‹ፋዘር ጆሲ›› በሚል አጠራር የሚታወቁት እኚህ መምህር በሀገራችን ስላለው ወቅታዊ አለመረጋጋትም ሲገልጹ ሕዝቡ በጣም ሰላማዊ እንደ ሆነና ችግሮችን እየፈጠሩ ያሉት አንድን ሕዝብ እንወክላለን የሚሉ ጽንፈኞች እንደ ሆኑም አብራርተዋል። ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት በምን ዓይነት መሪዎችና የአመራር ስልት እንደ ቆየች በጥቂቱ የገለጹት ዶክተር ጆሲ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር በማቆሙና በመጠበቁ ረገድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዋጽኦ ቀላል እንዳልነበርም አጽንዖት ሰጥተው መስክረዋል። ሆኖም አሁን በሀገሪቱ ያሉ ጽንፈኞች ቤተ ክርስቲያንን አብዝተው መክሰሳቸውና ከብሔር ጋር ማያያዛቸው ቤተ ክርስቲያኒቱን ዋነኛ ተጠቂ እንዳደረጋትም አስረድተዋል። በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱት የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠልና የኦርቶዶክሳውያን መሠዋትም የጥቂት ጽንፈኞች የተሳሳተ የስብከት ፍረጃ ውጤት መሆኑን አብራርተዋል። ‹‹ቤተ ክርስቲያን ኩላዊት ናት እንጂ የአንድ ብሔር ብቻ አይደለችም›› ካሉ በኋላም ‹‹እባካችሁ ቤተ ክርስቲያን የኹሉም ናትና ከአንድ ብሔር ጋር ብቻ አታያይዟት›› ሲሉም መክረዋል።  
Read 932 times