Friday, 16 October 2020 00:00

 ተስፋ  አያሳፍርም (ሮሜ ፭፥፭)

Written by  ዲ/ን ዐብይ ሙሉቀን
የሰው ልጅ ጥንት አታድርግ የተባለውን ሲያደርግ፣ አትብላ የተባለውን ሲበላ የተሰጠውን ተነጠቀ፤  ልጅነቱን፣ ገዥነቱን፣ ክብሩን  ወዘተ አጣ። ይሁን እንጂ በተሰጠው አእምሮ ተጠቅሞ በሠራው ስሕተት ተጸጸተ፤ የበደለውን አምላኩን ይቅር በለኝ በማለት አነባ። የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትን የማይነሣ አምላክ ጽኑዕ የሆነ ቃል ኪዳን ሰጠውና  የተወሰደችበትን ልጅነት በዚህም ምክንያት ያጣትን ርስት፣ እንደሚያገኝ ጸኑዕ ተስፋን ሰንቆ በተፈቀደለት ምድር መኖር ጀመረ።  ዛሬም ቢሆን ሰው አእምሮውን ጨርሶ ካላጣ በቀር ባለተስፋ ነው። ምን አልባት ተስፋ የሚያደርገው ነገር ይለያይ እንደሆነ እንጂ በውስጡ ተስፋውን ሰንቆ የማይጓዝ የለም።  አንዳንዱ ሥራውን ተስፋ ያደርጋል፤ አንዳንዱ ትምህርቱን ተስፋ ያደርጋል፤ አንዳንዱ ሀብቱን ተስፋ ያደርጋል። ይህ ሁሉ ግን የሚያዋጣ አይደለም። ምክንያቱም አንድ ቀን ያልፋልና፤ ጭንቅ ሲመጣ ከመጣው መከራ አያድንም ራሱም አይድንም። ክርስትናውን በአግባቡ የተረዳው ደግሞ ፈጣሪውን ተስፋ ያደርጋል። ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ “ሰው ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው።” (ሰቆ. ኤር. ፫፥፳፮) እንዲል። ስለዚህ ሰዎች እግዚአብሔር አምላካቸውን በማመን ማዳኑን ፣ ጥበቃውን፣ መግቦቱን፣ ይልቁንም ለሰው ልጅ ያለውን ጽኑዕ ፍቅር በማሰብ ተስፋ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በዚህ ርእሰ ጉዳይ የተስፋን ምንነት፣ ተስፋ የሚያስቆርጡ ፣ በተስፋ ብንኖር የምናገኛቸውን ነገሮችና መሰል ጉዳዮችን እንመለከታለን። ተስፋ ምንድን ነው? ተስፋ ወደፊት እንዲሆንልን፣ እንዲደረግልን፣ እንዲሰጠን የምንፈልገውን ነገር ይሆንልኛል፤ ይሰጠኛል፤ ይደረግልኛል ብሎ ማመን ነው። ይህንንም አስመልተው ደስታ ተክለ ወልድ ዐዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት በተሰኘ መጽሐፋቸው “ተስፋ፡- አለኝታ፣ ወደፊት አገኛለሁ የማለት ጽኑዕ እምነት” (ገጽ ፲፪፻፸፬) በማለት ይገልጹታል። ስለሆነም እንደ እርሳቸው አገላለጽ ተስፋ ማለት የወደፊት ምኞት፣ አገኛለሁ፣ ይሆንልኛል፣ ይደረግልኛል የሚል ጽኑዕ እምነት እንደሆነ ነው። ተስፋ በክርስትና ሕይወት መሠረታዊው ጉዳይ ነው፡፡ ሰው በሚያየውና በሚጨብጠው ነገር ቢተማመን ምንም የሚያስደንቅ ነገር የለውም፡፡ ነገር ግን በሥጋዊ ዐይን የማያዩትን፣ በሥጋዊ እጅ የማይዳስሱትንና የማይጨብጡትን አምላክ “የፈለግሁትን ይሰጠኛል፤ የሚጠቅመኝን ያደርግልኛል ለምኘው አያሳፍረኝም” ብሎ ማመን እጅግ የሚደንቅ ነገር ነው፡፡ ስለሆነም በሃይማኖት ስንኖር ዋናው እና ትልቁ መሣሪያችን ተስፋ ነው፡፡ ሃይማኖት ፈጣሬ ሰማያት ወምድር የሆነውን እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ ነው የተባለውም ለዚህም ነው፡፡ ተስፋ የሚታየውን በማይታየው ይቀይራል፡፡ አብርሃም በሽምግልና ዘመኑ ያገኘውን አንድ ልጁን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው በዐይነ ሥጋ ሳይሆን በዐይነ ኅሊና የሚታይ የተሻለ ጥቅም ስለነበረው ነው፡፡ በመጽሐፍ ‹‹አብርሃምም እግዚአብሔር በፈተነው ጊዜ ልጁን ይስሐቅን ይሠዋው ዘንድ በእምነት ወሰደው፡፡ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል ብሎ ተስፋ ያደረገለትን አንድ ልጁን አቀረበው፡፡ እግዚአብሔር ከሙታን ለይቶ ሊያስነሣው እንደሚችል አምኗልና፤ ስለዚህም ያው የተሰጠው መታሰቢያ ሆነለት›› (ዕብ.፲፩፥፲፯-፲፱፤ ዘፍ.፲፪፥፩) ተብሎ የተነገረው ለዚህ ነው፡፡ አብርሃም የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ በተስፋም ከሚያውቀው ሀገር፣ ከሚያውቀው ሕዝብ ወጥቶ ወደማያውቀው ሀገር፣ ወደማያውቀው ሕዝብ ሄደ።  በሰው ሰውኛው ሲታይ አብርሃም የፈጸመው ትክክል አይደለም ሊባል ይችላል፡፡ ምክንያቱም ‹‹በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃል›› እየተባለ ያንኑ የዘሩ መጠሪያ የሆነውን ሠዋ ሲባል ‹እሺ› ብሎ መሄድ ምን ያህል እምነትና ጽኑዕ ተስፋ እንዳለው የሚያስረዳ ነው፡፡ አብርሃም አንድ ልጁን ለእግዚአብሔር አልከለከለውም፤ እንዲሁ እግዚአብሔርም አንድያ ልጁን ለአብርሃም አልከለከለውም፡፡ እንኳን ለአብርሃም በእምነት ለታዘዘው፣ የሚታየውን በማይታየው ለውጦ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጎ ከሀገሩ ለወጣው ይቅርና ለጠላቶቹ እንኳን አልከለከላቸውም፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት በእንደዚህ ያለ ጽኑዕ ተስፋ ያኖራል፤ በተስፋ መኖር ብቻም ሳይሆን ከክፉ ሁሉ ያለ ድንጋጤ ያሳርፋል። ስለሆነም “ተስፋ አያሳፍርም” በማለት ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ የገለጸውን ልብ ማለትና በልቡና ሠሌዳ ማተም ያስፈልጋል።  ተስፋ በምቾት ጊዜ፣ ምንም መከራና ፈተና በሌለበት ወቅት ሳይሆን በሰው ሰውኛው አይቻልም በሚባልበት የጭንቅና የመከራ ዘመን ሊታጠቁት የሚገባ ረቂቅ መንሣሪያ ነው።  ተስፋ መቁረጥ ከምን ሊመጣ ይችላል? ሰዎች ሥጋዊ ፍላጎት በሚያይልበት ዓለም፣ የክፋት፣ የተንኮል፣ የኃጢአት ወሬ በሚሰማበት ዓለም እየኖሩ የዚህ ችግር ሰለባ ሳይሆኑ በሃይማኖት ጸንተው በጎ ምግባር ሠርተው መኖር ባለመቻላቸው ተስፋ ይቆርጣሉ። ተስፋ የሚቆርጡባቸው ምክንያቶች ደግሞ በርካታ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህ ክፍል ግን የተወሱትን ብቻ እንመለከታለን። ፩. የእግዚአብሔርን ቃል አለመስማት እግዚአብሔር አስቀድሞ መስማት እንድንችል ጆሮ፣ እንድናስተውል አእምሮ፣ የሰማነውን ደግሞ በተግባር ማዋል የሚያስችል አቅም ፈጥሮልናል። መቼም ቢሆን እኛ የማንችለውን አላዘዘንም፤ አያዘንምም። ነገር ግን የምንችለውን ባለማድረጋችን ሁሌም ስንጎዳ እንኖራለን። አዳም የእግዚአብሔርን ቃል ባለመስማት ተጎዳ፤ በርካታ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ባለመስማት ተጎዱ፣ ሰብአ ትካትን፣ ሰብአ ሰዶምን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። በአንጻሩ የእግዚአብሔርን ቃል የሰሙት የነነዌ ሰዎች ደግሞ ከመጣባቸው መዓት ድነዋል። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ማለት አድርጉ የተባልነውን ማድረግ፣ አታድርጉ የተባልነውን ደግሞ አለማድረግ ነው፤ ቃሉ ሕይወት ነውና። ወንጌላዊው ዮሐንስ በመልእክቱ ‹‹ንዜንወክሙ በእንተ ውእቱ ዘሀሎ እምቅድም ውእቱ ዘሰማዕናሁ በዕዘኒነ ወዘርኢናሁ በአዕይንቲነ ወዘጠየቅናሁ ወዘገሠሣሁ እደዊነ በእንተ ነገረ ሕይወት፤ ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያ የነበረውንና በጆሯችን የሰማነውን በዓይናችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን  እናወራለን›› በማለት ስሙት የተባልነው ቃል የሕይወት ቃል እንደሆነ ጽፎልናል፡፡ (፩ዮሐ.፩፥፩) ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በጾመ ድጓ ድርሰቱ ‹‹ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኵሉ ዘያሐዩ በቃሉ፤ ከላይ ከሰማይ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት፤   በቃሉ የሚያድነውን የሁሉ ጌታ ምንም አላወቁትም›› (ጾመ ድጓ፣ ዘዘወረደ)  በማለት ስሙት የተባልነው ቃል መድኃኒት መሆኑን፤ መድኃኒት የሆነው ቃል ደግሞ በቦታ የማይወሰን አምላክ ሲሆን ልዕልናውን ለመግለጽ ከላይ የወረደውን ተብሎ የተነገረለት የሕይወት ቃል መሆኑን ያስረዳናል። ይህን ከላይ የወረደውን አምላክ አይሁድ የሰቀሉት፣ የሁሉ ጌታ፣ በቃሉ የሚያድን እነርሱ ግን ያላወቁት አምላክ እንደሆነ ሊቁ ያስረዳናል። ስለዚህ ይህን ቃል ካለመስማት የተነሣ ተስፋ መቁረጥ ላይ ያደርሳል።  መፍቀሬ ጥበብ ሰሎሞን ‹‹ ቃሌን የሚሰማ ግን በተስፋ ይኖራል፤ ከክፉም ሁሉ ያለድንጋጤ ያርፋል›› (ምሳ. ፩፥፴፫) በማለት የገለጸውን ማስታወስ ያስፈልጋል። የእስራኤል ንጉሥ ጠቢቡ ሰሎሞን በንግሥናው ዘመን ለሕዝቡ በምሳሌ ቃሌን ስሙ እያለ በተደጋጋሚ ይናገር ነበር። ነገር ግን ቃሌን ስሙ የሚለው የእርሱን ቃል ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቃል ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ደግሞ ጥበበኛ ያደርጋል፤ ተስፋን ያለመልማል፤ ከክፉም ይታደጋል። ስለዚህ ‹‹ቃሌን የሚሰማ ግን በተስፋ ይኖራል፤ ከክፉም ሁሉ ያለድንጋጤ ያርፋል›› በማለት ያስረዳናል። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል የሚሰማ በተስፋ ይኖራል በአንጻሩ የእግዚአብሔርን ቃል የማይሰማ ግን ተስፋ ይቆርጣል። ፪. በሐሰተኛ ትምህርት መሞላት ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ምእመናን በላከው መልእክቱ “ሌላ ልዩ ትምህርት አታምጡ፤ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩት እነዚያ አልተጠቀሙምና” (ዕብ. ፲፫፥፱) በማለት እንደገለጸው ለምእመናን የማይገባ ትምህርት ተስፋ ያስቆርጣል። በዘመናችን እየተስተዋለ ያለው የወጣቱ የሥነ ምግባር ዝቅጠት መማር ያለበትን ሳይሆን መማር የሌለበትን የሐሰት ትምህርት እየተማረ ስላደገ ነው። በእናት በአባቶቹ ተስፋ የቆረጠ፣ በሀገሩ ተስፋ የቆረጠ፣ ለማንነቱ ዋጋ የማይሰጥ፣ ከሰውነት የወጣ ሥራ እየሠራ ያለው፣ የተማረው ትምህርት የሚገነባ ሳይሆን የሚያፈርስ፣ ተስፋ የሚያስሰንቅ ሳይሆን ተስፋ የሚያስቆርጥ ስለሆነ ነው።   ፫. ለምድራዊ ሕይወት መጨነቅ የሰው ልጅ ፍላጎቱ የበዛ በውስጡ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት ያለው አቅም ግን እጅግ ውሱን የሆነ ፍጥረት ነው። ፍላጎቱ ከመብዛቱም የተነሣ በሚጠቅመውም በማይጠቅመውም፣ በሚያስፈልገውም በማያስፈልገውም፣ በሚያስደስተውም በማያስድስተውም ብቻ በብዙ ነገር ይጨነቃል። ይልቁን በዘመናችን እንደተከሠተው ዓይነት ለዓለም ስጋት የሆነ፣ በሰው ሰውኛ ሠልጥነናል ያሉ ሀገራት ሊቋቋሙት ያልቻሉት በሽታ፣ በሃይማኖታቸውና በዘራቸው እየተለዩ እንደ በግ የሚታረዱበት ሁኔታ ሲከሠት ሰዎች እጅግ ይጨነቃሉ። ይሁን እንጂ አለማሰብ ባይቻልም አለመጨነቅ ግን ይቻላል። ይቻላል ብቻ ሳይሆን እንዳንጨነቅም ታዝዛናል። መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ እንዳንጨነቅ ብቻ ሳይሆን በመጨነቃችን አንዳች የምንጨምረው ነገር እንደሌለን “ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማነው” (ማቴ. ፮፥፳፯) በማለት አስተምሮናል። ስለሆነም ምእመናን ከአላስፈላጊ ጭንቀት ወጥተው እንዲያደርጉ የታዘዙትንና ማድረግም የሚችሉትን ብቻ እያደረጉ በሌላው ነገር ሁሉ ግን እግዚአብሔርን በመለመን እርሱን ብቻ ተስፋ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ሰዓት የመምህራን ድርሻም የሚሆነው የተባለውንም ሆነ ያልተባለውን ምእመናን የሚያንጸውንም ሆነ የሚያፈርሰውን እየተናገሩ በጭንቀት ላይ ጭንቀት ከመደራረብ ተቆጥበው የሚያጸናውንና የሚያጽናናውን የእግዚአብሔርን ቃል ማስተላለፍ ይኖርባቸዋል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ምእመናን መማር የሚገባቸውን መሠረታዊ ትምህርት ባይማሩ ከላይም እንደተገለጸው በሐሰተኛ ትምህርት ተሞልተው፣ ለምድራዊው ሕይወት ብቻ እየተጨነቁ ተስፋ መቁረጥ ላይ ሊደርሱ ይችላሉና መጠንቀቅ ያስፈልጋል።  ፬. የመከራ ጽናት ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን በየጊዜው ልዩ ልዩ መከራ ሲፈራረቅባቸው ኖረዋል። በዘመናችንም እጅግ የሚከብድና የሚዘገንን መከራ እየደረሰባቸው ነው። በዚህ ዓለም እስከ ኖሩና የክርስቶስንና የክርስቶስ ወዳጆች የሆኑትን ቅዱሳን አብነት እስካደረጉ ድረስ  ወደፊትም ሊቀጥል ይችላል። ፳፻፲፪ ዓ.ም ካሳለፍናቸው ዐሥር ዐሥራ አምስት ዓመታት በተለየ መልኩ መከራው የተፈራረቀበት ዓመት ነበር። መከራው ሰው ሠራሽም ተፈጥሯዊም፣ መንግሥታዊም፣ ግለሰባዊም፣ የውስጥም የውጭም ሊባል ይችላል። ተፈጥሯዊ ሲባል የጎርፍና የእሳት አደጋዎች፣ በድርቅ ምክንያት የሚከሠት ጽኑዕ ረኀብና  ዓለማቀፋዊውን መቅሰፍት የኮቪድ ፲፱ ወረርሽኝን ጨምሮ መጥቀስ ይቻላል። ሰው ሠራሽ ደግሞ የእርስ በእርስ ጦርነት፣ የዘር ጭፍጨፋ፣ የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ የሰዎች ከቀያቸው መፈናቀል፣ ወዘተ ሁሉ ተጠቃሽ ነው። ይህ መከራ የሰው ልጅ መከላከል የሚችለውም የማይችለውም ነበር። ተፈጥሯዊ የሆነውን መከላከል ባይችልም  ሰው ሠራሹን ግን መከላከል ይቻል ነበር። ይህ ማለት በቀጥታ አደጋው የደረሰበት አካል መከላከል ባይችልም አደጋውን ያመጣው አካል እንዲሁም የሚመለከተው የመንግሥት አካል መከላከል ይችል ነበር። ያም ሆነ ይህ በሚከብድና በሚዘገንን መከራም ቢሆን ከ፳፻፲፪ ዓ.ም ወደ ፳፻፲፫ ዓ.ም ተሸጋግረናል። በመሆኑም ሰዎች የዚህ ከባድ መከራ ተሸካሚ ሲሆኑ የጸኑት መከራውን ተቋቁመው ሊያልፉ ይችላሉ። ያልጸኑት ደግሞ ተስፋ ቆርጠው ሃይማኖታቸውን እስከ መለወጥም ሊደርሱ ይችላሉና የመከራው ጽናት የተስፋ መቁረጥ ምክንያት ሊሆን ይችላል።  በተስፋ መኖር የሚያስገኛቸው ነገሮች   ፩. ከክፉ ያሳርፋል የእግዚአብሔርን ቃል መስማትና በተስፋ መኖር ከክፉ እንድንድን። በሐዲስ ኪዳንም የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው ጽኑዕ የሆነውን ተስፋ የሰነቁት ሐዋርያት እሳቱን እና ስለቱን ታግሠው ለበለጠ ክብር በቅተዋል። ከመካከላቸው የእግዚአብሔርን ቃል ያልሰማው ይሁዳ ግን ተለይቷል፤ አልሰማም ማለት በዕዝነ ሥጋው አልሰማም ማለት አይደለም፤ በዕዝነ ልቡናው ግን በእርግጥም አልሰማም። ስለዚህ ምንም እንኳን ከሐዋርያት ጋር ቢቆጠርም፣ ትምህርቱ፣ ተአምራቱ ባይነፈገውም ክብርን ግን አላገኘም።  የእግዚአብሔርን ቃል በአግባቡ አልሰማምና። (ኢሳ.፮፥፩-፲) ምን አልባትም በተስፋ ከመኖር ይልቅ ተስፋ በመቁረጡ ግኡዝ የሆነችው እንጨት ብትሰብከው እንኳን መመለስ አልቻለም። በተስፋ መኖር እንደፈያታዊ ዘየማን የመጨረሻ ሕይወትን ያሳምራል። ተስፋ መቁረጥ ግን እንደይሆዳ በመጨረሻ ከቤት መውጣትን እስከ መጨረሻው አለመመለስን ያስከትላል። ተስፋ መቁረጥ እጅግ የከፋ አደጋ ላይ ይጥላልና።  በዘመናችንም ሰው የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ስለማያደርግ ሥጋዊ መፍትሔው ብቻ ይታየዋል። በእርግጥ ሥጋዊ መፍትሔውም የሚገኘው በእግዚአብሔር ነው። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር የሥጋም የነፍስም ድኅነት እንደሆነ አለመቀበል በብዙኃኑ ዘንድ ይስተዋላል። ይህ የሆነው ደግሞ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ካለማድረግ የመጣ ነው። ሥጋዊ ዕውቀትን ብቻ ተምሮ ያደገ ሰው ሁሌም የሚታየው ሥጋዊ ድሎት ነው፤ ‹‹በቃልህ እዘዝ፤ ልጄ ይድናል›› ያለው የመቶ አለቃው ቃል ትዝም አይለው፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ባለመስማቱም በመጨነቅ፣ በመሸበር፣ ለውጥ የማያመጣ መፍትሔ ሲያፈላልግ ዘመኑን በከንቱ ይጨርሳል። (ማቴ. ፰፥፰) የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ማድረግና በጽኑዕ ተስፋ መኖር የተስፋ ቃሉንም በትክክል ሰምቶ በተግባር ላይ ማዋል ከክፉ የሚታደገን መሆኑን ሐዋርያው ያዕቆብ ‹‹ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ቃሉን ሰምቶ የማያደርገው ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስታዎት እንደሚያይ ሰው ይመስላል። ራሱንም ተረድቶ ይሄዳል፤ ወዲያውም እንዴት እንደሆነ ይረሳል›› በማለት ያስረዳናል። ይህ ማለት የተስፋ ቃሉን ሰምቶ በሕይወት መተርጎም ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ሕይወት ነው፤ ከክፉም ያለምንም ድንጋጤ ያድናል።  ያሳለፍነው ዘመን እጅግ የከፋ መከራው ተፈራረቀበት ዘመን እንደነበር ከላይ ለመግለጽ ተሞክሯል። ያሳለፍነው ዘመን ብቻ ሳይሆን ዐዲሱን ዓመትም በተቀበልን ማግስት በጎርፍ አደጋ ምክንያት በርካታ ሰዎች ሀብት ንብረታቸውን እንዳጡ፣ ከመኖሪያ ቀያቸው እንደተፈናቀሉ፤ በሃይማኖታቸውና በዘራቸው እየተመረጡ እንደተገደሉ የበርካታ መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ ሆኗል። ነገር ግን ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “ተስፋ አያሳፍርም” በማለት እንደነገረን የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ አድርገን መልካሙን ዘመን እንዲያመጣልን፣ የክፉዎችንም ልቡና እንዲያራራልን፣ የተፈጥሮውንም ሆነ ሰው ሠራሹን አደጋ በቸርነቱ እንዲያስታግሥልን አጥብቀን መለመን ይኖርብናል። እግዚአብሔር አምላካችን በጽኑዕ ተስፋ እንደሚደረግልን አምነን የጠየቅነውን ሁሉ ያደርግልናልና። ፪. የመንግሥተ ሰማያት ወራሽ ያደርጋል። ሰው ከሞተ በኋላ በእግዚአብሔር በሕይወት እንደሚኖር ባለመጠራጠር ማመን ተስፋ መንግሥተ ሰማይ ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ እንደተነሣ ካመንን እንዲሁ እግዚአብሔር ሙታንን በኢየሱስ ያስነሣቸዋል፤ ከእርሱም ጋር ያመጣቸዋል›› በማለት እንዳስረዳን በሥጋዊ ዐይናችን ሳናይ ሰምተን ብቻ የተቀበልነው ሃይማኖት ነው፡፡ (፩ኛ ተሰ. ፬፥፲፬) በዐይን የማይታየውን በእጅ የማይዳሰሰውን መውረስ ደግሞ በጽኑዕ ተስፋ የመኖር ውጤት ነው። መንግሥተ ሰማያት እንዳለች፣ እንደምንወርሳት፣ በደስታ እንደምንኖርባት፣ ከአወቅን በኋላ እንደማናጣትም አምነን የተቀበልነው ለመንግሥተ ሰማያት የምታበቃውን ርትዕት የሆነችውን ሃይማኖት አጽንተን በእግዚአብሔርም ቸርነት እንወርሳታለን የሚለው ሙሉ ተስፋ ስላለን ነው፡፡ ደግሞም ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹እምነትስ ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የምታረጋግጥ፣ የማናየውንም ነገር የምታስረዳ ናት›› ብሎ እንደነገረን ተስፋ የምናደርገው ነገር አለ፤ እርሱም መንግሥተ ሰማያት ነው፡፡ ይህን ተስፋ የምናደርገውን ነገር ደግሞ በእምነት እንወርሳለን፡፡ በሃይማኖት ጸንተን በጎ ምግባር ሠርተን ስንኖር ያን ተስፋ ያደረግነውን ርስት ሊያወርሰን እርሱ የታመነ አምላክ ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው›› በማለት ያስረዳናል፡፡ (ዕብ.፲፩፥፩፤ ፩ቆሮ.፩፥፱) ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድም በድርሰቱ “ተስፋ ሕይወት ተሠራ በሰማያት ተስፋ ሕይወት ተሠራ በሰማያት ተስፋ ሕይወት ተሠራ፤ የሕይወት ተስፋ በሰማያት ተሠራ” በማለት ሦስት ጊዜ እየደጋገመ ይነግረናል። ይህ ሊቁ በሰማያት ተሠራ ያለው የሕይወት ተስፋ በሃይማኖት ጸንተው በጎ ምግባር ሠርተው የሚወርሱት መንግሥተ ሰማያት ነው። የእግዚአብሔርን የባሕርይ አምላክነት፣ አምኖ፣ በዐይነ ሥጋ የማይታይ ዘለዓለማዊ መንግሥቱን ያወርሰኛ ብሎ በተስፋ ጸንቶ ለኖረ የሚወረስ ነውና እንዲህ በማለት ገለጸው። ከጥንት ጀምሮ ቅዱሳን አበው እና ቅዱሳን ነቢያት የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት መከራ የተቀበሉት የማይቀር፣ የማያሳፍር ተስፋ ስለነበራቸው ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሲገልጽ ‹‹እነርሱ በእምነት ተጋደሉ፤ ነገሥታትን ድል ነሡ፤ ጽድቅን አደረጉ፤ ተስፋቸውን አገኙ፤ የአናብስትን አፍ ዘጉ›› (ዕብ.፲፩፥፴፫) ሲል ያስረዳል፡፡ እነርሱም የተጋደሉት በእምነት ነው፤ ተጋድለውም ነገሥታትን ድል አደረጉ፤ ይጠባበቁት የነበረውን ተስፋም አገኙ፡፡ ተስፋቸው ደግሞ ድኅነት ነው፤ ርስተ መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ነውና፤ ይህም ሆነላቸው፡፡  እግዚአብሔር አምላካችን መቼም ቢሆን ተስፋችንን አያሳጣንም፡፡ ነገር ግን ተስፋ የምናደርገው ነገር ለእኛ የሚያስፈልገን መሆን አለበት፤ የሚጎዳንን አይሰጠንምና፡፡ ‹‹በእርሱም አማካኝነት ወደቆምንበት ወደ ጸጋው በእምነት ተመራን፤ በእግዚአብሔርም ክብር ተስፋ እንመካለን፡፡ የምንመካ በእርሷ ብቻ አይደለም፤ በመከራችን ደግሞ እንመካለን እንጂ፤ መከራ በእኛ ላይ ትዕግሥትን እንደሚያመጣ እናውቃለንና፡፡ ትዕግሥትም መከራ ነው፤ በመከራ ተስፋ ይገኛል፡፡ ተስፋም አያሳፍርም፤ በሰጠን በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን መልቷልና›› (ሮሜ ፭፥፪-፭) በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ምእመናን በላከው መልእክቱ ይነግረናል፡፡  በአጠቃላይ አባታችን አዳምን ከገነት ሲያስወጣው ጽኑዕ ተስፋ ሰጥቶ ወደዚች ምድር እንዲኖር ያደረገ አምላክ የሰጠውንም ተስፋ ያላስቀረ ታማኝ አምላክ ዛሬም ከኖሩበት ቦታ ተፈናቅለው፣ በማንነታቸው ተሸማቅቀው፣ በአንድ በኩል በሰው ሠራሽ አደጋ በሌላ በኩል በተፈጥሮ አደጋ እየተጨነቁ ያሉት ሁሉ ተስፋ አያሳፍርምና በተስፋ እግዚአብሔርን መለመን ያስፈልጋል። ነቢየ እግዚአብሔር ዕንባቆም “በለስ አታፈራምና በወይኑም ፍሬ ሐረግ አይሆንም፤ ወይራ ሥራዋን አበለች እርሻዎችም እህልን አላፈሩም፤ በጎች ከግጦሽ ታጡ፤ ላሞችም በበረት ውስጥ አልተገኙም፤ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሤትን አደርጋለሁ።” (ዕንባ. ፫፥፲፯-፲፰) በማለት እንደተናገረው በሃይማኖታችን ጸንተን በጎ ምግባር እየሠራን በእግዚአብሔር ቤት በተስፋ ልንኖር ይገባል።  በሚመጣብን መከራ ሁሉ በሃይማኖት ጸንተን፣ በጎ ምግባር ሠርተን፣ የተስፋውን ቃል በልቡናችን ማኅተም አትመን የምንችለውንና የሚጠበቅብንን ሁሉ ሠርተን በመጨረሻይቱ ዕለት “እናንተ የአባቴ ቡሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን የአባቴን መንግሥት ትወርሱ ዘንድ ወደ እኔ ኑ” የሚለውን የሕይወት ቃል ያሰማን ዘንድ እግዚአብሔር አምላካችን ይፍቀድልን አሜን።    
Read 1166 times