Saturday, 02 January 2021 00:00

የጌታችን የልደት በዓል በዓለም ዙሪያ

Written by  ዲ/ን ኅሊና በለጠ

Overview

ልደተ እግዚእን እኛ በታኅሣሥ ፳፱ (January 7) ስናከብር፡ ምዕራባውያን በታኅሣሥ ፲፮ (December 25) ያከብራሉ። ከእኛ ጋር በአንድ ዓይነት ቀን የሚያከብሩ ብዙ የኦሪየንታልና የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት አሉ። ጥቂቶቹን ከአከባበር ሥርዓታቸው ጋር እስኪ በጥቂቱ እንዳሳቸው።  ከግብፅ አጠቃላይ ሕዝብ ክርስቲያኑ ፲፭ በ፻ ይሆናል። ከነዚህ መካከል ብዙዎችን የያዘችው የቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጌታችንን የልደት በዓል የምታከብረው በደመቀ ሁኔታ ነው። በዓሉ የሚውልበት የቅብጥ ወር ‹‹ኪያክ (Kiahk)›› ሲባል፡ ቅብጣውያኑ ከበዓሉ በፊት ለ፵፫ ቀናት ጾመ ነቢያትን ይጾማሉ። በጾሙ ወቅት ከሰንበታተ ክርስቲያን አገልግሎት በፊት ዘወትር ቅዳሜ ማታ ምእመናን ልዩ መዝሙራትን ይዘምራሉ። በበዓሉ ዋዜማ በታኅሣሥ ፳፰ ማታ ከሦስት ሰዓት ጀምሮ ምእመናን በየአብያተ ክርስቲያናቱ ይገኛሉ። የመቅደሱ ሥርዓት አራት ሰዓት ተኩል ሲል ይጀምርና እኩለ ሌሊትን ተሸግሮ ብዙ ጊዜ እስከ ሌሊቱ አሥር ሰዓት ይዘልቃል። የመቅደሱ አገልግሎት ተፈጽሞ ካህናቱ ሕዝቡን ካሰናበቱ በኋላ፡ ምእመናን ወደየቤታቸው በመሔድ ‹በትልቁ የልደት ገበታ› ከቤተሰባቸው ጋር ተሰይመው ጾማቸውን ይፈታሉ። ‹‹የኦርቶዶክስ የገና ዕለት›› ተብሎ በሚታወቀው በቀጣዩ ቀን፣ ማለትም በታኅሣሥ ፳፱ ምእመናን በየቤቱ እየሔዱ በመጠያየቅ በዓሉን በደስታ ያከብራሉ። ብዙ ጊዜ ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው ሲሔዱም ‹‹ካህክ (Kahk)›› የተባለውን ልዩጣፋጭ ብስኩት በስጦታነት ይወስዳሉ። የግብፅ ሕዝብ አብዛኛው ክርስቲያን ባይሆንም፡ የገና በዓልን ግን በአብዛኛው እንደ ብሔራዊ በዓል ማክበር ይፈልጋሉ፤ በዓሉ በሚከበርበት ወቅት ብዙ የገበያ እንቅስቃሴ ይኖራል፤ መንገዶች በዓሉን በሚገልጹ ጌጣጌጦች ያጌጣሉ። የግብፅ ሕፃናት እነርሱ ‹‹ባባ ኖኤል (Baba Noel)›› የሚሉት የገና አባት በበዓሉ ዕለት ስጦታ እንዲሰጣቸው ይናፍቃሉ። ከጣፋጭ ብስኩቶችም ‹‹ለባባ ኖኤል›› ብለው ያስቀምጣሉ።(https://www.whychristmas.com/cultures/egypt.shtml) የሕንድ የማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም በዓሉን በተመሳሳይ የአምልኮ ሥርዓት ብታከብርም፣ በቤተ መቅደስ ውስጥ ከሚፈጸመው አገልግሎት ውጪ ደመራን መደመርም በቤተ ክርስቲያኗ የተለመደ ነው። ቀሲስ ዶክተር ኬኤም ጊዮርጊስ የተባሉት የቤተ ክርስቲያኗ ካህን ይህን በተመለከተ እንዲህ ይላሉ፡- ‹‹ከልደተ እግዚእ በዓል አገልግሎት አንዱ የሆነው ደመራን የመደመር ሥርዓት ከሶሪያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተወረሰ ትውፊት ነው። ደመራው በሚለኮስበት ቦታ ምእመኑ ከበውት ይቆማሉ። በዚያም የሉቃስ ወንጌል ይነበባል።›› ደመራውን ከበው በዓሉን የሚያከብሩት ምእመናን በእጃቸው ዕጣንን ይይዛሉ። ከዚያም በታዘዙ ጊዜ ዕጣኑን ወደ ደመራው እሳት ይጨምሩታል። የዕጣኑ መልካም መዓዛ የምሕረት፣ የቅድስና፣ የንጽሕና ምሳሌ ነው። እሳቱ ነዶ ካለቀ በኋላም ምእመናን አመዱን አፍሰው በመውሰድ በጸበል በመበጥበጥ ቤት ውስጥ ታሞ ላለ ሰው ይሰጡታል፤ ይህም ለሥጋዊም ለመንፈሳዊም ፈውስ የሚጠቅም ነው። የደመራው እሳት በአንድ በኩል በብርሃኑ የክርስቶስን ብርሃንነት የሚመስል ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በማቃጠል ባሕርይው የጌታችንን ፈራጅነት ይመስላል። (https://www.google.com/amp/s/indianexpress.com/article/religion/christmas-celebration-indian-church-jesus-birth-ritual-5508260/lite/) የሶሪያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አከባበሯ በብዛት ከሕንድ ጋር የሚመሳሰል ስትሆን የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግን በዓሉን በተለየ መልኩ አንድ ቀን ቀደም ብላ በታኅሣሥ ፳፰ ቀን ታከብራለች። በዕለቱ የጌታችንን ልደት ብቻ ሳይሆን ጥምቀቱንም አክብረው ያልፋሉ። አንዳንድ አርመናውያን ከበዓሉ በፊት ያለውን ሳምንት ሙሉ ይጾማሉ። የገና ዋዜማ ላይ የሚመገቡት ምግብ ‹‹ኬቱም (Khetum)›› ተብሎ ይጠራል። (https://www.whychristmas.com/cultures/armenia.shtml):: ከኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ውጪ ያሉት የራሺያና የግሪክ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትን የመሰሉት የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትም በዓሉን በታኅሣሥ ፳፱ በቅዳሴና በተለያዩ መሰል የአምልኮ ሥርዓቶች በድምቀት ያከብራሉ።
Read 281 times