Friday, 04 September 2020 00:00

የጥያቄዎቻችሁ መልስ

Written by  ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን

Overview

 በጥያቄዎቻችሁ መልስ ዓምዳችን ወርኀ ጳጕሜንና የዘመን መለወጫ (ዕንቁዕጣጣሽን) በተመለከተ የሚነሡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርገን ምላሽ ይሰጡን ዘንድ በማኅበረ ቅዱሳን መደበኛ አገልጋይ የሆኑትን አባ ዐሥራተ ማርያም ደስታን ጋብዘናቸዋል። ቆይታችንን እንዲህ አዘጋጅተነዋል፤ መልካም ቆይታ፡፡ ሐመር፡- አባታችን የምናነሣቸው ጥያቄዎች ከጳጕሜንና ከዘመን መለወጫ ጋር የተያያዙ ይሆናሉ፡፡ ለመሆኑ ጳጉሜን ማለት ምን ማለት ነው? አባ ዐሥራተ ማርያም፡- ጳጕሜን ማለት ቃሉ የጽርዕ ወይም የግሪክ ሲሆን ሄፓጎሜን ይባላል፡፡ ትርጓሜውም ጭማሪ ማለት ነው። በግእዝ ተውሳክ ይባላል። በሌላ አገላለጽ ከዐውደ ወርኅ ስለተረፈና በዓመት መጨረሻ ስለተገኘ ተረፈ ዓመት ይባላል። በዓመተ ዑደተ ፀሐይ አንድ ዓመት ፫፻፷፭ ቀናት ነው። ይህን ለ፴ ስናካፍል ፲፪ ይደርስና ፭ ይቀራል። እነዚህ ፭ ቀናት ጳጕሜን ተብለው ስለሚጠሩ ጳጕሜን ማለት ጭማሪ ወይም ተረፈ ዓመት ተብሎ ይጠራል።  ሐመር፡- አባታችን ከዚህ ጋር ተያይዞ ጳጒሜን ሦስቱን ዓመታት አምስት አምስት ቀናት ሆነው ሲውሉ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ ስድስት ቀን ይሆናል፡፡ ምክንያቱን  ቢያብራሩልን? አባ ዐሥራተ ማርያም፡- ይህ የሚሆንበት ምክንያት ከእያንዳንዱ ዓመት ተጨማሪ ስድስት ስድስት ሰዓት ትርፍ አለ። ይህ ስድስት ሰዓት በዐራተኛው ዓመት ፳፬ ሰዓት (አንድ ቀን) ይሆናል። በዘመነ ሉቃስ ጳጕሜን ስድስት የሚሆነው በየዓመቱ የተረፉት ስድስት ስድስት ሰዓታት ተደምረው አንድ ቀን ሲለሚሞሉ ነው።

 

ሐመር፡- በጳጕሜን ወር ሰዎች ይጠመቃሉና ምክንያቱ ምንድነው?

አባ ዐሥራተ ማርያም፡- ይህን በሁለት መንገድ ማየት ይቻላል። የመጀመሪያው ከኢዮብ ጋር ተያይዞ ሲተላለፍ የመጣ ነው። ኢዮብ በደዌ ሥጋ በተመታ ጊዜ በማየ ዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ተፈወሰ፤ አዲስ ማንነትንም አገኘ። ዛሬም ሰዎች በዚያ ልማድ አምስቱንም ወይም ስድስቱንም ዕለታት በአካባቢያቸው ወደ ሚገኘው ወንዝ እየሄዱ ይጠመቃሉ። አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ ለመቀበል ሲሉ የሚያደርጉት ነው። ታሪካዊ አመጣጡ ኢዮብን መሠረት ያደረገ ነው።

ሁለተኛው ግን በዚህ በጳጕሜን ወር ሁለት ዐበይት ነገሮችን ልብ ማለት ያስፈልጋል። እነርሱም አንደኛው ርኅወተ ሰማይ ሲሆን፣ ሁለተኛው የሊቀ መልአኩ የቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ በዓል ነው። ርኅወተ ሰማይ ሲባል በሰማይ መከፈት መዘጋት ኑሮበት አይደለም። እስጢፋኖስ የእግዚአብሔርን ክብር ባየ ጊዜ ሰማይ ተከፍቶ አየሁ በማለት እንደተናገረው ዓይነት ነው። በሐዋርያት ሥራ “በእስጢፋኖስም ላይ መንፈስ ቅዱስ መላ፤ ወደ ሰማይም ተመለከተ፤ የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየ። እነሆ ሰማይ ተከፍቶ የሰው ልጅም  በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ አለ” (ሐዋ.፯፥፶፭-፶፮) ተብሎ እንደተጻፈ የማይታይና የማይገለጥ ምሥጢር ተገልጦ ሲታይ ሰማይ ተከፈተ ተባለ። እንደዚሁ ሁሉ የእግዚአብሔር ምሕረት ቸርነት ወደ ሰው፣ የሰው ጸሎት ልመና ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ መሆኑን የሚያመለክት ነው።  የመልአኩ የቅዱስ ሩፋኤልን ዓመታዊ በዓልም የምናከብረው በዚህ ወር ውስጥ ማለትም በጳጕሜን ፫ ነው። በዚህ ዕለት የቅዱስ ሩፋኤል በዓለ ሢመት ነው። እንዲሁም በዚህ ዕለት የጸለይነውን ጸሎት ወደ እግዚአብሔር ያደርስልናልና እናከብረዋለን። 

በዚህ ዕለት ዝናም የዘነመ እንደሆን ሰዎች ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ እንፈወሳለን ብለው ስለሚያምኑ ይጠመቃሉ። ከላይም እንደተገለጸው ርኅወተ ሰማይ ማለት የሰው ጸሎት ልመና ወደ እግዚአብሔር  ሲደርስ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ ምሕረት፣ ፈውስ ወደ ሰው ይደርሳል። ሰው የሚጠመቀውም ለመፈወስ ነው። ይህ ማለት የእግዚአብሔርን ምሕረት፣ ቸርነት ለማግኘት ማለት ነው። ስለዚህ በዚህ በጳጕሜን ወር የሚደረገው ጥምቀት በቅዱስ ሩፋኤል ስም በፈለቀ ጠበል የሚደረግ ጥምቀት ማለት ነው።  

ሐመር፡- ጳጕሜንን  በዚህ መልኩ ከተመለከትን ከዚሁ ጋር ተያይዞ ዕንቍጣጣሽም አለና እስኪ ምንነቱን ቢያስረዱን?

አባ ዐሥራተ ማርያም፡- ዕንቍጣጣሽ የተለያየ ትርጕም አለው፤ የተወሰነውን ለመጥቀስ ያህል፡- አበባ፣ ዕንቍዕ ዕፅ አወጣሽ፣ ዕንቍዕ ዕጣ ወጣሽ፣ ዕንቁ ለጣጣሽ ማለት ነው። እያንዳንዱ ለምን እንዲህ እንደተባለ ዘርዘር አድርጎ ማየት ስለሚያስፈልግ ከላይ በተጠቀሱበት ቅደም ተከተል እንመለከት፡-

ሀ. ዕንቍጣጣሽ፡- አበባ ማለት ነው። ዕንቍጣጣሽ አበባ የሚባለው እንደሚታወቀው ይህ ወቅት አበባ የሚፈነዳበት ነው። አበባ ለፍቅር፣ ለደስታ መግለጫ ስጦታ ሆኖ ስለሚሰጥ ለአዲስ ዓመትም ስጦታ መስጠት የተለመደ ነው። በአዲስ ዓመት ልጃገረዶች ለታላላቅ ሰዎች የሚሰጡት ስጦታ አበባ ሲሆን ዕንቍጣጣሽ ሰጡን ይባላሉ። ያልሰጡትንም ዕንቍጣጣሽ ሰጠሽ? እየተባባሉ ይጠያየቃሉ። በሚሰጡበትም ጊዜ ዕንቍጣጣሽ በማለት ይሰጣሉ። አበባ እነሆ እንደማለት ነው። ስለዚህ ዕንቍጣጣሽ ማለት አንደኛው ትርጕም አበባ ማለት ነው።

ለ. ዕንቍጣጣሽ፡- ዕንቍዕ ዕፅ አወጣሽ፡- ሁለተኛው ትርጕም ዕንቍዕ ዕፅ አወጣሽ ማለት ሲሆን ከኖኅ ዘመን ክሥተት ጋር የተያያዘ ነው። ኖኅ የመጣውን የጥፋት ውኃ በመርከብ ሆኖ ካለፈ በኋላ እየቀነሰ ሲሄድ መርከቧም ከአራራት ተራራ ላይ አርፋ ነበርና መሥዋዕት ሠውቶ መጉደል አለመጉደሉን ለማወቅ አስቀድሞ ቁራን ላከው። በዚያው ሳይመለስ ቀረ። ዛሬ በሀገራችን የቁራ መልክተኛ የሚባለው ከዚያ ጋር ተያይዞ ነው። ርግብን ሲልካት ፍሬ ያለው አበባ ቆጽለ ዕፀ ዘይት አመጣች፤ የወይራ ቅጠል ማለት ነው። በዚህ ጊዜ ኖኅ ውኃው እንደጎደለ ስለተረዳ ከመርከብ ወጣ፡፡ ምድር ለምልማ፣ አጊጣና አምሮባት ሲያገኛት “ዕንቍዕ ዕፅ አወጣሽ” በማለት ተናገረ። እኛም ዛሬ ክረምቱ አልፎ ምድር ለምልማ፣ በአበባ አጊጣና አምሮባት የምትታይበት ወቅት ስለሆነ እንቁጣጣሽ እንላለን።

ሐ. ዕንቍ ዕጣ ወጣሽ ማለት ነው፡- ይህም ከኖኅ ልጆች ጋር የተያያዘ ታሪክ አለው። ታሪኩም ኖኅ ከጥፋት ውኃ በኋላ በመልአኩ ዳኝነት በዕጣ ርስት ሲያከፋፍል ለካም ወደ አፍሪካ ደረሰውና የካም ልጅ ኩሽ ወደ ኢትዮጵያ መጣ። ኢትዮጵያን ሲያገኛት እጅግ የለመለመች መልካም ሀገር ሆና አገኛት። በዚህ ጊዜ “ዕንቍ ዕጣ ወጣሽ” በማለት ደስታውን ገለጸ።

መ. ዕንቍዕ ለጣጣሽ ማለት ነው። የመጨረሻው ከንግሥተ ሳባ ጋር የተያያዘ ነው። ይህም ንግሥተ ሰባ የሰሎሞንን ዝና ሰምታ ልዩ ልዩ ስጦታዎችን  ይዛ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች። እርሷ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዳ ንጉሥ ሰሎሞንን ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን ጠይቃ የጠየቀቻቸውም ጥያቄዎች ተመልሰውላት እንደተመለሰች በመጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ ፲፥፩-ፍጻሜ የተጻፈ ሲሆን አባቶች ከዚህ ጋር አያይዘው በታሪክ መዝገብ ተጽፎ ባይገኝም በትውፊት አባቶች የሚናገሩት ታሪክ አለ። እርሱም ከሰሎሞን ጋር ተገናኝታ፣ ለእርሱ ልዩ ልዩ ስጦታዎችን አበርክታ፣ እንቆቅልሿ ተፈቶላትና ቀዳማዊ ምኒልክን ፀንሳ ስትመለስ እርሱም በፈንታው “ዕንቁ ለጣጣሽ፣ ለቤትሽ ጣጣ ይሁንሽ” ብሎ ዕንቍዕ ሰጥቶ ሰደዳት። ስለዚህ ዕንቍዕ ለጣጣሽ ማለት ነው ተብሎ ይተረካል። 

ሐመር፡- አባታችን ዕንቍጣጣሽ አንዳንዴ የዘመን መለወጫ እየተባለም ይጠራልና ትክክለኛው ስያሜ ይህ ነው ማለት ይቻላል? ከተቻለ ቢገልጹልን።

አባ ዐሥራተ ማርያም፡- በአጠቃላይ ዕንቍጣጣሽ ማለት ከላይ የዘረዘርናቸውን ትርጕሞች የሚይዝ ሲሆን በስያሜ ደረጃ አዲስ ዓመት፣ ቅዱስ ዮሐንስ፣ ርእሰ ዐውደ ዓመት ወዘተ እየተባለ ይጠራል። የስያሜው ጉዳይ ሳይሆን ለምን እንደዚህ ተብሎ ይጠራል የሚለው ነው መታየት ያለበት።

ርእሰ ዓውደ ዓመት የተባለው በዘመኑ መለወጫ የሚውል የመጀመሪያው ዓመታዊ በዓል ስለሆነ ነው። ለዚህ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም “ርእሰ ዐውደ ዓመት ዮሐንስ ወላዴ መጥቅዕ ወአበቅቴ፣ መጥቅዕንና አበቅቴን የሚወልድ የዐውደ ዓመት ሁሉ ራስ ዮሐንስ” ብሎ ነው ገለጸው። በዚህ ዕለት መገበሪያ፣ ወይን፣ ዕጣን ወዘተ ቀርቦ ጸሎተ ዕጣን ይደገማል፤ ሊቃውንቱ ባሕረ ሐሳብ ያወጣሉ፤ በባሕረ ሐሳብ የሚወጡት የዓመቱ በዓላትና አጽዋማት ተሰልተው ይታወጃሉ። ስለዚህ ርእሰ ዐውደ ዓመት ተብሎ ይጠራል። የበዓላትና የአጽዋማት ራስ መገለጫ፣ መታወቂያ ማለት ነው።

ሌላኛው ስያሜ ቅዱስ ዮሐንስ ነው። ይህ ስያሜ የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ምትረተ ርእስ መስከረም ሁለት ስለሚታሰብ ከዚህ ጋር አያይዞ ለመግለጽ ነው። ምትረተ ርእሱን ለማስታወስ ቅዱስ ዮሐንስ “ዋርሳ አትውረሱ” እያለ ሲያስተምር ሄሮድስንም “የወንድምንህን የፊልጶስን ሚስት ታገባ ዘንድ አይገባህም” እያለ ስለገሠጸው አስሮት ነበርና የልደት በዓሉን በሚያከብርበት ጊዜ የሄሮድያዳ ልጅ በዘፈን አስደሰተችው። በዚህ ጊዜ ከደስታው ጽናት የተነሣ የለመንሽኝን ሁሉ አደርግልሻለሁ አላት። እናቷን ብታማክር የዮሐንስን ራስ ቆርጦ ይስጥሽ አለቻት። በዚህ ጊዜ እንቢ እንዳይላት የገባው ቃል አስጨነቀው። እሺ እንዳይላት ዮሐንስን እንደ ነቢይ ይቆጥሩት ነበርና ሕዝቡን ፈራ፡፡ ይሁን እንጂ “ሕዝቡን በጦር እታገለዋለሁ” ብሎ የዮሐንስን ራስ አስቆርጦ ሰጣት። ይህ የሆነበት መስከረም ሁለት ቀን ስለሆነ በዓሉን ከዚያ ጋር አያይዞ ለማክበር አዲሱን ዘመን ቅዱስ ዮሐንስ ብለን እንጠራዋለን።

ከላይ የተገለጸው አንደኛው ምክንያት ሲሆን በዋናነት ግን ቅዱስ ዮሐንስ ተብሎ የሚጠራበት ምክንያት ቅዱስ ዮሐንስ መንገድ ጠራጊ ይባላል። የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣት ከስድስት ወር አስቀድሞ የሰበከ፤ እኔ የጫማውን ማሰሪያ እፈታ ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በፊት የነበረው ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ነው። “እኔ ለንስሓ  በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን ለመሸከም የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም  ያጠምቃችኋል” (ማቴ.፫፥፲፩)  እያለ ያስተማረ የሐዲስ ኪዳንን መምጣት የነገረ ነቢይ ወሐዋርያ ነው። እርሱ የብሉይ ኪዳንና የሐዲስ ኪዳን መሸጋገሪያ ድልድይ ነው። ስለዚህ አበው ከአሮጌው ዘመን ወደ ሐዲሱ ዘመን የምንሸጋገርበትን ዘመን በቅዱስ ዮሐንስ ሰይመውታል። ቅዱስ ዮሐንስ ከብሉይ ኪዳን ወደ ሐዲስ ኪዳን መሸጋገሪያ እንደሆነ ሁሉ በቅዱስ ዮሐንስ የተሰየመው የእኛም አዲስ ዓመት ከክረምት ወደ መፀው የምንሸጋገርበት ነው። ስለዚህ የሐዲሱ ዓመትና የአሮጌው ዓመት መሸጋገሪያ ቅዱስ ዮሐንስ ይባላል።

ሐመር፡- አባታችን ይህ ስያሜ ከአራቱ ወንጌላውያን አንዱ በሆነው ዮሐንስ የተሰየመ ነው ብለው የሚያስቡ ሊኖሩ ይችላሉ ደግሞም አሉና ይህን ቢያብራሩልን?

አባ ዐሥራተ ማርያም፡- አራቱ ወንጌላውያን ዘመኑን ለአራት ተከፋፍለው እየተፈራረቁ ምግብናቸውን ያከናውናሉ። በየራሳቸው ዘመን ዘመነ ማቴዎስ፣ ዘመነ ማርቆስ፣ ዘመነ ሉቃስና ዘመነ ዮሐንስ እየተባሉ ይጠራል። ከስያሜያቸውም በወንጌልም አጉልተው ከጻፉት አንጻር የየራሳቸው ምሳሌ አላቸው። ማቴዎስ በገጸ ሰብእ፣ ማርቆስ በገጸ አንበሳ፣ ሉቃስ በገጸ ላህም፣ ዮሐንስ በገጸ ንስር ይመሰላሉ። የአዲስ ዓመት ስያሜ ቅዱስ ዮሐንስ ተብሎ የሚጠራው በመጥምቁ ዮሐንስ እንጂ በወንጌላው ዮሐንስ አይደለም። ይህ ከላይም እንደተገለጸው መጥምቁ ዮሐንስ የብሉይ ኪዳን እና የሐዲስ ኪዳን መሸጋገሪያ ድልድይ ነውና የዘመኑም ስያሜ ክረምት አልፎ በጋው የሚተካበት ስለሆነ አሮጌው ዘመን አልፎ ሐዲሱን ዘመን የምንቀበልበት ዓመታዊ በዓል በመጥምቁ ዮሐንስ ተሰይሟል።

ሐመር፡- አባታችን የኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ ለምን በመስከረም ሆነ? ለምን እንደሌሎች በታኅሣሥ ወይም በሌላ ወር አልሆነም? 

እንግዲህ በመጽሐፍ እንደሚታወቀው እስራኤላውያን ከግብፅ ከ፬፻፴ የመከራ ዘመናት በኋላ ወጥተው፣ በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት፣ በሙሴ መሪነት ባሕር ተከፍሎላቸው፣ ጠላት ተገድሎላቸው ሲወጡ ይህን ነፃ የወጡበትን ዕለት የአዲስ ዓመት መለወጫ አድርገውታል። ይህ ወር ሚያዝያ ነው። ከመከራ የወጣንበት ነው፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን የተሸጋገርንበት ነው ለማለት ነው።

እንደዚህ ሁሉ የእኛም አዲስ ዓመት በረከታቸው ይድረሰንና የቀደሙ አባቶቻችን እንዳስተማሩን የኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ በመስከረም የሆነበትን ምክንያት፤ ክረምት የመከራ፣ የጨለማና የሥቃይ ምሳሌ ነው። ስለዚህ ከዚህ መከራ የምንሸጋገርበትን፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን የምንወጣበትን ወቅት አዲስ ዓመት ብለን እናከብራለን በማለት ያስረዳሉ። ደግሞም ከላይም እንደተገለጸው መስከረም ማለት ምስየተ ክረምት፣ የክረምት መካተቻ፣ ማለት ነውና ክረምቱ አልፎ ምድር በአበባ የምታሸበርቅበት ወቅት ሲመጣ አዲስ ዓመት እናከብራለን። ቅዱስ ያሬድም “ኀለፈ ክረምት ቆመ በረከት ተሠርገወት ምድር በሥነ ጽጌያት፣ ክረምት አለፈ፤ በረከት ተተካ፤ ምድርም በአበቦች አጌጠች” ብሎ እንደገለጸው ምድር የምትፈካበት፣ በአበቦች የምታጌጥበት፣  እውነትም አዲስ ዘመን የምናይበት ነውና በዚህ ወቅት ተደርጓል።

አዲስ ዓመት ማለት አዲስ ነገር ስናይ ነውና በውኃ ተሸፍና የነበረችው ምድር ውኃዋ ጎድሎላት፣ ዕፅዋቱ ለምልመው አብበው፣ አሸብርቀው ለምድር ጌጥ ሆነው፣ ሙላቱ፣ ጨለማው፣ ጭቃው፣ መከራው አልፎ በአበባ ያሸበረቀች ምድር፣ በዕፅዋት ልምላሜ የፈካች ምድር የምናይበት ነው። ከላይ እንደተገለጸው ኖኅ በውኃ ተሸፍና የነበረችው ምድር ውኃው ጎድሎላት በልምላሜ አጊጣ፣ አብባ ሲመለከታት ዕንቍ ዕፅ አወጣሽ እንዳላት እኛም በውኃ ሙላት ስትናጥ  የነበረችው ምድር በልምላሜ፣ በአበባ ወዘተ አጊጣ ስንመለከት እነዚህን አበቦች እያየን የምንደሰትበት ወቅት ነውና በዚህ ወቅት አዲስ ዓመት ብለን እናከብራለን።

ሐመር፡- አባታችን ጊዜዎን ሰጥተው ላቀረብንልዎ ጥያቄ ተገቢ የሆነውን መልስ ስለሰጡን እግዚአብሐሔር ያክብርልን፤ የአገልግሎት ዘመንዎን ይባርክልን፤ ቃለ ሕይወት ያሰማልን።

አባ ዐሥራት፡- አሜን እናንተንም እግዚአብሔር ይባርክልን፣ ማኅበሩን ይጠብቅልን። 

 

Read 741 times