Friday, 06 November 2020 00:00

የጥያቄዎቻችሁ መልስ

Written by  በዲ/ን ኃይለማርያም

Overview

ቅዱስ ሲኖዶስ “የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የማስጠበቅ የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ራስን የመከላከል እንቅስቃሴ በሰንበት ት/ቤቶች ይመራል” የሚል መግለጫን መስጠቱ ይታወሳል። እኛም በዚህና በተለያዩ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት  ምክትል ሰብሳቢ ከሆኑት አቶ መንክር ግርማ ጋር ቆይታ አድርገናል። ሐመር፡- “የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የማስጠበቅ የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ራስን የመከላከል እንቅስቃሴ በሰንበት ት/ቤቶች ይመራል” የሚል የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወቃል። ይህ አፈጻጸሙ እንዴት ነው የሚሆነው? መንክር፡- አፈጻጸሙን በተመለከተ የቅዱስ ሲኖዶስ ሙሉ ውሳኔ እና በሚያስቀምጠው አቅጣጫ ይሆናል ብለን እናምናለን። በዝግጁነት ደረጃ በሁለት ከፍለን እንየው።  ሀ. በአወቃቀር፡- ወጣቶችንም ሆነ ምእመናንን ለማስተባበር አወቃቀሩ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ደረጃ የተዋቀረ እና ወጣቶችን የያዘ ሌላ መዋቅር የለም። በዚህ ረገድ ቅዱስ ሲኖዶስ በሕግ አዋቅሮ በቃለ ዐዋዲ ደንግጎ ሕፃናትና ወጣቶችን ዐቅፎ እንዲያገለግል የተዋቀረ አካል ከመሆኑ አንፃር በኔ ግምት ከዚህ የተሻለ ሌላ አማራጭ  የለም። ለ. በመሪነት ደረጃም፡- ከወሰድን መዋቅሩ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል እና በአብዛኛው አጥቢያ ከመገኘቱ አንጻር የተወሰነ ሥራ ከተሠራ አንጻራዊ እድል አለ ብዬ አስባለሁ። ከዚያም ባሻገር በተለይ በርካታ ነዋሪዎች ባሉበት ከተሞች በአቅም ደረጃም ብዙ የሰንበት ትምህርት ቤት አገልጋዮች አሉ። ይህ ማለት የተዋጣለት በሁሉ ነገር የተደራጀ ሰው እና ግብአት (ሪሶርስ) አለ ለማለት ሳይሆን በአንጻራዊነት ሕዝቡ ጋር ለመድረስ ከሰንበት ትምህርት ቤት የተሻለ አደረጃጀት የለም። ይህን በአቅሙ ሁሉም ከተረባረበ በአጭር ጊዜ ያለንን የሰው ኃይል እና መዋቅር ተጠቅመን ቅዱስ ሲኖዶስ በሚሰጠው አቅጣጫ የጉዳቱን መጠን መቀነስ የምንችልበት ዕድል አለ ብዬ አምናለሁ።   ሐመር፡- መደራጀት የቤተ ክርስቲያንን ህልውና ከመጠበቅ አንፃር ምን ትርጉም አለው?  መንክር፡- እንደ እምነታችን ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም የተመሠረተች በመሆኗ ባለቤቱ አይተዋትም፤ ፈታኞችም ድል ይነሣሉ፤ ቤተ ክርስቲያንን ታግሎ ያሸነፈ የለምና። አምላክ ይህን ከፈቀደ እኛ መሣሪያ እንሆናለን የሚለውን ታሳቢ አድርገን ከኛ የሚጠበቀውን ማድረግ ይጠበቅብናል። በዚህም መሠረት፡- መደራጀት በሃይማኖታዊም በዓለማዊም አስተምህሮ ውጤታማ ያደርጋል። ለዚህም በመጽሐፍ ቅዱስ ሙሴ ሕዝበ እስራኤልን መከራ ከበዛበት ካራን ተስፋ ወደሚያደርጓት ከነዓን ሲጓዙ ሕዝቡን ለመምራት ተቸግሮ ነበር። በአማቱ ዮቶር ምክር የሺህ አለቆችን፣ የመቶ አለቆችን፣ የአምሳ አለቆችን አድርገህ ሹማቸው ባለው መሠረት በዚያ አደራጅቶ በተሰጠው ጊዜና ሰዓት ሕዝቡ ፍትሕን እንዲያገኝ አድርጓል። ‹‹አንተም ከሕዝቡ ሁሉ አዋቂዎችን፥ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፥ የታመኑ፥ የግፍንም ረብ የሚጠሉትን ሰዎች ምረጥ ከእነርሱም የሺህ አለቆችን፥ የመቶ አለቆችን፥ የአምሳ አለቆችን፥ የአሥርም አለቆችን ሹምላቸው።›› እንዲል። (ዘጸ.፲፰፥፳፩)። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአምሳ ሚሊዮን ያላነሰ አማኝና ተከታይ አላት ይህን ሕዝብ በተገቢ መልኩ ብታደራጅ፡ እንኳን ለራሷ በዓለም ደረጃም ከፍተኛ ተፅዕኖን መፍጠር ትችላለች። ስለዚህ ‹‹ካልተደራጀ ዐሥር ሺህ ወታደር የተደራጀ መቶ ወታደር ይሻላል›› እንደሚባለው እኛም በተገቢው መልኩ ብንደራጅ እጅግ ጠቃሚ ይሆናል። መደራጀቱ ጥቃት ሲደርስ ለመከላከል ብቻ ሳይሆን፡ አስቀድሞም ለማጥቃት የሚያስቡ እኩያንን ለማጋለጥ ይጠቅማል። በአንድነት ተደራጅተን ስንቆም ማንም ሊያጠቃን አይሞክርም። ምክንያቱም የዚህ የተደራጀ ኃይል ሰላማዊ ምላሽ ለአጥቂው ከፍተኛ ኪሳራ የሚያደርስ ይሆናልና ነው።  ሐመር፡- እስካሁን ባለ መደራጀታችን ምን አጣን?  መንክር፡- ለዚህ መልሱ ቀላል ነው። አሁን የምናየው በየቦታው ያለው ኦርቶዶክሳዊ በሃይማኖቱ ምክንያት ሲገደል፤ ሲዘረፍ፣ ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠል ከጊዜያዊ የሚዲያ ጩኸት የዘለለ ይህ ነው የሚባል የተደራጀ አካሔድ አይስተዋልም። በመሆኑም ተደጋጋሚ እና የማያቋርጥ የሆነውን  ጥቃት በመደራጀት ልንመክተው ይገባል።  በሌላ በኩል አሁን አሁን ሁሉም እንደ ፈለገ ቤተ ክርስቲያንን የሚዘልፈው፣ እንደ ፈለገ ቦታዋን የሚቀማው፣ በዓላቷ እንዳይከበሩ እንቅፋት የሚሆነው፣ የበዓላት ማክበሪያ ይዞታዎቻችን በመንግሥት ትኩረት የማያገኙትና በተገቢ መልኩ ለማስከበር አፋጣኝ ምላሽ የማይሰጣቸው በተገቢው መልኩ ባለመደራጀታችን ነው።  ሐመር፡- ለቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን ጥቅም የተመሠረቱ ብዙ ማኅብራት እያሉ፡ የቤተ ክርስቲያንን ፈተና ማቃለል ለምን አልተቻለም? መንክር፡- ቤተ ክርስቲያናችን ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አንድ ምእመን ድረስ የሚደርስ መዋቅር ያላት ተቋም ናት። ይሁንና ተቋሟ በተገቢው ሁኔታ በሰው ኃይልና በበጀት ተጠናክሮ ባለ መሥራቱ ብዙ ዋጋ አስክፍሏታል። ይህም ከወለዳቸው አገልግሎቶች መካከል በማኅበራት ተደራጅቶ ቤተ ክርስቲያንን በተቻለ መጠንና አቅም በፈቀደ መልኩ ለማገልገል የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ነው። በዚህ ዓይነት ዓላማ ተመሥርተው ዘወትር ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ የሚደክሙ ማኅበራትና ምእመናን አሉ። ነገር ግን ይህም ከቤተክርስቲያን ሰፊ አገልግሎት  አንጻር ያልተደራጀና ያልተማከለ አሠራር ስለሆነ ማኅበራቱ የሚለኮስ እሳትን ከማጥፋት በዘለለ ዘለቄታዊ መፍትሔን ለማምጣት ተቸግረዋል። አሁንም ዘለቄታዊ መፍትሔ እንዲመጣና የቤተ ክርስቲያን ችግር እንዲፈታ፡ የአቅማቸውን የሚሠሩ ማኅብራትን ቤተ ክርስቲያን ባሏት መዋቅሮች ሁሉ ማሳተፍ ያስፈልጋል። እንዲህ ሲሆን፡ ያለውን የሰውና የገንዘብ ሀብት በተደራጀ መልኩ መጠቀም ይቻላል። መዋቅሩን አቅም ባላቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች በማጠናከርና በመደገፍ ሁሉም በአንድነት መንቀሳቀሱ ጥቅሙ ብዙ ነው። በተናጠል ከመዋቅሩ ርቀው የሚመሠረቱ ማኅበራት ግን ጊዜያዊ እና በጣም አናሳ አስተዋጽኦ ከማድረግ የዘለለ የቤተ ክርስቲያንን ችግር በዘላቂነት ሊፈቱ አይችሉም።  ሐመር፡- የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ተደራጅቶ ከመሥራት አንፃር ምን ያህል እየተንቀሳቀሰ ነው?  መንክር፡- በሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ከመደራጀት አንፃር ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፤ ከአዲስ አበባ ብንነሣ፡ ሁሉም ክፍለ ከተሞች በንቃት አገልግሎታቸውን የሚሰጡበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ከዚያም ባለፈ ከ፬-፮ አጥቢያዎች በጋራ የሚያስተባብር አደረጃጀት ላለፉት 4 ዓመታት ተሠርቶበት ጥሩ ውጤት እያመጣ ይገኛል። ከዚያም ባለፈ አጥቢያ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ራሳቸውን ከማደራጀት አልፈው የቤተ ክርስቲያን ወጣቶችን እንዲያደራጁ ኃላፊነት የሰጠቻቸው አካላት በመሆናቸው፡ ኦርቶዶክሳዊ ወጣቶችን ወደ መዋቅር የማደራጀት ሥራ በስፋት እየተሠራ ይገኛል። በሌሎች በተለያዩ ዘርፎችም፡ ማለትም በሀገራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችም ወጣቱ እንዲሳተፍ በማደራጀት ላይ እንገኛለን። በሀገር አቀፍ ደረጃ ስናይም ካሉት ፶፮ አህጉረ ስብከቶች ፴፰ቱን አህጉረ ስብከቶች የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በቅርበት መረጃ የመለዋዋጥና የማደራጀት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። በዚህ ዓመት ከፍተኛ ሥራ ይሠራበታል ተብሎ ይታሰባል።  ሐመር፡- ከማደራጃ መምሪያው ጋር ምን ያህል ተናባችሁ ትሠራላችሁ?  መንክር፡- ማደራጃ መምሪያው ከመቼውም ጊዜ በላይ አገልግሎታችንን እያገዘ ይገኛል። ለዚህም ዋናው መገለጫ በጣም ጥሩ ይዘት ያለው የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ በእኛው አባላት ከመምሪያው ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን፡ ዕቅዱን መሠረት በማድረግም የሀገረ ስብከት ዕቅድ ተዘጋጅቷል። ሀገረ ስብከቶችም ይህን ዕቅድ ከክፍለ ከተማ/ወረዳ አንድነት ጋር በመተባበርና ከዚሁ መሪ ዕቅድ ጋር እንዲናበብ ሆኖ እንዲሠራ አቅጣጫ ተሰጥቶ በዛ መሠረት ከላይ እስከ ታች በዕቅድ ተናበን እየሠራን እንገኛለን። በዚህም ማደራጃ መምሪያው ተገቢውን ድጋፍ አድርጎልናል። ይህን ለማድረግም የሚያስፈልገውን አመራር ለማምጣት ክፍለ ከተሞች በሙሉ ነጻነት ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ልጆች ወደ አመራር እንዲመጡ ተደርጓል። በዚህም የማደራጃ መምሪያው የውስጥ መመሪያዎች ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ኃላፊና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በሆኑት በብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ መልካም ፈቃድ እና አባታዊ መመሪያ ተሻሽሎ በጥሩ ሁኔታ የተናበበ ሥራ እየተሠራ ይገኛል።  ሐመር፡- ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ያቀረባችሁት ጥያቄ ምን ነበር? ምንስ ለውጥ ያመጣል ብላችሁ ትጠብቃላችሁ? መንክር፡- ጥያቄዎቹ በዋናነት፡- ፩. በቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ስላለው ጥቃት፣ ፪. የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች አለመፈጸም፣ ፫. የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መዋቅራዊ አደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ፣ ፬. የቤተ ክርስቲያን መሪ ዕቅድ፣  ፭. የቅድመ አደጋ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት፣  ፮. የቤተ ክርስቲያን የአእመሮ ሀብት ንብረት ምዝገባ እና የመሳሰሉት ሲሆኑ፡ ቅዱስ ሲኖዶስ አሁን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ያቀረብናቸውን አሳቦች ተወያይቶበታል።   በነዚህ ፍሬ አሳቦች ላይ ተወያይቶም መመሪያ ሰጥቶባቸዋል።  ራሱ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰናቸው ውሳኔዎች ለብዙ የቤተክርስቲያን ችግሮች መፍትሔ መሆን የሚችሉ ቢሆኑም ውሳኔዎቹ ለዓመታት አለመፈጸማቸው ዋጋ አስከፍሎናል። ይህንን የማስታወሱን ሥራ ነው የሠራነው። ምን ለውጥ ያመጣል ለተባለው፡ ከዚህ በኋላ ለውጥን ለሆነ አካል የምንተወው አይደለም። ይልቁኑ በተግባር ተሳትፈን የምናመጣው ነው በሚል እንደእኛ ስምምነት ላይ ተደርሷል። በዚህ መሠረት ጥያቄያችንና ቀጣይ አካሔዳችንን ለቅዱስ ሲኖዶስ አሳውቀናል። ይህንንም በተዋረድ እስከ አጥቢያ ውይይት እየተካሔደበት ነው። ስለዚህ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት የለውጡ እንቅፋቶችን የሚጋፈጡ የለውጡ አራማጆችን የሚታዘዙ የሚያግዙ ይሆናሉ። በቀጣይ በዓመት ሁለት ጊዜ የሲኖዶስ ስብሰባ ሲመጣ ጥያቄ የማቅረብ ብቻ ሳይሆን አስፈጻሚውን ‹ለምን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አልተፈጸመም› ብሎ የሚጠይቅና ሲጠይቅም በሙያና በዕውቀት ማገዝ በሚያስችል መልኩ ለማድረግ አንድነቱ ተዘጋጅቷል። ትልቁ ለውጥ ብለን ያስቀመጥነው እኛ ለለውጥ የድርሻችንን ለማበርከት መነሣታችን እና ቅዱስ ሲኖዶስም ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ መመሪያ መስጠቱን ነው።  ሐመር፡- ሒደቱ የተገታው የመሪ ዕቅድ ትግበራን ከወቅቱ ጋራ አስማምቶ በማስቀጠል፣ ቤተ ክርስቲያንን ለአስከፊ ጥቃት ያጋለጣት የአሠራር ጉድለት መስተካከል እንዳለበትም ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አስተላልፏልና ራስን ከመከላከል አንጻር ምን ዓይነት ፋይዳ አለው ብለው ያምናሉ?   መንክር፡- የመሪ ዕቅድ አለመተግበር ብዙ ኪሣራ አድርሷል። መሪ ዕቅዱ ፳፻፮ ዓ.ም. ላይ ጸድቆ ከ፯ ዓመት በኋላ ይፈጸም እያልን እጠየቅን ነው። ይህ መሪ ዕቅድ ቤተ ክርስቲያናችን በስትራቴጂና በዕቅድ እንድትመራ ከማድረጉ በተጨማሪ እንደ ተቋም መዋቅሮቿን በደንብ የሚፈትሽና በተገቢው የሰው ኃይል እና በጀት እንዲጠናከር መንገድ የሚከፍት ነበር። ይህ ማለት የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ላይ ያሉ መመሪያዎች በተገቢው ደረጃ እና የሰው ኃይል ተጠናክረው እንዲሠሩ ያስችላል። ይህም ቤተ ክርስቲያናችንን በስብከተ ወንጌል፣ በወጣቶች፣ በገዳማትና አድባራት፣ በሕግ፣ በሚዲያ፣ በሰበካ ጉባኤ ባሏት በሁሉም መመሪያ የተደራጀና የታቀደ ሥራ እንድትሠራ ያስችላት ነበር። ይህ ተፈጻሚ ሆኖ ቢሆን አሁን ላይ  ከሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሕዝቧን  በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ወጣቶቿን  በገዳማት መምሪያ ገዳማቷንና አድባራቷን    በሕግ መምሪያ የአእምሮ ንብረቷን፤ ያሏትን ንብረቶቿን አስከብራ እንድትሔድ እና አሁን የገጠመንን ችግር ከግማሽ በላይ መቀነስ ይቻል ነበር።  ሐመር፡- በስተመጨረሻ ያልተነሣ ጉዳይ አለ ብለው የሚያስቡ ከሆነ ቢገልጹልን? መንክር፡- በቀጣይ የጥምቀት በዓልን አስመልክቶ ምንም እንኳን ጥምቀት የቤተ ክርስቲያኗ ሀብት ብቻ ሳይሆን በዩኔስኮ ተመዝግቦ በዓለም ቅርስ የሆነ ቢሆንም፡ መንግሥትንና ባለ ድርሻ አካላት ተገቢውን ትኩረት አለመስጠታቸው እንደ ሰንበት ትምህርት ቤት አንድነት ሥጋት ፈጥሮብናል። ለዚህም ማሳያ የጃንሜዳ ነጋዴዎችን የማንሣት ሥራ አለመጀመር፣ ብዙ የጥምቀት ማክበሪያዎች የይዞታ ማረጋገጫ አለማግኘት፣ ይዞታዎች ከተሰጡ በኋላ መወረራቸው እና ሌሎችም በዚህ በአጭር ጊዜ ሊገለጡ የማይችሉ ፈተናዎች የተጋረጡበት መሆኑ ሁሉ አሳሳቢነው። በቀጣይ በስፋት ውይይት ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ከግንዛቤ ተወስዶ እኛም እንደ አንድነት ማሰረጃ አደራጅተን እንቅስቃሴ እየጀመርን ስለ ሆነ የእናንተም ሚዲያ ተገቢውን ሽፋን እንዲሰጥ ከወዲሁ ጥያቄያችንን እናቀርባለን። ሐመር፡- ጊዜዎን ሠውተው ለቃለ መጠይቁ ማብራሪያ ሐሳብ ስለሰጡን በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን። መንክር፡- እኔም ለዚህ ጉዳይ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።  ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን። አሜን!
Read 567 times