Wednesday, 10 March 2021 00:00

ዐቢይ ጾም (ጾመ ሁዳዴ)

Written by  እህተ ሚካኤል
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! እንደምን ከረማችሁ? ደህና ናችሁ? አሜን እግዚአብሔር ይመስገን!   ልጆች የአንደኛ ሰሚስተር ውጤት እንዴት ነው? መቼም ባለፈው ባስተላለፍንላችሁ ምክር መሠረት በደንብ አጥንታችሁ ጥሩ ውጤት እንዳመጣችሁ ተስፋ እናደርጋለን። በርቱ እሺ! ነገ አድጋችሁ የቤተ ክርስቲያንና የሀገር ተረካቢ የምትሆኑት እናንተ ናችሁ፤ ለዚህ ደግሞ በመንፈሳዊውም በዓለማዊውም እውቀት ማደግ አለባችሁ።  ልጆች! ዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነው ስለ ዐቢይ ጾም ወይም ስለ ጾመ ሁዳዴ ነው፤መልካም ንባብ ይሁንላችሁ!     ልጆች! በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት በዓመት ውስጥ ሰባት የአዋጅ አጽዋማት አሉ። እነዚህን አጽዋማት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታይ የሆነ ምእመን ሁሉ ከልጅ እስከ አዋቂ የሚጾማቸው ነው። ልጆች! በቤተ ክርስቲያን ሕፃናት ከሰባት ዓመታቸው ጀምሮ መጾም እንዳለባቸው ፤እንዲሁም አጽዋማት የአዋጅ እና የፈቃድ ተብለው እንደሚከፈሉ ከዚህ በፊት በጻፍነው ጽሑፍ ውስጥ ገልጠንላችሁ ነበር አስታወሳችሁ? ደህና።  ልጆች ዐቢይ ጾም(ጾመ ሁዳዴ) ከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት ውስጥ አንዱ ነው። ይህ ጾም ዐቢይ ጾም የተባለበት ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ጾም ስለሆነ ነው። ሌላው ደግሞ ከሌሎቹ አጽዋማት ብዙ ቀናት የሚጾም ጾም በመሆኑ ነው። ጾመ ሁዳዴ መባሉም ‹‹ሁዳድ›› ማለት ሰፊ የእርሻ ቦታ ወይም ማንኛውም ብዙ ሕዝብ የሚሳተፍበት ሥራ ማለት ነው። ይህም ጾም ታላቅ ጾም በመሆኑ እና ብዙዎች የሚጾሙት ጾም በመሆኑ ምክንያት ጾመ ሁዳዴም ይባላል።   ዐቢይ ጾም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር ዕለቱኑ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ በመሄድ ፵ ቀንና ፵ ሌሊት የጾመው ጾም ነው። ልጆች! ጌታችን የጾመው ኃጢአት ኖሮበት ሳይሆን ለኛ አብነት ለመሆን ነው። በዚህም መሠረት ዐቢይ ጾምን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በኋላ ሐዋርያት ጾመውታል፤ እኛም ክርስቲያኖች እነሱን አብነት በማድረግ እንጾማለን። ልጆች! የዐቢይ ጾም ወይም ጾመ ሁዳዴ ስምንት ሳምንታት እና ሃምሳ አምስት ቀናትን የያዘ ነው። እነዚህ ቀናት ሰባት ቅዳሜና ስምንት እሑድን ሲይዙ በአጠቃላይ አሥራ አምስት ቀን ይሆናሉ ማለት ነው። የዐቢይ ጾም ሃምሳ አምስት ቀናት ናቸው ስንል ጌታ የጾመው ፵ ቀናት ነው። ለምን ሃምሳ አምስት ቀን ሆነ? ሲባል ከጾሙ መጀመሪያ እና መጨረሻ ላይ የተጨመሩ ሁለት ሳምንታት ወይም አሥራ አምስት ቀናት ስላሉ ነው። እነሱም የመጀመሪያው ሳምንት ጾመ ሕርቃል ሲባል ፤ የመጨረሻው ሳምንት ሰሙነ ሕማማት በመባል የሚታወቅ ነው። እነዚህ ሁለት ሳምንታት የተጨመሩበት የራሳቸው ታሪክ እና ምክንያት አላቸው። ልጆች የዐቢይ ጾም ሳምንታት የየራሳቸው መጠሪያም አላቸው። እነዚህንም የዐቢይ ጾም ሳምንታት የሰየመው የቤተ ክርስቲያናችን የዜማ ሊቅ የሆነው ቅዱስ ያሬድ ጾመ ድጓ በሚለው መጽሐፉ ነው። ስምንቱ የዐቢይ ጾም ሳምንታት መጠሪያዎችም፡-  1. ዘወረደ 2. ቅድስት 3. ምኩራብ 4. መጻጉዕ 5. ደብረ ዘይት 6. ገብርኄር 7. ኒቆዲሞስ 8. ሆሣዕና በመባል ይታወቃሉ። በዚህ ክፍል ከስምንቱ ሳምንታት ስያሜዎች ሁለቱን ማለትም ‹‹ዘወረደ››ን እና ‹‹ቅድስት››ን አንስተን ለምን ይህ ስያሜ እንደተሰጣቸው በዝርዝር እናያለን። 1. ዘወረደ ፡- ከዐቢይ ጾም ሳምንታት መካከል የመጀመሪያው ሳምንት ‹‹ ዘወረደ›› በመባል ይጠራል። ዘወረደ ማለት ከላይ የመጣ፣ የወረደ ማለት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምንና ልጆቹን ለማዳን ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም መምጣቱን፤ ለሰው ልጆች ሲል መከራ ሞት መቀበሉን፣ እንዲሁም በመስቀል ተሰቅሎ ዓለሙን ማዳኑን ያመለክታል። ‹‹ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው›› ዮሐ ፫፥፲፫ ካለው ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በመነሳት ይህ ስያሜ ተሰጥቶታል። ይህ ሳምንት ‹‹ጾመ ሕርቃል›› በመባልም ይታወቃል።  ልጆች ሕርቃል የሚባል የቤዛንታይን ንጉሥ ነበር። እርሱ ንጉሥ በነበረበት ዘመን ፋርሶች ኢየሩሳሌምን በመውረር የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ማርከው ወደ ሀገራቸው ወስደውት ነበር። ንጉሡ ሕርቃልም ወደ ፋርስ በመዝመት የጌታን መስቀል ለማስመለስ ተነሣ፤ ነገር ግን ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው ‹‹ነፍስ የገደለ ሰው እስከ ዕድሜ ልኩ ይጹም›› ብለው ሥርዓት ሠርተው ነበርና ፈራ። ይህን ፍርሃቱን የተረዱት የኢየሩሳሌም ምእመናንም ‹‹ጠላታችንን አጥፍተህ መስቀሉን አስመልስልን እንጂ ጾሙን አምስት አምስት ቀን ተከፋፍለን እኛ እንጾምልሃለን›› በማለታቸው ፋርስ ድረስ ዘምቶ መስቀሉን አስመልሷል። ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ሥርዓት መሠረት በማድረግ እንዲሁም ሐዋርያትን አብነት በማድረግ የዐቢይ ጾም የመጀመሪያውን ሳምንት ‹‹ጾመ ሕርቃል›› በሚል ሰይማ እንዲጾም አድርጋዋለች። (ስንክሳር መጋቢት ፲፪) 2. ቅድስት፡- የዐቢይ ጾም ሁለተኛው ሳምንት ‹‹ቅድስት›› በመባል የሚታወቅ ሲሆን፤ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ ከርኩስነታችን የምንቀደስበትን ሥርዓት ሊሠራልን በገዳመ ቆሮንቶስ መጾም መጀመሩን ቤተ ክርስቲያን ታስተምረናለች። ልጆች ቅድስት ማለት ጽኑዕ፣ ክቡር ማለት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኛ አብነት ይሆነን ዘንድ ጾሙን የጀመረበት ሳምንት በመሆኑ ቅድስት ተብሎ ይጠራል። ይህ ሳምንት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ ቅድስና የሚነገርበት ሳምንት ነው። ሰንበት የእረፍት ቀን እንድትሆን በኦሪትም በሐዲስም እግዚአብሔር አምላክ የቀደሳት ዕለት መሆንዋን የሚናገር፤ እግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆነ የፈጠረው ሰውም ቅድስናን መያዝ እንደሚገባው የሚያሳስብም ነው። ዘፍ ፪፥፫፤ ፩ኛ ጴጥ ፩፥፲፭—፲፮።  ባጠቃላይ ቅድስት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾሞ የጾምን ጥቅምና ሥርዓት ሊያሥተምረን መጾም የጀመረበት ሳምንት ነው። ልጆች! ስለተቀሩት የዐቢይ ጾም ሳምንታት ስያሜና ትርጉም በሚቀጥለው እትማችን እናስተምራኋለን፤በሚቀጥለው ትምህርት እስከምንገናኝ ጾሙን እንድትጾሙና እንደትጸልዩ እንመክራችኋለን።  ደኅና ሰንብቱ ጾሙን የበረከት ያድርግላችሁ!
Read 1381 times