Wednesday, 28 April 2021 00:00

ዐቢይ ጾም (ጾመ ሁዳዴ)

Written by  በእህተ ሚካኤል
ልጆች! ባለፉት ሁለት እትሞቻችን በዐቢይ ጾም (በጾመ ሁዳዴ) ውስጥ ከሚገኙ ሳምንታት እና መጠሪያዎቻቸው ውስጥ ከዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት ጀምሮ ‹‹ዘወረደ››፣ ‹‹ቅድስት››፣ ‹‹ምኩራብ››፣‹‹መጻጉዕ›› ፣‹‹ደብረ ዘይት›› እና ‹‹ገብር ኄርን›› ስያሜያቸውንና ታሪካቸውን ነግረናችሁ ነበር። ስያሜያቸውንና ታሪካቸውን በደንብ እንደተረዳችሁ ተስፋ እናደርጋለን። እነሆ በዚህ ዝግጅት ደግሞ ስለ ‹‹ኒቆዲሞስ››፣ ‹‹ሆሣዕና›› እንዲሁም ስለ ሰሙነ ሕማማት ይዘንላችሁ ቀርበናል ተከታተሉን።  7. ኒቆዲሞስ  ልጆች! ሰባተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ‹‹ኒቆዲሞስ›› በመባል ይጠራል። ኒቆዲሞስ ከፈሪሳውያን ወገን ሲሆን ኢየሩሳሌም ውስጥ ካሉት የአይሁድ አለቆች እና መምህራን አንዱ ነው። ኒቆዲሞስ የብሉይ ኪዳንን ትምህርት ጠንቅቆ የሚያውቅና መምህር ፣ በሀብት ደረጃ ከፍ ያለ ሀብት ያለው ከመሆኑም በላይ የአይሁድ አለቃና ባለ ሥልጣንም ነው። ኒቆዲሞስ ወንጌልን ለመማር ከአይሁድ ቀድሞ በሌሊት ወደ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣ መምህረ አይሁድ ነው። (ዮሐ ፫፥፩—፳፩)

 

ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደ ጌታችን ከመጣ በኋላ የተለያዩ ጥያቄዎችን ጠይቆታል። ልጆች! ኒቆዲሞስ ጌታችንን ከጠየቃቸው ጥያቄዎችና ጌታችን ከመለሰለት መልሶች መሀከል የሚከተሉት ይገኙበታል።

ኒቆዲሞስ ፦ ‹‹መምህር ሆይ ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን፤ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርገውን ይህ ተአምር ሊያደርግ የሚችል የለምና›› አለው 

ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ፦ ‹‹ እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት  ለማየት  አይችልም›› አለው።

ኒቆዲሞስም ፦ ‹‹ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይችላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኅፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን?››   አለው።

ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ እውነት እውነት እልሃለሁ ዳግመኛ ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነውና።›› በማለት ለኒቆዲሞስ ስለ ምሥጢረ ጥምቀት በሚገባ አስተምሮታል። 

ልጆች! ኒቆዲሞስ የብሉይ ኪዳን አዋቂ የኦሪት መምህር ቢሆንም  በሌሊት ወደ ጌታችን እየሄደ ወንጌልን ለመማርና በክርስቶስ ለማመን በቅቷል። ወገኖቹ አይሁድ ጌታን ሰቅለው በገደሉት ጊዜም ከክፉ ሥራቸው ጋር ያልተባበረ ጻድቅ ሰው ነበረ። ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር በመሆንም ወደ ሀገረ ገዢው ጲላጦስ በመሄድ የጌታችንን ቅዱስ ሥጋ ከመስቀል አውርዶ ይቀብረው ዘንድ በመለመን ለራሱ ባሠራው አዲስ መቃብር ቀብሮታል ዮሐ ፲፱፥፴፱። ከዐቢይ ጾም ሳምንታትም ሰባተኛው ሳምንት ኒቆዲሞስ የሚባለው ኒቆዲሞስ የተባለው የአይሁድ መምህር ከጌታ ዘንድ ለመማር በሌሊት በመሄዱ ነው።

8.  ሆሣዕና

ልጆች! የዐቢይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት ሆሣዕና በመባል ይጠራል። ሆሣዕና ከስምንቱ የዐቢይ ጾም እሑዶች አንዱ ሲሆን ከትንሣኤ ቀድሞ የሚገኝ የመጨረሻው ሳምንት ነው። ሆሣዕና የእብራይስጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ‹‹አቤቱ እባክህ አሁን አድን፣ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና›› ማለት ነው። አንዲሁም ሆሣዕና ማለት ‹‹መድኃኒት›› ማለት ነው። በዚህ ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ንጉሥ በአህያ ላይ ተጭኖ ኢየሩሳሌም በክብር የገባበት ቀን ነው። 

ልጆች! በወንጌል ላይ ተጽፎ እንደምናገኘው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ከቢታንያ ተነስቶ ወደ ደብረ ዘይት ሲደርስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ጠርቶ ‹‹በፊታችሁ ወዳለች መንደር  ሂዱ ያንጊዜም የታሰረች አህያ ከውርንጭላዋም ጋር ታገኛላችሁ፤ፍቱና አምጡልኝ ። ምን ታደርጋላችሁ? የሚላችሁ ቢኖርም ጌታቸው ይሻቸዋል በሉ ያን ጊዜ ይሰዱአችኋል››  አላቸው (ማቴ ፳፩፥፩—፫) 

ሐዋርያትም እንደታዘዙት አህያዋን ከውርንጭላዋ ጋር ፈተው አመጡለት አጠገቡም ሲደርሱ ልብሳቸውን በአህያይቱ ላይ አንጥፈው ጌታችንን አስቀመጡት። ጌታም በአህያይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። ልጆች! ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የፋሲካን በዓል ለማክበር ከተለያዩ ሀገራት እና ከተማዎች የመጡ እንዲሁም ከሞተ እና ከተቀበረ አራት ቀን በኋላ ጌታ ከሙታን ያስነሳውን አልአዛርን ለማየት የተሰበሰቡ ብዙ ሕዝብ በኢየሩሳሌም ነበሩና የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ (ዘንባባ የሰላም፣ የድል አድራጊነት ምልክት ነው።)፣ ልብሳቸውን በየመንገዱ ላይ በማንጠፍ ‹‹ሆሣዕና በአርያም በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የተባረከ ነው›› እያሉ ሕፃናት ሳይቀሩ ይዘምሩለት ነበር። 

ነገር ግን ፈሪሳውያን በዚህ ጅግ በመበሳጨታቸው ጌታችንን ‹‹መምህር ሆይ ደቀ መዛሙርትህ እንዳይዘምሩ ተቆጣቸው›› አሉት። ጌታችንም ‹‹ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮሃሉ›› ብሎ መለሰላቸው (ሉቃ ፲፱፥፴፱)። ከዐቢይ ጾም ሳምንታትም ስምንተኛው ሳምንት ሆሣዕና የተባለበት ምክንያት ጌታችን በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም በመግባቱ ነው። 

ሰሙነ ሕማማት ፦ ልጆች!  በዐቢይ ጾም ከሰርክ ሆሣዕና ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያሉት ዕለታት ሰሙነ ሕማማት በመባል ይጠራሉ። ቤተ ክርስቲያን ከትንሣኤ በፊት ያለውን ሳምንት ሰሙነ ሕማማት በማለት ትዘክረዋለች። ‹‹ሕማማት የሚለው ቃልም ‹‹ሐመ፣ ታመመ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማሙ፣ እንግልቱና ሞቱ የሚዘከርበት፣ የሚነገርበት ሳምንት ነው። 

ልጆች! ስለ ዐቢይ ጾም በጻፍነው በመጀመሪያው እትማችን ላይ ስለ ጾመ ሁዳዴ ስንነጋገር የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት እና የመጨረሻው ሳምንት የተጨመሩ መሆናቸውን ነግረናችሁ ነበር አስታወሳችሁ? የጾሙ የመጀመሪያ ሳምንት ‹‹ጾመ ሕርቃል›› እንደሚባል እንዲሁም የጾሙ የመጨረሻው ሳምንት ‹‹ሰሙነ ሕማማት›› በመባል ስያሜያቸውን እንዳገኙ ነግረናችሁ ነበር። ሰሙነ ሕማማት ጌታችን መድኃኒታችን ለሰው ልጆች ደኅንነት ሲል በሥጋው መከራ መቀበሉን የምናስብበት ሳምንት ነው። 

የሰሙነ ሕማማት  ዕለታት የተለዩ ናቸው። በዚህ ሳምንት ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም፣ ጸሎተ ፍትሐት (ለሞተ ሰው የሚደረግ ጸሎት) አይደረግም፣ ምሥጢረ ጥምቀት (ጥምቀተ ክርስትና) አይደረግም፤ መስቀል አንሳለምም፣ ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ሳምንት ውስጥ የንግሥ በዓል አይደረግም። 

ልጆች! በሰሙነ ሕማማት ሳምንት በሚገኙ ዕለታት የተለያዩ ክንውኖች የሚካሄዱ ሲሆን እነሱም የሚከተሉት ናቸው፦

አለመሳሳም - በሰሙነ ሕማማት መጨባበጥ፣ ትከሻ ለትከሻ ተገናኝቶ በተቀደሰ አሳሳም መሳሳም ክልክል ነው፤ ይህም ይሁዳ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ‹‹እኔ የምስመው እሱ ክርስቶስ ነውና›› ያዙት ብሎ በመሳም ጌታን ለአይሁድ አሳልፎ መስጠቱን በማሰብ ነው። 

ሕጽበተ እግር - ‹‹ጸሎተ ሐሙስ›› በመባልም ይታወቃል። ጌታችን በዚህ ዕለት በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበት፣ ምሥጢረ ቁርባንን ያከናወነበት ዕለት  በመሆኑ ስያሜውን ያገኘው ከዚያ ነው። 

አክፍሎት -  በሰሙነ ሕማማት በዕለተ ዓርብ ከስግደት በኋላ እህል ቀምሰው እስከ እሑድ (ትንሣኤ)  የሚጾመው ጾም አክፍሎት ይባላል። አንዳንድ የበረቱ ሰዎች ደግሞ ሐሙስ በልተው እስከ ትንሣኤ የሚያከፍሉ አሉ።

ጉልባን - ጉልባን ከባቄላ ክክ እና ከተፈተገ ስንዴ ወይም ገብስ ጋር ተቀቅሎ የሚዘጋጅ ሲሆን የጸሎተ ሐሙስ ዕለት ከቅዳሴ በኋላ ይበላል።

ጥብጣብ - በዕለተ አርብ (የስቅለት ዕለት) ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ሲሰግዱና ሲጸልዩ ከዋሉ በኋላ ወደቤት ከመመለሳቸው (ከቤተ ክርስቲያን ከመሰናበታቸው) በፊት ወደ ካህናት ቀርበው ኃጢአታቸውን ይናዘዛሉ(ይናገራሉ) ካህናቱም በወይራ ቅጠል ትከሻቸውን እየጠበጠቡ(ቸብ ቸብ እያደረጉ) የሚያዙአቸው ተጨማሪ ስግደት ነው። 

ቀጤማ -  በስቅለት ማግሥት ቅዳሜ የሚታደል ቀጤማ (እርጥብ ሳር ነው)። በዚህ ዕለት ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል እያቃጨሉ እና እርጥብ ቀጤማ በመያዝ በየመንደሩ እየዞሩ ‹‹በመስቀሉ ሰላምን አደረገ፤ትንሣኤውንም ገለጠልን›› በማለት ቀጤማውን ለምእመናን ያድላሉ። ምእመናንም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ስጦታ ለካህናቱ ሰጥተው ቀጤማውን  ተቀብለው በራሳቸው ላይ ያስራሉ።

ልጆች! ከዚህም በተጨማሪ የሕማማት ሳምንት ዕለታት የየራሳቸው ስያሜና ታሪክ  አሉአቸው። 

ሰኞ -  ‹የቤተ መቅደስ መንጻት ቀን›› ይባላል። ጌታች መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመቅደሱ ውስጥ እና ዙሪያውን ይሸጡ ይለውጡ የነበሩ ነጋዴዎችን ገርፎ ከቤተ መቅደስ ያስወጣበት እና ቤተ መቅደሱን ያነጻበት ቀን ነው።

ማክሰኞ -  ‹‹የጥያቄና መልስ ቀን›› በመባል ይታወቃል። ጌታችን ሰኞ ባደረገው ነገር ላይ(ሻጮችና ለዋጮችን ለምን ገርፎ እንዳስወጣ) አይሁድ ጥያቄ የጠየቁበትና እርሱም መልስ የሰጠበት ቀን ነው።

ረቡዕ - ‹‹የምክር ቀን›› ይባላል። የአይሁድ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚችሉ የመከሩበት ቀን ነው። ‹‹የመልካም መዓዛ ቀን›› እና ‹‹ የለቅሶ ቀን›› በመባልም ይታወቃል።

ሐሙስ - ‹‹ጸሎተ ሐሙስ›› በመባል ይታወቃል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁድ ሊይዙት እስኪመጡ ድረስ በጌቴሴማኔ የአትክልት ሥፍራ ሲጸልይ የነበረበት ቀን ስለሆነ ነው። ጌታችን ዝቅ ብሎ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ያጠበበት ቀን ስለሆነ ‹‹ሕጽበተ እግር›› በመባልም ይጠራል። ጌታችን ምሥጢረ ቁርባንን የጀመረበት ቀን በመሆኑም ‹‹የምሥጢር ቀን›› በመባል ይጠራል።

ዓርብ - ይህ ቀን አይሁድ በክፋት እና በምቀኝነት ተነሳስተው ጌታን የሰቀሉበት ቀን በመሆኑ ‹‹ዕለተ ስቅለት›› ይባላል። ይህ ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአዳምን ዘር በሙሉ ለማዳን በመስቀል ላይ የተሰቀለበት ታላቅ ቀን ነው።

ቅዳሜ - ‹‹ ቀዳም ሥዑር›› በመባል ይታወቃል። በዚህ ቀን ጌታችን በመቃብር አርፎ የዋለባት ቀን በመሆኑ ይጾማል። ቀዳም ሥዑር የተባለበትም በዓመት አንድ ቀን ስለምትጾም ነው።

ልጆች! በሰሙነ ሕማማት ክርስቲያኖች ሁሉ የጌታችንን ውለታ እያሰቡ የሚጸልዩበት፣ የሚያዝኑበት ፣የሚሰግዱበት ከሌሎች ቀናት የተለዩ ቀናት ናቸው። እናንተም ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄዳችሁ እንድትጸልዩ፣ እንድትሰግዱ እንነግራችኋለን እሺ ልጆች!

መዋዕለ ጾሙን አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም ያድርሰን ያድርሳችሁ!

Read 578 times